ከኅብረተሰብዓዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት (ደርግ) እስከ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢሕዲሪ) መንግሥት፣ ከመንግሥታዊ ተቋም ዋና ዳይሬክተርነት እስከ ሚኒስትርነት አገልግለዋል፡፡ በቀድሞ አጠራሩ የድኩማን ማቋቋሚያ ድርጅት የበላይ ኃላፊነት እስከ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትርነት የደረሱት ካሳ ከበደ (ዶ/ር)፣ በዲፕሎማትነትና በአምባሳደርነት ሠርተዋል፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማገልገል የጀመሩት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ከ1960ዎቹ መባቻ ጀምሮ ነው፡፡
የ1969 ዓ.ም. የጎረቤት አገሯ ሶማሊያ ወረራ ተከትሎ 300 ሺሕ ሚሊሺያዎችን (ሕዝባዊ ሠራዊት) ለማሠልጠን ሲታለም፣ ሥጋ ሜዳን በታጠቅ ጦር ሠፈርነት ሲደራጅ ከትልሙ እስከ ፍፃሜው ከተሳተፉት ባለሙያ ሹማምንት መካከል በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ፡፡ የጀግኖች አምባና የሕፃናት አምባ ዕውን እንዲሆኑ ካደረጉት መካከልም ከፊት የሚመጡትም እሳቸው መሆናቸው ገጸ ታሪካቸው ያስረዳል፡፡
በ1979 ዓ.ም. በአውሮፓና በአሜሪካ ተዘዋውሮ አገራዊና ባህላዊ ሙዚቃን ያቀረበው የሕዝብ ለሕዝብ አደይ አበባ የባህል ቡድንን ከመሩት መካከልም ይጠቀሳሉ፡፡
የ1983 ዓ.ም. የመንግሥት ለውጥ በተደረገበት ዋዜማ ከአገር የወጡት ካሳ (ዶ/ር)፣ ለሦስት አሠርታት በዘለቀው የስደት ሕይወታቸው በልዩ ልዩ አገራዊ ተግባራት ተሰማርተው ነበር፡፡
በልጅነታቸው ድቁናን የተቀበሉት ሹሙ ለዓመታት ‹‹የአገር ቤትና የውጭ ሲኖዶስ›› በሚል ተከፍላ የቆየችውን ቤተ ክርስቲያን ወደ አንድ ለማምጣት በነበረው ከፍተኛ እንቅስቃሴ ላይ በመሳተፍም ይታወቃሉ፡፡
ከአባታቸው ከደጃዝማች ከበደ ተሰማና ከእናታቸው እመት ይታጠቁ ኪዳኔ የካቲት 18 ቀን 1934 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ የተወለዱት ካሳ (ዶ/ር)፣ ትምህርታቸውን በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤትና በእስራኤል ሂብሩ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ማኅበረሰብ ትምህርት ተከታትለው እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ደርሰዋል፡፡
ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በሚኖሩበት አሜሪካ ሜሪላንድ ግዛት ታኅሳስ 16 ቀን 2014 ዓ.ም. በ80 ዓመታቸው ያረፉት ካሳ (ዶ/ር)፣ ሥርዓተ ቀብራቸው ታኅሣሥ 27 ቀን በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡
ነፍስ ኄር ካሳ ከበደ የሦስት ልጆች (አንድ ወንድና ሁለት ሴቶች) አባት ነበሩ፡፡