- ከቧንቧ ውኃ ሞልቶ ሲሸጥ የተገኘው አምራች ድርጅት መከሰሱ ታውቋል
በምስጋናው ፈንታው
በተለያዩ ድርጅቶች እየተመረተና እስከ 20 ሌትር በሚይዝ የውኃ ፕላስቲክ (ጃር) እየተሞላ በመሸጥ ላይ የሚገኘው፣ የመጠጥ ውኃ፣ ቁጥጥር የማይደረግበትና ለጤና አደገኛ መሆኑ ተነገረ፡፡
የንግድ ፈቃድ አግኝተው ወደ ምርት የሚገቡ ድርጅቶች፣ ምርታቸውን ለተጠቃሚው ከመሸጣቸው በፊት የፕላስቲኩን ጥራት፣ የመጠቀሚያ ጊዜ፣ ለጤና ተስማሚ መሆኑንና ደረጃውን የጠበቀ ስለመሆኑ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማት ቁጥጥር ማድረግ ተቀዳሚው ሥራቸው ቢሆንም፣ አንዱ በሌላኛው ላይ ከማሳበብ ያለፈ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ እንዳልሆነ ታውቋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ቦታዎች የውኃ ፕላስቲክ (ጃር) አጠቃቀምን በተመለከተ የውኃው ጥራት ላይ ተፅዕኖ በሚፈጥርና ለጤና አሥጊ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን ተጠቃሚዎች እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ የውኃ ፕላስቲኩን አጠቃቀም በተመለከተ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት፣ የደረጃዎች ኤጀንሲና የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን እያደረጉት ያሉትን ቁጥጥር በተመለከተ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት የውኃ ፕላስቲክ መልሶ መጠቀም ‹‹Recycling›› ለጤና አሥጊና ጥራት በሌለው መንገድ ጥቅም ላይ እየዋለ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ ፕላስቲኩ በተደጋጋሚ ለመልሶ ጥቅም በመዋሉ ምክንያት የፅዳት፣ የውኃ ማፍሰስና፣ የመጫጫር ችግሮች እንዳሉበት የድርጅቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አቤል አንበርብር ተናግረዋል፡፡
የውኃ ፕላስቲክ መልሶ መጠቀም በጤና ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከልም ገደብ ሊበጅለት እንደሚገባ፣ ይኼንን መነሻ በማድረግ ድርጅቱ ለኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ምርቱ ደረጃ እንዲዘጋጅለትና በደረጃው መሠረት የምርት መግለጫ ተለጥፎ ቁጥጥር እንዲደረግበት ቢያቀርብም፣ እስካሁን የደረጃ ማውጣት ሥራ እንዳልተከናወነለትም አቶ አቤል ገልጸዋል፡፡
የተጠየቀውን የደረጃ ማውጣት ሥራ ተግባራዊ ማድረግ ስላልተቻለበት ምክንያት ጥያቄ የቀረበለት የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ፣ ኤጀንሲው ደረጃ ለማውጣት ለውኃ አምራቾች ማኅበር ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ አለማግኘቱን ገልጿል፡፡
‹‹ደረጃ እንዲወጣ ኃላፊነቱን ወስዶ ጥያቄ ማቅረብ ያለበት የውኃ አምራቾች ማኅበር ነው፡፡ ነገር ግን እኛ ይህ የፕላስቲክ ውኃ (ጃር) ደረጃ እንዲወጣለት ለማኅበሩ ብናቀርብም፣ እስካሁን አንድም ደረጃ እንዲወጣለት የጠየቀ ድርጅት የለም፤›› ሲሉ የኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ይስማ ጅሩ ገልጸዋል፡፡
ስለሆነም ደረጃ የሌለውና ጥራቱ የተጓደለ ምርት ወደ ገበያ ሲቀርብ፣ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ተከታትሎ ምርቱ ወደ ገበያ እንዳይቀርብና አምራቾቹ ደረጃ እንዲያወጡ ማድረግ አለበት ሲሉ አቶ ይስማ አክለዋል፡፡
የውኃ ፕላስቲክ (ጃር) መልሶ መጠቀም ላይ ችግር መኖሩን የውኃ አምራቾችም ይስማማሉ፡፡ የዴይሊ ውኃ የሴልስና ማርኬቲንግ ኃላፊ አቶ ኢዮብ መንገሻ ፕላስቲኩ ለምን ያህል ጊዜ መልሶ ጥቅም ላይ እንደዋለ እንደማይታወቅና በቂ እጥበት የማይደረግለት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹የፅዳት ማሽኑ በአገር ውስጥ ስለማይገኝ፣ በተጨማሪም አንዱ ያመረተውን ሌላው የሚጠቀም በመሆኑ በምርቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው፤›› ብለዋል፡፡
የውኃ ፕላስቲኩ ደረጃ እንዲወጣለት በተጠየቀው መሠረት የውኃ አምራቾች ማኅበር ደረጃ እንዲወጣለት ለምን አልጠየቀም በማለት ሪፖርተር ላነሳው ጥያቄ፣ የኢትዮጵያ የታሸገ ውኃ፣ የለስላሳ መጠጥ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾችና አቀነባባሪዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ መርዕድ ደረጃውን ለማውጣት በቂ ጥናት ያልተደረገበትና አምራቾች በጥራት እንዲያመርቱ መተማመን ላይ የተመሠረተ ስምምነት ከማድረግ በቀር፣ መልሶ መጠቀሙን ለመወሰን የሚያስችል መመዘኛ ማውጣትና ደረጃ ይውጣ ብሎ ለማቅረብ አስቸጋሪ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ በመዋል ጥራቱ ላይ ጥያቄ የሚነሳበት የውኃ ፕላስቲክን በተመለከተ ቁጥጥር በማድረግ ዕርምጃ የሚወስደው የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን፣ አጠቃቀሙን የሚወስን መመርያ በማዘጋጀት ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡
‹‹በጥር ወር ወደ ሥራ ለማስገባት አቅደን እያዘጋጀን ያለነው መመርያ እንደገና ጥቅም ላይ የሚውሉ የውኃ ፕላስቲኮች ለምን ያህል ጊዜና በምን ሁኔታ መመረት አለባቸው የሚለውን የሚወስን ነው፤›› ያሉት የባለሥልጣኑ የምግብ ተቋማት ቁጥጥር ኃላፊ አቶ በትረ ጌታሁን፣ እስካሁን ጥራቱን ባልጠበቀ መንገድ ሲያመርቱ በተገኙ ሦስት ድርጅቶች ላይ ዕርምጃ ተወስዶ እንዲያስተካክሉ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ፕላስቲኩ ለተለያዩ ወንጀሎች የተጋለጠ ነው ብለው ስሙን መግለጽ ያልፈለጉት አንድ ድርጅት፣ የቧንቧ ውኃ ሞልቶ ሲሸጥ መገኘቱንና ክስ እንደተመሠረተበት ጠቁመዋል፡፡
አምስት የሚሆኑ የውኃ ፕላስቲክን መልሰው የሚጠቀሙ ድርጅቶች መኖራቸውን የገለጹት አቶ በትረ፣ በገበያ ላይ የሚገኙ የውኃ ፕላስቲኮችን ናሙና በመውሰድ ለምን ያህል ጊዜ መልሶ መጠቀም ይቻላል የሚለው እንደሚወሰንና ችግር የሚያመጣ ውጤት ከተገኘ መልሶ መጠቀም ሊታገድ እንደሚችል አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል የውኃን የማዕድን (Mineral) ይዘት የሚወስን ደረጃ ወጥቶ አምራቾቹ በስድስት ወራት ውስጥ እንዲተገብሩ የወጣው መመርያ፣ በውኃ አምራቾች ላይ ቅሬታ እየገጠመው መሆኑን የውኃ አምራቾች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ ገልጸዋል፡፡
በማኅበሩ ሥር 13 የማዕድን ውኃ አምራቾች መኖራቸውን የገለጹት አቶ አሸናፊ፣ አንዳንዶቹ ለሁለት ዓመት የሚሆን የውኃ ይዘት መግለጫ የገዙ አሉ፡፡ በዚህ የተሰጠው ጊዜ አጭር ነው የሚል ቅሬታ አቅርበዋል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የማዕድን መጠኑ ከፍተኛ፣ መካከለኛ ወይም ዝቅተኛ በሚል እንዲቀመጥ መታዘዙ በምርቱ ተፈላጊነት ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል የሚል ሥጋት እንዳሳደረባቸው ተናግረዋል፡፡
‹‹አምራቾቹ ይህን ቢሉም ከትርፍ አንፃር ብቻ ሳይሆን፣ ከኅብረተሰቡ ጥቅም አንፃር በማየት ቅሬታውን ለማስተናገድ ጊዜ ተወስዶ ውይይት ከተደረገ በኋላ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ በተባለው ጊዜ እንዲፈጸሙ ይጠበቃል፤›› ሲሉ የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን የምግብ ተቋማት ቁጥጥር ኃላፊው አቶ በትረ ገልጸዋል፡፡