መንግሥት በሐምሌ ወር መጨረሻ 2013 ዓ.ም. ለሦስት ወራት ዕግድ ከጣለባቸው ሦስት የውጭ የዕርዳታ ድርጅቶች ውስጥ አንዱ የሆነውና ከሁለት ወራት በፊት እንዲፈርስ የውሳኔ ሐሳብ ቀርቦበት የነበረው ኖርዌጂያን ሬፊውጂ ካውንስል (NRC)፣ ዕግዱ ታኅሳስ 24 ቀን 2014 ዓ.ም. እንደተነሳለት ተገለጸ፡፡
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ‹‹ድርጅቱ ጥፋቱን ከማረም ይልቅ መሸፈፋን›› በመምረጡ፣ ከሌሎቹ ድርጅቶች በተለየ ለተጨማሪ ሁለት ወራት ዕግዱ እንዲቀጥልበት የተደረገ ሲሆን፣ አሁን ግን ከመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ጋር ዕግዱ ተነስቶለታል፡፡
መንግሥት ሐምሌ 28 ቀን 2014 ዓ.ም. የአገሪቱን ሕግ ጥሰዋል ያላቸው ኤምኤስኤፍ ሆላንድ፣ ኖርዌጂያን ሬፊውጂ ካውንስልና አልማክቱም ፋውንዴሽን የተሰኙ ሦስት የውጭ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ የሦስት ወራት ዕግድ መጣሉን አስታውቆ ነበር፡፡ ሦስቱም ድርጅቶች በአገሪቱ ውስጥ የሥራ ፈቃድ የሌላቸውን የውጭ አገር ዜጎች ቀጥረው ከስድስት ወራት ለሚልቅ ጊዜ ማሠራታቸው ተገለጸ ሲሆን፣ ኤምኤስኤፍ ሆላንድና ኖርዌጂያን ሬፊውጂ ካውንስል ደግሞ ‹‹በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ሐሰተኛ መረጃዎችን ሲያሠራጩ ነበር፤›› የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡ በተጨማሪም ሁለቱ ድርጅቶች በመንግሥት ፈቃድ ያላገኘ የሳተላይት መሣርያ በሕገወጥ መንገድ ወደ አገር ወስጥ ማስገባትና መጠቀምም ለዕገዳ ከዳረጋቸው ምክንያቶች ውስጥ አንዱ መሆኑን አቶ ፋሲካው አስረድተዋል፡፡
ድርጅቶቹ ጉዳያቸው የመጨረሻ ዕልባት እስኪያገኝ ድረስ ለሦስት ወራት እንዲታገዱ ውሳኔ ተላልፎ የነበረ ሲሆን፣ አልማክቱም ፋውንዴሽ ለዕግድ የዳረገው ጥፋት ቀላል በመሆኑ ማስተካከያ አድርጎ ዕገዳው በአንድ ወር ውስጥ እንደተነሳለት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ ኤምኤስኤፍ ሆላንድ የተሰኘው ድርጅት ደግሞ ‹‹ጥፋቶቹን›› አስተካክሎ በመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ከሦስት ወራት ዕግድ በኋላ ወደ ሥራው እንደተመለሰ አስታውቀዋል፡፡
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ኖርዌጂያን ሬፊውጂ ካውንስል (NRC) የተሰኘው ድርጅት 14 ያህል የውጭ ዜግነት ያላቸውን ሰዎች ያለ ፈቃድ ሲያሠራ እንደነበረ ተናግረው፣ ‹‹ዕግድ በተጣለበት ሦስት ወራት ውስጥ ጥፋቱን ከማስተካከል ይልቅ፣ በተለያየ መንገድ ጫና ለማድረግ ሙከራ ሲያደርግ ነበር፤›› ብለዋል፡፡ ድርጅቱ ለዕግድ የዳረገውን ችግር ከማስተካከል ይልቅ መሸፋፈንና ውሳኔውን ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ለማስመሰል ለማድረግ ሞክሯል ብለዋል፡፡
ይኼንን ተከትሎም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ኖርዌጂያን ሬፊውጂ ካውንስል (NRC) እንዲፈርስ የውሳኔ ሐሳብ ለባለሥልጣኑ ቦርድ አቅርቦ እንደነበር ያስታወቁት አቶ ፋሲካው፣ ይሁንና ቦርዱ ዕግዱን በሁለት ወራት እዳራዘመው አስረድተዋል፡፡ ዕግዱ በተራዘመባቸው ሁለት ወራት ውስጥ ቦርዱ ጉዳዩን የማጣራትና ሰነዶችን የመመልከት ሥራዎችን ማከናወኑን፣ በተጨማሪም ባለሥልጣኑና ድርጅቱ ቀርበው እንዳስረዱም ገልጸዋል፡፡
አቶ ፋሲካው ጉዳዩ ለቦርዱ ከቀረበ በኋላ ድርጅቱ የማስተካከያ ዕርምጃዎችን መውሰዱን የገለጹ ሲሆን፣ በድርጅቱ ውስጥ ያለ ፈቃድ ሲሠሩ የነበሩ የውጭ ዜጎችን ከአገር ማስወጣቱንና የተገኘበትን የሳተላይት መሣሪያ ለኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ማስረከቡን አስታውቀዋል፡፡ ድርጅቱ ዕገዳ በተጣለበት ጊዜ የነበሩት የድርጅቱ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር በሌላ እንደተተኩ የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ ድርጅቱ ኃላፊ የቀየረበት ምክንያት ዕግዱን ተከትሎ የተፈጠረውን አለመግባባት ለመቅረፍ በማሰብ ነው የሚል ግምት እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡
አቶ ፋሲካው እነዚህ ዕርምጃዎች መወሰዳቸውን ተከትሎ በድርጅቱ ላይ የተጣለው ዕግድ ባለፈው ሳምንት ዓርብ ታኅሳስ 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ከመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ጋር እንደተነሳለት ገልጸው፣ ‹‹አሁን የተሰጣቸው የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ በመሆኑ ከዚህ በኋላ ጥፋት ሠርቶ ቢገኝ በቀጥታ ይፈርሳል፣ ወይም ከአገር ይባረራል፤›› ብለዋል፡፡
ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ ሲንቀሳቀስ የቆየው ኖርዌጂያን ሬፊውጂ ካውንስል ኦሮሚያ፣ ትግራይና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎችን ጨምሮ በሰባት ክልሎችና በአዲስ አበባ ከተማ ይንቀሳቀሳል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2020 ከ600 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ዕርዳታ ማቅረቡን ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
ድርጅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ሲታገድ የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ ያን ኤግላንድ በነሐሴ ወር ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር መነጋገራቸው ይታወሳል፡፡ በተጣለበት ዕግድ ምክንያት ከሠራተኞቹና ከአጋሮቹ ጋር ያለው ግንኙነት ይበላሻል በሚል ሥጋቱን ሲገልጽ የነበረ ሲሆን፣ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች መኖራቸውን በመጥቀስም ዕገዳው እንዲነሳለት ጠይቆ ነበር፡፡
‹‹የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ፍላጎቱ የሲቪል ማኅበረሰቡ እንዲጎለብትና ለአገር እንዲጠቅም ነው፤›› ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ ይሁንና ጥቂቶች ሕግ ስለሚጥሱ ክትትል ማድረጉን እንደሚቀጥልና የክትትል ማኑዋል ጭምር ማዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡
አቶ ፋሲካው፣ ‹‹እንደ አገር በራሳችን አቅም መለወጥ ብንፈልግም የሚደግፈን የልማት አጋር ሲገኝ እንቀበላለን፤›› ብለው፣ ነገር ግን ድጋፉ የአገሪቱን ሕግና ሉዓላዊነት በመጣስ የሚደረግ መሆን እንደሌለበት አስረድተዋል፡፡