Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉከገንዘብ ለውጥ በኋላም ጥሬ ገንዘብ ንጉሥ ነው

ከገንዘብ ለውጥ በኋላም ጥሬ ገንዘብ ንጉሥ ነው

ቀን:

በተስፋዬ ቦሩ (ዶ/ር)

መነሻ

በኢትዮጵያ ውስጥ ሕጋዊ የሆነ ገንዘብ በሥራ ላይ የማዋል ሒደት የብዙ ዓመታት ጉዞና ጥረት ውጤት ነው፡፡ በፊት ከነበረው ሸቀጥን በሸቀጥ ከመለወጥ እስከ ሕጋዊ ገንዘብ የማሳተም የታሪክ ሒደት ያለው መጠነ ሰፊ ሐተታና ጥልቅ የታሪክ ምርምርን የሚሻ ጉዳይም ነው፡፡ ከአክሱም ዘመን የሳንቲም ኅትመት፣ የአሞሌ ግብይት፣ የማርትሬዛ፣ የመጀመርያው የወረቀት ገንዘቦች፣ የወርቅ፣ የነሐስና የብር ሳንቲሞች ኅትመት ሒደቶች ብዙ ጊዜ በጣምራ፣ በቅርቡም ሙሉ በሙሉ በማዕከላዊ ባንክ ዕውቅና ያለው የገንዘብ ዓይነትን የማስፈን ሥርዓቶች በአገራችን ሲፈራረቁ እንደነበሩ ማየትም ይቻላል፡፡ ተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ የባንክ ሥርዓት በተቋቋመበት ዘመን፣ ኢትዮጵያዊ የሆነ ገንዘብን ለማስተዋወቅ እጅግ አስቸጋሪ እንደሆነም ታሪክ ያሳያል፡፡

የድሮውን ታሪክ ወደ ጎን ትተን ከጣሊያን ወረራ በኋላ በ1937 ዓ.ም. በንጉሣዊው ሥርዓት የተዋወቁት የአንድ፣ የአምስት፣ የአሥር፣ የሃምሳ፣ የመቶና የአምስት መቶ ብር ኖቶች በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኙ በአዋጅ የተደነገገበት፣ የመቶና ይኼም ገንዘብ ለረጅም ጊዜ ለአገልግሎት እንዲውል የተደረገበት፣ እንዲሁም በፊት የነበረውን በወረቀት ገንዘብ ያለ መጠቀም ልምድ የተቀየረበት ዘመንን የገንዘብ ለውጥ ጅማሮ አድርጎ ለመውሰድም ያስደፍራል፡፡ ከዚያ ጊዜ በኋላ የመጡት መንግሥታት እንደ አቋም በዘመነ መንግሥታቸው ገንዘብን መለወጥ ግዴታ የሚመስል አካሄድ መከተላቸው፣ ገንዘብና መንግሥት ምን ያህል ጥብቅ ትስስር እንዳላቸውም ማሳያ ሆኖ አልፏል፡፡

ያንስ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ድረስ መንግሥትም ገንዘብም ሲቀያየሩ ኖረዋል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ለውጦች ቢኖሩም ገንዘብን ራሱ አዘምኖ ወደ ጥሬ ገንዘብ አልባ የኢኮኖሚ አካሄድ ለመጓዝ ገና ብዙ የሚቀረው፣ አሁንም ቢሆን ጥሬ ገንዘብ ንግሥናውን ይዞ እንዲቀጥል የተፈቀደለት ነው፡፡ ምንም እንኳ ለገንዘብ ለውጡ የተለያዩ ምክንያቶች ቢሰጡም በደምሳሳው የአገር የገንዘብ ለውጥ ምክንያቶች ወይ በኢኮኖሚ አሊያም በፖለቲካ ሰበቦች እንደሆነ፣ የኢትዮጵያም የገንዘብ ታሪክ ከዚህ የተለየ አመክኖ እንደማይኖረው ግልጽ ነው፡፡ ሚዛኑ ወደ የትኛው ያመዝናል ካልሆነ በስተቀር ሁለቱንም አንጓዎች መያዙ አይቀርም፡፡ የጽሑፉም ዓላማ የገንዘብ ታሪክን የመተንተን ሳይሆን፣ በቅርቡ (ከአንድ ዓመት በፊት) የተደረገው የገንዘብ ለውጥ ከታሰበለት ዓላማ አንፃር ምን ያህል ውጤት እያስገኘ መሆኑን በደምሳሳው ለማየት መሞከር ነው፡፡

ባለፉት ሦስት መንግሥታት የተደረጉ የገንዘብ ለውጦች አጭር ገለጻ

በ1937 ዓ.ም. በአዋጅ ቁጥር 70 በምክትል የገንዘብ ሚኒስትር ይልማ ዴሬሳ ተፈርሞ የወጣው አዋጅ እንደሚያሳየው፣ ከገንዘብ ለውጡ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት የገንዘብ ዓይነቶች ዋነኛ ሚና ነበራቸው፡፡ አንደኛው የማርትሬዛ ገንዘብ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት የተያዙ አገሮች የሚጠቀሙበት የምሥራቅ አፍሪካ ሽልንግ እንደሆነ በግልጽ ያሳያል፡፡ አዋጁም የማርትሬዛ ገንዘብ ሕጋዊ ገንዘብ ሆኖ ለማንኛውም የግብይት ዓይነት መጠቀም እንደማይቻል ይደነግጋል፡፡ በተጨማሪም ይህንን ገንዘብ ለኢትዮጵያ የመንግሥት ባንክ (State Bank of Ethiopia) መለወጥ እንደሚቻል፣ ነገር ግን እንደ ተቀማጭ ገንዘብ ሊያገለግል እንደማይችልም ያስታውቃል፡፡

በሌላ መልኩ ባንኩ በምሥራቅ አፍሪካ ሽልንግ የተቀመጡ ሒሳቦች የብድሮችና ሌሎች ሒሳቦችን በኢትዮጵያ ዶላር (አንድ የኢትዮጵያ ዶላር በሁለት የምሥራቅ አፍሪካ ሽልንግ) ተለውጦ እንደሚገዙ ፈቃድ ሰጥቶ፣ የምሥራቅ አፍሪካ ሽልንግን በተቀማጭ ሒሳብና ለክፍያም በባንኩ ፈቃድ መሠረት መዋል እንደሚችም ደንግጓል፡፡ አንድ፣ አምስት፣ አሥር፣ ሃምሳ፣ መቶና አምስት መቶ ብር የባንክ ኖቶች ከኢጣሊያን ወረራ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ታትመው በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኙ በአዋጅ የተደነገገበትና የራስ የሚባል ገንዘብ የተሠራጨበት ጊዜም ነው፡፡ ብዙዎች ከላይ የገለጽናቸው የገንዘብ መጠኖች በስፋት በሕዝብ ተቀባይነት ኖሯቸው ጥቅም ላይ ሲውሉ፣ የ500 ብር ኖት ቀስ በቀስ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ሥርጭት እየቀነሰና እየጠፋ መምጣቱን ይገልጻል፡፡ በሳንቲም ረገድም በመደብ የሚታተሙ የአንድ፣ የአምስት፣ የአሥርና የሃያ አምስት ሳንቲሞች፣ እንዲሁም ከብር የተሠሩ የሃምሳ ሳንቲሞች ሥራ ላይ እንዲውሉም ተደርጓል፡፡

በኢጣሊያን ወረራ ጊዜ የኢጣሊያን ገንዘቦች፣ የእንግሊዝ ገንዘብና የሌሎች አገሮችን ገንዘብ አገራችን ስትጠቀም እንደነበር ታሪክ ቢያሳየንም፣ ከላይ የጠቀስነው አዋጅ የምሥራቅ አፍሪካ ሽልንግና ዶላር (አንድ የኢትዮጵያ ዶላር በ40 የአሜሪካ ሳንቲም)፣ ፓውንድ ስተርሊንግ (አንድ የኢትዮጰያ ዶላር በ0.1 ፓውንድ) በአገራችን ውስጥ የመገበያያ ገንዘብ ሆኖ ሲያገለግሉ እንደ ነበር ምስክርነት ይሰጣል፡፡ ከሌሎች መንግሥታት በተለየ ይህ ሥርዓት የአገራችን የነፃነት መገለጫ የሆነውን ኢትዮጵያዊ ገንዘብ የማስተዋወቅ ትልቅ ዓላማ ይዞ የተነሳ ከመሆኑም አንፃር፣ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውና ገንዘብ ከኢኮኖሚ ፋይዳ ባለፈ የነፃ አገር ምልክት እንደሆነም ያስገነዘበ የታሪክ ቅርስ ነው፡፡

የ1969 ዓ.ም. የገንዘብ ለውጥ

በ1937 ዓ.ም. የታተሙት የተለያዩ የገንዘብ መጠኖች አብዛኛውን የንጉሡን ፎቶና የሥርዓቱ መገለጫ የሆኑ ምልክቶች ተካተውበትም ስለነበር፣ የመንግሥት ለውጥን ተከትሎ የመጀመርያው ዕርምጃ (በ1969) የገንዘብ ለውጥ ማድረግ መሆኑን መገመት ይቻላል፡፡ በተለይ ይህ ሥርዓት ፊውዳል ብሎ የሰየመውን መንግሥት ከሥጋም ከህሊናም ለመፋቅ ከነበረው ተነሳሽነት አንፃር አፋጣኝ ዕርምጃዎች በዚህ ዙሪያ መውሰዱ የሚገርም አይሆንም፡፡ በተጨማሪም የእዚህ ገንዘብ ለውጥ ዓላማ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ሊኖረው ቢችልም፣ በአብዛኛው የፖለቲካ ርዕዮት ለውጥ ነፀብራቅ መሆኑን በደርግ ዘመን ከተቋቋሙና የወቅቱን የሶሻሊስት ፖለቲካ ርዕዮት የሚያሳዩ ምልክቶች በገንዘቦች ላይ መታተምና መታየታቸው ምስክር ይሆናል፡፡ በ1969 ዓ.ም. የነበረው የገንዘብ ለውጥ ሥርዓቱ እስከ አበቃበት ድረስ፣ እንዲሁም ከሥርዓቱም መፍረስ በኋላም በጥቅም ላይ እንዲውል የተደረገበትና ኢሕአዴግ አገሪቱን ማስተዳደር ከጀመረበት እስከ ስድስት ዓመት ድረስ ጥቅም ላይ ውሎ እንዲቀጥል ተደርጓል፡፡ ይኼም በገንዘቡ ላይ ያሉ ምልክቶች በወቅቱ ከተለመዱት የንጉሣዊ ስሞች ዓርማና የሥርዓት መገለጫ ይልቅ፣ አገራዊና ወቅት ታካኪ ያልሆኑ መገለጫዎችም ተለግሷቸው እንደነበር ማሳያም ነው፡፡

ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውን ብናይ በደርግ ጊዜ ከገንዘብ ለውጥ በኋላ የነበረው የኢኮኖሚ ዕድገት መጠን ወደ 1.9 በመቶ ሲሆን፣ ይህም ከገንዘብ ለውጡ በፊት ከነበረው የዕድገት መጠን አንፃር ሲወዳደር የ0.2 በመቶ ዕድገት የተስተዋለበት ነው፡፡ በተመሳሳይ የዋጋ ንረት መጠን ከአንድ በመቶ በታች ሲሆን፣ ይህም በፊት ከነበረው የተለየ ሳይሆን፣ በመጠኑ ከፍ ብሎ ይታያል፡፡ በተመሳሳይም ከወለድ ምጣኔ አንፃር የተለየ ባህሪ ሳይኖር፣ የተቀማጭ ገንዘብና የብድር ወለድ ተመን ለውጥ ሳይኖራቸው ቀጥለዋል፡፡ ይኼም የወለድ ተመን መጠን ለተቀማጭ ሒሳብ የዝቅተኛ ክፍያ መጠንን ከማዕከል በመወሰኑ ምክንያት፣ በገበያ ላይ የተመሠረተ ዋጋ ለማየት የሚያስችል አሠራር ባለመኖሩም በዚህ ረገድ ለውጥ መጠበቁም እምብዛም የሚያስኬድ አይደለም፡፡ ሌላኛው ቀጥተኛና ተጠባቂ ውጤት ከባንክ ውጪ ያለን ገንዘብ ወደ ፋይናንስ ዘርፍ የማምጣት ሒደትም እምብዛም የተሳካ እንዳልነበር ያመለክታል፡፡ የረጅም ጊዜ ዕይታንም ቢሆን ብንመለከት ከባንክ ውጪ ያለ ገንዘብ መጠን እስከ ሥርዓቱ ማብቂያ 1983 ዓ.ም. የዕድገት ጉዞውን የቀጠለ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መደበኛ ባልሆነ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ገንዘብ ሲዘዋወር እንደነበርም ማሳያ ይሆናል፡፡ ከኢኮኖሚው ዘርፍ አወቃቀር አንፃርም አብዛኛው የኢኮኖሚ ዘርፍ ድርሻ በእርሻ ዘርፍ የበላይነት በመቀጠል በፊት የነበረውን አወቃቀር ይዞ ቀጥሏል፡፡

የ1989 ዓ.ም. የገንዘብ ለውጥ

በኢሕአዴግ ጊዜም (በ1989) የተደረገው የገንዘብ ለውጥም ሙሉ በሙሉ እነዚህን  ምልክቶች ያልቀየረና ነገር ግን ተጨማሪ የጥንቃቄ መገለጫዎችን በተለይ ከፍ ባሉ የገንዘብ መጠኖች (50 እና 100) ላይ ጨምሮ የመጣ መሆኑ፣ የገንዘብ ቅያሪ ዓላማው ከፖለቲካ ይልቅ ጥንቃቄና የኢኮኖሚ ፋይዳውን ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑን ለመመልከት ያስችላል፡፡ ነገር ግን ይህ የገንዘብ ለውጥ በአገራችን ተከስቶ ከነበረው የኢትዮጵያና ኤርትራ ጦርነት ጋርም በስፋት ቁርኝነት እንዳለው ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል ብዙዎች ሲናገሩ ይሰማል፡፡ ይኼም አሁንም ቢሆን የገንዘብ ለውጥ ዓላማው ሙሉ በሙሉ ከፖለቲካዊ አመክንዮ ነፃ ነው ብሎ ደፍሮ ለመናገር እንዳንችል ያደርገናል፡፡

የፖለቲካ ስኬቱን በድፍረት መናገር ባይቻልም፣ የኢሕአዴግ የገንዘብ ለውጥ የአጭር ጊዜ የኢኮኖሚ ተፅኖ ውጤቶች ስናይ ከገንዘብ ለውጡ በፊት በነበረው አካሄድ የተሻለ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲታይ አስተዋጽኦ እንደነበረው ማየት ያስችላል፡፡ ምንም እንኳ በጦርነት ደቆ የነበረና ከኔጋቲቭ ስድስት በመቶ በታች የነበረው የኢኮኖሚ ዕድገት ወደ ፖዘቲቭ ሦስትና አራት በመቶ ዕድገት እንዲያስመዘግብ ብቻውንም ባይሆን ከሌሎች የኢኮኖሚ ሁነቶች ጋር ተጣምሮ የዕድገት መስመሩ እንዲቀየር ድጋፍ እንደሰጠ ለማየት ይቻላል፡፡ ይኼም እንዲያውም በገንዘብ ለውጥ ጊዜ ሊከሰት ከሚችለው ተጠባቂ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ አንፃር ሲታይ በተቃራኒው የተጓዘ ነበር፡፡ ከዋጋ ንረት መጠን አኳያ ገንዘብ ሲቀየር በተለይ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በኢመደበኛ የኢኮኖሚ ዘርፍ ጉልህ ድርሻ ያላቸው አገሮች፣ ከባንክ ውጭ ያላቸውን ገንዘብ ወደ ፋይናንስ ዘርፍ በማስገባት የገንዘብ ዝውውር መጠን በማሳደግ የሚመጣ የዋጋ ንረት መጨመር የሚጠበቅ ነው፡፡ በወቅቱ የነበረው ሒደትም ይህንን ማስረጃ  የሚያጠናክር ነው፡፡ ከገንዘብ ለውጡ በኋላ የዋጋ ንረት መጠኑ ወደ ሦስት በመቶ በመሆን፣ በፊት ከነበረው  የዋጋ መውረድ (Defelation) አንፃር ጨምሮ የታየና በኢኮኖሚ ትንታኔ ከሚጠበቀው  ውጤት ያልራቀ ባህሪም የተስተዋለበት ነው፡፡

አሁንም በዚህ ጊዜ ከባንክ ውጪ ያለው የገንዘብ መጠን ዕድገት በአጭርም ሆነ በረጅም ጊዜ የዕድገት መጠኑ እየሰፋ የሄደበት መሆኑን ያሳየናል፡፡ በወቅቱ በገበያ እንዲወሰን የተደረገው የብድር መጠንም ቢሆን ምንም ዓይነት ለውጥ የሌለበት ሲሆን፣ ይኼም የገንዘብ ለውጡ ሊፈጥር የሚገባው በባንኮች ካዝና የሚገኘውን ገንዘብ መጠን በመጨመር የብድር ተመንን የማውረድ አካሄድ ላይ ተፅዕኖ ያልነበረው መሆኑንም መረዳት ይቻላል፡፡ በወቅቱ የነበረው የተቀማጭ ሒሳብና የወለድ ተመን አማካይ  ወደ ስድስት በመቶና 12 በመቶ እንደ ቅደም ተከተል ሲሆን፣ ይህም በፊት ከነበረው የስምንት በመቶና የ12 በመቶ መጠኖች አንፃር ሲታይ ለውጡ በስፋት የታየው በተቀማጭ ገንዘብ ምጣኔ ላይ መሆኑንና የብድር ወለድ ያለ ለውጥ  እንደቀጠለ ነው፡፡ ከለውጡ በኋላ ባሉ ዓመታት የተቀማጭም ሆነ የብድር ወለድ ተመኖች እንዲወርዱ የተደረገበት፣ ነገር ግን የዕድገት መጠናቸው እምብዛም ሳይጎዳ የሄደበትም ነው፡፡ በተመሳሳይም የኢኮኖሚ መዋቅር ለውጥ ሳይኖር አሁንም የእርሻ ዘርፉ የኢኮኖሚው ሞተር ሆኖ የቀጠለ ሲሆን፣ ቀስ በቀስ የአገልግሎት ዘርፍ በኢኮኖሚው ውሰጥ ያለው ድርሻ እያደገ ሲሄድ የተስተዋለበት ነው፡፡ በሁለቱም የገንዘብ ለውጥ ጊዜያት ከገንዘብ (Cash) ወደ ቴክኖሎጂ የመሸጋገር፣ እንዲሁም የባንክ ተጠቃሚ ቁጥርን በማብዛት ረገድ የተለየ ሊነገርለት የሚችል ገድል ማንሳት የሚችልባቸው ጊዜያትም አልነበሩም፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት የተደረገው የገንዘብ ለውጥ

የገንዘብ ለውጥ በጥሬ ትርጉሙ በሥራ ላይ የነበረውን ገንዘብ በሙሉ ወይም በከፊል ከኢኮኖሚው በማስወጣት በአዲስ የመተካት ሒደት ነው፡፡ ዓምና በመስከረም ወር የተደረገው የገንዘብ ለውጥም ይህንን ትርጉም ያዘለና ኢትዮጵያ በኢሕአዴግ ጊዜ ትጠቀምባቸው የነበሩትን የ10፣ የ50 እና 100 ብር ኖቶች አዲስ ይዘት ባላቸው ገንዘቦች የመተካት፣ ከዚህ በፊት በገበያው ውስጥ ያልነበረውን የ200 ብር አዲስ ኖት የሚያስተዋውቅ ሒደት የነበረው ነው፡፡ ነገር ግን ከ10 ብር በታች ያሉ ገንዘቦች ቅያሪ ሳይደረግባቸው እንዲቀጥሉ የፈቀደ ሲሆን፣ 262 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው 29 ቢሊዮን ገንዘቦች በ3.2 ቢሊየን ብር ታትመው የገንዘብ ቅያሪውን ለማከናወን ዝግጁ የተደረገበት ነበር፡፡

የገንዘብ ለውጡ ዓላማ በአብዛኛው ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች እንደነበሩት ሲገለጽ፣ በዋነኝነት ከባንክ ውጪ የነበረው ገንዘብ ወደ ፋይናንስ ዘርፉ እንዲመለስ የማድረግ ገዥ ምክንያት ነበረው፡፡ በተጨማሪም የሕገወጥ ገንዘብ መስፋትን የመግታት፣ የሙስና ተጋላጭነትን መቀነስና የባንኮችን የጥሬ ገንዘብ ይዞታ አስተማማኝ የማድረግ ዓላማዎችንም ይዟል፡፡ ነገር ግን አንዳንዶች እንደሚሉት ቀደም ሲል በሥልጣን ላይ ከነበረው መንግሥት ጋር ተያይዞ ብዙ ገንዘብ በሕገወጥ መንገድ ለተለያዩ የፖለቲካ ዓላማዎች ማስፈጸሚያ ሲውል እንደነበር፣ የገንዘብ ለውጡም በተጓዳኝ ይኼንን አካሄድ የመቀየር ዓላማም እንደያዘም ነው፡፡ ስለዚህም የለውጡ ምክንያት ሁለቱንም ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ምክንያቶች እንደያዘ በማረጋገጥ፣ በትኩረትና በጥንቃቄ የተከናወነ ስኬታማ አፈጻጸም የነበረው ተብሎም ይቀመጣል፡፡ ይኼም በታቀደለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ከመጠናቀቁም ባሻገር፣ በፀጥታና በሌሎች ጉዳዮች የመስተጓጎል ችግርም አልተስተዋለም፡፡ በተጨማሪም የባንክ አገልግሎት በቅርበት በማይገኝበት አካባቢ እንኳ ቢሆን የገንዘብ ለውጥ አገልግትን ከማዳረስና ከመፈጸም አኳያ የተመዘገበ ጉልህ ዕክል አለመኖሩም፣ በጥንቃቄ የተደረገ ለውጥ እንደሆነ ማሳያ ነው፡፡

ከገንዘብ ለውጡ ጋር የተያያዙ መመርያዎች

የገንዘብ ለውጥ ሥራ ከባንክ ውጭ ያለውን ገንዘብ ወደ ባንክ ከማምጣት ባሻገር፣ በባንክ ውስጥ እንዲቆይ እንዲያግዝ በማለም የተላያዩ የአፈጻጸም መመርያዎች ድጋፍም የተቸረው ነው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ፣

በግለሰብና ሕጋዊ በሆኑ ድርጅቶች ከባንክ ሊወጣ የሚችለውን የገንዘብ መጠን መወሰን

በፋይናንስ ተቋማት ከጥሬ ገንዘብ ውጪ ባሉ የክፍያ መንገዶች ተገልጋዮች እንዲስተናገዱና ለዚህ የሚሆን መዋቅር እንዲኖራቸው ከማበረታታትም አልፎ፣ በግለሰብ ደረጃ በቀን ሁለት መቶ ሺሕ ብር በወር ከአንድ ሚሊዮን በላይ ገንዘብ ማውጣት እንደማይቻል ያስቀምጣል፡፡ ለሕጋዊ ድርጅቶች ይኼ ጣሪያ ከሦስት መቶ ሺሕ ብር በቀንና ሁለት ሚሊዮን አምስ መቶ ሺሕ በወር እንዳይበልጥ በመመርያ ወሰን ተበጅቷል፡፡ ይኼም በኋላ ላይ በግለሰብና ሕጋዊ ሰውነት ላለው አካል በቀንና በወር ማውጣት የሚቻለውን የገንዘብ መጠን ወሰን፣ በፊት ከነበረው መጠን ዝቅ በማድረግ ጉዳዩን የማጠናከር ሥራም ተሠርቷል፡፡

በባንክ አሠራር ፈቃድ ከተቀመጠው የጥሬ ገንዘብ ወጪ ወሰን በላይ ባንኮች እንዲያስተናዱ መፍቀድ

እንዳስፈላጊነቱ ከላይ ከተጠቀሰው የገንዘብ መጠን በላይ ወጪ ለሚጠይቅ ድርጅት፣ በባንክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይም በእሱ በሚወከል አመራር ፈቃድ የወጪ ፈቃድ እንዲሰጥ የሚፈቅድ መመርያ ወጥቷል፡፡ እነዚህ በልዩ ሁኔታ ፈቃድ ሊያገኙ የሚችሉ አካላትን በዝርዝር የመለየት የአሠራር ግልጽነትን ለማስፈን ተሞክሯል፡፡

በግለሰብና በሕጋዊ ድርጅቶች እጅ ሊያዝ የሚገባውን የገንዘብ መጠን መወሰን

በግለሰብ ደረጃ በእጅ ሊያዝ የሚችለውን ገንዘብ ከአንድ መቶ ሺሕ ብር፣ እንዲሁም ሕጋዊ ሰውነት ባለው አካል ከሁለት መቶ ሺሕ ብር በላይ መብለጥ እንደሌለበትና የባንክ አዋጁን በመጥቀስ ከተቀመጠው ወሰን በላይ ገንዘብ ይዞ መገኘት፣ ሊያስወርስና ለሌላ ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚዳርግ በግልጽ ተቀምጧል፡፡

በሳምንት ውስጥ ሊደረግ ሚገባውን የገንዘብ እንቅስቃሴ መወሰን

የፋይናንስ ተቋማት ማንኛውም አስቀማጭ በሳምንት ከአምስት ጊዜ በላይ ከሒሳብ ወደ ሒሳብ የሚደረግን የገንዘብ ዝውውርን እንዳይፈቅዱ ክልከላ ተደርጓል፡፡

በጥሬ ገንዘብ ወደ ሦስተኛ አካል ሒሳብ ውስጥ ተቀማጭ ማድረግን መከልከል

ማንኛውም የፋይናንስ ተቋም በጥሬ ገንዘብ ወደ ሌላ ሰው/ድርጅት ሒሳብ ውስጥ ገንዘብ ተቀማጭ ማድረግ እንደማይቻል የሚወስን መመርያም ተላልፏል፡፡ ከእነዚህም ሌላ ስለሒሳብ አከፋፈት፣ አጠራጣሪ ግብይቶችንና በአንድ ባንክ ውስጥ አንድ አካል ከአንድ በላይ ሒሳብ እንዳይከፍት የሚያስገድዱ መመርያዎች ከለውጡ በኋላ እንዲተገበሩ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል፡፡ ምንም እንኳ መመርያዎቹ ብዙ ይዘት ቢኖራቸውም፣ ትልቁ መልዕክታቸው የገንዘብ ለውጡን ከማሳካት አንፃር የተቀመጡ ዓላማዎችን ዳር ለማድረስ የታቀዱና እምብዛም ከገዥ ምክንያቶች ውጪ ያልሆኑ ናቸው፡፡

ከገንዘብ ለውጡ በኋላ የታዩ ለውጦች

እነሆ የገንዘብ ለውጡ ከተከናወነ ከአንድ ዓመት በላይ የተቆጠረ ሲሆን፣ ወቅቱ በዓለማችን ላይ የተከሰተው ወረርሽኝ በአገራችን ኢኮኖሚ ላይ ተፅዕኖ ከማሳረፍም አልፎ፣ በተለይ የሰላም ዕጦትና ጦርነት በብዙ የኢኮኖሚ መዋቅሮች ላይ አሻራውን ማሳረፉ የማይቀር ነው፡፡ ስለዚህም በኢኮኖሚው ላይ የታዩ አንዳንድ ለውጦች የገንዘብ ለውጥ ውጤት አድርጎ መውሰድም ሆነ፣ የእዚህን ተፅዕኖ ለብቻ ነጥሎ ለመተንተን መሞከር ትርጉም አልባ ያደርገዋል፡፡ የወቅቱ ኢኮኖሚ ሁኔታ ከገንዘብ ለውጥ በላይ ተፅዕኖ ሊፈጥሩ የሚችሉ ሁነቶች ግፊት ውጤት በመሆኑ፣ የገንዘብ ለውጥ በኢኮኖሚያችን ላይ ይኼንን አስከተለ ብሎ ለመናገር ድፍረት የሚለግስ በቂ አመክንዮ በማግኘትም ከባድ ያደርገዋል፡፡ ነገር ግን በደምሳሳው ከገንዘብ ለውጥ በኋላ የሚጠበቁ ለውጦች ምን ያህል በታሰበላቸው አቅጣጫ እየተጓዙ መሆኑን ማሳየት ብቻ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ነው፡፡

የኢኮኖሚው ዕድገት

ከገንዘብ ለውጡ በፊት የነበረው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት በተወሰነ መልኩ በወረርሽኝ ምክንያት በፊት ሲጓዝበት በነበረው መጠን እንዳይጓዝ ጫና የነበረበት ሲሆን፣ በወቅቱ የነበረው የአይኤምኤፍ የኢኮኖሚ ትንበያ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከሁለት በመቶ ባልበለጠ እንደሚያድግ ያስቀመጠ ነው፡፡ ከገንዘብ ለውጡ በኋላ የድርጅቱ ትንበያ የኢኮኖሚ ዕድገቱን መጠን አላስቀመጠም፡፡ በተለያዩ ገፊ ምክንያቶች የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አካሄድን ለመገመት አስቸጋሪ እንደሚሆንና ተቀባይነት ያለው ግምት ማስቀመጥ አዳጋች እንደሚያደርገው ገልጿል፡፡ በመርህ ደረጃ ከገንዘብ ለውጡ በኋላ የኢኮኖሚ ዕድገት መጠን በብዙ ምክንያቶች ሊቀዘቅዝ እንደሚችል፣ ከሌሎች አገር ልምዶች ማየትም ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በህንድ የተካሄደው የገንዘብ ለውጥ የኢኮኖሚ ዕድገት መጠኑን በሁለት በመቶ ወደ ታች እንደጎተተ ማስተዋል ይቻላል፡፡ ይህም የአንድ አገር የኢኮኖሚ ዕድገት መለኪያዎች አካል የሆኑት ኢንቨስትመንት፣ የመንግሥትና የግለሰብ ወጪዎችና የተጣራ የወጪ ንግድ እንቅስቃሴዎች በገንዘብ ዝውውር መጠን መቀነስ ምክንያት ስለሚወርዱ፣ በኢኮኖሚ ዕድገቱ ላይ ተፅዕኖ እንደሚኖራቸውም ይገለጻል፡፡ በተመሳሳይ በአገራችን ከገንዘብ ዝውውር መጠን መቀነስ ጋር ብቻ ሳይሆን፣ በወቅቱ በተከሰቱ ጦርነትና ወረርሽኝ ምክንያት ኢኮኖሚያዊ መቀዛቀዝ መኖሩን ማየት ብዙም ከባድ አይሆንም፡፡

ከባንክ ውጭ ያለ ገንዘብ

ለገንዘብ ለውጡ እንደ ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ የተወሰደውና በኢትዮጵያ የባንኮች ማኅበር ዕውቅና የተሰጠው ጉዳይ፣ ከባንክ ውጪ ያለ የገንዘብ መጠን ጉልህ እንደነበር ነው፡፡ በወቅቱ የነበረው የማኅበሩ ጥናትና የብሔራዊ ባንክ መረጃ እንደሚያሳየው፣ ከባንክ ውጪ ያለው ገንዘብ መጠን ወደ 96 ቢሊዮን ብር እንደሚደርስ፣ የገንዘብ ለውጥ በማድረግና ይህንን ገንዘብ ወደ ባንክ እንዲመጣ በማድረግ መቀነስ እንደሚቻል ሐሳብ የቀረበበት ነው፡፡ ለዚህም እንዲረዳ ከላይ ያነሳናቸው ጥብቅ መመርያዎች እንደ የወጪ መጠንን መቀነስና በእጅ የሚያዝ ገንዘብን መገደብ የመሳሰሉት ዕርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ ነገር ግን አሁንም ከባንክ ውጪ ያለው የገንዘብ መጠን ወደ 133 ቢሊዮን ብር የተጠጋ ሲሆን፣ ይህም ከገንዘብ ለውጡ በፊት ከነበረው መጠን ጨምሮ እንደሚገኝ ያሳያል፡፡

በተለይ ከባንክ ውጪ ያለውን ገንዘብ ወደ ባንክ በማዞር የባንኮችን የፋይናንስ አቅም የማጎልበት ሒደት የአጭር ጊዜ እምርታን ያሳየ ቢሆንም፣ ገንዘብ ከፋይናንስ ዘርፍ ውጪ ተመልሶ በመውጣቱ ይኼንን ዓላማም ሙሉ በሙሉ አሳክቷል ለማለት ያስቸግራል፡፡ የገንዘብ ለውጡን ተከትሎ ዕድገት ያሳየው ተቀማጭ ሒሳብ ተመጣጣኝ የሆነ የብድር ፍላጎት በመኖሩ ባንኮች ለማበደር ሰይቸገሩ እንዲቆይ ያደረገ ነው፡፡ በኋላም የአገሪቱን የገንዘብ ዝውውር (Broad Money) ዕድገት ወደ ላይ በማምጣት ለዋጋ ንረት መጨመር ጉልህ ድርሻ እንደያዘም፣ በቅርቡ ከወጡት የገንዘብ ፖሊሲዎች መረዳት ይቻላል፡፡ በተለይ በባንኮች እጅ ያለውን ገንዘብ መጦ ከማውጣትና ብድርን ከማቆም አንፃር በተወሰዱ ዕርምጃዎች፣ በባንክ ዘርፉም ቢሆን የነበረው የገንዘብ እንቅስቃሴ ዕድገት እንደነበረው ነው፡፡

የዋጋ ንረት

ለገንዘብ ለውጥ ሌላኛው ምክንያት ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው አንዱና ዋነኛው ምክንያት፣ ጠንካራ የገንዘብ ፖሊሲን በመተግበር የዋጋ ግሽበት መጠንን መቆጣጠር ነው፡፡ በአገራችንም የዋጋ ንረት ከገንዘብ ለውጡም በፊት የሁለት አኃዝ ደረጃን ይዞ የቆየ ሲሆን፣ ለውጡ ከተደረገበት ጊዜም በኋላ ይኼው አካሄድ በተጠናከረ መንገድ ቀጥሏል፡፡ እንዲህም የኑሮ ውድነት ደረጃውን እያጎለበተ የሄደበት ነው፡፡ በመርህ ደረጃ ከገንዘብ ለውጥ በኋላ አብዛኛው ገንዘብ በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ በመንቀሳቀስ በተወሰነ ደረጃ የዋጋ ንረትን የማለዘብ ባህሪ ሊያመጣ እንደሚችል ነው፡፡ ነገር ግን የዋጋ ግሽበት እያደገ የመጣና መንግሥት በኋላም ለወሰዳቸው የኢኮኖሚ ዕርምጃዎች መነሻ ቁልፍ ምክንያት ሆኗል፡፡ የባንኮች በብሔራዊ ባንክ ተቀማጭ የሆነው የገንዘብ መጠን (Reserve) ከአምስ በመቶ ወደ አሥር በመቶ እንዲያድግ፣ በተወሰኑ ምርቶችና አገልግሎቶች የዋጋ ቁጥጥር፣ የብድር ዕገዳና ሌሎች ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲዎች ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ ውጤቱም በተወሰነ ደረጃ በቅርቡ የግሽበት መጠኑ መጠነኛ ቅናሽ እንዲያስመዘግብ እያገዘ ነው፡፡ ነገር ግን የገንዘብ ለውጥ ብቻውን ለዋጋ ንረት ያለው አስተዋጽኦ እምብዛም አመርቂ እንዳልሆነ ያሳየ፣ ከሌሎች የፖሊሲ ግብዓቶች ድጋፍ ውጪ ትርጉም ያለው ለውጥ በኑሮ ውድነት ላይ ሊያመጣ እንደማይችል ያመላከተ ነው፡፡ በሌላ አነጋገርም የአገራችን የዋጋ ግሽበት መነሻ በወቅቱ ከነበረው የገንዘብ ዝውውር መጠን ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ቢኖረውም፣ ሌሎች እንደ ምርታማነት መጨመር፣ ከገበያ መዛባት፣ ከኢኮኖሚ አሻጥርና ከሌሎች ገፊ ምክንያቶች ጋር በስፋት የተቆራኘ መሆኑንም አስተምሮ ያለፈም ነው፡፡

የወለድ ተመን (የገንዘብ ዋጋ)

ከገንዘብ ለውጥ በፊት የነበሩት የተቀማጭ ገንዘብና የብድር የወለድ ምጣኔ መጠን አሁንም ብዙ ሳይቀየሩ የቀጠሉ ሲሆን፣ በተለይ በባንኮች በኩል ከሚገኘው የገንዘብ መጠን መጨመር ጋር ተያይዞ በተለይ የብድር ተመን መቀነስ የሚጠበቅ ቢሆንም፣ በዚህ ረገድ እምብዛም ለውጥ አልታየም፡፡ ይኼም የባንኮች የማበደሪያ ተመን መነሻ ሆኖ የሚያገለግለው በማዕከላዊ ባንኩ ለተቀማጭ ገንዘብ እንዲከፈል የተቀመጠው ዝቅተኛው የወለድ ተመን ያልተቀየረ ከመሆኑ አንፃር፣ የብድር ተመን ላይ ለውጥ አለመታየቱም እምብዛም የሚያስደንቅ አይደለም፡፡ እንዲያውም ወደኋላ የወጡት የሪዘርቭ ከፍ ማለት፣ የብድር ዕግድ፣ የውጭ ምንዛሪና የቦንድ ግዥ መመርዎች በባንኮች ገቢ ላይ ተፅዕኖ ከማሳደራቸው አኳያ የማበደሪያ የወለድ ተመንን ከፍ እንዲል አስተዋጽኦ ሊኖራቸው እንደሚችልም የሚጠበቅ ነው፡፡ በተለይ ደግም ከባንክ ውጪ ካለ ገንዘብ መጨመር ጋር ተያይዞና በአንዳንድ ከላይ ያነሳናቸው ፖሊሲዎች ምክንያት፣  የባንኮች የተከማቸ ገንዘብ መውረድ ወይም ውስንነት ምክንያት የገንዘብ ዋጋ ሊጨምር እንጂ ሊቀንስ እንደማይችል መገመት አይከብድም፡፡ ይህንን አባባል ሊቀይር የሚችለው ለተቀማጭ ገንዘብ የሚከፈለው የወለድ መጠን ዝቅ ማለት መሆኑን ግን ከታሪክ መማር ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በኢሕአዴግ ጊዜ የነበረው የገንዘብ ለውጥ ከሦስት ወይም ከአራት ዓመት በኋላ ለተቀማጭ ገንዘብ የሚከፈለው የወለድ መጠን ከስድስት ወደ ሦስት ፐርሰንት ያወረደ ሲሆን፣ ይህም የማበደሪያ መጠኑን ክ12 ወደ 10 እና 11 በመቶ ዝቅ አድርጓል፡፡ አሁን ያለው የባንኮች የማበደሪያ ወለድ መጠን በራሱ ትልቅ የሚባልና ወደፊትም ኢንቨስትመንትን ሊጎዳ የሚችልበት መጠን ላይ ከመድረሱ በፊት የፖሊሲ ዕይታን ሊቸረው የሚገባም ይመስላል፡፡ የገንዘብ ለውጡም በዚህ ላይ ያደረገው አስተዋጽኦ አለመኖሩም የሚያስቆጭ ነው፡፡

የባንክ ሒሳቦችና ቁጠባ

የገንዘብ ለውጡ ዋነኛ የስኬት መንገድ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችው፣ በተወሰነ ደረጃ የባንኮች የተቀማጭ ገንዘብ መጠንን መጨመርና በባንክ የሚከፈቱ ሒሳቦችን ማሳደግ ናቸው፡፡ ከገንዘብ ለውጡ በኋላ የባንኮች ተቀማጭ ሒሳብ ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ የደረሰ ሲሆን፣ ይህም በፊት ከነበረው መጠን አንፃር ጥሩ ዕድገት ያለው ነው፡፡ በሌላ በኩል ጠቅላላ የባንኮች ሒዳብ ወደ ስልሳ ሚሊዮን እንዳደገ የተገለጸ ቢሆንም፣ መሬት ላይ ካለው እውነታ አንፃር መመርመርን የሚሻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁንም የባንክ አገልግሎት ያልደረሰባቸው አከባቢዎችና የባንክ ልምምድ የሌላቸው ዜጎች በስፋት ከመኖራቸው አንፃር፣ የቀረበው ሪፖርት ችግሮች እንዳሉበት መመስከር ይቻላል፡፡ ይህም ትክክለኛ የባንኮች ሒሳብ (አካውንት) ዕድገት ምንጩ እስካሁን ባንክ  ተጠቃሚ ካልሆነው የኅብረተሰብ ክፍል ይሁን አልያም በአንድ ደንበኛ የሚከፈቱ ብዛት ያላቸው ሒሳቦች ምክንያት መሆኑ መለየቱ ጠቃሚ ነው፡፡ አሁን ካለው የኅብረተሰባችን ባንክን የመጠቀም ባህሪ አንፃር፣ እንዲሁም ከባንክ ውጪ ካለው የገንዘብ መጨመር አኳያ ወደኋላ የተነሳው ምክንያት ሚዛን የደፋ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ ለዚህም ይመስላል ወደኋላ የመጣው የብሔራዊ ባንክ መመርያም አንድ ደንበኛ በአንድ ባንክ ውስጥ ከአንድ ሒሳብ በላይ እንዳይኖረው፣ ለዚህም ባንኮች ብቸኛ መለያ የመስጠት ግዴታን ሊደነግግ የቻለው፡፡

ይህ መመርያ ከገንዘብ ለውጥ ጎን ለጎን አብሮ ሊተገበርና በተለይ የብሔራዊ መታወቂያን ቁጥር በመጠቀም ለሁሉም ባንክ የሚያገለግል መለያ ቢቀመጥ፣ ትክክለኛውን የባንክ ተጠቃሚ ቁጥር ለመለየት የሚያስችል ቢሆንም፣ ቢያንስ በተቀማጭ ገንዘብ ረገድ የታየው ዕድገት መጠን በተወሰነ ደረጃ ከባንክ ውጪ የነበረውን ገንዘብ ተመልሶ ወደ ባንክ እንዲገባ እንዳገዘ የሚያሳይ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ከባንክ ውጪ ያለው ገንዘብ ተመልሶ መጨመርም ግራ የሚያጋባና ጥልቅ ጥናት ተደርጎ፣ ወደፊት የፖሊሲ ዕርምጃዎችንም ለመውሰድ የሚጋብዝ ነው፡፡ ነገር ግን በማክሮ በኩል ያለውን የቁጠባ መጠን መለካት ስለሚቻል ጉዳዩ እምብዛም አከራካሪ የሚሆን አይደለም፡፡ አሁንም ቢሆን የአገራችን የቁጠባ መጠን ከአገራዊ ምርት አንፃር ያለው ጥምረት አነስተኛ ሲሆን፣ ይህም ከሰሐራ በታች ካሉ አገሮች አማካይ መጠን አንፃርም ሲታይ ዝቅ ያለ ሆኖም ቀጥሏል፡፡ ስለዚህ ከገንዘብ ለውጥ ባሻገር ቁጠባን የሚያበረታቱ ዕርምጃዎች ወደፊትም አስፈላጊ እነደሚሆኑ አያጠያይቅም፡፡

ዲጂታላይዜሽንና ጥሬ ገንዘብ አልባ (Cashless) ኢኮኖሚ

የአንድ አገር ኢኮኖሚ ሙሉ ለሙሉ በቴክኖሎጂ ብቻ በታገዘ የገንዘብ ዝውውር ብቻ የማካሄድ ሥራ በአንድ ሌሊት የሚገኝ ተዓምር እንደማይሆን ይታወቃል፡፡ በዚህ ረገድ የአገሮችን ልምድ ብናስተውል ያደጉ የሚባሉ አገሮች እንኳ ሙሉ ለሙሉ የጥሬ የገንዘብ አልባ ኢኮኖሚ የላቸውም፡፡ ይህንንም አሠራር በቴክኖሎጂ በታገዘ አካሄድ እየሸረሸሩ የመሄድ እንጂ የማጥፋት ታሪክ በዓለም ላይ እንደሌለ ነው፡፡ ነገር ግን እንደ ሳዑዲ ያሉ አገሮች የጥሬ ገንዘብና የአገራዊ ምርት ጥምርታ እስከ ሦስት በመቶ ድረስ ዝቅ ያለ ከመሆኑ አንፃር፣ የገንዘብ ለውጡ ይዞ የተነሳው ዓላማ አበረታችና ለወደፊቱም የቴክኖሎጂ ዕድገት በር ከፋች የሚሆን ነው፡፡

ከገንዘብ ለውጥ በኋላም ጥሬ ገንዘብ ንጉሥ ነው

እዚህ ላይ ከላይ በገለጽነው ምክንያት አሁንም ቢሆን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በጥሬ ገንዘብ ላይ ያለው ጥገኝነት ያልቀነሰ ከመሆኑ አንፃር፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ከማስተዋወቅና ከማላመድ አንፃር ሰፊ ሥራ የሚጠይቅ ነው፡፡ የሞባይል፣ የዋሌት፣ የኢንተርኔትና የሌሎች ግልጋሎቶች ተጠቃሚነት እያደገ እየሄደ ሲሆን በመንግሥት ደረጃ እንደ ቴሌ ብርና ሌሎች የኤሌክትሮኒክ የክፍያ ዘዴዎችን ለኅብረተሰቡ የማቅረብ ሒደት የታየው በጎ ጎን ይበል የሚያስብልም ነው፡፡ በኢቲስዊች መሪነት የተጀመረው የባንኮችን የዋሌትና የሞባይል ሒሳቦች የማስተሳሰር ሥራም ለወደፊቱ የዲጂታል አካሄድ ጥሩ ግብዓት የሚሆን፣ ባንኮችም ሆነ ተጠቃሚዎችም የወደፊቱ የባንክ ሥርዓት ወደ ቴክኖሎጂ እንዲያመራ በተዘዋዋሪም አቅጣጫም ቢሆን ያሳየ፣ እንዲሁም በኅብረተሰቡ በኩልም ቴክኖሎጂን የመልመድ ባህሪን ያስጀመረ በመሆኑ ለወደፊቱ ተጠናክሮ መሄድ ከሚገባቸው ጉዳዮች ዋነኛ ሆኖ እንዲነሳ ያደርገዋል፡፡

ሙስናና ሕገወጥ ገንዘብ ዝውውር

እንደ (ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል) የሙስና ሪፖርት መሠረት ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2020 ከ180 አገሮች ውስጥ በሙስና 94 ደረጃ ያገኘች ስትሆን፣ ይህም የሙስና መጠን እያደገ ከመጣባቸው አገሮች ተርታ ውስጥ ትመደባለች፡፡ የገንዘብ ለውጡ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ በዚህ ረገድ የታየው ለውጥ ለመቃኘት የሚያስችል መረጃ ማግኘት ከባድ ቢሆንም፣ በወቅቱ የነበረው የሙስና መጠን መለኪያ ችግሩን በስፋት የሚስተዋል መሆኑንም ያሳየ ነው፡፡ በመርህ ደረጃ የገንዘብ ለውጥ ማድረግ ለብቻው ሙስናን ከማስወገድ አንፃር የሚኖረው ደረጃ በጣም ውስን እንደሆነ፣ ሌሎች የባህሪና የመልካም አስተዳደር ለውጥን ሊያመጡ የሚችሉ የዕርምት ዕርምጃዎችን ድጋፍ ከመሻቱ አንፃር ብዙ ሥራ የሚጠይቅ ነው፡፡ ከሕገወጥ ገንዘብ ዝውውር አንፃርም ተመሳሳይ የተጋላጭነት ባህሪዎች እንዳሉት በተለያየ ጊዜ የሚወጡት (Financial Action Task Force FATF) ሪፖርቶች የሚያሳዩ ሲሆን፣ በተለይ የዚህ መገለጫ ሆኖ የሚታየው በባንክና በትይዩ ገበያ ያለው የምንዛሪ ዋጋ ልዩነት ከገንዘብ ለውጡም በኋላ ለፍትሕና ለቁጥጥር አዳጋች የሆነበት ደረጃ መድረሱ ነው፡፡ ይህም ከኢኮኖሚያዊ ምክንያት ባሻገር ከፖለቲካዊ ዳራዎች ጋር ተገናኝቶ በቅርቡ የጥቁር ገበያውን ዋጋ በኢኮኖሚ አሻጥር ወደ ላይ የመስቀል አዝማሚያ በማሳየቱ፣ መንግሥት በወሰዳቸው አበረታች ዕርምጃዎች በቁጥጥር ሥር እንዲውል መደረጉን ማንሳት ይቻላል፡፡ ነገር ግን የተጋላጭነቱ መጠን በገንዘብ ቅያሪው ምክንያት ያልተገታና እየጨመረ የመጣ፣ ሌሎች የኢኮኖሚ ማረጋጊያ ድጋፎችና የመንግሥት ሕጋዊና አስተዳደራዊ ዕርምጃዎችንም የጠየቀ ነው፡፡

ይህም የገንዘብ ቅያሪን ሕገወጥ ድርጊትን ከመከላከል አንፃር ብቸኛ መንገድ እንዳልሆነ፣ እንዲያውም በዚህ ዓላማ ለመጠቀም ማሰብ ከመነሻውም ትክክለኛ የሚባል አካሄድ እንዳልነበረ ያሳያል፡፡ ተጨማሪ ዕርምጃዎች መወሰዳቸው አግባብነት ያለውና ወደፊትም በዚህ ዙሪያ ጠንከር ያለ አካሄድን መከተል ኢኮኖሚን ከመታደግ አልፎ፣ ወንጀልን ከመከላከል አንፃር ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው ያስተማረም ነው፡፡ በተለይ ከዝውውር ውጪ ያለ ገንዘብ መጨመር ሒደት አሁንም ለሕገወጥ ገንዘብ ዝውውር ያለው የተጋላጭነት መጠን ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ያለ በመሆኑ፣ የቁጥጥር መጠኑ በዚህ ልክ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ማሳያም ነው፡፡

በግብር አሰባሰብ ረገድ

በኢትዮጵያ ከግብር የሚገኝ ገንዘብ ከአገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት አኳያ ለብዙ ጊዜያት ከአሥር በመቶ በታች ሲሆን፣ ከዓለም አቀፍ መሥፈርት አንፃር (Collin Clark Critical Limit-25% Revenue Per GDP) በታች ነው:: የገንዘብ ለውጥን ተከትሎ አብዛኛው ገንዘብ በባንክ ዝውውር መስኮቶች የሚከናወን በመሆኑ፣ በፊት ከነበረው ግብርን የመደበቅና ገቢን ለማስላት መቸገርና ካለመክፈል ችግሮች አንፃር የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታትና መረጃ ለማግኘት ስለማያስቸግር፣ የገቢ ግብርን ከመጨመር አንፃር አዎንታዊ ውጤት እንደሚኖረው ይጠበቃል፡፡ ይህም አገሪቱ የሚገጥማትን የበጀት ጉድለት በተወሰነ መጠን ለመሸፈን የሚያስችል ሲሆን፣ የተጠናከረ የገቢ ግብር አሰባሰብ ሥርዓት ከማስፈን አንፃርም የራሱ የሆነ አዎንታዊ ውጤት ይኖረዋል፡፡ ነገር ግን ገቢን ሊያውኩ የሚችሉ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ፣ ጦርነትና ወረርሽኝ ችግሮች በስፋት ከመኖራቸው አኳያ የትኛው ተፅዕኖ ይበልጥ በገቢ ግብር አሰባሰብ ላይ ጫና ይኖረዋል የሚለው ወደፊት የሚታይ ነው፡፡ በመንግሥት ደረጃ ከወጣው ዕቅድ አንፃር በዚህ በኩል ሊመጣ የሚችለው መሻሻልም በአዎንታዊ ጎኑ መውሰድ የሚቻል ነው፡፡ ባለፉት አምስት ወራት የታየው አፈጻጸም ከታቀደው አንፃር ጉድለት ቢኖረውም፣ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንፃር ዕድገት ማሳየቱም በከፊልም ቢሆን (በአሠራር ሒደቱ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎች እንዳሉ ሆነው) በግብር ሥርዓቱ ላይ ያለውን መሻሻል ጠቃሚ ማድረግ ያስችላል፡፡

የፋይናንስ አካታችነት

ከፋይናንስ አካታችነት አንፃር በኢትዮጵያ ውስጥ የባንክ ሒሳብ ያላቸው ሰዎች ወደ 35 በመቶ እንደሆኑ ሪፖርቶች ሲያሳዩ፣ ከገንዘብ ለውጡ በኋላ በባንክ ውስጥ ያለው የአካውንት ቁጥር ወደ 60 ሚሊዮን እንደደረሰ ይነገራል፡፡ ይህም ካለው የሕዝብ ብዛት አንፃር 60 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የባንክ ሒሳብ አለው ወደ ሚል ድምዳሜ ላይ የሚያደርስ ቢሆንም፣ በተለይ ከገንዘብ ለውጡ ሒደት ጋር ተያይዞ በአንድ ግለሰብ ወይም ድርጅቶች የሚከፈቱ ሒሳቦች ላይ ወሰን ባለመኖሩ ቁጥሩን የፋይናንስ አካታችነት መለኪያ አድርጎ ለመውሰድ የሚያስቸግር ነው፡፡ አሁንም በአገራችን ጥሬ ገንዘብ ላይ ያተኮረ ግብይት የበላይነት ከመያዙ አንፃር፣ የባንክ ሒሳብ የሌለው ወይም በባንክ ተጠቃሚ ያልሆነ የኅብረተሰብ ቁጥር ብዙ እንደሆነ ማስተዋል አያዳግትም፡፡ በዚህ መሥፈርት አገራችን በቅርባችን ካሉ አገሮች ለምሳሌ እንደ ኬንያ (80 በመቶ) የፋይናንስ አካታችነት ሒደት ላይ ስንወዳደር ብዙ መከናወን የሚገባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ምስክር ነው፡፡ በተለይ ከድህነት፣ ከባንክ ተደራሽነት፣ ሒሳብ ለመክፈት ከሚጠየቁ ሰነዶችና የአገር አቀፍ መታወቂያ ካለመኖርና ከሌሎች ምክንያቶች አንፃር ዘርፈ ብዙ የፖሊሲ ማሻሻያዎች እንደሚያስፈልጉም ማሳያዎች ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ ኅብረተሰቡን ዲጂታል የክፍያ ዘዴዎችን የማለማመድ፣ አስፈላጊ የቴክኖሎጂ ዝርጋታና ተደራሽነት፣ የባንኪንግ ትምህርትና ድጋፍ በስፋት ተቀርፀው ሊሠራበትም የሚገባ ነው፡፡ ነገር ግን በገንዘብ ለውጥ ምክንያት የመጣን የፋይናንስ አካታችነት መጠን በትክክል ለማስቀመጥ የሚያስችል መረጃ በአገራችን ውስጥ ማግኘት ለመንግሥትም ቢሆን ቀላል አይሆንም፡፡

ማጠቃለያ

በአገራችን ሕጋዊ የሆነ የወረቀት ገንዘብን የማስተዋወቅ ታሪክ የራሱ ትልቅ ዳራ ያለው ነው፡፡ ነገር ግን መጀመርያ የተደረገው የገንዘብ ለውጥ በዚህ ረገድ  የአገራችን የነፃነት መገለጫ የሆነውን ኢትዮጵያዊ ገንዘብ የማስተዋወቅ ትልቅ ዓላማ ይዞ የተነሳ ከመሆኑም አንፃር፣ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውና ገንዘብ ከኢኮኖሚ ፋይዳ ባለፈ የነፃ አገር ምልክት እንደሆነም ያስገነዘበ የታሪክ ቅርስ ነው፡፡ በቀጣይ የተደረጉትም የገንዘብ ለውጦች የራሳቸው በቂ ምክንያቶች ቢኖራቸውም፣ በደምሳሳው በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ ወይም በሁለቱም ምክንያቶች እንደሆነ ታሪክ ያሳያል፡፡

በተለይ ከንጉሡ በኋላ ባሉ ሁለት ሥርዓቶች የተደረገው የገንዘብ ለውጥ በአንዳንድ የኢኮኖሚ ባህሪያት ላይ ያመጣውን የአጭርና የረጅም ጊዜ ለውጥ መጥኖ ለማየት አስቸጋሪ ቢሆንም፣ በተለይ በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ካልሆነ በቀር በምክንያትነት በሚጠቀሱት ጉዳዮች ላይ የተለየ ለውጥ አይስተዋልም፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገት ለውጥ፣ የዋጋ ንረት፣ ከባንክ ውጪ ባለ ገንዘብ፣ በወለድ ምጣኔ፣ በኢኮኖሚ መዋቅርና በመሳሰሉት ላይ ከሚጠበቀው የኢኮኖሚ መርህ አካሄድ አኳያ በብዛት ያልተጠበቁ ውጤቶችን ሲያስገን ይስተዋላል፡፡ በተመሳሳይ ከአንድ ዓመት በፊት የተደረገው የገንዘብ ለውጥ በታቀደለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ከመጠናቀቁም ባሻገር፣ በፀጥታና በሌሎች ጉዳዮች የመስተጓጎል ችግርም አልተስተዋለም፡፡ ነገር ግን ከተቀመጠለት ዓላማ አንፃር በተለይ አሁንም ከባንክ ውጪ ያለውን የገንዘብ መጠን (ወደ 133 ቢሊዮን ብር) ከመቀነስ፣ በቴክኖሎጂ በታገዘ የገንዘብ ዝውውርን ከማስፈን፣ ከፋይናንስ አካታችነት፣ ሕገወጥነትን ከመግታት፣ የወለድ መጠንን ከማውረድ አኳያ ተጨማሪ የፖሊሲ ድጋፎችን ወደፊት የሚጠይቅ መሆኑን ያሳለፍነው አንድ ዓመት ያሳየ ነው፡፡ በተለይ የወንጀል ምንጭ የሆነው ከባንክ ውጪ ያለ ገንዘብ ማደግ፣ አሁንም ቢሆን ጥሬ ገንዘብ የንግሥናው ቦታ ላይ መፈናጠጡን የሚመሰክር በመሆኑ ልዩ ትኩረት ይፈልጋል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...