ወደ ባንክ ለመሸጋገር ዝግጅት እያደረገ ያለው አዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም በተጠናቀቀው የ2013 የሒሳብ ዓመት 490 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አመላከተ፡፡
ከተቋሙ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በሒሳብ ዓመቱ ያገኘው ትርፍ ከቀዳሚው 2012 የሒሳብ ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ64 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡
እስከ በ2013 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ድረስ በተበዳሪዎች እጅ ያለው አጠቃላይ የብድር መጠኑ 5.02 ቢሊዮን ብር መሆኑን ከተቋሙ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ከዚህ ውስጥ ሥጋት ላይ ያለ ብድር ምጣኔ 4.9 በመቶ መሆኑን የሚያመለክተው የተቋሙ መረጃ፣ ይህ ሥጋት አለ ከተባለው የብድር ምጣኔ መጠኑ፣ በዓለም አቀፍ የብድር አመላለስ ሥሌት መሠረት ጤናማ የሚባል መሆኑንም ይጠቅሳል፡፡ ወደ 95.1 በመቶ የሚሆነው ብድር ማስመለስ ስለመቻም ይገልጻል፡፡
ተቋሙ በአሁኑ ወቅት ወደ ባንክ ያድጋሉ ተብለው ከሚጠበቁ የብድርና ቁጠባ ተቋማት መካከል አንዱ ሲሆን፣ ለዚህም የተለያዩ የዝግጅቶችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አስታወቋል፡፡
በብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት መደበኛ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶችን እያደረገና አስፈላጊ ናቸው የተባሉ መሠረተ ልማቶችን በተለያዩ መልኩ እያሟላ የሚገኝ መሆኑም ተገልጿል፡፡ ወደ ባንክ ለማደግ ውሳኔ ተላልፎ የካፒታል መጠኑ እንዲያድግ ከማድረግ ባሻገር ለኮር ባንኪንግ መሠረተ ልማት የሚያስፈልጉ መሥፈርቶችን ለማሟት እየሠራ ስለመሆኑም ተጠቅሷል፡፡
ተቋሙ ከዚህ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ካፒታሉን ወደ አሥር ቢሊዮን ብር ለማድረስ የወሰነ ሲሆን፣ ተቋሙን ወደ ባንክ ለማሳደግ በተወሰነው ውሳኔ መሠረት በአሥር ቢሊዮን ብር የተመዘገበ ካፒታልና በ3.7 ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ‹‹ባንክ ኦፍ አዲስ›› በሚል ስያሜ ወደ ባንክ አገልግሎት ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የአዲስ ብድርና ተቋም አ.ማ. የአዲስ አበባ አስተዳደርን ጨምሮ አሥራ አንድ ባለአክሲዮኖችን የያዘ ሲሆን፣ እስከ ሰኔ 2013 መጨረሻ ድረስ አጠቃላይ የሀብት መጠኑ 7.7 ቢሊዮን ብር እንደደረሰም አመላክቷል፡፡
አዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም በአዋጅ ቁጥር 40/1996 መሠረት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ በማግኘት የብድርና ቁጠባ አገልግሎት ለመስጠት እ.ኤ.አ. ጥር 27,200 በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን ሥራ አጥነት ለመቅረፍና ድህነትን ለመቀነስ ዓላማ አድርጎ መቋቋሙ ይታወቃል፡፡