Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የሚገኙ መካነ መቃብሮች በዕድሳት ምክንያት ሊነሱ እንደሚችሉ ተነገረ

በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የሚገኙ መካነ መቃብሮች በዕድሳት ምክንያት ሊነሱ እንደሚችሉ ተነገረ

ቀን:

ለአገር ውለታ የዋሉና የታዋቂ ሰዎችን የቀብር ሥፍራ የያዘውን የመንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን ሕንፃና ቅጥር ግቢን ለማደስ በመታሰቡ፣ በውስጡ የሚገኙ መካነ መቃብሮች ሊነሱ እንደሚችሉ ተገለጸ፡፡

በካቴድራሉ የሰበካ ጉባ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት ጌታቸው ማሩ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በቅርቡ ይጀመራል ተብሎ የሚጠበቀውን ዕድሳት ለማከናወን ሲባል መቃብሮቹ ሊነሱ ይችላል፡፡ ‹‹አፅሞቹን ሰብስበን ልዩ ቦታ አድርገን ግቢውን ለምዕመናን በሚመች ሁኔታ እንሠራለን፤›› ያሉት ምክትል ሊቀመንበሩ፣ በቅጥር ግቢው ውስጥ የሚገኙትን የሃይማኖት አባቶችን መቃብር ወደ ‹‹ክብር ቦታ›› በማዛወር ግቢውን ‹‹ጠዋትና ማታ የሚቀደስበት›› የማድረግ አቋም መኖሩን አስረድተዋል፡፡ ይሁንና ጉዳዩ በጥናት ላይ ያለና አጥኚዎች የሚወስኑት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የካቴድራሉ ዋና አስተዳዳሪ ሊቀ ሥልጣናት ቆሞስ አባ ሲራክ አድማሱ በበኩላቸው፣ በካቴድራሉ የሚደረገው ዕድሳት ቅጥር ግቢውን ከዚህ በበለጠ የቱሪስት መዳረሻ የማድረግ ዕቅድ እንዳለ አስረድተዋል፡፡ በግቢው ውስጥ የሚገኙት የመቃብር ሥፍራዎች የሐውልት አቀማመጣቸው ውበት ኖሮት ለጉብኝት አመቺ የሆነ ሁኔታ ለመፍጠርና ‹‹የተዘበራረቀ›› እንዳይሆን ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የመቃብር ሥፍራውንም የሚያካትተው ዕድሳት፣ የካቴድራሉ ሕንፃና በውስጡ ያሉ ቅርፃ ቅርፆችና ሐውልቶች ላይ የደረሰውን ጉዳት ለመጠገን የያዘው ዕቅድ አካል ነው፡፡ ዕድሳቱ በሁለት ምዕራፍ የሚደረግ ሲሆን፣ በመጀመርያው ምዕራፍ ዕድሳት የሚደረገው ለቤተ ክርስቲያኑ ሕንፃ ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያኑ ላይ የደረሰውን ጉዳት ለመለየት ፋሲል ጊዮርጊስ በተባለው አማካሪ ድርጅት አማካይነት ዘጠኝ ወራት የፈጀ ጥናት መደረጉን የተናገሩት የዕድሳት ቲክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሥርዓት አየለ (ኢንጂነር)፣ ከካቴድራሉ አሠራር የተነሳ ወደ ዕድሳት ሥራ እንዲገባ የሚያስችል ሰነድ የተገኘው ለዘጠኝ ጊዜያት የጥናት ሰነድ ከቀረበ በኋላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተደረገው ጥናት በሕንፃው መሠረት ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው የውኃ ሥርገት እንዳለ፣ እንዲሁም ሕንፃውን በያዙት ምሰሶዎችና በቤተ ክርስትያኑ ጣራ ላይ ከፍተኛ ስንጥቅ እንዳለ እንዳረጋገጠ ተገልጿል፡፡ በቤተ ክርስትያኑ ጣርያ ላይ በተከሰው ስንጥቅ ምክንያት ውኃ ወደ ውስጥ እየገባ በመሆኑ፣ በሕንፃው ምሰሶ ላይ ያሉት ቅርፃ ቅርፆች እየወደቁ መሆናቸውን ሥርዓት (ኢንጂነር) ተናግረዋል፡፡

ከ90 ዓመታት በፊት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የተገነባው መንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፣ ከተገነባ ጊዜ አንስቶ እንደ ቀለም መቀባት ካሉ አነስተኛ ዕድሳቶች ውጪ ሙሉ ጥገና እንዳልተደረገለት ታውቋል፡፡ የደረሰበትን ጉዳት አስመልክቶ የተደረገው ጥናት ሕንፃው አሁን ባለበት ሁኔታ የአገልግሎት ዘመኑን መጨረሱን ማመላከቱም ተገልጿል፡፡ ዕድሳቱ ሲጀመር በዓይን የማይታዩና የጉዳቱን ደረጃ ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ ጉዳቶች ይገኛሉ የሚል ሥጋት እንዳላቸው ሥርዓት (ኢንጂነር) አስረድተዋል፡፡

ዕድሳቱን ለማከናወን ቢያንስ ሁለት ዓመት እንደሚፈጅና ከ80 እስከ 100 ሚሊዮን ብር እንደሚጠይቅ በጥናቱ ማረጋገጡ ታውቋል፡፡

ካቴድራሉ ጥናቱን ለማከናወን ፍላጎት ያላቸው ተቋራጮች የፍላጎት መግለጫቸውን እንዲያስገቡ ከአንድ ወር በፊት አስታውቆ የነበረ ሲሆን፣ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ፍላጎታቸውን ካሳወቁት ተቋራጮች ውስጥ የተሻለ ልምድ አላቸው ያላቸውን አራት ተቋራጮች መርጦ ለካቴድራሉ ልኳል፡፡ ቫርኔሮ ኮንስትራክሽን፣ ሚሳክ ጄኔራል ኮንስትራክሽን፣ ፕላኔት ሙዚየም አክቲቪቲስና ፕሪዘርቬሽን፣ ሂስቶሪክ ሳይት ኦፍ ቢዩልዲንግስና ኤልሚ ኦሊንዶ ኮንስትራንሽን ፒኤልሲ በባለሥልጣኑ የተጠቆሙ ተቋራጮች መሆናቸውን ሪፖርተር ባለሥልጣኑ ለካቴድራሉ ከላከው ደብዳቤ ተመልክቷል፡፡

እነዚህ ተቋራጮች ያላቸው ቴክኒካዊ ብቃትና የሚያቀርቡት ዋጋ ታይቶ አሸናፊ ከሚሆነው ተቋራጭ ጋር ሥራ የሚጀመርበት ደረጃ ላይ መደረሱን ሥርዓት (ኢንጂነር) አስረድተዋል፡፡ ይሁንና ተቋራጮቹ ለጨረታ ዋጋቸውን ከማቅረባቸው በፊት በቤተ ክርስቲያኑ ላይ የደረሰውን ጉዳት በራሳቸው እንዲመለከቱና እንዲያጠኑ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡ ለዚህም ሲባል በካቴድራሉ ውስጥ የሚገኘው ታቦተ ሕግ ጥር 7 ቀን 2014 ዓ.ም. ዕድሳቱ እስከሚጠናቀቅ ድረስ በጊዜያዊነት ወደ በዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን እንደሚዘዋወር ታውቋል፡፡

የዕድሳት ሥራው በቅጥር ግቢው ውስጥ ያለውን የኤሌክትሪክ መስመሮች ጥገና፣ ማሻሻልና ግቢው ውስጥ የሚገኙትን ሐውልቶች፣ እንዲሁም በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ያሉትን ሥዕላት ማደስን እንደሚያካትትም ታውቋል፡፡ በዚህም የተነሳ ዕድሳቱን የሚያከናውነውን ተቋራጭ ለመምረጥ በቅርቡ በሚደረገው ጨረታ ላይ ተቋራጮቹ ከሚያቀርቡት ዋጋ በተጨማሪ፣ ሥራውን ለማከናወን ያላቸው አቅም ከፍተኛ ቦታ እንደሚሰጠው ሥርዓት (ኢንጂነር) አስረድተዋል፡፡

ካቴድራሉ ሊደረግለት የታሰበው ዕድሳት ሲጠናቀቅ ለተጨማሪ 50 ዓመታት ሌላ መሠረታዊ የሕንፃ ዕድሳት ሳይደረግለት እንዲቆይ ማድረግ እንደሚያስችል ታውቋል፡፡ የካቴድራሉ አስተዳዳሪዎች ቤተ ክርስቲያኗ የጥገናውን ሙሉ ወጪ ስለማትሸፍን ምዕመናንም ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...