ከአዲስ አበባ ከተማ በ164 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘውና የሰሜን ሸዋ ዞን ሞረትና ጅሩ ወረዳ መቀመጫ ከሆነችው እነዋሪ ከተማ አቅራቢያ ያለ ሰፊ እርሻ ላይ፣ ጤፍና ስንዴ የሚያመርቱት አርሶ አደር አቶ እንደራስ ቸርነት በመስከረም ወር ከዘመቱበት የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከተመለሱ ጥቂት ጊዜያቸው ነው፡፡ በክረምቱ ወራት የለፉበትን እርሻ ትተው ወደ ጦርነት ዘመቻው ሲያቀኑ፣ ባለቤታቸው እርሻውን በሽቦና በእንጨት ቢያሳጥሩትም ከሄዱበት ዘመቻ ሲመለሱ አጥሩ ተነቃቅሎ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ‹‹ስመለስ እርሻው ተበልቶ ሳየው አዝኛለሁ›› የሚሉት አቶ እንደራስ የአከባቢው ሰዎች ስንዴ እርሻቸውን ቢሰበስቡላቸውም የጤፍ እርሻቸውን ሳይታጨድ ሰንብቷል፡፡ ‹‹አማራጭ ስላልነበረኝ አጫጆችን ለመቅጠር አስቤ ነበር›› ያሉት አርሶ አደሩ፣ ለዚህም በቀን እስከ 3,000 ሺሕ ብር ያወጡ እንደነበር እንስተዋል፡፡ በመንግሥት ደረጃ የተጀመረው የዘማች አርሶ አደሮችን ሰብል የመሰብሰብ ሥራ ከዚህ ወጪ ታድጓቸዋል፡፡ ታኅሳስ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ወደ አከባቢው ያቀኑት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ሠራተኞች በአንድ ቀን ውሎ ከአንድ ሄክታር በላይ በሆነ መሬት ላይ የበቀለውን ሰብላቸውን በመሰብሰብ ረድተዋቸዋል፡፡