ፋብሪካዎች ከአቅማቸው 50 በመቶ በታች እያመረቱ መሆናቸውን ይናገራሉ
የመድኃኒትና የሕክምና ግብዓት አስመጪዎች እየተዘጉ ነው
ባለፉት አራት ወራት በመድኃኒቶችና በሕክምና ግብዓቶች ላይ እስከ 40 በመቶ የሚደርስ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን የመድኃኒት አምራቾች፣ አቅራቢዎችና ተጠቃሚዎች ለሪፖርተር ተናገሩ፡፡
በአገር ውስጥ የሚመረቱም ሆነ ከውጭ የሚመጡ መድኃኒቶችና የሕክምና ግብዓቶች እጥረት መከሰቱን፣ 40 በመቶ የሚደርስ የዋጋ ጭማሪም መታየቱን የመድኃኒት አምራቾችና አቅራቢዎች ገልጸዋል፡፡
የሃቨን መድኃኒት ቤት የሽያጭና የፋርማሲ ባለሙያ ወ/ሪት ሐያት ብርሃኑ፣ በተለይ የአገር ውስጥ መድኃኒቶች እጥረት መኖሩንና በዋጋቸውም ላይ ጭማሪ መታየቱን ገልጸው፣ ከውጭ የሚመጡ መድኃኒቶችንም ቢሆን በበቂ ሁኔታ ማግኘት አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡
እንደ ጓንትና ፋሻ የመሳሰሉ የሕክምና ግብዓቶችን ከዚህ በፊት ያቀርቡ እንደነበር፣ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ዋጋቸው ከመጨመሩም በላይ በገበያ ውስጥ ለማግኘት አስቸጋሪ በመሆናቸው በመድኃኒት ቤቱ መሸጥ ማቆማቸውን ገልጸዋል፡፡
አልፋ ሜድ የመድኃኒትና የሕክምና ግብዓቶች አስመጪ ከህንድና ከአሜሪካ የሕክምና ግብዓቶችንና መድኃኒቶችን በማስመጣት ከስድስት ዓመታት በላይ ቢቆይም፣ ካለፉት አምስት ወራት ወዲህ ግን በተፈጠረበት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ምርቶችን ከውጭ ማስመጣት ባለመቻሉ ድርጅቱ ሙሉ ለሙሉ መዘጋቱን የድርጅቱ የቢዝነስ አማካሪ ወ/ሮ ህልዳና ታደሰ ገልጸዋል።
«መድኃኒትና የሕክምና ግብዓቶችን ለማስመጣት የውጭ ምንዛሪ እንዲቀርብ ቢባልም፣ ከባንኮች የውጭ ምንዛሪ ስላላገኘን ምርቶቹን ማስመጣት አዳጋች ሆኗል፡፡ በዚህም ምክንያት ድርጅታችንን ዘግተን ሌላ ቢዝነስ ውስጥ ገብተናል፤» ብለዋል።
የኢትዮጵያ መድኃኒት ፋብሪካ በበኩሉ ባጋጠመው የግብዓት እጥረት ምክንያት መድኃኒቶችን ለማምረት መቸገሩን አስታውቋል። የፋብሪካው ዋና ሥራ አስፈጻሚ መሐመድ ኑሪ (ዶ/ር) ለፋብሪካው የሚያስፈልጉ 95 በመቶ ግብዓቶች ከውጭ የሚመጡ በመሆናቸው፣ በዚህ ወቅት የተባባሰ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በመኖሩ ፋብሪካው ከ50 በመቶ በታች በሆነ አቅሙ እያመረተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የመድኃኒት ፍላጎት በአገር ውስጥ አምራቾች የሚሸፈነው ከአሥር በመቶ በታች መሆኑን የገለጹት መሐመድ (ዶ/ር)፣ በዋጋም መሠረታዊ ከሚባሉት መድኃኒቶች በስተቀር ከ30 እስከ 40 በመቶ ጭማሪ መኖሩን አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ መድኃኒት የሚያመርቱ አሥር ፋብሪካዎች ቢኖሩም፣ የአገር ውስጥ ፍላጎትን ለመሸፈን ባለመቻላቸው ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት መድኃኒቶች በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት (የቀድሞ ኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ) አማካይነት ከውጭ እየተገዙ ለመንግሥት ጤና ተቋማት እንደሚሠራጩ መረጃዎች ያሳያሉ።
የመድኃኒቶችን እጥረትና የዋጋቸውን ጭማሪ በተመለከተ የአገልግሎቱ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኑኬሽን ኃላፊ አቶ አወል ሐሰን፣ ‹‹በተለያዩ መድኃኒቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ መታየቱ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን አገልግሎቱ ትኩረት አድርጎ የሚሠራው በመንግሥት ጤና ተቋማት ላይ በመሆኑ ለግል መድኃኒት ቤቶችና ሆስፒታሎች ማቅረብ አይችልም፤›› በማለት፣ ቀሪው የሚሸፈነው በተለያዩ አምራቾችና አስመጪዎች አማካይነት መሆኑን አስረድተዋል።
«መድኃኒቶቹና የሕክምና ግብዓቶቹ በአገር ውስጥ በብዛት እንዲመረቱ አገልግሎቱ ድጋፍ ያደርጋል፤» ያሉት አቶ አወል፣ ነገር ግን የውጭ ምንዛሪና የግብዓት እጥረት ከፍተኛ ማነቆ ሆኗል ብለዋል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ ለ1,020 ያህል የመድኃኒት ዓይነቶችን በመግዛት ለ5,000 የጤና ተቋማት የሚያሠራጨው የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት፣ 38 በመቶ የሚሆነውን የአገር ውስጥ ምርት አቅርቦት የሚሸፍንለት የአዲግራት መድኃኒት ፋብሪካ በአሁኑ ጊዜ ስለማያመርት፣ እነዚህን ምርቶች ከውጭ ለማስመጣት ተገዷል ብለዋል።
የውጭ ምንዛሪ እንዲያገኙ በመመርያ ቅድሚያ ከተፈቀደላቸው ዘርፎች መካከል በፋርማሲዩቲካል ዘርፍ የተቀመጡት መድኃኒቶች፣ የመድኃኒት ማምረቻዎች፣ አምራቾች፣ ግብዓቶችና የቤተ ሙከራ ውሁዶች፣ እንዲሁም የላቦራቶሪ ኬሚካሎች ይገኙበታል፡፡
በዚህም መሠረት የመድኃኒት ዘርፍ የውጭ ምንዛሪውን በተገቢው መንገድ እያገኘ አይደለም የሚሉትን የዘርፉ ተዋንያንን ጥያቄ ሪፖርተር ለብሔራዊ ባንክ ያቀረበ ሲሆን፣ የባንኩ የውጭ ምንዛሪ ሞኒተሪንግና ሪዘርቭ አስተዳደር ዳይሬክተር ወ/ሮ የእኔሐሳብ ታደሰ፣ ለመድኃኒትና ለሕክምና ግብዓቶች 15 በመቶ የውጭ ምንዛሪ ተፈቅዷል ብለዋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረት መኖሩ የሚታወቅ ቢሆንም፣ በመመርያ የተፈቀደውን ያህል ባንኮች ቅድሚያ ሰጥተው እንዲያስተናግዱ ክትትል ይደረጋል በማለት፣ ቅሬታ ያለባቸው አካላት ቅሬታቸውን እያቀረቡ እንደሚታይላቸው አስታውቀዋል፡፡
«የውጭ ምንዛሪ ፍላጎቱ ከፍተኛ ቢሆንም ባንኮች ለአምራቾችም ሆነ ለአስመጪዎች መስጠት የሚችሉት፣ ባላቸው የምንዛሪ ግኝት መሠረት እንጂ በተፈለገው ልክ አይደለም፡፡ ሒደቱንም በተመለከተ የባንኮችን አሠራር ቁጥጥር እናደርጋለን፡፡ የምንዛሪ ጥያቄ ሲቀርብም ሆነ ሲፈቀድ በእኛ በኩል የሚያልፍ በመሆኑ፣ እስካሁን በባንኮች በኩል የአሠራር ችግር አላጋጠመንም፤» ብለዋል።