ከድምፃዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ሻሸመኔ፣ አርሲ ነገሌ፣ ባሌና የተለያዩ አካባቢዎች በሚኖሩ የሌላ ብሄር ተወላጆች ላይ በተፈጸመ ግድያና የንብረት ውድመት ጋር በተያያዘ ከሰኔ 22 ቀን 2012 ዓም ጀምሮ ታስረውና ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩት አቶ ጃዋር መሀመድ፣ በቀለ ገርባ፣ ሀምዛ መሀመድን ጨምሮ 24 ተከሳሾች ዛሬ ታህሣሥ 29 ቀን 2014 ዓም በምህረት ተፈቱ።
በተያያዘ ዜና በሰሜን ዕዝ መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓም ከደረሰው ጥቃት ጋር በተያያዘ ከተፈጠረው ጦርነት ምክንያት በቁጥጥር ሥር ውለው ክስ የተመሰረተባቸው አቶ ስብሐት ነጋ፣ወሮ ቅዱሳን ነጋ ፣ አቶ ዓባይ ወልዱ፣ አቶ አባዲ ዘሙ፣ወሮ ሙሉ ገብረ እግዚአብሔር ፣አቶ ኪሮስ ሐጎስን ጨምሮ ሌሎቹም ተከሳሾች በምሕረት እንዲፈቱ መወሰኑ ታውቋል
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ማምሻውን በሰጠው ሰጠ መግለጫ እንዳስታወቀው፣የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋትና ለአካታች ሀገራዊ ምክክር ሲል መንግሥት በምሕረት የፈታቸው አካላትም፣ ካለፈው የጥፋት መንገድ ተምረው፣ የተሻለ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ አስተዋጽዖ በማድረግ፣ ሀገራቸውንና ሕዝባቸዉን ይክሳሉ ብሎ መንግሥት ያምናል። ከግጭትና ከከፋፋይ መንገዶች ይልቅ ለሰላማዊ ፖለቲካ የበኩላቸውን እንደሚያደርጉም መንግሥት ተስፋ ያደርጋል። መንግሥት ይሄንን ውሳኔ በአንድ በኩል ሲወስን በሌላ በኩል ደግሞ ያለፉ ዋጋ አስከፋይና ግጭት ጠማቂ አካሄዶች በጭራሽ እንዲደገሙ አይፈቅድም። ፍትሕና ምሕረትም በየሚዛናቸው እንዲጓዙ መንግሥት ይፈልጋል። በሂደቱ የተጎዱ ወገኖች እንደሚኖሩ መንግሥት ያምናል። የእነዚህ ተጎጂ ዜጎች ቁስል በሽግግር ፍትሕ የሚካስ ይሆናል። እነዚህ ተጎጂ ዜጎች ሕመማቸው ለኢትዮጵያ የከፈሉት ዋጋ በመሆኑ ሸክማቸውን መንግሥትና ሕዝብ በጋራ እንሸከምላቸዋለን። ከእሥር የተፈቱ ወገኖችም ጭምር የተጎጂዎችን ሸክም የመሸከም ዕዳ አለባቸው። መንግሥት ይሄንን ውሳኔ የወሰነው በዋናነት ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ ነው። ኢትዮጵያ የመሐሪነቷን ዋጋ እንድታገኝ፣ የኢትዮጵያን ምሕረት ያገኙት አካላት፣ ምሕረቱን ያገኙበትን ዋጋ ይረዱታል ብሎ መንግሥት ያምናል። የኢትዮጵያ ነባር ችግሮች የሚፈቱት በሰላማዊ ፖለቲካዊ ተዋሥኦ፣ በሆደ ሰፊነትና አዎንታዊ ሚናን በመጫወት ነው። ለዚህ ደግሞ መንግሥት ዋጋ ከፍሎም ቢሆን ቅድምናውን ይወስዳል። ዛሬም ለዘላቂ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና ሰላም ሲል መንግሥት የተወሰኑ እሥረኞችን በምሕረት መፍታቱን አብራርቷል።