በብሩክ አብዱና በአማኑኤል ይልቃል
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ)፣ ከመንግሥት መዋቅር ጋር ትይዩ የሆነ የካቢኔ አባላት ያሉት የመንግሥት መዋቅር መዘርጋቱን አስታወቀ፡፡
ፓርቲው ይኼንን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ‹‹የትይዩ ካቢኔ›› ብሎ የሰየመውንና ከመንግሥት ተቋማት ሹማምንት ጋር ተመሳሳይ ኃላፊነት ያላቸው ነገር ግን መንግሥታዊ ሥልጣን የሌላቸውን የካቢኔ አባላት የያዘ መዋቅር ማዋቀሩን ገልጿል፡፡
ኢዜማ መግለጫውን ከማውጣቱና መዋቅሩን ይፋ ከማድረጉ አስቀድሞ ሰኞ ታኅሳስ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ፣ የፓርቲው አባላት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሕንፃ በሰማያዊና በግራጫ ቀለሞች ተሥሎ የሚታይበትን ምሥል በየማኅበራዊ ገጾቻቸው ሲለጥፉ የነበረ ሲሆን፣ አባላቱ ለምን ይኼንን እያደረጉ እንደሆነ የተጠየቀው ፓርቲው፣ በተመሳሳይ ቀን ማምሻውን መግለጫ እንደሚያወጣ አስታውቆ ነበር፡፡ ሆኖም ፓርቲው መግለጫውን ያወጣው ማክሰኞ ታኅሳስ 26 ቀን 2014 ዓ.ም. ጠዋት ነበር፡፡
ፓርቲው ያወጣው መግለጫ፣ ‹‹አንድ ፓርቲ መንግሥት ሲሆን ሊያደርጋቸው የሚችላቸውን ወሳኝ ሥራዎች ለመሥራት አስቀድሞ ራሱን በመንግሥት ጫማ ውስጥ በማስቀመጥ፣ በመንግሥታዊ ቁመናና ቅርፅ ራሱን ማደራጀት መቻሉ ትልቅ ሚና ሊጫወትለት እንደሚችል ከሌሎች አገር ልምዶች ማየት ይቻላል፤›› በማለት የተመሠረተውን መዋቅር የሚያብራራ ሲሆን፣ ‹‹የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት መገንባትን እንደ ትልቅና ወሳኝ ቁም ነገር ለሚወስድና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ያለ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና አማራጭ ሐሳቦች ማሰብ እንደማይቻል ለሚገነዘብ እንደ ኢዜማ ላለ ፓርቲ፣ የመንግሥት ሥልጣንን ቢይዝ ያሉትን አማራጭ ሐሳቦች ለሕዝብ የሚያሳይበት አደረጃጀትና መዋቅር መፍጠር መቻል በቀጣይ ምርጫ እንደ ሀቀኛ ተፎካካሪ እንዲቆጠር ከማድረግም ባለፈ፣ የሠለጠነ ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካን ለአገራችን ለማስተዋወቅና ለማጎልበት ከፍተኛ በጎ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፤›› ሲል ምክንያቱን ያስረዳል፡፡
በአውሮፓ አገሮች በተለይም በእንግሊዝ ‹‹ሻዶ ካቢኔ›› ወይም ‹‹ሻዶ ሚኒስቴር›› (Shadow Cabinet or Shadow Ministry) በተቃዋሚ ፓርቲዎች ተመሥርቶ ‹‹ተጠባባቂ መንግሥት›› የሚባል ሲሆን፣ ለእያንዳንዱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ትይዩ የሆኑ የተቃዋሚ ሹማምንት ይቀመጣሉ፡፡ የእንግሊዝ ፓርላማ ድረ ገጽ እንደሚያስረዳው፣ የሻዶ ካቢኔት አባላት በተቃዋሚ ፓርቲው መሪ የሚመደቡ ይመደባሉ፡፡ እያንዳንዱ አባል በፓርቲው የተለየ የፖሊሲ ዘርፍ እንዲመራ የሚመደብ፣ በመደበኛው ካቢኔ ውስጥ ያሉ ሚኒስትሮች የሚሠሩትን እንዲጠይቅና እንዲከታተል የሚያደርግ አደረጃጀት ነው፡፡ በዚህም አግባብ ተቃዋሚው መንግሥት ለመሆን በመጠባበቅ ላይ ያለ አማራጭ እንደሆነም ያሳያል፡፡ የእንግሊዝ የሌበር ፓርቲ ተመሳሳይ መዋቅር 32 አባላት ያሉት አደረጃጀት ነው፡፡ ሆኖም ትይዩ ካቢኔ በመደበኛው አደረጃጀት ካሉ የካቢኔ ቁጥሮች ጋር መተካከሉ የግድ እንዳልሆነ፣ ተቃዋሚ ፓርቲው ያስፈልገኛል ብሎ ያሰበውን የፖሊሲ ዘርፍ መርጦ ለተመረጡት ብቻ ትይዩ ካቢኔ ማዋቀር እንደሚችል የእንግሊዝ ኢንስቲትዩት ፎር ገቨርመንት ያትታል፡፡
ኢዜማ በበኩሉ 22 አባላት ያሉት አደረጃጀት የመሠረተ ሲሆን፣ የቆይታ ዘመናቸውም በሕገ መንግሥቱ የአንድ መንግሥት የቆይታ ጊዜ የሆነው አምስት ዓመት እንደሆነ ተነግሯል፡፡
የትይዩ ካቢኔ ጸሐፊ አቶ ይመስገን መሣፍንት ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በመንግሥት ሹመት የተሰጣቸው የፓርቲው አባላት በዚህ ትይዩ ካቢኔ ውስጥ እንደሚኖሩና በፓርቲው መሪ ሥር የሚዋቀር አደረጃጀት ነው፡፡ ከመደበኛ የመንግሥት መዋቅር ጋር ከሰነድ ልውውጥ የዘለለ ግንኙነት እንደማይኖራቸውም አስታውቀዋል፡፡
ታዋቂው የሕግ ምሁርና ተንታኝ አደም ካሴ (ዶ/ር) የኢዜማን ውሳኔ አስመልክተው በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ምልከታ፣ ይኼ አሠራር እንደ እንግሊዝ ባሉ ሁለት ፓርቲ ባለባቸው አገሮች የተለመደ እንደሆነ በመጠቆም፣ የፓርቲው መሪ የሚመራው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
አደም (ዶ/ር) አክለውም፣ ‹‹ለይፋዊ የተቃዋሚ መሪ ዕውቅና መስጠት፣ ተቃዋሚዎችንና ሚናቸውን ማጠናከር፣ ተቃዋሚዎችን በመንግሥት ካቢኔ ውስጥ ከማካተት ያላነሰ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል፤›› ብለው፣ ‹‹ለወደፊት በአገር፣ በክልልና በአካባቢ ደረጃ አሸናፊ ፓርቲ ሁሉን ጠቅልሎ የሚወስድበትን የፖለቲካ ሥርዓት ለመቀየር ቁልፍ ተገማች መሆን ይኖርበታል፤›› በማለት ያሳስባሉ፡፡
ሆኖም አሁን በኢዜማ የተመሠረተው ትይዩ ካቢኔ ለጀርመን የባለሙያዎች ምክር ቤት ቀረቤታ ያለውለ ነው ይላሉ፡፡
የጀርመን የባለሙያዎች ምክር ቤት ከተመሠረቱለት የኢኮኖሚ ዘርፍ አንዱ ሲሆን፣ ይህ ምክር ቤት እ.ኤ.አ. በ1963 የተመሠረተ ነበር፡፡ ምክር ቤቱ ከየትኛውም የመንግሥትና የፓርቲ ተፅዕኖ ነፃ የሆነ ሲሆን፣ ሳይንሳዊ ጥናት በማድረግ ለፖሊሲ ውሳኔዎች ግብዓት ይሰጣል፡፡ ይኼም ኮሚሽን በሕግ ከሚቀመጡለት ዓላማዎች በስተቀር ምንም ዓይነት መንግሥታዊ ሥልጣን እንደሌለውና ሳይንሳዊ ግኝቶቹን በአግባቡ ካልተነተነና አናሳ ድምፅ ያላቸውን አባላቶቹን ሐሳብ ሳያካትት ከቀረም፣ በሕግ የተሰጠውን ጥበቃ ሊያጣ እንደሚችል በ1973 የጀርመን ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ምክር ቤት አባል ሆነው ለስድስት ዓመታት ያገለገሉት ኸርበርት ጌርሽ ባሳተሙት ጥናት አስረድተዋል፡፡
ኢዜማ በበኩሉ ያቋቋመውን የሻዶ ካቢኔ በተመለከተ ባወጣው መግለጫ የእንግሊዝን አሠራር ከግምት እንዳስገባ የጠቆመ ሲሆን፣ ‹‹ከአገራችን ወቅታዊና ሕጋዊ ሁኔታ አንፃርም የተፎካካሪ ፓርቲነት መዋቅር፣ ልምድ፣ ሰነዶችና መሰል የካበቱ አሠራሮች ባለመኖራቸው ፓርቲዎች ቁመናቸውን በዚህ ልክ ከፍ ማድረግ የሚችሉበት ዕድል ባለመኖሩ ትይዩ/ጥላ ካቢኔ ሳይሞከር ቆይቷል፤›› ሲል አስፈላጊነቱን ያስረዳል፡፡
ፓርቲው አክሎም፣ ‹‹ተፎካካሪ ፓርቲዎች በአመዛኙ ምርጫ ሲቃረብ ካልሆነ በቀር ገንቢ ሚናቸውን ማሳየት ሳይችሉ፣ አማራጭ ሐሳቦቻቸውን ለሕዝብ በቋሚነት ሳያደርሱ፣ እንዲሁም ራሳቸውን በዕውቀትና በመንግሥትነት ልምድ ሳያሳድጉ በመጨረሻው የምርጫ ዓመት ብቻ አቧራቸውን አራግፈው ከመንቀሳቀስ በቀር ቀጣይነት ያለው ሥራ ሳይሠሩ ቆይተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ሐሳብን መሠረት አድርጎ የመፎካከር ፖለቲካ በአገራችን ሥር ሳይሰድ ጭንጫ ላይ እንደበቀለ ተክል የመጣው ንፋስ ሁሉ ሲወስደው ቆይቷል፡፡ ፓርቲዎች ራሳቸውን በጠንካራ መሠረት ላይ ለማኖርና በማንኛውም ወቅት ከአንድ ተፎካካሪ ፓርቲ የሚጠበቀውን አማራጭ ሐሳብ የማፍለቅ ሥራ ለመሥራት፣ አማራጭ መዋቅራዊ መንገዶችን ማሰስና መተግበር ይጠበቅባቸዋል፤›› ሲል አስገንዝቧል፡፡
አቶ ይመስገን እንደሚያስረዱት፣ ኢዜማ ያቋቋመው ትይዩ ካቢኔ ሦስት መሠረታዊ ሥራዎችን የሚሠራ ሲሆን አንደኛው እንደ ጤና፣ ትምህርትና ግብርና ባሉ ዘርፎች መንግሥት ምን ሠራ የሚለውን መገምገምና አስተያየት መስጠት ነው፡፡ በትይዩ ካቢኔ ውስጥ እያንዳንዱን ዘርፍ የሚመሩ ትይዩ ሚኒስትሮችና ቡድናቸው እንደተቋቋመና የመንግሥት ሥራን ገምግሞ መግለጫና አስተያየት ሊሰጥ ይችላል ብለዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ትይዩ ካቢኔው ኢዜማ በፓርላማ ውስጥ ያሉት አባላቱ የሚረቀቁ ሕጎች ላይ አስተያየት በሚጠየቁበት ጊዜ፣ ሕጉን የሚመለከተው ዘርፍ ትይዩ ሚኒስትርና ቡድኑ ተወያይቶ የፓርቲውን አቋም በፓርላማ አባላቱ በኩል እንዲያቀርብ እንደሚደረግ አቶ ይመስገን ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ ምርጫ ኢዜማ የሚያቀርበውን አማራጭ ፖሊሲ የሚያዘጋጀው ይኼው ካቢኔ መሆኑን ገልጸው፣ ካቢኔው በአምስት ዓመታት ቆይታው ይኼንን እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡
ትይዩ ካቢኔው የሚመራው በኢዜማ የመሪ መዋቅር በኩል መሆኑን ያስረዱት አቶ ይመስገን፣ በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት የትይዩ ካቢኔ አባላትን የሚያቀርቡት የፓርቲው መሪ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ይሁንና የኢዜማ መሪ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) በትምህርት ሚኒስትርነታቸው ካለባቸው የሥራ ጫና አንፃር አባል የሚሆኑ ሰዎችን የሚያቀርብና ተወያይቶ የሚያፀድቅ፣ የፓርቲውን መሪና ምክትል መሪውን ጨምሮ አምስት አባላት ያሉት ጽሕፈት ቤት መዋቀሩን አስረድተዋል፡፡
ፓርቲው በትይዩ ካቢኔ ውስጥ የአባልነት ሥልጣን የሰጣቸውን አባላቱን ዝርዝር እስካአሁን ባያስታውቅም፣ ትይዩ ካቢኔው ከጥቅምት 8 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ሥራ እንደጀመረ ተገልጿል፡፡ የጤና ትይዩ ሚኒስትሩና ቡድናቸውም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበው የጤና መድን አዋጅ ላይ እየተወያዩ መሆናቸውን አቶ ይመስገን አስረድተዋል፡፡
የኢዜማ ትይዩ ካቢኔ በተለያዩ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ተጠቃሚዎች ዘንድ ትኩረትን የሳበ ሲሆን፣ በተለይ የኢዜማ አባል የመንግሥት ካቢኔ ውስጥ ተካትተው ሳለ በአንድ በኩል ፖሊሲ እያስፈጸሙ በሌላ ወገን ደግሞ ሊተቹ ነው ወይ ሲሉ የሚጠይቁ ነበሩ፡፡
ይኼንን አስመልክተው ‹‹የግል አስተያየት›› በፌስቡክ ገጻቸው ያሠፈሩት የኢዜማ ሥራ አስፈጻሚ አባልና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ግርማ ሰይፉ፣ ‹‹መጀመሪያ በሃያ አንድ ትይዩ ካቢኔ ሚኒስቴር ቦታዎች ውስጥ በአንዱ ውስጥ ኢዜማ ስለሚገኝ፣ በሌሎቹ ላይ ትርጉም ያለው የክትትልና ግምገማ ሥራ ለመሥራት የሚከለክል አሠራር ሊኖር አይችልም፡፡ በእንግሊዝ ጥምር መንግሥት ቢመሠርቱ የሻዶ ካቢኔ ተግባር ሊቆም እንደማይችል እናውቃለን፡፡ በእንግሊዝ ትይዩ ካቢኔ በሕግ ድጋፍ ያለው አደረጃጀት ነው፡፡ በተመሳሳይ አንድ ሰው ሳይሆን ብዙ የሚኒስትር ቦታዎች በካቢኔ ውስጥ ቢኖረንም፣ የተለየ የፓርቲ ሐሳብ ለማራመድና ለሕዝብ ለመንገር የሚከለክል አሠራር የለም፡፡ የትይዩ ካቢኔ ሥራ መቃወም ብቻ ሳይሆን፣ አማራጭ የተለዩ ሐሳቦች ቢታዩ ብሎ መጠቆም መሆኑን መዘንጋት አያስፈልግም፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡