Tuesday, May 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግል ንግድ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ግኝትና የወጭ ንግድ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በ2013 የሒሳብ ዓመት ሁሉም ባንኮች በሚባል ደረጃ ከውጭ ምንዛሪ ግኝት ጋር ተግዳሮት የገጠማቸው መሆኑን በሪፖርታቸው አመልክተዋል፡፡ ባንኮች ከዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት ያገኙት የውጭ ምንዛሪ መጠን ዕድገት በጣም ዝቅተኛ ከመሆኑም በላይ አንዳንድ ባንኮች ከ2012 የሒሳብ ዓመት ያነሰ የውጭ ምንዛሪ ማግኘታቸውን ሪፖርት አድርገዋል፡፡

ከዚሁ ዓመታዊ ሪፖርታቸው መገንዘብ እንደሚቻለው ከተወሰኑ ባንኮች ውጭ አብዛኛው መጠኑ ይለያይ እንጂ ከዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት ያገኙት ገቢ ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ መጠነኛ ዕድገት ይታያል፡፡

ከዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት በሒሳብ ዓመቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ካገኙት ባንኮች መካከል አንዱ አዋሽ ባንክ ነው፡፡ አዋሽ ባንክ በሒሳብ ዓመቱ ከ900 ሚሊዮን ዶላር በላይ ያገኘ ሲሆን፣ ይህ ገቢ ከ2012 የሒሳብ ዓመት አንፃር ሲታይ 26 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑን ሲያመለክት የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን 2.7 በመቶ ብቻ ያሳደገው ቡና ባንክ ደግሞ በሒሳብ ዓመቱ ያገኘው 163.9 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያገኘው አቢሲኒያ ባንክ ደግሞ ይህ ገቢው ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ በመቶ ብልጫ ያለው ነው፡፡

ከዚሁ ባንኮቹ ሪፖርት መረዳት እንደሚቻለው ከዓመታዊ የውጭ ምንዛሪ ግኝታቸው አብዛኛው የተገኘው ከወጪ ንግድ ጋር ከተያያዘ ገቢ መሆኑን ያመለክታል፡፡ አዋሽ ባንክም አብላጫውን ያገኘው ከወጪ ንግድ ሲሆን፣ ቡና ባንክም 61.8 በመቶ የሚሆነውን የውጭ ምንዛሪ ያገኘው ከወጪ ንግድ መሆኑን አሳውቋል፡፡ ሌሎች ባንኮችም አብዛኛው ወይም ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነውን የውጭ ምንዛሪ ማግኘት የቻሉት ከወጪ ንግድ ጋር ከተያያዘ አገልግሎት ነው፡፡

ይህ የሚያሳየው ከውጭ አገር በሃዋላና በስዊፍት ከሚላክ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ አነስተኛ መሆኑን ነው፡፡ ከ2013 የሒሳብ ዓመት ሪፖርታቸውም የሚያሳየው ይህንን ነው፡፡

አዋሽ ባንክ ከ900 ሚሊዮን ዶላር ከውጭ አገር በሃዋላ ከተላከ ያገኘው የውጭ ከ30 በመቶ የሚበልጥ አይደለም፡፡ ቡና ባንክ ደግሞ 25.4 በመቶ ከሃዋላ አግኝቷል፡፡

እነዚህ ባንኮችም ሆኑ ሌሎች ባንኮች ከሃዋላ ያገኙት የውጭ ምንዛሪ 30 በመቶውን ያልዘለለ ነው፡፡

እንዲህ ያሉ ሪፖርቶች መረዳት እንደሚቻለው በ2013 ባንኮቹ ካገኙት የውጭ ምንዛሪ ውስጥ በሃዋላ ያገኙት ገቢ አነስተኛ መሆኑን ነው፡፡ ከወጪ ንግድ የውጭ ምንዛሪ ገቢ በላይ አገሪቷ ከሬሚታንስ የምታገኘው ገቢ የሚበልጥ ቢሆንም በሒሳብ ዓመቱ የባንኮች አብዛኛው የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከወጪ ንግድ ጋር የተያያዘ እንደሆነም አሳይቷል፡፡ የሒሳብ ዓመቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ከሐምሌ 2013 ዓ.ም. ወዲህ ግን በተለይም ባለፉት ሁለትና ሦስት ወራት ባንኮች በሃዋላ ወይም በሕጋዊ መንገድ በሚመነዘር የሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ መጠን እየጨመረ ስለመምጣቱ እየገለጸ ነው፡፡

በተለይ ዳያስፖራው ማኅበረሰብ ከውጭ ወደ አገር የሚልከውን ገንዘብ እንዲሁም እዚህ ከገባ በኋላ በሕጋዊ መንገድ እንዲልክ የተላለፈውን መልዕክት በመቀበል ተግባራዊ እያደረገ መምጣቱ ባንኮች ከዚህ ቀደም ሲያገኙት ከነበረው የውጭ ምንዛሪ በላይ ማግኘታቸውንም እየገለጹ ነው፡፡

በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የተለያዩ ባንኮች ፕሬዚዳንቶች እንደጠቆሙትም  ከቅርብ ወራት ወዲህ በሕጋዊ መንገድ የሚላክ ወይም የሚመነዘር የውጭ ገንዘብ ከፍ ብሏል፡፡ ዳያስፖራው እያሳየ ያለው ተነሳሽነት ለውጦች አሳይቷል፡፡

የዘመን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ደረጀ ዘነበ እንደሚገልጹት ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዳያስፖራው አገርንና መንግሥትን ለመደገፍ እያሳየ ያለው በጎ እንቅስቃሴ ከውጭ ወደ አገር የሚላከውን ገንዘብ በሕጋዊ መንገድ እየተጠቀመ መሆኑና በጥቁር ገበያ ላለመመንዘር እያሳየ ላለው ፍላጎት ማደግ በሕጋዊ መንገድ የሚመነዘረውንም ሆነ የሚላከውን የውጭ ምንዛሪ ማሳደጉ አይቀርም ብለዋል፡፡

ዳያስፖራው በተለያየ መንገድ አገርን ለመደገፍ መንግሥትንም ለማገዝ እያሳየ ያለው ቁርጠኝነት እየተገለጸባቸው ካሉ ጉዳዮች አንዱ በሕጋዊ መንገድ ገንዘብ በባንክ በመላክና በመመንዘር እየሆነ በመምጣቱ ለውጥ ምምጣቱ አይቀርም፡፡

ከዚህ ባሻገር በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የጥቁር ገበያ የሚካሄድባቸው አካባቢዎች ያሉ መደብሮች መታሸጋቸውም የውጭ ምንዛሪን ይዞ ወደ ባንክ የሚመጡትን መንዛሪዎች ቁጥር ከፍ የሚያደርግ በመሆኑ ያለ ጥርጥር በሕጋዊ መንገድ የሚደረግ የምንዛሪ መጠኑን ያሳደግዋል ይላሉ፡፡

ሌላው ቀርቶ ዓለም አቀፍ ካርድ ይዘው በሆቴልና በሌሎች አገልግሎቶች እየተጠቀሙት በመሆኑም ለውጭ ምንዛሪ ግኝቱ ዕድገት የራሱ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አቶ ደረጀ ጠቁመው እንዲህ ያለው ሒደት መቀጠልና መለመድ ያለበት ስለመሆኑ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

የእናት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ኤርሚያስ በበኩላቸው ከጥቂት ወራት በተለይም ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በሕጋዊ መንገድ የውጭ ገንዘብ እየተመነዘረ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ከዚህ በፊት የውጭ ምንዛሪ አስተናግደው የማያውቁ ቅርንጫፎች ሳይቀሩ የውጭ ገንዘብ እየመነዘሩ መሆኑ ትልቅ ለውጥ እየታየ መሆኑን የሚጠቀሱት አቶ ኤርሚያስ፣ በአሁኑ ወቅት በዳያስፖራው አካባቢው ከፍተኛ መነቃቃት እየታየ በመሆኑ በሕጋዊ መንገድ የሚመነዘረው የገንዘብ መጠን እንደሚጨምር አመላክተዋል፡፡

ይህ ለአንድ አገር ትልቅ ትርጉም እንዳለው የጠቀሱት አቶ ኤርሚያስ ይህንን መነቃቃት እንዲቀጥል ማድረግ የሚገባ መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡ አሁን ለውጡን የዚህን ያህል ደረጃ ዕድገት አሳይቷል ብሎ መግለጽ አስቸጋሪ ቢሆንም ነገር ግን ትርጉም ያለው ለውጥ ስለመታየቱ አስታውቀዋል፡፡ ይህ መነሳሳት አሁን ካለው አገራዊ ሁኔታ ጋር የተፈጠረ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ኤርሚያስ ሒደቱ ቀጣይ ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

አሁን ላይ የውጭ ምንዛሪ በሕጋዊ መንገድ የመመንዘር ፍላጎት ከፍ እያለ መምጣቱን መታዘብ እየተቻለ መሆኑን የጠቆሙት አንድ የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያ በበኩላቸው ዳያስፖራው በሕጋዊ መንገድ ገንዘብ ለመላክ እያሳየ ያለው መነቃቃት ሊፈጠር ከቻለባቸው ሁኔታዎችአንዱ በሕጋዊ መንገድ ገንዘብ መላክ ማለት ምን እንደሆነ ትርጉም እንዳለው በተለያየ መንገድ በተለያዩ አክቲቪስቶች ጭምር ቅስቀሳ በመደረጉ ነው ይላሉ፡፡ እኔም የዚህ ካምፔን አካል ነኝ ያሉት ባለሙያው እንዲህ ያለው ንቅናቄ ብዙ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ በሕጋዊ መንገድ ገንዘብ መላክ ወይም መመንዘር ለአንድ አገር ትልቅ ትርጉም ያለው ነውም ብለዋል፡፡

በተለይ ለአገሪቱ መሠረታዊ የሚባሉ ለምሳሌ ምግብ ነክና ሌሎች ምርቶችን ለማስገባት በሕጋዊ መንገድ በሚገባ የውጭ ምንዛሪ የሚገዛ በመሆኑ ይህንን ለመግዛት የሚያስችል የውጭ ምንዛሪ መንግሥት እንዲያገኝ ያግዛል፡፡ በብላክ ማርኬት መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶች ሊገቡ ስለማይችሉና በሕጋዊ መስመር የሚመነዘር የውጭ ምንዛሪ ለአገሪቷ የሚያስፈልጉ ምርቶችን ለማስመጣት የሚጠቅም በመሆኑ ግንዛቤ ተወስዶ ሁሉም የበኩሉን ማድረግ ይገባዋል ብለዋል፡፡ ሌላው በሕጋዊ መንገድ ምንዛሪን ማከናወን ባንኮች የውጭ ምንዛሪ የመያዝ አቅማቸው ስለሚያሳድግ ለሚቀርብላቸው ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ስለሚመሰጡ በባንክና በጥቁር ገበያ መካከል ያለው ልዩነት እየጠበበ እንደመጣም ጠቅሰዋል፡፡ ጥቁር ገበያ እንቅስቃሴ ሲቀንስ ደግሞ ወደ ባንክ የሚመጣው የውጭ ምንዛሪ ያግዛል፡፡

የበለጠ አሸናፊ እየመጣ ሲሄድ ደግሞ ሰዎች የሚፈልጉትን የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ሲጀምሩ ወደ ጥቁር  ገበያ የመሄድ ዕድሉ ይጠባል፡፡ ይህ ሲሆን በጥቁር ገበያና በባንክ መካከል ያለው የምንዛሪ ዋጋ ልዩነት በወራት ጊዜ ውስጥ እየጠበበ ስለሚመጣ ትልቅ ጥቅም ሊያመጣ ይችላል የሚል እምነት እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡

አሁን እንደታየው በሕጋዊ መንገድ የውጭ ገንዘብ የመመንዘር ባህሉ እንዲያድግ ከተፈለገ ደግሞ በጥቁር ገበያ አካባቢ የሚታየውን አሠራር በሕግ መቀየር እንደሚገባ የሚገልጹት አቶ ኤርሚያስ በተለይ በዚህ ወቅት የጥቁር ገበያ በግልጽ የሚካሄድባቸውን መደብሮች እንዲታሸጉ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡ የጥቁር ገበያ መደብሮችን አንዱን አሽጎ ሌላውን መተው ሳይሆን በጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ይህንን የግብይት ሥፍራ ቢያንስ ለሁለትና ለሦስት ወራት ማሸግ ብዙ ጠቀሜታ የሚኖረው መሆኑንም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ይህ አሁን ካለው የዳያስፖራው መምጣት ጋር ተያይዞ ሊወሰድ የሚገባ ዕርምጃ መሆኑንም የጠቀሱት አቶ ኤርሚያስ ለዘለቄታው ግን ምናልባት ጥቁር ገበያውን ሕጋዊ የማድረግ አሠራር መከተል ተገቢ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማሉ፡፡

ከባንክ ውጭ የምንዛሪ አገልግሎት የሚሰጡ አካላት በብሔራዊ ባንክ ታውቀው የምንዛሪ ተመናቸው ገደብ ኖሮት ቢመነዝሩ ምናልባት የሆነ ለውጥ ሊመጣ ይችላል የሚል እምነት አላቸው፡፡ ሌሎች አገሮችም እንዲህ የሚሠሩ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ኤርሚያስ እስካሁን በክልከላ፣ በማሸግና በመሳሰለው መንገድ ተወሰደ የተባለው ዕርምጃ ለውጥ ካላመጣ እስኪ ሕጋዊ እንዲሆን አድርገነው እንሞክረው ማለት ገቢ ነው፡፡ ይህንን በማድረግ ውጤት የማያመጣ ከሆነ መለወጥ ይቻላልና እንዲህ ያሉ አማራጮችን መመልከቱ ጥሩ ነው የሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚው ባለሙያው ግን ከአቶ ኤርሚያስ የተለየ ምልከታ አላቸው የጥቁር ገበያ ሕጋዊ እንዲሆኑ ማድረግ ይቻላል ይሆናል፡፡ ሕጋዊ እናድርጋቸው ቢባሉም እሺ ይላሉ ግን በዚያ ሕጋዊነት መስመር ለመሄድ ፈቃደኛ ይሆናሉ ተብሎ አይታመንም፡፡ ዋናው ነገር መንግሥት የሚተምነውና እነሱ የሚሸጡበት ዋጋ በፍፁም ሊቀራረብ አይችልም፡፡ ምክንያቱም እነሱ ከዚያ በላይ ማግኘት የሚፈልጉ በመሆኑ ሌላ ጥቁር ገበያ መፍጠር ስለሚሆን እነሱን ሕጋዊ አድርጎ መሥራት ብዙ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል የሚል እምነት የላቸውም፡፡ አሁን ግን ዳያስፖራው እያሳየ ያለው መነቃቃትና በሕጋዊ መንገድ መመንዘር ከተገባ ጥቁር ገበያውን ሊያደክም የሚችል መሆኑንም እኝሁ ባለሙያ ገልጸዋል፡፡ ‹‹በጥቁር ገበያ አንመነዝርም›› የሚለው አመለካከት እያደገ ከመጣ የጥቁር ገበያን አቅም እየቀነሰው በባንክና በጥቁር ገበያ ያለውን ምንዛሪ መጠን ሊያጠበው ሁሉ ይችላል ይላሉ፡፡ ባለሙያ ማብራሪያ ደግሞ ዳያስፖራው አሁን እያሳየ ያለው ለውጥ በመሆኑም ይህንን እንዲቀጥል ለማድረግ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን በተፋጠነ ሁኔታ መሠራት ይኖባቸዋል ይላሉ፡፡

በፖሊሲ ደረጃ መወሰድ አለባቸው ብለው ከጠቀሱዋቸው መካከል የውጭ ምንዛሪ ሪዘርቫችንን ማሳደግ አንዱ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ተመኑን ማስተካከል ግድ መሆኑንም ሌላው የምናገኘውን የውጭ ምንዛሪና የምናወጣውን ወጪ ማመጣጠን ያስፈልጋል፡፡

በሕጋዊ መንገድ ወደ ባንክ የሚመጣው የውጭ ምንዛሪ እያደገ መምጣት የአገርን አቅም ከማሳደግ ባለፈ ከጥቁር ገበያ መገታትንም የሚያመጣ ስለመሆኑ አሁን ዳያስፖራው ያሳየው ንቅናቄ የአንድ ሰሞን እንዳይሆን ማድረግ እንደሚገባውም ተገልጿል፡፡

ይህ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ያለው ለውጥ ከባንኮች አንፃር ምን ጠቀሜታ አለው? ለሚለው ጥያቄ የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያው ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ጥያቄዎችን በአግባቡ እንዲያስተናግዱ ይረዳል ይላል፡፡ ባንኮች የራሳቸው ፕራየሪቲ ተሰጥቷቸው የሚሠሩ ቢሆኑም በዚህ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው አስቀድሙ ተብሎ በተሰጣቸው መመርያ ነውና ይህንን ቅድመ ተከተል እስካስተካከሉ ድረስ ከዚያ በላይ ሊያደርጉ የሚችሉት ነገር እንደሌለም መታወቅ አለበት ይላሉ፡፡ ‹‹እነሱ ጋር የሚመጣውን የውጭ ምንዛሪ መንግሥት ባስቀመጠው መመርያ መሠረት የሚፈጸም በመሆኑ መሠረታዊና ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ምርቶችን ለማስመጣት በቂ የውጭ ምንዛሪ እንዲኖር ከማስቻሉም በላይ የተከማቸውን የውጭ ምንዛሪ ጥያቄ በአግባቡ መለስ የሚያስችል ዕድል ይኖረዋል፤›› በማለት አክለዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር ግን የውጭ ምንዛሪን በአግባቡ ከመጠቀም አኳያ የአገር ውስጥ ምርቶችን መግዛት ልምድን ማዳበር አንዱ መፍትሔ መሆኑን ነው ባሙያው የጠቆሙት የአገር ውሰጥ አምራቾች ያለባቸው ችግር መሸጥ አይደለም፡፡ አይደለም የሚሉት ባለሙያው ችግራቸው ማምረቻ ነው፡፡ አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በአብዛኛው ተወዳዳሪ ስላልሆኑ በተቻለ መጠን የአገር ውስጥ ምርቶችን መጠቀም በጣም አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ሌላው አሁንም መንግሥት የገበያ ማረጋጋት ሥራውን መዘንጋት የለበትም ብለው ይመክራሉ፡፡

በሕጋዊ መንገድ ገንዘብ የመመንዘር ልምድ ለማስቀጠል አቶ ኤርሚያስ ይበጃል ብለው ያመለከቱት ሌላው ነጥብ ዜጎች በሕጋዊ መንገድ የውጭ ገንዘብን መመንዘር ለአገር ምን ያህል ጠቀሜታ እንዳለው ማስተማር አለማቋረጥ ለዘለቄታው ጠቃሚ መሆኑን ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች