Friday, March 1, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሕገወጥ ዕርድ ምክንያት ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ እንደሚያጣ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ቄራዎች ድርጅት ከ5,000 በላይ የእንስሳት ዕርድ እንደሚያቀርብ አስታወቀ

ሕገወጥ የእንስሳት ዕርድ ለአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት እንደ ማነቆ፣ ለከተማ አስተዳደሩ ደግሞ አሳሳቢ ችግር መሆኑንና የከተማ አስተዳደሩ ከግብር በዓመት ማግኘት የሚገባውን ከ1.53 ቢሊዮን ብር ገቢ እንደሚያጣ ተገለጸ፡፡

ቄራዎች ድርጅት ከአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች ማኅበር ጋር በመተባበር ለገና በዓል እየተደረጉ በሚገኙ ቅድመ ዝግጅቶች ላይ፣ በድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤት ማክሰኞ ታኅሳስ 26 ቀን 2014 ዓ.ም. መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ወ/ሪት ርብቃ ማስረሻ፣ ድርጅቱ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ከ2,500 እስከ 3,000 የሚደርሱ የዳልጋ ከብቶችን፣ እንዲሁም ከ1,500 እስከ 2,000 የሚሆኑ ትንንሽ እንስሳት ተብለው የሚጠሩትን የበግና የፍየል ዕርዶችን ለማከናወን አቅዷል ብለዋል፡፡

በዓሉን ምክንያት በማድረግ ብቻም ሳይሆን በማንኛውም ወቅት የሚደረግ ዕርድ ከመከናወኑ በፊት ድርጅቱ የሚያደርጋቸው ሁለት ዓይነት የሥጋ ምርመራዎች እንዳሉ ያስረዱት ወ/ሪት ርብቃ፣ እንስሳቶቹ ለዕርድ አገልግሎት ከመቅረባቸው በፊት በቁም በሚደረግላቸው ቅድመ ምርመራና ከዕርድ በኋላ ሥጋው ተመርምሮ  ወደ ኅብረተሰቡ የሚሠራጭበት ድኅረ ምርመራ ነው፡፡

ቄራዎች ድርጅት ይህንን ሒደት የሚከታተሉ 40 የሚደርሱ የእንስሳት መርማሪ ባለሙያዎች እንዳሉት የተገለጸ ሲሆን፣ በዚህ ሒደት ያለፈ የዕርድ አገልግሎት የኮቪድንም መስፋፋት ከግንዛቤ በመክተት ከበፊቱ በተለየ መልኩ ጥንቃቄ በማድረግ የሚከናወን እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችን በመከላከል ጤንነቱ በሕክምና የተረጋገጠ የዕርድ አገልግሎት ለኅብረተሰቡ ለማቅረብ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል ያሉት ወ/ሪት ርብቃ፣ በመሆኑም የድርጅቱ የዕርድ አገልግሎትና ተረፈ ምርት ሠራተኞች ሙሉ የጤና ምርመራ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡

ከሠራተኞች ባሻገር የዕርድ ክፍሎች ፀረ ተህዋሲ በሆኑ ኬሚካሎች እንዲፀዱ መደረጉ የተገለጸ ሲሆን፣ የዕርድ ማሣሪያዎችም እንዲሁ ዕርድ ከመከናወኑ ከሰዓታት ቀደም ብሎ ከፀረ ተህዋሲ ማንፃት (ሳኒታይዝ) እንደሚደረግ ተብራርቷል፡፡ ሰላሳ አምስት የድርጅቱ ሥጋ ማመላለሻ ተሸርካሪዎችም እንዲሁ ሙሉ በሙሉ የኬሚካል እጥበት እንደሚደረግላቸው ተገልጿል፡፡

ድርጅቱ ከዕርድ አገልግሎት ባሻገር የስጋ ዋጋ ማረጋጋት ሥራ እንደሚሠራ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም በአራት መደብሮቹ ልኳንዳ ቤቶች ከሚሸጡበት ባነሰ ዋጋ የበሬ፣ የበግና የፍየል ሥጋዎችን በበዓሉና ከበዓሉ ቀጥሎ ባሉት ቀናት እንደሚያቀርብ ተጠቅሷል፡፡

የአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አየለ ሳህሌ ለሪፖርተር በሰጡት አስተያየት፣ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች በርካታ ኢትዮጵያውያን እንግዶች በመምጣታቸው የሥጋ ፍላጎት እንደሚያይልና ይህንን ፍላጎት መሠረት በማድረግ ልኳንዳ ቤቶች በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ ከአባላት ጋር ምክክሮች ተደርገዋል ብለዋል፡፡

ማኅበሩ 5,550 አባላት እንዳሉት የተናገሩት አቶ አየለ፣ በአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅትና በአቃቂ ቄራዎች ድርጅት የሥጋ ንፅህና አጠባበቅን በተመለከተ 23 ሠራተኞችን በማሰማራት ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡

የልኳንዳ ነጋዴዎች ዋጋ ከቁም እንስሳት ግብይት ዋጋ ከፍና ዝቅ ማለት ጋር የሚገናኝ እንደሆነ ያስታወቁት አቶ አየለ፣ ሆኖም የልኳንዳ ነጋዴዎች ከኅብረተሰቡና ወደ አገር ውስጥ ከገቡት እንግዶች ጋር በመተሳሰብና በመተዛዘን ላይ የተመሠረተ ዋጋ ያቀርባሉ ብለው እንደሚያምኑ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች