Friday, April 19, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

በሐሳብ ልዩነት ውስጥ መኖር ይለመድ!

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የሚታዩ ህፀፆች ዕርማት ስለማይደረግባቸው፣ ለሕጋዊና ለሰላማዊ ፉክክር ሲያስቸግሩ ይስተዋላሉ፡፡ የፖለቲካ ባህሉ ለሐሳብ ልዩነት ዕውቅና ከመስጠት ይልቅ፣ ተቃራኒን በጠላትነት ፈርጆ ለማደባየት ርብርቡ ይበረታል፡፡ ለሐሳብ ልዕልና የሚሰጠው ሥፍራ እዚህ ግባ የሚባል ስላልሆነ፣ ፍሬ ነገሩ ላይ ከማተኮር ይልቅ ከበስተጀርባው ሊኖር ስለሚችል ሴራ ይተረካል፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ ኋላቀርና ዘመኑን የማይዋጅ የፖለቲካ ባህል ምክንያት፣ በርካታ ለአገር የሚጠቅሙ ጉዳዮች ባክነው ቀርተዋል፡፡ አገርን ከጉስቁልና የሚገላግሉ ዜጎች ከአደባባይ ጠፍተዋል፡፡ ኢትዮጵያን ከግጭትና ከውድመት የሚታደጉ ሐሳቦች ነጥፈው፣ ኢትዮጵያውያን ለዕልቂትና ለመፈናቀል ተዳርገዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን በየዕለቱ ኑሮአቸው ለሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች መፍትሔ ለመፈለግ፣ በዕርጋታ ተቀምጠው ሐሳብ ለመለዋወጥ ችግር የለባቸውም፡፡ ፖለቲካው ሠፈር ያሉ ተዋናዮችና አጃቢዎቻቸው ግን ይህንን ዘመን ተሻጋሪ እሴት በማኮሰስ፣ አገርን ሲዖል ለማድረግ የሚረዱ ነገሮች ላይ ነው ሲረባረቡ የኖሩት፡፡ በሰላማዊ ፉክክር የሕዝብ ድምፅ አግኝተው አገር ለመምራት ራሳቸውን ማደራጀት ቢለማመዱ፣ ኢትዮጵያ የግጭት መጠንሰሻና የሕዝብ ዕልቂት ምድጃ አትሆንም ነበር፡፡ ልዩነትን ይዞ መፎካከር አለመቻል ትርፉ ውድመት ብቻ ነው፡፡

በኋላቀሩ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ውስጥ የሐሳብ ልዩነት ክብር የለውም፣ ዕውቅናም አይሰጠውም፡፡ በሐሳብ የተለየን እንደ ደመኛ ጠላት ማሳደድ፣ ማሰር፣ መግደል ወይም ማሰናከል የተለመደ ድርጊት ነበር፣ አሁንም ነው፡፡ ‹‹ልዩነት ለዘለዓለም ይኑር›› የሚለው መርህ በዓለም ላይ ከተስተጋባ በርካታ ዓመታት ቢያስቆጥርም፣ ብዙዎቹ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ልሂቃን ግን አይረዱትም፡፡ በዚህ መርህ እንመራለን የሚሉ ጥቂቶች ቢኖሩም፣ በጉልበት አምላኪዎች ይደፈጠጣሉ፡፡ ጨፍጋጋው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ትልቁ ጉዳቱ ለልዩነት ቦታ አለመስጠቱ ነው፡፡ እንኳንስ በሰላማዊ መንገድ ተቀምጦ ለመነጋገርና ለመደራደር፣ በምርጫ አሸንፎ መንግሥት ለመሆን የሚያስችል ቁመና መያዝ ያዳግታቸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም አንድ ላይ ሆነው ፓርቲ መሥርተው በሐሳብ ልዩነት ምክንያት በሰላም መሥራት ተስኗቸው የተፈረካከሱ ብዙ ናቸው፡፡ የስም ማጥፋት፣ የአሉባልታና የሴራ ሰለባ ሆነው ከፖለቲካዊ መድረክ የጠፉ በርካቶች ናቸው፡፡ ለተለየ ሐሳብ ክብር ቢሰጥ ኖሮ ተመሥርተው የሚፈርሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባልበዙ ነበር፡፡ ለፖለቲካ ምኅዳሩ የሚጠቅሙ ሰዎች የትም ባልተጣሉ ነበር፡፡ አሁንም የተለዩ ሐሳቦች እየተከበሩ ቢቻል አብሮ መሥራት፣ ካልተቻለ ደግሞ አማራጭን በሰላም መፈለግ ቢለመድ ለኋላቀሩ ፖለቲካ መድኅን ይሆነዋል፡፡ ለኢትዮጵያም ጠቃሚ ነው፡፡

ዴሞክራሲ የተለያዩ ሐሳቦች ከተለያዩ አቅጣጫዎች በነፃነት ቀርበው የሚወዳደሩበት ገበያ ማለት ነው፡፡ በዚህ የሐሳብ ገበያ ውስጥ በግልጽነት፣ በነፃነትና በሰላማዊ መንገድ የመፎካከር ኃላፊነት የፖለቲካ ኃይሎች ነው፡፡ በአንድ ፓርቲ ውስጥ የሐሳብ ልዩነት ሲያጋጥም ብያኔ የሚገኘው በአባላቱ ድምፅ እንደሆነው ሁሉ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የሚዳኙት የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት እንደሆነ በሚታሰበው የሕዝብ ድምፅ ብቻ መሆን አለበት፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሐሳባቸውን ለሕዝብ ለመሸጥ ከመውጣታቸው በፊት የቤት ሥራቸውን መጨረስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ የሚፈለገውን ዲሲፕሊን ያላሟላ የፖለቲካ ፓርቲ ለሕዝብ ብያኔ መቅረብ አይችልም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚመሩ ሰዎች ከፍተኛ የሆነ ብቃት፣ ልምድና ሥነ ምግባር ያስፈልጋቸዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲያቸውን ለፖለቲካ ጨዋታ ሕግ ማስገዛት የማይችሉ፣ ግልጽና የተብራራ አጀንዳ የሌላቸው አመራሮች፣ ሕዝብ ፊት በመውጣታቸው የሚያተርፉት ነገር እንደሌለ ሊረዱ ይገባል፡፡ ሕዝብን በጉልበት፣ በማታለል፣ የማይጨበጥ ቃል በመግባት ወይም አገር በማተራመስ ሥልጣን እንደማይገኝ ግንዛቤ ሊኖር ይገባል፡፡ ይልቁንም መንግሥትን ለመምራት የሚያስችል ቁመና ይዞ መገኘት ያዋጣል፡፡ አገር ለመምራት ዝግጁ መሆን ያስከብራል፡፡

ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የሐሳብ ልዩነትን የሚያከብር የፖለቲካ ምኅዳር ነው፡፡ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች ጥያቄ መነሻ ይኼ ነው፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ተከብሯል ከሚባልባቸው መሥፈርቶች አንዱ፣ ለሐሳብ ልዩነት ክብር መስጠት ነው፡፡ በሐሳብ የሚለይ ግለሰብም ሆነ ቡድን የሌሎችን መብት ማክበር መቻል አለበት፡፡ የሐሳብ ገበያው የሚፈልገው አንድን ሐሳብ መቃወም ብቻ ሳይሆን፣ የተሻለ ሐሳብ ይዞ መገኘትን ጭምር ነው፡፡ ዴሞክራሲ መለምለም የሚጀምረው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ በአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥም ሆነ በሌላ አደረጃጀት ሁሌም ሰዎች መስማማት አይጠበቅባቸውም፡፡ የልዩነታቸውን ነጥብ አስመዝግበው መወያየትና መከራከር ይጠበቅባቸዋል፡፡ አንድ ፓርቲ አገር ለመምራት የሚያስችለውን መስፈርት አሟልቶ ሕዝብ ዘንድ መቅረብ የሚችለው፣ አባላቱንና ደጋፊዎቹን ዓላማውን በተመለከተ ጠብሰቅ ያለ ዕውቀት ማስጨበጥ ሲችል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም አገሩን እንዲመራለት አደራ የሚሰጠው፣ በማንኛውም መመዘኛ ብቁ ሆኖ ሲያገኘው ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ላቅ ያለ ዕይታና ዕሳቤ ይዞ አደባባይ መውጣት ያስፈልጋል፡፡ ከሁሉም ነገር በላይ ለሐሳብ ልዩነት ክብር መስጠት ተገቢ ነው፡፡

ብዙዎቹ ፖለቲከኞች ያልተመቸ ነገር ሲያጋጥማቸው ችግሩን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ልማድ ባለማዳበራቸውና ነውጠኛ ደጋፊዎችን የማሰባሰብ ሴራ ውስጥ ስለሚገቡ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ለረዥም ዓመታት ከተዘፈቀበት አረንቋ ውስጥ መውጣት አቅቶታል፡፡ ፖለቲካውን በምክንያት ሳይሆን በስሜት ስለሚመሩት መሬት የረገጠ ጥንካሬ የላቸውም፡፡ የተሻለና ተመራጭ አጀንዳ ይዘው ከመቅረብ ይልቅ፣ ለሰበብና ለስሞታ ራሳቸውን ስለሚያዘጋጁ ካሉበት ንቅንቅ ማለት አቅቷቸዋል፡፡ የሰው ኃይላቸውን፣ ዕውቀታቸውን፣ ቁሳቁሳቸውንና የመሳሰሉትን አቀናጅተው ጠንክረው መውጣት ሲገባቸው የሌሎችን ጥንካሬ ሲያበሻቅጡ ይታያሉ፡፡ ‹‹ተመሳሳይ ላባ ያላቸው ወፎች አንድ ላይ ይበራሉ›› እንደሚባለው፣ ቢጤ ለቢጤ ተገኛኝቶ መተባበርን የመሰለ ምንም ነገር የለም፡፡ ከዚያ የሐሳብ ገበያውን ተቀላቅሎ በነፃነት ለሕዝብ ዳኝነት መቅረብ የግድ ይሆናል ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እንታገላለን የሚሉ ወገኖችም፣ ከየትም ወገን የሐሳብ ልዩነት ሲፈጠር ጠላትነትን ለማጠናከር ከማጋጋል መታቀብ አለባቸው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው የተለያዩ ሐሳቦች እንዲፋጩ ዕድል ሲኖር እንጂ፣ እንደተለመደው በአሳዳጅና በተሳዳጅ ኋላቀር የፖለቲካ ጀብዱ አይደለም፡፡ የፖለቲካው ምኅዳር ውስጥ አዲስ ዕይታና ሐሳብ ሲመጣ ግራ መጋባት አያስፈልግም፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያስፈልጉት የተለያዩ ሐሳቦች ይዘው የሚወዳደሩ ተፎካካሪዎች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር የናፈቀውም በሐሳብ ልዩነት ውስጥ የመኖር ሥልጣኔ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ግልጽነትና ኃላፊነት የጎደላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲስተናገዱበት፣ ግጭትና መገዳደልን ጨምሮ የአገርን ተስፋ የሚያጨልሙ ድርጊቶች ይበዙበታል፡፡ ሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር መኖር የሚችለው የፖለቲካ ፓርቲዎች በሥርዓት ሲመሩ ነው፡፡ ከውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ እስከ ውጫዊ እንቅስቃሴያቸው ድረስ ለሐሳብ ልዩነት ዕውቅና መስጠት አለባቸው፡፡ ችግር ሲያጋጥማቸው ለሰላማዊ መፍትሔ ቅድሚያ ሊሰጡ ይገባል፡፡ የሕግ የበላይነት ዋልታና ማገር እንዲሆን ከማንም በላይ መታገል አለባቸው፡፡ ሕግ ሳይከበር ሲቀር ሥርዓተ አልበኝነት እንደሚሰፍን ለእነሱ ነጋሪ አያስፈልግም፡፡ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ዕውን የሚሆኑት ሕግ ሲከበር ብቻ ነው፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ ሁሉንም አሳታፊ መሆን የሚችለው የሕግ የበላይነት ሲኖር ነው፡፡ ግለሰቦች ሐሳባቸውን በነፃነት መግለጽ የሚችሉት ለሕግ የበላይነት ክብር ሲሰጥ ነው፡፡ በሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር ተሳትፎ ለማድረግ የሚፈልጉ የፖለቲካ ኃይሎች በሙሉ ለሕግ የበላይነት ክብር ይስጡ፡፡ ምርጫ ነፃ፣ ተዓማኒ፣ ሰላማዊና ትክክለኛ የሚሆነው ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ለሰላማዊ ፉክክሩ ተገዥ ሲሆኑ ብቻ ነው፡፡ ልዩነትን ማክበርና ለተፎካካሪ ዕውቅና መስጠት ሲቻል፣ ኋላቀሩ የፖለቲካ ምኅዳር ለዘመናት ከታሰረበት እግር ብረት ይላቀቃል፡፡ ሕዝብ የሚፈልገው የተሻለ ሐሳብ ይዞ የሚቀርበውን በመሆኑ ለሐሳብ ልዕልና ከበሬታ ይሰጥ፡፡ በሐሳብ ልዩነት ውስጥ መኖር ይለመድ!

 

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...

እጥረትና ውጥረት!

ጉዞ ከስድስት ኪሎ ወደ ቃሊቲ፡፡ ‹‹ይገርማል ቀኑ እንዴት ይሄዳል?››...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለፋይዳ ቢስ ጉዳዮች የሚባክነው ጊዜና ሀብት ያሳስባል!

ኢትዮጵያ በወጣት የሰው ኃይል፣ ዕውቀትና ልምድ ባካበቱ አንጋፋዎች፣ በሰፊ ለም መሬት፣ በአፍሪካ ተወዳዳሪ በሌለው የውኃ ሀብት፣ በበርካታ የማዕድናት ዓይነቶች፣ ብዛት ባላቸው የቱሪዝም መስህቦችና የአየር...

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...