Thursday, December 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እንለወጥ!

ሰላም! ሰላም! በበዓል ማግሥት መገናኘት ደስ ይላል፡፡ በተለይ ደግሞ ከተጎሳቆሉ ወገኖች ጋር በዓሉን ማክበርም ሆነ፣ ድጋፍን ማበርከት ደስታን የበለጠ ይጨምራል፡፡ የሰሞኑ ሁኔታችንም ደስ የሚያሰኝና ተስፋ ሰጪ ስለነበር፣ ወገን ማሰብ ባህላችን ይሁን እላለሁ፡፡ መቼም እንደምታውቁት የደላላ ጆሮ ንቁ ነው፡፡ ከየአቅጣጫው የሚባለውን በቅጡ ካላዳመጠ የእንጀራ ገመዱ ተበጠሰ ማለት ነው፡፡ አንበርብር ምንተስኖት ጆሮው ብቻ ሳይሆን ሁለነገሩ ያዳምጣል፡፡ ያዳምጣል ብቻ ሳይሆን የተባለውን ሁሉ በየፈርጁ ይተነትነዋል፡፡ የተነተነውን ወደ ገንዘብ ለመለወጥ እነዚያ እንደ መቃ የሰለሉ እግሮቹን ለጉዞ ያዘጋጃቸዋል፡፡ እሱ ወደ ጥሪት ፍለጋ ሲኳትን ሞባይሉም ሥራ አይፈታም፡፡ ዕድሜ ለምሁሩ የባሻዬ ልጅ በመልዕክት ማስተላለፊያው አሁንም አሁንም ወደ ተለያዩ ሰዎች የሚፈልገውን ይልካል፣ የመጡለትን ይቀበላል፡፡ ወጪ በመቆጠብ የተሻለ ገቢ ማግኘት ብቻ ሳይሆን፣ በስልክ እየለፈለፉ መረጃን አሳልፎ መስጠትም ጎጂ ልማድ መሆኑን አውቆታል፡፡ ስለዚህ በ‹‹ቴክስት ሜሴጅ›› ከወዳጆቹና ከደንበኞቹ ጋር መገናኙቱን ቀጥሏል፡፡ ሥልጣኔ ይባላል!

እንደሚታወቀው የአገሩን ጥሪ ተቀብሎ እንደ ጎርፍ የመጣው ዳያስፖራን በተቻለ መጠን ማስተናገድ ተገቢ ነው፡፡ ይኼ ሁሉ ዳያስፖራ ዶላርና ዩሮ ተሸክሞ ሲመጣ ቁጭ ብሎ ማየት ለደላላው አይዋጥለትም፡፡ የሆቴል ምግብ በድለላ የሚቀርብ ባይሆንም፣ ለሌሎች አገልግሎቶች ግን ተግቶ መጠበቁ ሳያዋጣ አይቀርም፡፡ ታክሲ፣ ምሽት ክበቦች፣ የጌጣ ጌጥ፣ የባህላዊ ልብሶችና ዕቃዎች መደብሮችና ሌሎች ሌሎች የማይነገሩ ነገሮች ሁሉ የደላላን ጣልቃ ገብነት ይሻሉ፡፡ ተጭኖ የመጣን ገንዘብ እንደ መጣህ በሰላም ወደ አገርህ ተመለስ ማለት፣ ለደላላው አንበርብር ምንተስኖት ከዕብደት የማይተናነስ ሞኝነት ነው፡፡ በዚህ ወቅት አገልግሎት ሰጪዎች፣ ታክሲዎች፣ ሬስቶራንቶች፣ ክለቦች፣ የተለያዩ መዝናኛዎችና የመሳሰሉት በምሪት የመጣላቸውን ቁጭ ብለው ይቀበላሉ፣ ካልሆነም በአስጎብኚና በሌሎች እየተላኩላቸው ኮሚሽን ከፍለው ያስተናግዳሉ፡፡ ጊዜው የቢዝነስ ነው!

ዳያስፖራን ይዞት የመጣውን ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ከሚኖርበት አገር ይዞ የመጣውን አዳዲስ የቢዝነስና የሥራ ፈጠራ ሐሳብ መቀበል አስፈላጊ ሲሆን፣ ወደፊት ከአገሩ ጋር ቁርኝቱ የበለጠ እንዲጨምር የሥራ አጋርና ሽርካ ማድረግም ሊታሰብበት ይገባል ባይ ነኝ፡፡ የባሻዬ ልጅ አዳዲስ መረጃዎችን በመልዕክት መቀበያው በኩል ያደርስልኛል፡፡ ወዳጆቼ ደግሞ በየእንግዳ መዳረሻ አካባቢ ያሉትን የሲሳይ ማግኛ ዘዴዎችን ይጠቁሙኛል፡፡ ደላላው አንበርብር በየሄደበት ሥፍራ ድል እየቀናው ነው፡፡ በኢትዮጵያ ገንዘብ እየተተረጎመ የሚሰጠው ዳጎስ ያለ ዕለታዊ ገቢ የልብ ልብ እየሰጠው ነው፡፡ ቀኑን ሙሉ ያለ እረፍት እንዲህ ከተሠራ፣ ዘንድሮ የአንበርብርና የማንጠግቦሽ የዕድገት ጉዞ ዕቅድ መሳካት ይጀምራል፡፡ ሲሳይን ቤት ድረስ ይመጣል ብሎ ተቀምጦ መጠበቅ የለየለት ጅልነት ነው፡፡ ሁሉም ችሎታውንና ያለውን ይዞ አደባባይ ሲወጣ እንጀራውን ማብሰል አያቅተውም፡፡ ይህ ዩኒቨርሲቲ የማይታወቅ ባህላዊ ዕውቀት ቢሞከር መልካም ነው ይላል የእናንተው አገልጋይ ደላላው አንበርብር፡፡ እስቲ አንዳንዴ ስሙኝ!

ቀኑን ሙሉ የአዲስ አበባን ጎዳናዎች ሳካልል ውዬ አመሻሽ ላይ ስደርስ፣ ማንጠግቦሽ ቤታችንን በሚገባ አጫጭሳና አሟሙቃ ነበር የጠበቀችኝ፡፡ የቡናው እንፋሎት የቤቱን አየር እያወደው ባልና ሚስት ገና ጫጉላቸውን እንዳልጨረሱ ተጋቢዎች የመሆን ያህል እስኪሰማን ድረስ በሐሴት ተሞልተናል፡፡ ዛሬም እንደ ትናንት ሆጨጭ ብሎ የመጣው ረብጣ ብር ማንጠግቦሽ እጅ ሲገባ የአንበርብር ብኩንነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያበቃለት ይመስል ነበር፡፡ ከድለላ ይገኝ የነበረው ኮሚሽን ከላዩ ላይ ለመጠጥ ግብዣና ለአዝማሪ ይቀሽብለት እንዳልነበር፣ ዛሬ ግን በእርግጥም ታሪክ ሆኗል፡፡ በባሏ የአስተሳሰብና የባህርይ ለውጥ የተደመመችው ማንጠግቦሽ፣ ‹‹የአገራችን አንዳንድ መፈክሮች ቢቀየሩ?›› አለችኝ፡፡ ግራ ገብቶኝ በመደነቅ እያየኋት፣ ‹‹የትኞቹ መፈክሮች?›› በማለት ስጠይቃት፡፡ ማንጠግቦች በእኔ ግራ መጋባት እየተደመመች፣ ‹‹ድህነትን ታሪክ ነው ተረት እናደርጋለን የሚሉት…›› ስትለኝ ተግባብተን አንድ ላይ በረዥሙ ሳቅን፡፡ በበዓል ሰሞን ሳቅ ደስ ይላል!

የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹አገር በመፈክር አይለወጥም…›› በማለት ዘወትር ይነግረኝ ነበር፡፡ ‹‹በየመንገዱና በየጥጋጥጉ መፈክር ሰቅሎ እንቅልፍ የሚለጥጥ አገር አያልፍለትም…›› ይለኛል፡፡ ይህ መልዕክት ለእኔ አዲስ ባይሆንም ማንጠግቦሽም ዛሬ ደገመችው፡፡ እርግጥ ነው ይህንን ከደምና ከአጥንቴ ጋር የተዋሀደ ንግግር መርሳት የለብምኝ፡፡ ዕቅድ የሚሳካው ዕቅዱን ሊደግፉ የሚችሉ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች በስልትና በጥበብ ሲታገዙ ብቻ ነው፡፡ የመፈክር ጋጋታ ሲበዛ አንድ ችግር አለ ብዬ አስባለሁ፡፡ ‹‹መፈክር የሚያበዙ ለመሥራት ያልወሰኑ፣ ወይም ከንድፈ ሐሳብ ተላቀው ወደ ተግባር ለመግባት የማይችሉ ናቸው…›› ሲልም የነገረኝ ይኼ የዘወትር መምህሬ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው፡፡ የባሻዬ ልጅ አስተምህሮ እኔን የማለዳ ወፍ አድርጎኛል፡፡ የተገኘውን ቀራርሞ ወደ መጠጥ ቤት የሚደረገው ጉዞ እንዲያበቃና ኑሮ በፕሮግራም መመራት እንዳለበት የሚጎተጉተውም እሱ ነው፡፡ ስለዚህ ከእኔና ከማንጠግቦሽ ቤት ድህነት በተግባር ታሪክ የሚሆንበት ጫፍ ላይ ተደርሷል፡፡ ስለዚህ ከሚገኙት መልካም አጋጣሚዎች የሀብትን መንገድ በሥራ ማመቻቸት፣ የእኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት የማይቀለበስ ዕቅድ ሆኗል፡፡ በቃ!

አዛውንቱ ባሻዬ በምርኩዛቸው እየተረዱ ደረሱ፡፡ የማንጠግቦሽ ቡና አፍንጫቸውን የቀሰቀሰው በመሆኑ እንጂ ሲመሻሽ የትም መሄድ አይፈልጉም ነበር፡፡ ‹‹ቡናሽ እንደ አቶሚክ ቦምብ ነቀነቀኝና ሳልወድ በግድ እየተጎተትሁ መጣሁ…›› አሏት፡፡ ማንጠግቦሽ ምንም እንኳን የባሻዬን በዚህ ሰዓት መምጣት ባትፈልገውም፣ የቡናዋ መሞገስ ደስ ስላሰኛት በፈገግታ ነው የተቀበለቻቸው፡፡ ባሻዬ ሰላም ብለውኝ፣ ‹‹ልጅ አንበርብር ሥራ እንዴት ነው እባክህ? ዳያስፖራው የኢትዮጵያን ምድር ሲያጥለቀልቅ ይህንን ባውንድ እያፈስከው ነው አሉ…›› በማለት ፀጥታውን ገፈፉት፡፡ ‹‹እግዚአብሔር የተመሠገነ ይሁን፣ ከላይና ከታች እየተሯሯጡ የሚያገኙት የሀቅ ገንዘብ ያስደስታል፡፡ ምንም ሳይለፉ እንደ መና በምትኃት የሚወርደው የገንዘብ ዶፍ ምንጩ አልገባን አለን እንጂ የእኔ ምን አላት ብለው ነው?›› በማለት ፊቴን ቅጭም አድርጌ ነገርኳቸው፡፡ ባሻዬ መሬቱን በከዘራቸው እየቆረቆሩ፣ ‹‹ልክ ነህ፣ እኔ እኮ አፍላ ኮበሌና ግማሽ እንጀራ የምትበላ የማትመስል ኮረዳ የሚሊዮን ብር አውቶሞቢል ነው የሚያሽከረክሩት ሲባል ቅዥት ይመስለኛል…›› አሉ፡፡ የምን ይመስለኛል ነው ልክ ናቸው፡፡ ያቃዣል!

ከተማውን ሙሉ ከሚያስሱ ደላላ ጓደኞቼ ጋር የሚያነጋግረኝ ይኼ ባሻዬ ያነሱት ነገር ነው፡፡ አንድ ጊዜ አንድ የታወቀ የከተማው ቱጃር አንዱን ደላላ በወር ውስጥ ለአራተኛ ጊዜ የሚከራይ ሙሉ ቪላ ፈልግልኝ ያለውን ፈጽሞ አይረሳውም፡፡ አንዲት እንቡጥ ልጅነቷ ዓይኖቿና መላ አካላቷ ላይ የሚያሳብቁባትን አስረግዞ ለማስቀመጥ መፈለጉን ሲነግረው፣ ሰውዬው ያለውን ገንዘብ በሙሉ በየቦታው እያስወለደ የሚያስቀምጣቸው ሴቶችና ሕፃናት ላይ ኢንቨስት የሚያደርገው ያስመሰለው ነበር፡፡ እነዚህ እንቡጥ የትናንት ልጃገረዶች በወለዱ ማግሥት ያማረ ቪላ ውስጥ እየተንፈላሰሱ የሚሊዮን ብሮች አውቶሞቢል ጎዳናው ላይ እንደሚያሽከረክሩ ቢነገር ማን ያምናል? ስልም ራሴን እጠይቃለሁ፡፡ በየምሽት ጭፈራ ቤት፣ በውስኪና ቮድካ መቸርቸሪያ ጓዳዎች ውስጥ የሚታደሙት ወጣት ሚሊየነሮችና የእነሱ የዕድሜ ተቃራኒ የሆኑ አናረጅም ባይ ወይዛዝርት ድሪያን ሳስብ በሐሳብ ጭልጥ እላለሁ፡፡ ምስኪኑ ተሯርጦ ያገኛትን አምላኩን ባርክልኝ ብሎ ሲተኛ፣ እነ አየር ባየር ‹‹ሌቱም አይነጋልኝ›› እያሉ በየባንኮኒውና በየዝጉብኝ ይሸፍታሉ፡፡ በአንድ አገር ውስጥ ሁለት የማይመሳሰሉ ፍጡራን መኖራቸው የፅድቅና የኩነኔ ማሳያዎች እንዲሆኑ ነው ወይ? በማለትም እመራመራለሁ፡፡ ያም ሆነ ይህ ኡደቱ እየቀጠለ የዓለም እንቆቅልሽነትም እየተጠናከረ መሄዱ ግን እውነት ነው፡፡ ማን ይክዳል!

ማንጠግቦሽ እንዲህ ዓይነቱ ውጣ ውረድ የበዛበት ውጥንቅጥ ሲነገራት ራሷን ያማታል፡፡ የፈጣሪ ትዕዛዝ ተጥሶ የሰው ልጅ ሕግጋቱን በተቃራኒ አቅጣጫ እየጠመዘዘ የሚነጉድ ስለሚመስላት፣ ‹‹ለኃጥያን የመጣ ለፃድቃን ይተርፋል…›› እያለች አምላኳን ትለማመናለች፡፡ ‹‹አገራችንንና ሕዝባችንን ሰላም ሰጥቶ፣ ፍቅር ሰጥቶ፣ በጤና ያኖር ዘንድ አምላካችንን እንማፀን…›› ስትልም ትደመጣለች፡፡ እኔ አንበርብር በበኩሌ፣ ክፋትና ኃጢያት ባሉበት ርኩሰት እንጂ ፅድቅ ስለማይኖር ወደ ፈጣሪ አቤት ማለት ያስፈልጋል እላለሁ፡፡ ባሻዬም፣ ‹‹የዓለም ፍጻሜ ስለመድረሱ የተነገሩት ምልክቶች እየታዩ ስለሆነ ንስሃ መግባት ያስፈልጋል…›› ማለታቸው የተለመደ ነው፡፡ የባሻዬ ልጅ ደግሞ ተጨማሪ ነገር አለ ይላል፡፡ እስቲ እንስማው!

‹‹ለህሊናም ሆነ ለፈጣሪ ሲባል የሰው ልጅ መተዛዘንና መከባበር አለበት፡፡ በሐሰት ውንጀላ፣ በሽንገላ፣ በምቀኝነት፣ በሰይጣናዊ መንፈስ በመነሳሳት ሰውን በማጥቃትና በመሳሰሉት አገርንና ሕዝብን ደም የሚያስለቅሱ ሞልተዋል…›› ሲል የሁላችንም ጆሮዎች ቆሙ፡፡ በዚህ መሀል ግን እኔ፣ ‹‹ከአጭበርባሪዎች የተለዩት እነዚህ ደግሞ ምንድናቸው?›› የሚል የዋህ ጥያቄ አቀረብኩ፡፡ ‹‹እነ እከሌ እያልኩ አልነግርህም፡፡ ነገር ግን በርኩሰት የተሞሉና ለአገር የማያስቡ አሉ፡፡ የራሳቸውና የቢጤዎቻቸው ፍላጎት እስከተሟላ ድረስ ለሌላው ደንታ የሌላቸው ሞልተዋል፡፡ የአገርንና የሕዝብን ጥቅም የሚመዝኑት ከራሳቸው ፍላጎት ጋር በማነፃፀር ብቻ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ባሉበት አገር ውስጥ እንዴት ዕድገት ይኖራል?›› በማለት ጥያቄ አቀረበ፡፡ ማንጠግቦሽ ለመልሱ ማንም አልቀደማትም፡፡ ‹‹ልክ ነህ፣ ‹ከራስ በላይ ነፋስ› የሚሉ ስግብግቦች ባሉበት አገር ውስጥ መፍትሔው ተባብሮ ቅንነትን ማሳየት ብቻ ነው፡፡ ትህትናና ቅንነት ይጠቅማሉ እንጂ አይጎዱም…›› ስትል ሁላችንም በመስማማት አንገታችንን ነቀነቅንላት፡፡ እኔም ፈገግ እያልኩ፣ ‹‹ልክ ነሽ፣ አገርን የማይለውጥ አጉል መፈክር ዱሮ ቀረ እያልን የአንቺን አስተያየት በሙሉ ልብ እንቀበላለን…›› ከማለቴ፣ ‹‹አንበርብር መፈክር በተግባር ቢቀየር እኮ ጎጂ አልነበረም፡፡ ዋናው ችግራችን ግን መለወጥ ነው ያቃተን፡፡ ራሳችንን መለወጥ ስንጀምር ተግባሩ ሩቅ አይሆንም፡፡ ዋናው ነገር እንለወጥ ነው ጥያቄው…›› ሲለን ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ወጋችን ተጠቃለለ፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት