Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊቤተ መንግሥቶቹ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ወደ ሌላ ቦታ እንደሚዛወሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታወቁ

ቤተ መንግሥቶቹ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ወደ ሌላ ቦታ እንደሚዛወሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታወቁ

ቀን:

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ቤተ መንግሥቶቹ ታላቁ ቤተ መንግሥት ‹ዳግማዊ ምኒልክ ቤተ መንግሥት› እና ብሔራዊ ቤተ መንግሥት ‹ኢዮቤልዩ› በጥቂት ዓመታት ውስጥ ካሉበት ቦታ እንደሚነሱ ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይኼንን የገለጹት የአብርሆት ቤተ መጻሕፍት የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ሲሆን፣ የተለያዩ ፕሮጀክቶች የተገነቡበትና እየተገነቡበት ያለው የቤተ መንግሥቶቹ መገኛ ሥፍራን የቱሪስት ማዕከል የማድረግ ፍላጎት እንዳለ ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) እና ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት ከታላቁ ቤተ መንግሥት ፊት ለፊት ባለው ቅያስ ላይ የተገነባውን የአብርሆት ቤተ መጻሕፍት ቅዳሜ ታኅሳስ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. መርቀው ከፍተዋል፡፡ የቤተ መጻሕፍቱ መጠሪያ የሆነው አብርሆት፣ ‹‹ብዙ የተቆለፉብን ታሪኮች፣ የሀብት መፍጠሪያና፣ የሰላም መፍጠሪያ መንገዶችን ሁሉ መክፈቻ ቁልፍ ነው፣›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የኢትዮጵያ ትልቁ ችግር የሆነውን ድንቁርናን ማጥፊያ ለሆነው ዕውቀት መሠረት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

ባለ አራት ወለሉ የአብርሆት ቤተ መጽሓፍት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የወጣበት መሆኑም ተገልጿል፡፡ በ19 ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈውን ኪነ ሕንፃውን ገንብቶ ለማጠናቀቅ 18 ወራት መፍጀቱን፣ በአፍሪካ ውስጥ ከሚገኙት የመጀመርያዎቹ አሥር ቤተ መጻሕፍት ውስጥ አንዱ መሆኑንም ከንቲባ አዳነች ተናግረዋል፡፡ የመጻሕፍት መደርደሪያዎቹ ርዝመት 1.5 ኪሎ ሜትር እንደሚያህል ተገልጿል፡፡ በቤተ መጻሕፍቱ ውስጥ ከ400 ሺሕ በላይ መጻሕፍትን (ኢ-ቡክ)፣ ከ240 ሺሕ በላይ ወረቀት አልባ መጻሕፍትን፣ ከ360 ሺሕ በላይ አገራዊ ጥናታዊ ጽሑፎችን፣ ከ120 ሺሕ በላይ ዓለም አቀፍ ጥናታዊ ጽሑፎችን ማግኘት እንደሚቻልም ከንቲባዋ አብራርተዋል፡፡

በአንድ ጊዜ ከሁለት ሺሕ በላይ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችለው አብርሆት ቤተ መጻሕፍት ቤተ መጻሕፍት በውስጡ ዘመናዊ ካፊቴሪያ፣ የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ ነፃ ኢንተርኔት፣ አምፊ ቴአትርና ከአንድ መቶ በላይ መኪናዎችን የሚያስተናግድ ሥፍራ ይዟል፡፡ ለአጥቢ እናቶችና ለሕፃናት የማንበቢያ ልዩ ሥፍራ መዘጋጀቱን፣ ለዓይነ ሥውራን የብሬል መጻሕፍት እንዳለው ወ/ሮ አዳነች አስታውቀዋል፡፡

‹‹በጦርነቱ የወደሙ ትምህርት ቤቶችና የትምህርት ተቋማትን እንዴት ትንሳዔ እንደምንሰጣቸው ይኼ ቤተ መጻሕፍት ምስክር ነው፤›› ያሉት ከንቲባዋ፣ ለቀጣይ 100 ዓመታት ዋስ የሚሆን ቤተ መጻሕፍት መገንባቱን ተናግረዋል፡፡

በቅርፃ ቅርፆችና ሐውልት የተዋበው አብርሆት ቤተ መጻሕፍት በመግቢያው ላይ ያሉት ሰባት ዓምዶች በ18 ቋንቋዎች ጥበብ የሚል ቃላት ተጽፈውባቸዋል፡፡ በዓለም ላይ ካሉ የራሳቸው መጻፊያ ፊደል ካላቸው 18 አገሮች ውስጥ አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ይህንን ለማሳየት ሲባል በቤተ መጻሕፍቱ መግቢያ ባሉ ዓምዶች ላይ በሁሉም ፊደላት የተጻፉ ቃላት መቀመጣቸውን ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአፍሪካ ኅብረት ያሉት የሥራ ቋንቋዎች ሁሉም በሚባል ደረጃ አፍሪካዊ እንዳልሆኑ ተናግረው፣ የአፍሪካ ቋንቋ የአፍሪካ ኅብረት የሥራ ቋንቋ አለመሆኑን በንግግር ከማሳመን በእንዲህ ዓይነት መንገድ ማሳየት ብዙዎችን ሊያነቃ እንደሚችል አክለው ገልጸዋል፡፡

ዓብይ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ከተገነቡ ፋይዳ ካላቸው ግንባታዎች ውስጥ አንዱ አብርሆት ቤተ መጻሕፍት መሆኑን ከተናገሩ በኋላ፣ ‹‹ከዚህ በትልቅነቱና በጥራቱ የሚበልጠው ከሸራተን ከፍ ብሎ እየተገነባ ያለው የሳይንስ ሙዚየም ነው፤›› ብለዋል፡፡ መንግሥት ቤተ መጻሕፍቱ፣ የሳይንስ ሙዚየምና ፓርኮችን የያዘው የቤተ መንግሥት አካባቢ የቱሪስት ማዕከል እንዲሆን ፍላጎት እንዳለው ያነሱት ዓብይ (ዶ/ር)፣ ቤተ መንግሥቶቹ ታሪክ የሚጠናባቸው እንዲሆኑ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከዚህ አካባቢ እንደሚነሱ ጠቁመዋል፡፡

የአብርሆት ቤተ መጻሕፍት ይነት ግንባታዎችን መጀመርና መጨረስ ብቻ ሳይሆን መገልገልና መጠበቅ እንደሚገባ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የከተማዋ ነዋሪዎችና በከተማዋ ውስጥ ያሉ ተቋማት በቅርበት ቤተ መጻሕፍቱን እንዲከታተሉና እንዲጠብቁ አሳስበዋል፡፡ ከንቲባ አዳነች በበኩላቸው ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲልኩ፣ ተመራማሪዎችም አሻራቸውን በቤተ መጻሕፍቱ ውስጥ እንዲያሳርፉ ጠይቀዋል፡፡

የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ታከለ ኡማ ያስጀመሩትና በ18 ወራት ውስጥ ግንባታው የተጠናቀቀው አብርሆት ቤተ መጻሕፍት ቫርኔሮ ኮንስትራክሽን በተሰኘው ተቋራጭ የተገነባ ሲሆን ኬቱኤ ኢንጂነሪንግና አርክቴክት አማካሪ ድርጅት የሕንፃው ንድፍ ላይ በአማካሪነት መሳተፉ ተገልጿል፡፡ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች በቤተ መጻሕፍቱ ግንባታ ላይ አስተዋፅኦ ላደረጉት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ ትምህርት ሚኒስቴርና የአዲስ አባባ ከተማ የትልልቅ ፕሮጀክቶች ጽሕፈት ቤት ምሥጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...