በሰሜኑ የኢትዮጵያ አካባቢ ተከስቶ በነበረውና አሁን ረገብ ባለው ጦርነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ከቀያቸው ተፈናቅለው ቆይተዋል፡፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ በተባለው የሕወሓት ቡድን ተይዘው በቆዩ ከተሞች የደረሰውን ውድመት፣ ዘረፋና ጦርነት ሽሽትም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቤት ንብረታቸውን ጥለው ተሰደዋል።
መንግሥት በአሸባሪው ቡድን ተይዘው የነበሩ ከተሞችን ካስለቀቀ በኋላ የተሰደዱ ዜጎች ወደ ቀዬአቸው እየተመለሱ ቢሆንም፣ ንብረታቸው በመዘረፉና በመውደሙ ለችግር ተዳርገዋል፡፡ ከዚህ ባለፈ ከቀያቸው ሳይወጡ ግፍና ጭካኔን የተጋፈጡ ዜጎች አሁናዊ ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ያላቸውን ንብረትና የሚላስ የሚቀመስ እስኪያጡ ድረስ በመዘረፋቸው ነው።
በጦርነቱ ሳቢያ አንዳንድ ከተሞች ላይ የመንግሥት መዋቅሮች አገልግሎት የማይሰጡ በመሆኑ የቤተ እምነት አባቶች ኅብረተሰቡን በማረጋጋትና በመደገፍ ትልቁን ድርሻ ይዘዋል። ከእነዚህም አካባቢዎች ውስጥ ላሊበላ፣ ዋግኽምራና ሰቆጣ ውስጥ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች ተጠቃሽ ናቸው። የቤተ እምነት አባቶች ባሰባሰቡት መረጃ መሠረትም ሌሎች በጎ ፈቃደኞችና ተቋማት ወደየአካባቢው የምግብ ፍጆታዎች እያደረሱ ይገኛሉ፡፡
የወሎ ቤተ አምሃራ በጎ አድራጎት ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ ይርጋለም ታደሰ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በአሸባሪው ቡድን ተይዘው የነበሩ ቦታዎች ላይ ሳይሸሹ የተጋፈጡ ዜጎች አሁንም ችግር ላይ ናቸው፡፡
በበጎ አድራጎት ድርጅቱና በመንግሥት የሚሰጠው ድጋፍ ከተጎጂዎች ቁጥር ጋር የሚመጣጠን ባለመሆኑ ዜጎች አሁንም ዕገዛ ይሻሉ።
እንደ አቶ ይርጋለም፣ በሕወሓት አገዛዝ ሥር ቆይተው በቅርቡ በተለቀቁ አካባቢዎች ማኅበረሰቡ ለከፍተኛ የምግብ እጥረት ስለተጋለጠ ድርጅቱ በላሊበላና ሰቆጣ ላይ ድጋፍ አድርጓል።
በላሊበላ ከተማ የመንግሥት መዋቅር በአግባቡ እየሠራ ባለመሆኑና ዕርዳታው ደግሞ ባሰቸኳይ መድረስ ስላለበት የተጠቀሙት መረጃ የላሊበላ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ከሆኑት መሆኑን ጠቁመዋል።
ከተማው በሕወሓት አገዛዝ ሥር በቆየበት ጊዜም እኝህ አባት ችግር ለገጠማቸው የአካባቢው ማኅበረሰብ አባላት ዕገዛ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አቶ ይርጋለም ተናግረዋል፡፡
በዋግኸምራ ሰቆጣ ከተማ 100 ኩንታል ዱቄት ለ400 አባወራዎች ድጋፍ ማድረጋቸውንና ለዚህም የመረጃ ምንጫቸው የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች መሆናቸውን ገልጸዋል። የዋግኸምራ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ በርናባስ ባቋቋመት ኮሚቴ መረጃ መሠረት ድጋፍ ማድረጋቸውን አክለዋል፡፡
አሁን ላይ በጎ አድራጎት ድርጅቱ ቅድሚያ ድጋፍ የሚያደርገው ለአረጋውያን፣ ለሕፃናት፣ ለእመጫት፣ ለነፍሰ ጡሮችና በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ነው። ከዚህ ቀደም ድጋፍ የሚያደርጉት በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ዜጎች መሆኑን ያስረዱት አቶ ይርጋለም፣ አሁን ላይ በአሸባሪው ቡድን አገዛዝ በቆዩ ከተሞች እየኖሩ ላሉት መሆኑን ተናግረዋል።
ጦርነቱ የነበረባቸው አካባቢዎች ወረርሽኝና ረሃብ ሊኖር እንደሚችል፣ ችግሩም ሁሉንም ስለጎዳ ዕርዳታ ሲሰጥ ጥቃቅን ችግሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
አቶ ይርጋለም፣ አሁን ላይ ያሉትን ጥቃቅን ችግሮች ከማውራት ይልቅ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ለችግር፣ ለረሃብና ለተላላፊ ወረርሽኝ እየተጋለጠ በመሆኑ እነሱን ማገዝ ቅድሚያ እንዲሰጠው ጠይቀዋል።
የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ከምግብ ዋስትና ቢሮዎች፣ ከግብርና ቢሮዎች፣ ከዕድሮችና ከቤተ እምነቶች መረጃ በማሰባሰብ ድጋፍ እንደሚያደርግ፣ ሌሎች ማኅበራትም ከችግሩ ስፋት አንፃር የሚሰጡት ዕገዛ ትንሽ ሊሆን ስለሚችል መረጃን መሠረት አድርገው መስጠት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
ከሕወሓት ቡድን ነፃ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖረው ሕዝብ ነፃ የወጣው ከአሸባሪዎች እንጂ ከብዙ ችግሮች እንዳልሆነ ጠቁመው፣ አሁንም ዕገዛ የሚሹ ብዙ ዜጎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
የብሔራዊ የአደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ እንደተናገሩት ደግሞ፣ ኮሚሽኑ መረጃን መሠረት በማድረግ ዕገዛ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች እየረዳ ይገኛል።
ከዚያ ውጪ የሚደረግ ዕርዳታ በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ብቻ ሳይሆን ላልተገባቸው ሊደርስ እንደሚችል፣ አሁንም ከዕርዳታው ውስጥ ለሽያጭ የሚቀርቡና ለማይገባቸው ሰዎች የሚደርሱ እንዳሉ አቶ ደበበ ጠቁመዋል።
ግለሰቦች፣ ቡድኖች፣ ማኅበራት እንዲሁም አብዛኛዎቹ ተቋማት ድጋፍ እንደሚያደርጉ የጠቆሙት አቶ ደበበ፣ ዕርዳታውን በራሳቸው መንገድ ለማድረስ የሚሄዱበት አካሄድ ግን ዕርዳታው ለሚገባቸው ዜጎች በትክክል እንዳይደርስ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ የሚያደርገው ዕርዳታ ለሕፃናት፣ ለሚያጠቡ እናቶች፣ ለነፍሰ ጡሮች ለአቅመ ደካሞች በመረጃው መሠረት ዕገዛ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች በትክክል ድጋፍ እንዲያገኙ በጋራና በትብብር መሥራት ያስፈልጋል ያሉት አቶ ደበበ፣ ድጋፍ ሰጪዎች ትክክለኛ መረጃ ኖሯቸው ለሚገባቸው ዜጎች ድጋፍ እንዲያደርሱ ከኮሚሽኑ ጋር መሥራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የወሎ ቤተ አምሃራ በጎ አድራጎት ድርጅትና ከሩብ ጉዳይ ቴአትር የተሰበሰበው ገቢ ከመንግሥት ጋር በመነጋገር ዕርዳታውን ቦታው ድረስ ሄደው እንደሚሰጡም ተናግረዋል።