ኢትዮጵያውያን ጠላቶቻችንን በጋራ መመከት የዘመናት ታሪክ አለን፡፡ አገር ላለማሳፈር በአሸናፊነት ማማ ላይ እንድንቆም ያደረገን አንድነታችንና ትብብራችን ነው፡፡ ይህም በየዘመኑ የታየ ስለመሆኑ አይታበልም፡፡ ቅድሚያ ለአገር የሚለው እምነታችን፣ ትብብራችን አሽናፊ አድርጎናል፡፡
በየትኛውም ሁኔታ የሚገጥሙንን ችግሮች ለመወጣት አሁንም የሚያስፈልገን ትብብራችንና አንድነታችን ነው፡፡ ተነጣጥሎ ጉዞ የትም እንደማያደርሰን ከጥንት እስከ ዛሬ ያለው ታሪካችን ይነግረናል፡፡ መከፋፈል የውድቀታችን መንደርደሪያ መሆኑን በሚገባ በተግባር ጭምር ለማረጋገጥ ያለንበት ዘመን ምስክር ነውና ያለአንድነት ድል እንደ ማይኖረን ተገንዝበን ይህንን ማጠንከር አለብን፡፡
ሽብርተኛው ቡድን አገር ለማፍረስ ሥሎት የነበረው ሰይፍ ባንተባበር ይቆራርጠን ነበር፡፡ እውነት በመያዛችና በጋራ በመነቃነቃችን ከየትኛውም ጊዜ በተለይ በመደማመጣችን አገር የማፍረስ ስሌቱ እንዳይሰምር ሆኗል፡፡
ጠላታችን ዛሬም የተኛልን ባይሆንም ከዚህም በኋላ በጋራ፣ በኅብረትና በመተሳሰብ ዕርምጃችንን ከቀጠልን በሁሉም መስክ ድል ማድረግ እንችላለን:: በወንበዴዎች የፈረሱ መሠረተ ልማቶቻችንን መልሰን እንገነባለን፡፡ የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን ወደ ቀዬአቸው መልሰን የቀደመ ሕይወታቸውን እንዲመሩ ማድረግ እንችላለን፡፡
የፈረሱ ትምህርት ቤቶችን ጠግነን ከትምህርት የቀሩ ልጆቻችንን ማስተማር እንቀጥላለን፡፡ ህልውናችን ላረጋገጡልን የዘማች ቤተሰቦች ደርሰን አብሮነታችን እናሳያለን፡፡ የጤና ተቋሞቻችንን መልሰን ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ለማድረግ ተባብረን መሥራት እንችላለን ብለን ከተነሳን እናደርገዋለን፡፡ በአጠቃላይ በውጭ ጠላቶቻችንም ሆነ በውስጥ ቦርቧሪዎችና አጥፊዎች የታመመውን ኢኮኖሚያችንንም ቢሆን በጥሩ ፖሊሲ ታግዞ ከሕመሙ እንዲፈወስ ማድረግ የምንችለው በትብብርና በመተሳሰብ ነውና እንችላለን የሚለውን እምነታችንን ማጠንከር አለብን፡፡
በአጠቃላይ ይህ ጦርነት ብዙ ያሳጣን ቢሆንም ኢትዮጵያን የበለጠ ከፍ እንድናደርግ፣ አንድነትና ትብብራችንን መልሰን እንድናመጣ ማድረጉ የማይታበል ሀቅ ነው፡፡ ይህንን መንፈስ በሁሉም መስክ ልንጠቀምበት ይገባል፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ያሉ ዜጎች እያደረጉት ያለው ትብብር ኢትዮጵያ ያላትን ትልቅ ተስፋ አመላክቷል፡፡ ሕወሓት ጦር ከሰበቀበት ጊዜ ጀምሮ አገር ለማዳን እየተደረገ ያለው ርብርብ የተጎዱ ወገኖችና የመከላከያ ሠራዊቱን ለመደገፍ እየተሰጠ ያለው ምላሽ ልብ ይሞላል፡፡ አሁንም የጠፋውን ለመመለስ ከዚህም የበለጠ ሥራ ለመሥራት እየተደረገ ያለው ድጋፍ ቀላል አይደለም፡፡
በዓይነት፣ በጉልበት፣ በዕውቀትና በጥሬ ገንዘብ የሚደረገው ድጋፍ እስከዛሬ ያልታየ ነው፡፡ ዳያስፖራው በጋራና በተናጠል እየሰጠ ያለው ድጋፍም ኢትዮጵያን ለማዳን ከልብ እየተከፈለ ከመሆን አልፎ ጠላትን በጦር ሜዳ ከማንበርከክ ባለፈ ሌሎች ችግሮቻችንንና ድኅነትን በትብብር ድል ማድረግ እንደምንችል ያሳየ ነው፡፡
ይህ ከውጭም ከውስጥም ለተለያዩ ዓላማዎች እየዋሉ ያሉ ድጋፎች ግን በአግባቡ ሊተዳደር እንዲሁም ለተፈለገው ዓላማ በማዋሉ ረገድ ክፍተትን መድፈን ይገባል፡፡
አሁን በየአቅጣጫው በተለያዩ መንገዶች የሚሰበሰቡ ዕርዳታዎችን፣ ስጦታዎችንና እየተገቡ ያሉ ቃሎችን በትክክል አደራጅቶና ሰንዶ ለሚፈለገው ዓላማ እንዲውል ማድረግ ካልተቻለ የብዙዎች ልፋት ከንቱ ሊቀር ይችላል፡፡ የትብብር መንፈስንም ይጎዳል፡፡
በየሰፈሩ ገንዘብ ይዋጣል፡፡ በዓይነት ይሰጣል፡፡ ይህ ትልቅ ሀብት ስለሆነ በትክክል መሰብሰብ አለበት፡፡ ለሚሰጡ ድጋፎች ማረጋገጫ እንዲሆን ደረሰኝ መሰጠት አለበት፡፡ እንዲህ ያለው ድጋፍ የሚሰበስቡ አካላት በትክክል ሕዝብ እንዲያውቃቸው ማድረግና ሕጋዊ መሆናቸውንም ማረጋገጥ ተገቢ ነው፡፡
ዕርዳታው ከማን ተሰጠ በማን አካል ተሰብስቦ ወደሚፈለገው ቦታ ደረሰ የሚለው አሠራር ግልጽ ሊሆን ይገባል፡፡ ሕጋዊ አሠራር ከሌለ በስንዴ መካከል እንክርዳድ አይጠፋምና ሊሰረቅ ሊመዘበር ስለሚችል የእራስ አሰባሰብ በየትኛውም መንገድ ይሁን በማከል ግን አንድ ተጠያቂ አካል ሊኖረው ይገባልና በዚህ ረገድ ፈጣን ዕርምጃ መወሰድ አለበት፡፡
ሕጋዊ አሠራርና ተጠያቂነት ያለበት ትግበራ ጥቅሙ ብዙ ነው፡፡ ዜጎች እኔ በረዳሁት ለውጥ መጥቷልና ብለው የበለጠ እንዲነሱ ያስችላል፡፡ በጋራ አገር የመለወጥ ስሜትን የበለጠ ያጎለብተዋል፡፡ ለተጎዱ ወገኖች በትክክል ለመድረስ ያስችላል፡፡ የችግር ጊዜያችን እንዲያጥርም ያግዛል፡፡ ዕርዳታው የት ደረሰ የሚለውን ጥያቄ በአግባቡ ሊመልስ የሚችል ሰብሰብ ያለ ሕጋዊ አሠራር ይኑረን፡፡ ይህን ስናደርግ ምኞታችን ይሰምራል፣ ድላችን የበለጠ ትርጉም ይኖረዋል፡፡
አገር በየትኛውም አጋጣሚ መልካም ዕድሎችን የሚያበለፅጉ ዜጎችን ትወልዳለች፣ ታሳድጋለች ሙሉ ማኅበረሰብ ትመሠርታለች፡፡ ማኅበረሰብ ፖሊሲዎችን፣ ሥርዓቶችን፣ ሕግጋትና መመርያዎችን ተቋማዊ መሠረት ይጥልባቸዋል፡፡
ኃላፊነትና ተጠያቂነት ተጨባጭ ሚዛን ይኖራቸዋል፡፡ መንግሥታዊ ብቻ ሳይሆን ኅብረተሰባዊና ዜጋዊ ድርሻን ይጎናጸፋሉ፡፡ መልካችን በስሜታችን በተግባራችን የአንድነት ፀዳል መልበስ፣ መለወጥ፣ በሌሎች አዕምሮ ውስጥም የራሱን ሥፍራ ይይዛል፡፡
ተግባራዊ የዕውቀትንም ሆነ የዓላማ ስኬትን ይመዝናል፡፡ ከግላዊነት ወደ አገራዊነት አልፎም ዓለም አቀፋዊ አበርክቶን የምናጠናክረው በትብብር በመተሳሰብና በሕጋዊ መንገዶች ስንጓዝ ነው፡፡ ትብብራችን አንድነታችን ይቀጥል ይፅና፡፡