Tuesday, April 16, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ኢትዮጵያን ከግጭት አዙሪት ማላቀቅ ይገባል!

ከአውዳሚው ጦርነት ውስጥ በመውጣት በፍጥነት ፊትን ወደ ልማት  ማዞር የወቅቱ ተቀዳሚ አጀንዳ መሆን አለበት፡፡ የኢኮኖሚው ድቀት ከጦርነቱ የባሰ ቀውስ ሊፈጥር ስለሚችል፣ አታካች ከሆነው የዘመናት አጉል ልማድ በመገላገል ለሥራ ታጥቆ መነሳት የግድ ይላል፡፡ ኢትዮጵያ የተደቀነባትን ፈተና ተሻግራ የተረጋጋ ማኅበራዊ ሕይወት ለመጀመር ያለው አማራጭ፣ የሰው ኃይሏንና የተፈጥሮ ፀጋዎቿን በመጠቀም ለዕድገት መነሳት ነው፡፡ ምዕራባውያን የድጋፍ እጃቸውን ሰብስበው ጀርባቸውን እየሰጡ ባሉበትና ይህ ነው የሚባል መጠባበቂያ ሀብት በሌለበት፣ የሚያዋጣው ተግባር የፖለቲካ አተካሮ አቁሞ ወደ ሥራ መሰማራት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ጥቃቅን ልዩነቶችንና ቅራኔዎችን እያነፈነፉ ግጭት መጠንሰስ፣ በንግግርና በምክክር ሊፈቱ የሚችሉ ጉዳዮችን በማጦዝ ለመተናነቅ ማድባትና በመጠኑ እየታየ ያለውን መረጋጋት ለማዳፈን መቅበዝበዝ ለአገር አይጠቅምም፡፡ ከዚህ በፊትም ተሞክሮ ያተረፈው ነገር ቢኖር የሕዝባችንን ዕልቂትና መፈናቀል ነው፡፡ ለመተመን የሚያስቸግር የአገር ሀብት ውድመት ነው፡፡ ከዚህ ዓይነቱ አሳዛኝ ድርጊት ውስጥ በፍጥነት በመውጣት ኢትዮጵያን ወደፊት ማራመድ ይገባል፡፡ ለዘመኑ በማይመጥን አሮጌ አስተሳሰብ በመታጀል አገር ላይ ማሴር ወንጀል ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከግጭት ቀንበር ተላቃ በዕድገት ወደፊት መገስገስ አለባት፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሥፍራ የሚሰጣቸው በርካታ አኩሪ ክንውኖች አሉ፡፡ የዚያኑ ያህል ደግሞ የኢትዮጵያን መፃኢ ዕድል ያጨለሙ ክስተቶችም ይታወቃሉ፡፡ እነዚህ ክስተቶች በተለያዩ ትውልዶች ውስጥ የቅራኔ መነሻ በመሆን፣ የሥልጣን ትንቅንቅ በመፍጠርና ግጭት በመቀስቀስ የበርካታ ኢትዮጵያዊያንን ሕይወት ቀጥፈዋል፡፡ በተከታታይ ትውልዶች ላይ ቂም በቀልና ጥላቻ ዘርተዋል፡፡ ለአገር ዕድገት መዋል የሚገባውን ጊዜ አባክነዋል፡፡ እጅግ መሪር ለሆነ ድህነት መንሰራፋት ምክንያት ሆነዋል፡፡ በታሪክ አጋጣሚ የተሻለ ሁኔታ ለመፍጠር የተነሱ ሰዎች ተስፋ እንዲቆርጡ አድርገዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ከአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት በኋላ ያሉ ዓመታትን በወፍ በረር ብንቃኝ፣ በርካታ መንግሥታት ቢለዋወጡም ተከትለው የመጡ ችግሮች አሁንም አላነቃንቅ እንዳሉ ነው፡፡ ወሳኝ በሆኑ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ተቀራራቢ ዕይታ መፍጠር ስላልተቻለ በሕዝብና በአገር ላይ በተደጋጋሚ ከፍተኛ ጉዳቶች ደርሰዋል፡፡ 1966 .. አብዮት ወዲህ በመደብ፣ በብሔር፣ እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ለበላይነት የሚደረጉ ትንቅንቆች የፈጠሩትና የሚፈጥሩት ችግር ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያ በርካታ የታሪክ አጋጣሚዎች መልካም ዕድል ይዘውላት ቢመጡም፣ በልጆቿ አርቆ አለማሰብ ምክንያት እንደመከኑባት አይካድም፡፡ ብዙዎች በሚያሳትሟቸው ግለ ታሪኮችና መጣጥፎች በፀፀት ገልጸውታል፣ እየገለጹትም ነው፡፡ ለዚህ ዘመን ፋይዳ ባይኖረውም፡፡

በአንድ ወቅት በሥልጣን ላይ የነበሩ ግለሰቦች ስለፈጸሙዋቸው አሳዛኝ ድርጊቶች ሲጠየቁ ይፀፀታሉ፡፡ ከእነሱ በፊት የነበሩ ሰዎችም ሲፀፀቱ ይታወቃል፡፡ አንዱ ከሌላው መማር አቅቶት ብዙ ጥፋት ከደረሰ በኋላ መፀፀት ፋይዳ ቢስ እየሆነ ነው፡፡ የአንዳንዶቹ ፀፀት ለምን ከፈጸምነው በላይ አላጠፋንም የሚል ስሜት ሲኖረው፣ የሌሎቹ ደግሞ እንዲህ ጥለን ለሄድነው ሥልጣን ለምን ተሸነፍን የሚል ቁጭት አለው፡፡ በሌላ በኩል ከእነ ጭራሹም ምንም የማይፀፀቱ መኖራቸውም ይገርማል፡፡ ይሁንና በደህናው ጊዜ ለአገራቸው ማከናወን የሚገባቸውን መልካም ነገር ባለማድረጋቸው የሚፀፀቱ ቅኖች ያጋጥማሉ፡፡ እነዚህ በጉብዝናቸው ጊዜ የብልሆችን ምክር የማይሰሙ፣ የሕዝብን ፍላጎት የማያጤኑ፣ በታሪክ ያጋጠሙ ውጣ ውረዶችን የማይረዱ፣ የተለዋዋጩን የዓለም ሁኔታ የማያገናዝቡና በጠቅላላው ከራሳቸው ያልተገራ አስተሳሰብ ወጣ ማለት ያዳገታቸው ናቸው፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ በዚህ ዘመንም በብዛት አሉ፡፡ እነዚህ ማስተዋል የጎደላቸው፣ ከራሳቸውና ከቡድናቸው ጥቅም ውጪ ማሰብ የማይፈልጉ፣ መልካም መካሪ ቢያጋጥማቸውም የሚንቁና ከእነሱ በላይ ማንም ያለ የማይመስላቸው ቅብዝብዞች ናቸው፡፡ የሚያሳዝነው እነዚህም ከወደቁ በኋላ በፀፀት ሲያላዝኑ ማየት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ በረዥሙ ታሪኩ የሚታወቀው በአስተዋይነቱና በአርቆ  አሳቢነቱ ቢሆንም፣ ከውስጡ ወጥተው ሥልጣን የሚቆናጠጡ ብዙዎቹ ግን ለዚህ ያልታደሉ ነበሩ፡፡ ቢታደሉማ ኖሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት የድህነት መጫወቻ ባልሆነ ነበር፡፡ አርቆ አሳቢዎች ቢሆኑ ኖሮ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቶቿ ለምተው ካደጉት አገሮች ተርታ ትሠለፍ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ስንዴ ማብቀል የሚችሉ ሰፋፊ ሁዳዶቿ ፆማቸውን አድረው ምፅዋት ጠባቂ አትሆንም ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚታወቅባቸው የግጭት አፈታትና የሽምግልና ሥርዓቶቹ ወደ ጎን ተብለው፣ ኢትዮጵያ የግጭት መናኸሪያ አትሆንም ነበር፡፡ የተለያዩ እምነቶች በሰላም መኖርን ለዓለም ባሳዩባት ኢትዮጵያ፣ የፖለቲካ ልሂቃን እርስ በርስ አይበላሉም ነበር፡፡ የዴሞክራሲን እሴቶች ከማንም ቀድማ ተግባራዊ ባደረገች አገር ውስጥ፣ አምባገነኖች እየተፈራረቁ ሕዝቡን አሳሩን አያበሉትም ነበር፡፡ ይሉኝታና ኃፍረት የሞራል ጥግ በሆኑበት ማኅበረሰብ ውስጥ፣ አገር የዘራፊዎች መፈንጫ አትሆንም ነበር፡፡ ጨዋነትና ቁጥብነት በሚያስከብሩባት አገር ውስጥ፣ መረኖችና ባለጌዎች አይፈነጩም ነበር፡፡ ሌሎች በርካታ ንፅፅሮችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ሁሌም ለፀፀት የሚዳርጉ ነገሮች እየበዙ ተስፋ ያስቆርጣሉ፡፡ ተስፋ መቁረጥ ደግሞ ከበርካታ መልካም አጋጣሚዎች ጋር ይለያያል፡፡ ከዚህ አዙሪት ውስጥ መውጣት ይገባል፡፡

በዚህ ዘመን ትዕግሥት፣ ማስተዋልና አርቆ አሳቢነት በጎደላቸው ፖለቲከኞችና ልሂቃን ምክንያት ከፍተኛ ጥፋት ደርሷል፡፡ ለሕዝብና ለአገር ኃላፊነት የማይሰማቸው በሕዝብ መካከል መጠራጠርና ጥላቻ ይዘራሉ፡፡ በብሔርና በሃይማኖት ለማጋጨት ያደባሉ፡፡ በእነሱ የተቀሰቀሱ ኃላፊነት የማይሰማቸው ወገኖች ግጭት በማስነሳት የንፁኃንን ሕይወት ያጠፋሉ፣ ንብረት ያወድማሉ፣ ቤተ እምነቶችን ያቃጥላሉ፡፡ ከዚህም አልፈው ተርፈው የአገርን ህልውና እየተፈታተኑ የሕዝብን ደኅንነት ያቃውሳሉ፡፡ ከእንዲህ ዓይነት ችግሮች በስተጀርባ ያሉ ኃይሎች ዓላማ ሥልጣን ይዞ እንዳሻቸው መሆን ስለሆነ፣ ለሕዝብም ሆነ ለአገር ሰላም ፈፅሞ ደንታ የላቸውም፡፡ ከታሪክ ስህተቶች ለመማር ፈቃደኛ ስላልሆኑ የሚደርሰው አደጋ ንፁኃንን ያጠፋል፡፡ ሕዝቡ ለዘመናት አብሮ የገነባቸውን ታሪካዊ እሴቶች መናድ ማለት አገር ማፍረስ እንደሆነ እያወቁ፣ ከራሳቸው አደገኛ ፍላጎት ውጪ ምንም ነገር አይታያቸውም፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ያጋጠመው እንዲህ ዓይነቱ ፈተና ነው፡፡ ሕዝብና አገርን የማይወጡት አዘቅት ውስጥ ከከተቱ በኋላ የአዞ ዕንባ የሚያስፈስስ ፀፀት ማሳየት ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ ለዘመኑ አይመጥንምና፡፡

ኢትዮጵያ ተስፋ ያላት አገር ለመሆኗ ማንንም ምስክር መጥራት አያስፈልግም፡፡ ነገር ግን ይህንን ተስፋ ዕውን ማድረግ ካልተቻለ ከሚያሰለቸው ፀፀት ውስጥ መውጣት አይቻልም፡፡ ኢትዮጵያዊያን አንድ ላይ ሲሆኑ ወራሪዎችንና ተስፋፊዎችን መመከት ብቻ ሳይሆን፣ የገቡበት ገብተው ድባቅ መምታት እንደሚችሉ ታሪክ ይመሰክራል፡፡ ይህንን ጀግንነት በልማት መስክ ማምጣት ቢቻል ደግሞ የአፍሪካ ቁንጮ መሆን አያቅትም፡፡ የኢትዮጵያ ልሂቃን ለዘመናት ከተዘፈቁበት አላስፈላጊ መናናቅ፣ ጥላቻ፣ ቂም በቀልና ኋላቀር ፉክክር ውስጥ በመውጣት እንደ ሠለጠኑት መሆን መቻል ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለሕዝቡ የዕለት እንጀራና ዘለቄታዊ ዕድገቱ ምንም ፋይዳ የሌላቸውን አጀንዳዎች እየፈበረኩ አገር ከሚያምሱ፣ በመጪው ትውልድ የሚያስከብራቸውን ተግባር ያከናውኑ፡፡ ለፀፀት ከሚዳርጉ አስከፊ ድርጊቶች በመራቅ በታሪክ የሚታወሱበት ቁም ነገር ይሥሩ፡፡ ሕዝብን በብሔርና በሃይማኖት እየከፋፈሉ አገር ለማተራመስ እንቅልፍ ከሚያጡ፣ ከህሊና ወቀሳ የሚያድንና የሚያስከብር ገድል ይፈጽሙ፡፡ የጠላት ተላላኪ ይመስል አገር ላይ መዶለት የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ፣ በሕግ የሚያስጠይቅበትና አንገት የሚያስደፋበት ወቅት ይመጣል፡፡ ያኔ ያላኖሩት በጎ ተግባር ምስክር ሆኖ ነፃ አያወጣም፡፡ ለዚህም ነው ዘመኑን ከማይመጥኑ ድርጊቶች መታቀብ የሚያስፈልገው፡፡ ኢትዮጵያን ከግጭት አዙሪት የማላቀቅ ኃላፊነት ሊኖር ይገባል!  

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

ስለዘር ፖለቲካ

በሀብታሙ ኃይለ ጊዮርጊስ  ‹‹በቅሎዎች ዝርያችን ከአህያ ነው እያሉ ይመፃደቃሉ›› የጀርመኖች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...

የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዳይዳፈን ጥንቃቄ ይደረግ!

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር አሁንም ጤና አልባ ሆኖ የተለመደው ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ ካለፉት ሃምሳ ዓመታት ወዲህ ሊሻሻል ያልቻለው የፖለቲካ ምኅዳር ሰሞኑን አዲስ...