Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየአሠልጣኝ ውበቱ የጨዋታ ምርጫና የዋሊያዎቹ የካሜሩን ቆይታ 

የአሠልጣኝ ውበቱ የጨዋታ ምርጫና የዋሊያዎቹ የካሜሩን ቆይታ 

ቀን:

ካሜሩን 33ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ለማሰናዳት ዝግጅት የጀመረችው፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ውስጥ ሆኖ ግራ በተጋባበት ወቅት ነበር፡፡ ይህም ሰበብ ሆኖ ዓምና መካሄድ የነበረበት ውድድሩ ወደ ዘንድሮ ተላልፏል፡፡

እሑድ ጥር 1 ቀን 2014 ዓ.ም. በይፋ የተጀመረው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሲጀመር፣ የ88 ዓመቱ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ፖል ቢያን ጨምሮ የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ከታዳሚዎቹ ይጠቀሳሉ፡፡ በመክፈቻው ቡርኪና ፋሶን በኦሊምቤ ስታዲየም የገጠመችው ካሜሩን በሜዳዋና በደጋፊዎቿ ፊት የመጀመርያውን የ2 ለ1 ድል አጣጥማለች፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንደ ቡርኪና ፋሶ ሁሉ በኬፕ ቨርዴ 1 ለ 0 ተሸንፏል፡፡            

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) የምድቡን ሁለተኛ ጨዋታ ሐሙስ ጥር 5 ቀን 2014 ዓ.ም. ከአስተናጋጇ ካሜሩን ጋር ይጫወታል፡፡ በመክፈቻው ከኬፕ ቨርድ በነበረው ጨዋታ በጉዳት ያልተጫወቱት ሽመልስ በቀለና ዳዋ ሁቴሳ ለካሜሩኑ ጨዋታ መደበኛ ልምምድ መሥራት መጀመራቸው ታውቋል፡፡ ዋሊያዎቹ በመክፈቻው ጨዋታ በጠባብ ውጤት መሸነፋቸውን ተከትሎ ከአስተናጋጇ ካሜሩን ጋር የሚያደርጉትን ጨዋታ ተጠባቂ አድርጎታል፡፡

ከሁሉ በፊት ከሜሩን ቀድመው የከተሙት አሠልጣኝ ውበቱ አባተና ስብስባቸው ከኬፕ ቨርዴ ጨዋታ ቀደም ብለው በአጠቃላይ በካሜሩን ስለነበራቸው ዝግጅት፣ እንዲሁም ከተጋጣሚዎቻቸው ወቅታዊ አቋም ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በሚመለከት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡ ዋና አሠልጣኙ በመግለጫቸው በዋናነት ቡድናቸው ከስምንት ዓመት በኋላ ወደ መድረኩ የተመለሰ ቡድን ከመሆኑ አኳያ ዝቅተኛ ግምት የተሰጠው መሆኑን ገልጸው፣ ግምቱ ለእሳቸውም ሆነ ለስብስባቸው ያን ያህል ልዩነት እንደማይፈጥር፣ እንዲያውም በመድረኩ የተሻለ ነገር ለማሳየት መዘጋጀታቸውን  መናገራቸው አይዘነጋም፡፡

ብሔራዊ ቡድኑ ከኬፕ ቨርዴ ጋር በነበረው ጨዋታ በስምነተኛው ደቂቃ ላይ ተከላካዩ ያሬድ ባየህ የቀይ ካርድ ሰለባ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ነገር ግን የቡድኑ እንቅስቃሴ በአብዛኛው በስህተት የታጀበ ሆኖ መታየቱ፣ ብዙዎች አሠልጣኙ ቡድናቸውን አስመልክቶ ቀደም ብለው የሰጡትን አስተያየት በመጥቀስ በአሉታዊ ጎኑ እንዲመለከቱት ምክንያት መሆኑ አልቀረም፡፡

አሠልጣኙ በመግለጫቸው፣ ‹‹ካሜሩን ጠንካራ ቡድን መሆኑ ብቻ ሳይሆን ጨዋታውን በሜዳውና በደጋፊው ፊት የሚጫወት መሆኑን እናውቃለን፡፡ በሜዳና በደጋፊ ፊት መጫወት ደግሞ በሌላ ጎኑ ጫና እንዳለው መዘንጋት የለብንም፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ ይህ ጫና እኛን ስለማይመለከት ነፃ ሆነን እንድንጫወት ዕድል የሚፈጥርልን በመሆኑ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጠቃሚ ነው፤›› ብለዋል፡፡

አሠልጣኙ አስተያየታቸውን ሲያጠቃልሉ፣ ምንም እንኳ ኢትዮጵያ የምትገኝበት ምድብ ጠንካራ ቢሆንም፣ ዕቅዳቸው ከምድብ ማለፍ እንደሆነ ግን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ ይሁንና በታክቲክ ደረጃ አሠልጣኝ ውበቱና ስብስባቸው በመጀመርያው ጨዋታ በአራት ተከላካይ፣ በሦስት አማካይና በሦስት አጥቂ ኬፕ ቨርዴን ለመግጠም ወደ ሜዳ የገቡበት ምርጫ፣ እንዲሁም የቡድኑ የጨዋታ እንቅስቃሴ ግን አሠልጣኙ ዕውን ያሰቡትን ውጤት ማሳካት የሚችል እንቅስቃሴ ነበር ወይ? የሚሉ ተችዎች እንዲደመጡ ምክንያት ሆኗል፡፡

በአሠልጣኝ ውበቱ የጨዋታ እንቅስቃሴ እምነት ያጡ የሚመስሉት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ ከወዲሁ በዋሊያዎቹ የካሜሩን ቆይታ ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርባቸው አድርጓል፡፡

ሪፖርተር በዚህ ጉዳይ ያነጋገራቸው የዘርፉ ሙያተኞች፣ አሠልጣኝ ውበቱና ቡድናቸው አሁን ላይ ቅድሚያ ሊሰጡት የሚገባው ጉዳይ ቢኖር፣ ዘመናዊ እግር ኳስ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በመረዳት ስህተቶችን እንዲያርሙ ነው፡፡  

በሌላ በኩል ከጨዋታው በፊት ካሜሩን ቀድመው መምጣቸው የወዳጅነት ጨዋታን ማድረግ ጨምሮ የካሜሩንን የአየር ፀባይ ለመላመድ እንደጠቀማቸው የተናገሩት አሠልጣኝ ውበቱ፣ ካሜሩን እንደደረሱ አንዳንድ ተጫዋቾቻቸው በኮቪድ-19 ተቸግረው እንደነበር አልሸሸጉም፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...