Monday, December 4, 2023

ከዳያስፖራው መጉረፍ ባሻገር መታየት ያለባቸው ጉዳዮች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ (ዶ/ር) እና የቢሯቸውን ጥሪ ተከትሎ ወደ አገር እየጎረፈ ያለውን የሰሞኑን የዳያስፖራ ማኅበረሰብ አመጣጥ ያየ፣ በ2000 ዓ.ም. መባቻ ለሚሊኒየም ክብረ በዓል ከያለበት የተሰባሰበውን ዳያስፖራ ስብስብ ትውስታ ማጫሩ አይቀርም፡፡ በወቅቱ ወደ ኢትዮጵያ በመጡ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ዳያስፖራ ዘንድም የዚህ ወቅት ትውስታ የማይሻር ሆኖ ቆይቷል፡፡ አንድም የታለሙ ሐሳቦች በነበራቸው አነሳስ ሳይቀጥሉ በመቅረታቸው ሲሆን፣ ሌላም ዳያስፖራው በወቅቱ ከነበረው መንግሥት ጋር የነበረው ግንኙነት መሻሻል ሳያሳይ በመቅረቱ ነው፡፡

በወቅቱ መንግሥት ከዳያስፖራው ጋር ያለውን ግንኙነት ለማሰማመር በማለም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥር የዳያስፖራ ጉዳዮች ዲሬክቶሬት ማቋቋሙ፣ ይኼንን ግንኙነት ፈቅ በማድረግ ረገድ የነበረው ሚናም አናሳ እንደነበር ሲነገር ከርሟል፡፡ ከዚህ ባለፈም መንግሥት በ1990ዎቹ አጋማሽ ላይ በውጭ ለሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተወሰኑ መብቶችን ለመስጠት በሚል የትውልደ ኢትዮጵያ ካርድ (ቢጫ ካርድ) እንዲያገኙ የሚፈቅድ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ተወላጅ የሆኑ የውጭ ዜጎችን በትውልድ አገራቸው የተለያዩ መብቶች ተጠቃሚ ለማድረግ የወጣ አዋጅ 270/1994›› ፀድቋል፡፡

አዋጁ የኢትዮጵያ ተወላጅ የሆኑ በርካታ የውጭ ዜጎች ከትውልድ አገራቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚፈልጉ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ ‹‹እነዚህ የውጭ ዜጎች ተለይተው አንዳንድ የመብት አጠቃቀሞችን የሚመለከቱ የሕግ ገደቦች ቢነሱላቸው፣ ለአገሪቱ ዕድገትና ለወገኖቻቸው ኑሮ መሻሻል የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ፤›› ዕሙን እንደሆነ ያትታል፡፡

ሆኖም የዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባል የሆኑት ኢትዮጵያውያን ከአገራቸው ጉዳዮች ሩቅ ሆነው የከረሙ ሲሆን፣ በበርካታ አጋጣሚዎችም ኢትዮጵያን የሚመራው መንግሥት ተቃዋሚዎች ሆነው ቆይተዋል፡፡ በአሜሪካና በአውሮፓ ከተሞች ሲያደርጓቸው የነበሩ የተቃውሞ ሠልፎች ላይ መንግሥት መብጠልጠሉ የተለመደ ነበር፡፡ በተለይም የመንግሥት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የመናገር ነፃነት ገደቦች የወቀሳ መነሻ ሆነው ቆይተዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም የጋዜጠኞች ነፃነት ከዓለም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኙ አገሮች ተርታ የሚሠለፍ ሲሆን፣ የጋዜጠኞች እስርና መሰል ገደቦች በተቃውሞ ሠልፎች ላይ የሚስተጋቡ ሐሳቦች ነበሩ፡፡

ይሁንና በጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ የተለወጠ ይመስል ነበር፡፡ እሳቸውም ገና ወደ ሥልጣን እንደመጡ ዳያስፖራውን በአገር ጉዳይ ለማሳተፍ ቁርጠኛ እንደሆኑና ዳያስፖራውም መልካም ምላሽ እንዲሰጥ ሲጠይቁ ተደምጠዋል፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያን በሚገኙባቸው የአሜሪካና የአውሮፓ ከተሞች በመዘዋወር ከዳያስፖራ ማኅበረሰብ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማስተካከል ውይይቶችንና ንግግሮችን አድርገዋል፡፡ እነዚህን ጉዞዎች ተከትሎም ዳያስፖራው በቀን አንድ ዶላር ለአገሪቱ ልማት እንዲለግስ በመጠየቅ የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ እንዲቋቋም ያደረጉ ሲሆን፣ መንግሥት በሚያዘጋጃቸው የኢኮኖሚ ዕቅዶችና በሚያስተላልፋቸው ኢኮኖሚ ተኮር ውሳኔዎች ላይ ሙያዊ ምክር የሚለግሱ የዳያስፖራና የአገር ውስጥ የኢኮኖሚ ባለሙያዎችን ያቀፈ የኢኮኖሚ አማካሪ ምክር ቤት ተመሥርቶም ነበር፡፡

ነገር ግን ሁለቱም ተነሳሽነቶች በተለይ በአባላቱ መካከል በሚነሱ ውዝግቦችና አለመግባባቶች ሳቢያ እንቅፋት የገጠማቸው ይመስላል፡፡ የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ አባላት በውስጣዊ አለመግባባቶች ሳቢያ ራሳቸውን ማግለል ጀመሩ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ ተመሳሳይ ችግሮች ከታዩበት የአማካሪዎች ምክር ቤትም እንደ ዓለም ባንክ ባሉ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና በትምህርት ተቋማት ልምድ ያካበቱ ባለሙያዎች ለቀዋል፡፡

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በውል ባይታወቅም፣ አንዳንድ መረጃዎች ሁለት ሚሊዮን ገደማ ይሆናል ይላሉ፡፡ እ.ኤ.አ. በነሐሴ 2021 ይፋ የተደረገው የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲና የዓለም አቀፉ የፍልሰት ተቋም (አይኦኤም) ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ 839 ሺሕ ገደማ ኢትዮጵያውያን ወደ ተለያዩ አገሮች ፈልሰዋል ይላል፡፡

‹‹በርካታ ቁጥር ያለው ፈላሽ የሚገኘው በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ሲሆን፣ ሳዑዲ ዓረቢያ ለ31 በመቶ ስደተኞች መዳረሻ ሆናለች፡፡ በመቀጠልም በደቡብ አፍሪካ (12 በመቶ) እና በተባበሩት ዓረብ ኤሚሬትስ (ዘጠኝ በመቶ) ይከተላሉ፤›› ይላል ጥናቱ፡፡

ይኼንን የማኅበረሰብ ክፍል ወደ ኢትዮጵያ ለመሳብም በቴሌቪዥን ማስታወቂያዎችና በቢልቦርዶች ዳያስፖራዎችን እንኳን ደኅና መጣችሁ በሚሉ መልዕክቶች በመሙላት መንግሥት እየተቀበላቸው ሲሆን፣ ባንኮችና ሌሎች ቢዝነሶች የመንግሥትን ጥሪ ተከትሎ ወደ አገር ቤት እየጎረፈ ለሚገኘው ዳያስፖራ የእንኳን መጣችሁ ለማለት የአገልግሎት ዋጋ ከማስተካከል አልፈው የተለየ አገልግሎት እስከ ማቅረብ ሲደርሱ ተስተውለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከንቲባ አዳነች አቤቤ አማካይነት የዳያስፖራ ፓርክን አስመርቆ ክፍት በማድረገ እንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል አድርጎላቸዋል፡፡

በርካቶች እንደሚስማሙት፣ የሰሞኑ የዳያስፖራ መጉረፍ ዳያስፖራው ከአገሪቱ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማደስና መንግሥትም ከዳያስፖራው ሊያገኝ የሚችለውን ድጋፍ እንዲያገኝ ሊያግዝ ይችላል፡፡ ሆኖም አሁንም ቢሆን የመንግሥት ትኩረት ዳያስፖራው በኢንቨስትመንት መስኮች የሚሰማራባቸውን አማራጮች በማሳየትና በሰሜኑ ጦርነት ሳቢያ የተጎዱ ኢትዮጵያውያንን እንዲደግፉ ከማበረታታት የዘለለ አይደለም፡፡

አሁን ወደ አገር ቤት የመጣውን ዳያስፖራ በቁጥር ይኼ ነው ብሎ ማስቀመጥ ባይቻልም፣ በርካቶች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተከትለው ወደ አገር ቤት እየጎረፉ እንደሚገኙ ማየት ይቻላል የሚሉት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበር የቢሮ ኃላፊና የኮሙዩኒኬሽን ማኔጀር አቶ ዳንኤል አበበ፣ አሁን ያለው የዳያስፖራ ፍሰት ከአሁን ቀደም ከነበረው ይለያል ባይ ናቸው፡፡

ምንም እንኳን በሚሊኒየም የነበረው የዳያስፖራ ፍሰት ከዚህ ጋር የሚነፃፀር ቢሆንም፣ የአሁኑ ግን ለየት ይላል ይላሉ፡፡ አገሪቱ የገጠማትን ጦርነት ለመመከት ወደ ግንባር በወረዱ ማግሥት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡት ጥሪ መሆኑና የምዕራቡ ዓለም አገሮች ዜጎቻቸው ኢትዮጵያን ለቅቀው እንዲወጡ ጥሪ እያቀረቡ ባሉበት ወቅት በመሆኑ ይለያል ባይ ናቸው፡፡

ከዚህ ባለፈም ዳያስፖራው በየሚኖርበት አገር እያደረገ ያለው የፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጫና አገሮቹንና ሚዲያዎቻቸውን እየፈተኑ ያሉበት ወቅት መሆኑንም በማንሳት፣ በተለይ ከሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ጦርነት ጋር በተያያዘ ያለውን የተዛባ አመለካከት ሞግተዋል ይላሉ፡፡ እነዚህ ተፅዕኖዎች፣ በተለይም ከኢትዮጵያ አልፎ አፍሪካዊና ዓለም አቀፋዊ እንቅስቃሴ የሆነው የኖ ሞር (በቃ) እንቅስቃሴ ለአገሪቱ ትልቅ የዲፖሎማሲ ግብዓት ነበር ይላሉ፡፡

እንደ እሳቸው አመለካከት፣ አሁን ያለው የዳያስፖራ ፍሰት ሦስት ዓላማዎች አለው፡፡ የመጀመሪያው ከሰሜኑ የአገሪቱ ጦርነት ጋር በተያያዘ ከዓለም አቀፍ ተቋማትና ከምዕራቡ ዓለም አገሮች በኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ያለው ጫና ከፍተኛ ስለሆነ አጋርነት ለማሳየትና ዜጎቻቸውን ውጡ ለሚሉ አገሮች ኢትዮጵያ ሰላም መሆኗን ለማረጋገጥ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በመደበኛ የሐዋላ (ሬሚታንስ) አገልግሎት በመጠቀም የኢኮኖሚ መነቃቃት ዕገዛ ማድረግ ነው በማለት፣ በሦስተኛ ደረጃ በአፋርና በአማራ ክልሎች የተጎዱ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም ዘላቂ የሆነ መንገድ ለመቀየስ ነው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

የደቡብ አፍሪካው የፋይናንስ አስተዳደርና አካታችነት ማዕከል እ.ኤ.አ. በ2018 ከሰሐራ በታች ባሉ አገሮች የሐዋላ ፍሰት ፈተናዎችን አስመልክቶ ባስጠናው ጥናት መሠረት፣ ከኢትዮጵያ ከሚወጣው የሐዋላ (ሬሚታንስ) መጠን ወደ አገር ውስጥ የሚገባው ይበልጣል የሚል ግኝት ያለው ቢሆንም፣ በርካታ የውጭ ሐዋላ የሚመጣው በኢ-መደበኛ መንገድ መሆኑን ይጠቁማል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ የሐዋላ ገቢ በየጊዜው የሚዋዥቅ ነው፡፡ በዓለም ባንክ እ.ኤ.አ. 2016 መረጃ መሠረት የኢትዮጵያ የሐዋላ ግኝት 742 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ወደ ኢትዮጵያ የገባው 772 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ከኢትዮጵያ የወጣው ደግሞ 30 ሚሊዮን ገደማ ነው፤›› ይላል፡፡

ሆኖም ታማኝ ዳያስፖራዎች ቀጣይነት ያለውንና ሲበዛ ኢ-መደበኛ የሆነውን የሐዋላ ፍሰት ሊያስተካክሉ ይችላሉ ሲል ጥናቱ በመፍትሔነት ይጠቁማል፡፡

አቶ ዳንኤል በበኩላቸው፣ ከዳያስፖራው ጋር የሚኖረው ግንኙነት የዘመቻና የእሳት ማጥፋት ዓይነት መሆን የለበትም ይላሉ፡፡ ይልቁንም ቀጣይ የሆነ መደበኛ የዳያስፖራ ግንኙነትን መመሥረት ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ ይኼንን መደበኛ ግንኙነትን ለመመሥረት መንግሥት በዳያስፖራ ኤጀንሲ አማካይነት እየሠራ የሚገኝ ቢሆንም፣ እስካሁን በውይይት ላይ የሚገኙ ናቸው ይላሉ፡፡ እንደ እሳቸው ምልከታ፣ መሻሻል የሚሻው አንድ ዘርፍ ለዳያስፖራው የሚስማማ ፖሊሲ በመቅረፅ ዳያስፖራው በተደጋጋሚ እንዲመጣ በማድረግ ነው፡፡ በዚህም ዳያስፖራው በሚኖርበት ዓለም የለመደውን ዓይነት አሠራር የሚቀራረብ አሠራርን ቢሮክራሲ መዘርጋት ያስፈልጋል በማለት ይገልጻሉ፡፡

‹‹ዳያስፖራውን ለመቀበል ጥሪው ከተላለፈበት ጊዜ አንስቶ ከአስተባባሪ ኮሚቴው ጋር ስንሠራ ነበር፡፡ መደበኛ ሕጎችና አሠራሮች ቢኖሩ ኖሮ በርካታ ነገሮችን ማከናወን ቀላል እንደሆነ ተመልክተናል፡፡ ትብብር እንደ ኤሌክትሮኒክ ቪዛና በመዳረሻ የሚሰጡ ቪዛዎችን ጨምሮ፣ እንደ ጉምሩክ ያሉ ሥራዎችን ማቅለል እንደሚቻል ተመልክተናል፤›› ሲሉም ያክላሉ፡፡

መንግሥት ለረዥም ጊዜ ለዳያስፖራው ተከልክሎ የቆየውን የፋይናንስ ዘርፍ ለመፍቀድ መመርያ ያሻሻለና ዳያስፖራው በውጭ ምንዛሪ በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ እንዲችል መፈቀዱ እንዳለ ሆኖ፣ ዳያስፖራው ይበልጡን በፖለቲካው ዘርፍም ተሳትፎ አስተዋጽኦ ማድረግ እንዲችል የሚጠይቁ አልጠፉም፡፡

ረሳስ በተባለ ድረ ገጽ ላይ እ.ኤ.አ. በ2018 የወጣ አንድ ጽሑፍ እንደሚያትተው፣ ‹‹እንደ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ስዊድን፣ አውስትራሊያና ደቡብ አፍሪካ ያሉ ጥምር ዜግነትን በሚፈቅዱ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለሕዝቦች የፖለቲካ ሕይወት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ ታይቷል፡፡ ስለዚህም ዳያስፖራው በአገሩ ፖለቲካ ተሳትፎ ያለውን ዕውቀትና ኃይል ማጋራት እንዲችልና ለአገሪቱም ዴሞክራሲያዊነት አስተዋጽኦ እንዲያደርግ፣ በአገሪቱ የፖለቲካ ሕይወት እንዲሳተፍ ሊፈቀድለት ይገባል፤›› በማለት ይከራከራል፡፡

ስለዚህም ጥምር ዜግነት እንዲፈቀድ የሚጠይቁ ድምፆች በመንግሥት ተቋማትና በዳያስፖራ ማኅበረሰብ ተወካዮች መካከል በሚደረጉ ውይይቶች መደመጣቸው አልቀረም፡፡ ሆኖም በመንግሥት እምብዛም ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ አይመስልምና በሥራ ላይ ያሉ ሕጎችን ለማሻሻል የተደረጉ እንቅስቃሴዎች አይታዩም፡፡

መንግሥት ዳያስፖራውን በፖለቲካ ለማሳተፍ የሚያስቸግረው በብሔር ላይ የተመረኮዘውን ፖለቲካ ለመቀየር ግድ ሊለው፣ ወደ ሐሳብ ፖለቲካ መምጣት ሊያስፈልግ ስለሚችል፣ እንዲሁም ይኼ ጉዳይ ያልታሰቡ የፖለቲካ ጥያቄዎችንና ውዝግቦችን አግተልትሎ ሊመጣ የሚችል ጉዳይ ስለሆነ ነው ሲሉ አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የዳያስፖራ አባል ይናገራሉ፡፡ ስለዚህም ይኼ ከአገሪቱ የፖለቲካ ሥርዓት ከመቀየር ጋር ስለሚያያዝ ሥጋት ይፈጥራል ይላሉ፡፡

በብሔር ላይ የተመረኮዘው የአገሪቱ የፖለቲካ አደረጃጀት አከራካሪ ሆኖ የከረመ ሲሆን፣ የዳያስፖራ ማኅበረሰብም ተቃውሞ ሲያሰማበት የቆየ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይም  በኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት በዳያስፖራው ዘንድ የሚደረጉ ተቃውሞዎች በዚህ ዙሪያ ያጠነጥኑ ነበር፡፡

ዳያስፖራውን በጥምር ዜግነት መብት ከመስጠት ባለፈ፣ የውጭ ዜጎች ሆነው ኢትዮጵያዊ ዜግነት ማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች ኢትዮጵያዊ ሆነው ያላቸውን ልምድ፣ ዕውቀትና ትስስር ለአገሪቱ ልማት ለማዋል የሚቻልበት ሥርዓት እንዲፈጠር የሚጠይቁም አልጠፉም፡፡ በዚህም መንገድ የአገሪቱን የልማት ፍላጎቶች የሚያግዙ ባለሙያዎችን መሰብሰብ ያስችላል ይላሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -