Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትተግዳሮቶች የበዙበት የካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅትና ጅማሮ

ተግዳሮቶች የበዙበት የካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅትና ጅማሮ

ቀን:

በካሜሩን አስተናጋጅነት የሚካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ከጅምሩ በበርካታ ምስቅልቅሎች ውስጥ አልፎ ጥር 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ይጀምራል፡፡ ውድድሩ በየሁለት ዓመቱ የአኅጉሪቱ ብሔራዊ ቡድኖች የሚገናኙበትና ከፍተኛ ትኩረት የሚደረግበት ዝግጅት ቢሆንም፣ በዋናነት በአውሮፓና መሰል አገሮች ግን፣ ‹‹ክዋኔው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም›› በሚል የሚያጣጥሉት አልጠፉም፡፡ በተለይም አኅጉሪቱ ያፈራቻቸው የእግር ኳስ ከዋክብት የሚጫወቱባቸው እንግሊዝን ጨምሮ የተለያዩ የአውሮፓ ክለቦችና አሠልጣኞቻቸው፣ የዝግጅቱን ዋጋ ቢስነት በመጥቀስ አገራቸውን እንዳይወክሉ ሲያጣጥሉና ሲናገሩ የተደመጡ በርካታ ናቸው፡፡

ለዝግጅቱ ዋጋ ቢስነት ሲጠቀሱ ከነበሩ ትችቶች መካከል ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መዛመት ብዙም ትኩረት በማይሰጥበት አኅጉር የሚደረግ ውድድር እንደመሆኑ፣ በተለይም ከአውሮፓ ክለቦች ለሚመጡ አፍሪካውያን ተጫዋቾች ችግሩ ይበልጥ አሳሳቢ ሊሆን እንደሚችል መጠቀሱ ማሳያ ተደርጎ ሲጠቀስ ሰንብቷል፡፡

ከዚህ ባለፈ የስታዲየም ጥራትን ጨምሮ ሌሎች መሠረተ ልማቶች አልተሟሉላቸውም ለሚባሉት የካሜሩን ስታዲየሞች የተሰጠው አነስተኛ ትኩረት፣ ውድድሩ ዕውን በአኅጉሪቱ ያንን ያህል ትኩረት አለው እንዴ? የሚል ጥያቄ እንዲያጭር አድርጎ ቆይቷል፡፡ ከደኅንነት አንፃርም እንዲሁ አሉታዊ አስተያየቶችና ትችቶች ሲያስተናግድ የቆየው የካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት፣ በደቡብ አፍሪካ አሊያም ወደ ሌሎች አገሮች ተዛውሮ ሊካሄድ የሚችልበት ዕድል እንዳለ ሲነገርም ነበር፡፡

በእነዚህና መሰል ገጽታዎች ያለፈችው አስተናጋጇ፣ ምዕራብ ማዕከላዊ አፍሪካዊቷ አገር ካሜሩን፣ አሁን ላይ 33ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅቷን በማጠናቀቅ እንግዶቿን ተቀብላ ውድድሩን በይፋ ታስጀምራለች፡፡ ካሜሩን፣ አትላንቲክ ውቅያኖስን ጨምሮ በደቡብ ምሥራቅ ናይጄሪያና በሰሜን ምዕራብ ኮንጎ ብራዛቪል፣ በሰሜን ምሥራቅ ሴንትራል አፍሪካ ሪፐብሊክና ቻድ፣ እንዲሁም በስተደቡብ ጋቦንና ኢኳቶሪያል ጊኒ ያዋስኗታል፡፡

የእግር ኳሱ ኢንዱስትሪ ባደገባቸው የአውሮፓ ክለቦች አንቱታን ማትረፍ የቻሉ ሮዠር ሚላ፣ ሳሙኤል ኤቶና ሌሎች በርካታ የእግር ኳስ ከዋክብት የፈሩባት ካሜሩን፣ 24 ቡድኖች የሚያገናኘውን 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በአምስት ከተሞች ታከናውናለች፡፡ 60 ሺሕ ተመልካቾች የመያዝ አቅም ያለውና በዋና ከተማዋ የሚገኘው ኦሊምቤ ስታዲየም እንዲሁም በወደብና በንግድ እንቅስቃሴዋ በምትታወቀው ዱዋላ ከተማ በሚገኘውና 50 ሺሕ ተመልካች የመያዝ አቅም ባለው ጃፖማ ስታዲየም ዋናዎቹ ሲሆኑ፣ በሁለተኛነት ደግሞ በዋና ከተማዋ ያውንዴ በሚገኙት ሦስት ትንንሽ ስታዲየሞች ማለትም ስታድ አህማዱ ኦሒጆ ስታዲየም (የመያዝ አቅሙ 42,500) ሩምዳ ስታዲየም (30,000) እና 20,000 ተመልካቾችን የመያዝ አቅም ባላቸው ኩኮንግ እና ሊምቤ ስታዲየሞች ጨዋታዎቹ የሚካሄዱባቸው ናቸው፡፡

የሕዝብ ብዛቷ ሃያ አራት ሚሊዮን መሆኑ የሚነገርላት ምዕራብ አፍሪካዊቷ ካሜሩን፣ 475,650 ሜትር ስኩዌር የመሬት ስፋቷ ሲኖራት፣ ፈረንሣይኛና እንግሊዝኛ ብሔራዊ ቋንቋ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ የአገሪቱ መገበያያ ገንዘብ ደግሞ ሴፋ ፍራንክ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የካሜሩን ብሔራዊ ቡድን እሑድ ጥር 1 ቀን 2014 ዓ.ም. የመጀመርያውን ጨዋታ 60,000 ተመልካቾችን የመያዝ አቅም ባለው ኦሊምቤ ስታዲየም የ33ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ መክፈቻ ጨዋታ ከቡርኪና ፋሶ ጋር ያከናውናል፡፡ ካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫን አምስት ጊዜ በማንሳት ሁለተኛዋ የምዕራብ አፍሪካ አገር መሆኗ ይታወቃል፡፡ ቡርኪና ፋሶ፣ ኬቬርድና ኢትዮጵያ በሚገኙበት ምድብ ሁለት የተደለደለችው ካሜሩን ብሔራዊ ቡድኗ ለዋንጫው ቅድመ ግምት ከተሰጣቸው አገሮች ተርታ ተጠቃሽ ሆናለች፡፡

በሊቨርፑሉ የፊት መስመር ፊታውራሪ የምትመራው ግብፅ እ.ኤ.አ. (1957፣ 1959፣ 1986፣ 1998፣ 2006፣ 2008፣ 2010) የአፍሪካን ዋንጫ ሰባት ጊዜ በማንሳት፣ ከካሜሩን (1984፣ 1988፣ 2000፣ 2002፣ 2017) ቀዳሚ ስትሆን፣ ጋና ሦስት ጊዜ (1963፣ 1965፣ 1978) ናይጄሪያ (1980፣ 1994፣ 2013) ሦስት ጊዜ፣ አልጄሪያ (1990 እና 2019) እና አይቮሪኮስት (1992 እና 2015) ሁለት ጊዜ፣ ቱኒዝያ (2004)፣ ሞሮኮ (1976)፣ ሱዳን (1970) እና ኢትዮጵያ (1962) አንድ፣ አንድ ጊዜ የአፍሪካን ዋንጫ ከፍ ያደረጉ አገሮች ናቸው፡፡

የካሜሩን ብሔራዊ ቡድን (የማይበገሩት አንበሶች) በአውሮፓ፣ ለፈረንሣዩ (ሊል)፣ ለቤልጂየሙ (ጂያት)፣ ለጀርመን (ባየር ሙኒክ) እና ለሌሎችም የአውሮፓ ክለቦች የሚጫወቱ ፕሮፌሽናሎች ጥንቅር የተዋቀረ ሲሆን፣ በዚሁ ምድብ የምትገኘዋ ቡርኪና ፋሶ በተመሳሳይ ለጀርመኑ ባየር ሊቨር ኩሰን፣ ለእንግሊዙ አስቶን ቪላ የሚጫወቱትን ኤድሞንድ ታብሶማና በርትራንድ ትራዎሬን ጨምሮ በተለያዩ የአውሮፓ ክለቦች የሚጫወቱ ፕሮፌሽናሎች የተዋቀረ ሰብስብ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ሌላው በምድብ አንድ የሚገኘውና በመክፈቻው ከኢትዮጵያ ጋር በመክፈቻው ዕለት የምትጫወተው በምዕራብ አፍሪካ የምትገኘው ኬፕ ቨርዴ ስትሆን፣ የብሔራዊ ቡድኗ ስብስብ በአብዛኛው ለአውሮፓና ለሌሎችም የውጪ ቡድኖች ማለትም ለፖርቱጋል፣ ለአውስትራሊያ፣ ለግሪክና ለቱርክ ክለቦች የሚጫወቱ ፕሮፌሽናሎች የሚበዙበት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህ ምድብ የምትገኘው ኢትዮጵያ ከሽመልስ በቀለና ሙጅብ ቃሲም በስተቀር ብዙዎቹ ከአገር ውስጥ ሊግ የተሰባሰቡ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

ከሁለት ሳምንት በፊት ለዝግጅት ካሜሩን ያውንዴ ከሁሉም ተሳታፊ አገሮች ቀድሞ የገባው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፣ ቀደም ሲል ልምምድ ሲያከናውንበት የነበረውን ሥፍራ የውድድሩ አዘጋጅ ኮሚቴ በያውንዴ ወዳዘጋጀለት ስታድግ ኔክሰስ ቁጥር ሁለት የልምምድ ሥፍራ ማምራቱ ይታወቃል፡፡

ብሔራዊ ቡድኑ ሁለተኛዋ የምሥራቅ አፍሪካ ተወካይ ከሆነችው ሱዳን ጋር አንድ የወዳጅነት ጨዋታ አድርጎ 3 ለ 2 ማሸነፍም ችሏል፡፡ ቡድኑ ወደ ካሜሩን ከማቅናቱ በፊት ለአቋም መለኪያ ይጠቅመው ዘንድ ቢያንስ ሦስት የወዳጅነት ጨዋታዎችን እንደሚያደርግ ተነግሮ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ አለመሳካቱ ነው የተነገረው፡፡

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. 1962 የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ ብትሆንም፣ የነበራትን ተሳትፎ ማስጠበቅ ተስኗት ከመድረኩ ለዓመታት ከራቁ አገሮች ተርታ ስትጠቀስ ቆይታለች፡፡ እስከ ደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ዋንጫ ድረስ ለ31 ዓመታት ያህል ከመድረኩ ርቃ የቆየችው ኢትዮጵያ፣ ለካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ ተፎካካሪነት የበቃችው ደግሞ ከ2012 የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎዋ ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ነው፡፡

በደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ዋንጫ ወቅት ከኢትዮጵያ ጋር አንድ ምድብ የነበረችው ቡርኪና ፋሶ፣ በካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በአንድ ምድብ ተገናኝተዋል፡፡ በምድብ ሦስት የተደለደሉት ሁለቱ፣ በደቡብ አፍሪካ ምቦ ምቤላ ስታዲየም ተጫውተው ቡርኪና ፋሶ አንድ ተጫዋች በቀይ ወጥቶባት 4 ለ 0 በሆነ ሰፊ ውጤት ኢትዮጵያን ማሸነፉ ይታወሳል፡፡

ያም ሆኖ በዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ወርኃዊ ደረጃ (50ኛ) ላይ ከምትገኘው አስተናጋጇ ካሜሩንና ኢትዮጵያ (137ኛ) በስተቀር ቡርኪና ፋሶም ሆነች ኬፕ ቨርዴ በአውሮፓ ክለቦች የሚጫወቱ በርካታ ከዋክብት ቢኖሯቸውም፣ ሁለቱም የአፍሪካን ዋንጫ ማንሳት ያልቻሉ አገሮች ናቸው፡፡

ካሜሩን ከቡርኪና ፋሶ ከሚያደርጉት የመክፈቻ ጨዋታ በኋላ፣ ኢትዮጵያ በዚሁ ስታዲየም በፊፋ ወርኃዊ ደረጃ 73ኛ ላይ ከምትገኘው ኬፕ ቨርዴ ጋር ትጫወታለች፡፡ የምድቡን ሁለተኛ ጨዋታ ደግሞ ከሦስት ቀን በኋላ ከአስተናጋጇ ካሜሩን ጋር በኦሊምቤ ስታዲየም ከተጫወተች በኋላ፣ የመጨረሻ የሆነውን የምድብ ጨዋታ ደግሞ ከዘጠኝ ዓመት በፊት በመድረኩ ከገጠመቻት ቡርኪና ፋሶ ጋር በያውንዴ ከተማ ኩኮንግ ስታዲየም የምትጫወት ይሆናል፡፡

ለካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የተመረጡ 25 ዋና እና 33 ረዳት የእግር ኳስ ዳኞች የተመደቡ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ የዓለም ዋንጫን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፋዊና አኅጉራዊ ውድድሮችን በመምራት የሚታወቀው ባምላክ ተሰማ ብቻ፣ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለመጀመርያ ጊዜ በሚተገበረው የቫር ዳኝነት ተመርጦ በካሜሩን ይገኛል፡፡ ከዚህ ባለፈ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራሮችን ጨምሮ የዲፓርትመንቱ ዳይሬክተሮች በሙሉ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር በካሜሩን እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ በርካታ ደጋፊዎችም ወደ ካሜሩን ያመሩ ስለመሆኑ ጭምር ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...