Sunday, July 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየመሬት ፖለቲካ ከብሔራዊ መግባባት አጀንዳነት አኳያ!

የመሬት ፖለቲካ ከብሔራዊ መግባባት አጀንዳነት አኳያ!

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

መሬት የከተማም ይባል የገጠር በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ወሳኝ ድርሻ ያለው ሀብት ነው፡፡ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ትናንትም ሆነ ነገ ይህ እውነታ በቀላሉ ሊቀር እንደማይችልም የታመነ ነው፡፡ ለዚህ ማሳያው ደግሞ ከፊውዳላዊው ሥርዓት ጥቅምን የማስከበር ፍልሚያ አንስቶ፣ በወታደራዊው የሶሻሊስት መንግሥት የመደብ ትግል የተፋፋመው በዋናነት መሬት ላይ ተንተርሶ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት የተከተልነው ፌዴራላዊ ሥርዓትም ቢሆን በዋናነት የማንነት አጀንዳ አራማጅ ይምሰል እንጂ፣ ውስጣዊ ፍትጊያው በወሰንና በመሬት ላይ መሆኑን መካድ ፈጽሞ መሳሳት ነው፡፡

ለዚህም ነው በአገራችን በተካሄዱ የተለያዩ ምርጫዎችና የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክሮች ወቅት፣ “መሬት የሕዝብና የመንግሥት” ወይም “የግል” ነው በሚለው ጭብጥ ላይ ሰፋፊ ሐሳቦች ሲሰነዘሩ የሚደመጡት፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን አገሪቱን ሲመራ የነበረው ኢሕአዴግ ይከተል የነበረውን የመሬት ፖሊሲ (መሬት የሕዝብ ቢሆንም፣ በመንግሥት ባለቤትነት መተዳደር አለበት የሚለው ዕሳቤ) ላለመቀየር “በመቃብሬ ላይ” ካልሆነ አልደራደርም እስከ ማለት ደርሶ ነበር፡፡

ለአብነት ያህል ከሰባት ዓመታት በፊት መጋቢት 18 ቀን 2007 ዓ.ም. የግብርናና የገጠር ልማት ስትራቴጂና ፖሊሲዎችን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ አምስት ፓርቲዎች ያደረጉትን ክርክር ዓይተን፣ ሰምተን ነበር፡፡ ብዙ ነጥቦች የተካተቱበት ክርክር ቢሆንም ዋነኛ ማጠንጠኛው ግን የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ እንደነበር አይዘነጋም (በነገራችን ላይ በምርጫ 2013 ዓ.ም. ብልፅግናን ጨምሮ ብዙዎቹ ተፎካካሪዎች ስለመሬትና መሬት አስተዳደር እዚህ ግባ ሚባል ሐሳብ ማራመዳቸውን ያልሰማን ሲሆን፣ ዛሬ ከመንግሥት ጋር በትብብር እየሠሩ ያሉ የያኔዎች ዋነኛ ተፎካካሪዎች አቋምም ምን እንደሆነ የታወቀ ነገር የለም)፡፡

በጠቀስኩት የቀደመው ጊዜ ግን ተቃዋሚዎች (በአሁኑ አባባል ተፎካካሪዎች) በአንድ ድምፅና ድምፀት መሬት የግለሰብ አርሶ አደሩ መሆን አለበት፡፡ የመሸጥ፣ የመለወጥና የማከራየት፣ የማልማት ጉዳይ የገበሬው ብቻ መሆን አለበት፡፡ መንግሥት በመሬት ጉዳይ እጁን ማስገባት ወይም ጣልቃ መግባት የለበትም… ባዮች ነበሩ፡፡

ብዙዎቻችን እንደምናስታውሰው አንዳንዶቹ መሬት የግለሰብና የወል ይሁን ብለዋል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ መሬት የግለሰብ፣ የወልና የመንግሥት መሆን አለበት ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ገዥው ፓርቲ ከዚህ በፊት በቀረፀውና በተግባር እየታየ ባለው ሁኔታ መሠረት “መሬት የሕዝብና የመንግሥት ነው፣ አይሸጥም…አይለወጥም!” ብሎ ሲከራከር ሀብቱ የተደቀነበትን አሻጥርና የእጅ አዙር ብዝበዛ እንኳን ለማስታወስ አይሞክርም ነበር፡፡ ምንም እንኳን በ2010 ዓ.ም. የሕዝቡ ምሬትና ቁጣ ገፍቶ ሲመጣ በዕውር ድንብር የተሃድሶ ግምገማ ነጥብ ቢያደርገውም፡፡

የዚያን ጊዜዎቹ ተፎካካሪዎች ግን፣ ‹‹አሁንም ቢሆን መሬት በቀጥታና በእጅ አዙር እየተሸጠ ነው፡፡ ገበሬው አይሽጥ እንጂ መንግሥት ግን መሬቱን እየሸጠ ነው፤›› ሲሉ ይከራከሩ እንደነበር ወደኋላ ማስታወስ አይገደንም፡፡ የገዥው ፓርቲና የመንግሥት ሰዎችም ‹‹መሬት እየተሸጠ አይደለም፣ ይኼ ፈጽሞ ሐሰት ነው፣ መሬት በኢትዮጵያ አይሸጥም፣ አይለወጥም፣ በእኛ መንግሥት ፖሊሲ መሠረት መሬት በይዞታነት የሚተላለፈው በሊዝ ነው፤›› ብለው መከራከራቸውን አስታውሳለሁ፡፡

በእርግጥ እኛ ብቻ ሳንሆን በዓለማችንም መሬት የሚሸጡ አገሮች አሉ፡፡ እኛ አገር ግን መሬት አይሸጥም የሚባለው እስከ መቼውም የተሸጠ ይዞታ ሆኖ፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚወራረስ ሀብት አልሆነም በሚል ይሆን ብለው የሚያስቡ ነበሩ፡፡ ይህም ቢሆን የማያስኬደው ግን መንግሥት መሬቱን መልሶ ለአርሶ አደሩ በፍትሐዊነት ላካፍል ካላለ መሬት በቤተሰብ እንደሚወራረስ ይታወቃል፡፡

በእኛ አገር መሬት ለውስጥ ባለ ሀብቶችም ሆነ ለውጭ ኢንቨስተሮች የሚሸጠው በሊዝ መሆኑም፣ በእኛ ብቻ ዕውን የሆነ አለመሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ በብዙ አገሮች የእኛን አገር ጨምሮ መሬት የመንግሥት መሆኑን፣ የማይሸጥና የማይለወጥ እንደሆነ በሕገ መንግሥታቸው ላይ መሥፈሩም የሚታወቅ ነው፡፡ ግን በምን ዓይነት ሥልትና ዘዴ፣ በእንዴት ያለ ቴክኖሎጂና የፍትሐዊነት ማረጋገጫ መሣሪያ ነው የሚፈጽሙት ማለት ነው የሚበጀው፡፡

እዚህ ላይ የሚነሳው ቁምነገር በተለይ የአርሶ አደሩን መሬት በብጥስጣሽ አጠቃቀም ምርታማነቱን ከማዳከም ለማውጣት እየተወሰዱ የነበሩ ዕርምጃዎች አሉ፡፡ አንዳንዶቹ አሁንም በአንዳንድ ክልሎች እየተሠራባቸው ነው፡፡ ለአብነት ያህል ግብርናና ገጠር ልማት ራሱን ከመቻል አልፎ ለአገሪቱ አጠቃላይ ዕድገትና ልማት የሚያደርገውን ግብዓት እንዲያመነጭ ለማድረግ፣ ኩታ ገጠም የሆነ መሬት ያላቸው ገበሬዎች ተቀናጅተው በዘመናዊ የግብርና ዘዴ እየተጠቀሙ እንዲያርሱ ከማድረግ በተጨማሪ፣ ሰፋፊ መሬቶችን ይዘው ለማልማት አቅሙና ፍላጎቱ ላላቸው ባለ ሀብቶች መንግሥት መሬት በሊዝ ይሰጣል (የሊዙ ነገር ባለፉት አራት ዓመታት የቆመ ቢሆንም)፡፡

እዚህ ላይ በገዛሁት ቤትና በተከራየሁት ቤት ላይ ያለኝ ሥልጣንና መብት የሰማይና የመሬትን ያህል እንደሚለያይ ሁሉ፣ ተከራዮች በተከራዩት መሬት ላይ ያላቸው መብትም ያንኑ ያህል የተለያየ ነው፡፡ ሊዝ በአብዛኛው ከ25 ዓመት እስከ 99 ዓመት ድረስ የሚቆይ የኪራይ ስምምነት ነው፡፡ በጣም ከፍተኛ ስፋት ያለው መሬት በዓለም ዙሪያ በዚህ መልክ (በሊዝ) ለአልሚ ባለሀብቶች ተሰጥቷል፡፡ መሬት በሊዝ በመስጠት እኛ የመጀመርያዎቹ ወይም ብቸኞቹ አይደለንም፡፡ ድፍን ዓለም የሚሠራበት ነው፡፡ መሬት ለባለሀብቱ በገፍ አለመቸብቸቡ ዛሬ ላይ ቆመን ስንመለከተው ክፋት እንደሌለው የሚያስገነዝበንም፣ ቢያንስ በኢንቨስትመንት ስም የአገር ሀብት ቢዘረፍም ሕዝቡ የመሬቱ ባለቤት ከመሆን ያልተናጠበ መሆኑን ስንታዘብ ነው፡፡

የምግብ ፖሊሲ ጥናትና ምርምር የተባለ ዓለም አቀፍ ተቋም በ2012 ዓ.ም. ባወጣው ጥናት መሠረት፣ ከ2008 እስከ 2012 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ በታዳጊ አገር ብቻ ከ15 እስከ 20 ሚሊዮን ሔክታር የእርሻ መሬት በሊዝ ተሰጥቷል፡፡ ሌላኛው ዓለም አቀፍ ተቋም (Land Portals Land Matrix) እ.ኤ.አ. በ2015 ባወጣው ጥናታዊ መግለጫ፣ በዓለም ዙሪያ 49 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ለአልሚዎች ተላልፏል፡፡ አብዛኛው መሬት ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች የተላለፈ ሲሆን፣ 26 በመቶ ያህሉ ለውጭ ኢንቨስተሮች የተላለፈ ነው፡፡ ለባለሀብቶች የተላለፈው መሬት መጠን (ስፋት) ይለያይ እንደነበር ጠቅሷል፡፡ እዚህ ላይ ለደሃ ሕዝብ መሬት በጤነኛ መንግሥት ቁጥጥር ሥር መሆኑ ክፋት አልነበረውም፡፡

የዓለም ባንክ ሪፖርት እንደሚያስረዳው በዓለም ላይ ለአልሚ ባለሀብቶች የተላለፈው መሬት መጠን 57 ሚሊዮን ሔክታር ነው፡፡ እ.ኤ.አ. የ2012 የፍሪስና ግሪንበርግ ሪፖርት በበኩሉ በአፍሪካ ብቻ ከ51 እስከ 63 ሚሊዮን ሔክታር በሊዝ ተላልፎ ለባለ ሀብቶች መሰጠቱን አስታውቆ ነበር፡፡ ግሬይን ዳታ ቤዝ (GDB) እ.ኤ.አ. በ2015 ባሳተመው መግለጫ ደግሞ ለአልሚዎች የተላለፈው የእርሻ መሬት 35 ሚሊዮን ሔክታር ነው፡፡ ያሉት መረጃዎች ሲጠቃለሉ የሚያሳዩት ከ20 እስከ 60 ሚሊዮን ሔክታር መሆኑን ነው፡፡

ዓለማችን ያላት ጠቅላላ የእርሻ መሬት ደግሞ አራት ቢሊዮን ሔክታር የሚደርስ ነው፡፡ ስለዚህ በሊዝ የተላለፈው መሬት ከአጠቃላዩ የእርሻ መሬት መጠን ጋር ሲተያይ ከአንድ መቶ ያነሰ ነበር፡፡  ከዚህ አንፃር በነፃ ገበያ ሥርዓት የሚመሩ አብዛኞቹ አገሮች፣ ‹‹መሬት የሕዝብና የመንግሥት ነው›› በሚለው ፖሊሲ ላይ የማይናወጥ አቋም ማራመዳቸው ብቻ ሳይሆን፣ ለባለሀብቱም ሆነ ለዜጋው መሬት የሚተላለፍበት የሊዝ ሥርዓት እየዘረጉ ነው (እኛ ጋ ያለው ትልቁ ችግር መሻማቱና የእኔ ነው/የእዚያ ነው የሚለው ኢምጣኔ ሀብታዊ የሆነው የማንነት ፍትጊያ ይመስለኛል)፡፡

በእኛ አገር ሁኔታም ምንም እንኳን ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ በተጀመረው ለውጥ ሒደት ለመረጋጋትና ለልማት ትኩረት ለመስጠት የሚችል ዕድል ጎልቶ ባይፈጠርም፣ የፖለቲከኞቻችን የመሬት ፖሊሲ ብዙም ለገበያ ቅርብ አልነበረም፡፡ በተለይ የከተማ መሬት በአንድ በኩል አይሸጥም አይለወጥም ስም አንዳንዶች ባለሀብቶችና በመዋቅሩ ውስጥ የተሰገሰጉ ምንደኞች እንዳሻቸው እንዲደረጉ እየፈቀደ፣ በሌላ በኩል በሊዝ ሥርዓቱ የሚተላለፍበትንም ሥርዓት ገድቦ እንደ ቆየ የምንታዘበው ነው፡፡

ያለ ምንም ጥርጥር ግን መሬት የሕዝብና የመንግሥት ብቻ መሆን አለበት፡፡ መሬት አይሸጥም አይለወጥም ይል የነበረው የቀድሞው መንግሥት፣ በሊዝ፣ በድርድርም ይባል መሬቱን ለልማት ተነሽ በማድረግ የሠራው ሥራ ፍትሐዊነት የተጓደለበት፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የዴሞግራፊ ተፅዕኖ የጎላበት፣ በብዙ የኢንቨስትመንት መሬቶች ላይ ደግሞ የሥርዓቱ ሰዎች ብቻ በልማታዊ ባለሀብት ስም የተጠቀሙበት እንደ ነበር ማስተባበል አልተቻለም፡፡ ይህ እውነታ ዛሬስ ምን ያህል ተቀይሯል የመንግሥት የእርምት ዕርምጃ ምን ገጽታ አለው? በመከልከልና በማገድስ የመሬት ሀብት ልማትን ማስቀጠል እንዴት ይቻላል? ብሎ መነጋገር ነው የመፍትሔ በር ሊያመላክት የሚችለው፡፡

በመሠረቱ በኢሕአዴግ ዘመንም ቢሆን የአሠራሩ ብልሽትና የኢንቨስትመንት መሬት ወደ ልማት ባለመቀየሩ ውጤት አለማምጣቱ እንጂ፣ አገሪቱ ካላት ለእርሻ የሚሆን መሬት መጠን አንፃር ለአገር ውስጥ ባለሀብቶችም ሆነ ለውጭ ኢንቨስተሮች በሊዝ የተላለፈው መሬት እጅግ በጣም ትንሽ ነበር፡፡ በወቅቱ ተጋግሎ የተራገበውን ያህልም አልነበረም፡፡

የዓላማው አሳማኝነት ሲታይም በተበጣጠሰ ሁኔታ ይታረስ የነበረውና ወይም ፈጽሞ ታርሶ የማያውቀውን መሬት ለባለሀብቶች በሊዝ መስጠት ከሚፈጥረው የምርት መጠን ጭማሪ፣ ከሥራ ዕድልና ከቴክኖሎጂ ሽግግር፣ እንዲሁም እንዲያመነጭ ከሚጠበቀው ካፒታልና ለዘመናዊ የኢንዱስትሪ ሽግግር ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ አንፃር ሲታይ የሚጠላ አልነበረም፡፡ ነበር ሆኖ መቅረቱ እንጂ፡፡

አሁንም የምንገኝበት ጊዜ ከቆየንባቸው የፍጥጫ የዞረ ድምሮች እየወጣን፣ በፍትሐዊነትና በእኩልነት ሕዝቦች የሚኖሩባትን አገር ለመገንባት እንቅስቃሴ የተጀመረበት መሆኑ ተደጋግሞ ተነግሯል፡፡ መንግሥት ምንም እንኳን ያጋጠመው የውስጥና የውጭ ተግዳሮት ከፍተኛ ቢሆንም፣ መላው የአገራችን ሕዝቦች በተለይም ምሁራንና ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች በዋና ዋና ሕገ መንግሥታዊና የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ መክረው፣ በረጋና በሰከነ መንገድ ተደማምጠው የሚቀራረቡበትን ብሔራዊ መግባባት እንዲያመጡ ከፍተኛ ፍላጎት አሳይቷል፡፡ የመሬት ሀብት ጉዳይም ምንም እንኳን ተነጥሎ የማይታይ ባይሆንም፣ ቀዳሚው ጭብጥ መሆኑ አይቀርም፡፡ የግድም ነው፡፡

እንደ አገር ከላይ በተጠቀሱት ማስረጃዎች ላይ ተመሥርተን የምንደርስበት ግልጽ አቋም፣ ‹‹መሬት የሕዝብና የመንግሥት›› መሆኑ በሕገ መንግሥቱ መሥፈሩ እጅግ በጣም ትክክል ወይስ ትክክል አይደለም ነው፡፡ መጠነኛ መሻሻል ያስፈልገዋል እስከ ማለት መሄድ ሊኖርብን ይገባል፡፡ መንግሥት የመሬት ሀብትን ጠብቆና ተቆጣጥሮ በሊዝም ሆነ በሌላ መንገድ እያስተላለፈ ለአገር ግንባታ ያውለው ከተባለስ እንዴትና በምን አግባብ፣ ከፌዴራላዊ ሥርዓት ፖለቲካ አንፃርስ በምን ዓይነት ቅኝት መጓዝ ይቻላል እየተባለ በዕውቀትና በመተሳሰብ መንፈስ መሥራት ይኖርበታል፡፡

ከዚህ ቀደም ብዙዎቹ ተቃዋሚዎች (ሁሉንም በአንድ ቅርጫት መክተት ቢያዳግትም) ‹‹መንግሥት መሬት ይሸጣል›› ብለው ብቻ አላቆሙም፡፡ ‹‹በቆላማ አካባቢዎች ያሉ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን በዝቅተኛ ዋጋ ይሸጣል›› የሚሉትም ነገር ነበራቸው፡፡ አንዳንዶቹም መንግሥት መሬትን እየተቆጣጠረ ልሽጥ ማለቱ የአፈናና የጉልበት ማግኛ ሥርዓትን ለማስቀጠል ከመሻት አድርገውም ያወሱ ነበር፡፡ መንግሥት በበኩሉ ይህን የሚሉት የኒዮ ሊበራሊዝም መንገድ ጠራጊዎችና ዜጎችን ባዶ እጅ ለማስቀረት ያሰፈሰፉ እስከ ማለት ደርሶ ነበር፡፡ 

በመሠረቱ ግን መንግሥት የምግብ እጥረትን ለማስወገድ፣ ሥራ አጥነትን  ለመቀነስ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማስገኘት፣ ለአጠቃላዩ ዕድገትና ልማት የሚሆን የካፒታል አቅም ለማመንጨት፣ ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን አቅርቦት ለመጨመር፣ ወዘተ ላለው ፖሊሲ ስኬታማነት ያልታረሰ መሬት ለባለሀብቶች ማስተላለፉ አማራጭ አልነበረውም፡፡ በሊዝ ለማስተላለፍ የቀየሰው ስትራቴጂ ደግሞ የመሬቱን ዋጋ አነስተኛ ለማድረግ እንደነበር የታመነ ነው፡፡ ቢያስወድድማ ማን ሊመጣለት? ችግሩ ያለው ግን እነማን መሬት ወሰዱ፣ ምን አስገኙልን ሲባል የሚገኘው ምላሽ ላይ ነው፡፡

እዚህ ላይ ከትናንቱ አካሄድ ትምህርት መወሰድ ያለበት ዋናው ቁም ነገር፣ መሬት በሊዝ የወሰዱ ባለ ሀብቶችና ኢንቨስተሮች በምን መሥፈርትና ግልጽነት ወደ ልማት ገቡ? አልሚዎች ፈጥነው ወደ ልማት እንዲገቡና ከእያንዳንዱ ሔክታር ብቻ ሳይሆን፣ ከእያንዳንዷ ካሬ ሜትር መሬት ላይ እንደ ሕዝብና አገር የበለጠ ጥቅም ማግኘታችንን ማረጋገጥ ያለብንስ በምን መንገድ ነው? ይህን ተግባር በቁርጠኛ የፖለቲካ አመራር ለመመራትስ ምን ዘዴ ይቀይሳል? ቢባል ጠቃሚ ነው፡፡ ተገዳዳሪውም ሆነ የአገር ተቆርቋሪው አንዱ በሌላው ጫማ ላይ እየቆመ የጋራ መፍትሔ ቢያመላክት ይበጃል፡፡

ከከተማም ሆነ የገጠር መሬት ጋር ተያይዞ የሚነሳው ሌላው ወሳኝ ነጥብ መሬት ለባለሀብት በመሰጠቱ፣ ነዋሪው (ገበሬ) የሚነሳበት (የሚፈናቀልበት) ሁኔታ እንዳይባባስ የሚያስረዳው ጭብጥ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በተለይ በእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ሲታይ በጥብቅ ሊታሰብበት እንደሚገባ መዘንጋት ትናንትን አለማስታወስ ነው፡፡ በተለይ እስካሁንም ድረስ አዲስ አበባን ለመሰሉ የከተማ መሬት የአርሶ አደሩ፣ የከተማው ነዋሪና የባለሀብቱ ፍላጎትና አቅርቦት የሚያስታርቅ ፍትሐዊ መንግሥታዊ መዋቅር መዘርጋት ፖለቲካዊ ዕርምጃ ሊሆን የግድ ነው፡፡

በክልሎችም አብዛኛው ለእርሻ ኢንቨስትመንት የሚሆነው ቆላማ መሬት ባይታረስ እንኳ፣ አልፎ አልፎ እዚህም እዚያም ሰዎች የሚኖሩበት አካባቢ አለ፡፡ ለኢንቨስተሮች የሚሰጠው መሬት ላይ ኗሪዎች ሊገኙ ይችላሉ፡፡ መሬቱ ለባለሀብት ሲሰጥ ለእነዚህ ሰዎች ዘላቂ መፍትሔ መቀየስ ያስፈልጋል፡፡ ለአጠቃላዩ ብሔራዊ ልማት ሲታሰብ ሰዎችን ከቦታ ቦታ ማዘዋወርን ይጠይቃል፡፡ ሌላ ተለዋጭ ቦታ ይሰጣቸዋል፡፡ ወይም ተገቢ ነው የተባለ ካሳ ይከፈላቸዋል፡፡ ከዚህ በፊት ግን ተነሺዎችን ማሳመንና ለምን እንደሚነሱ ስለዓላማው በቂ ግንዛቤ እንዲያገኙ ለመሥራት መታቀድ አለበት፡፡

በሚካሄደው የልማት ሥራ ውስጥ ተቀዳሚ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ዋስትና መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ለልማት ዓላማ ሲባል ሰዎች ከኖሩበት አካባቢ የሚነሱባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ ይህም በዓለም መሬት አቅራቢዎች ዘንድ የሚሠራበት ነው፡፡ በውስጡ ጤነኛ ያልሆነ ሴራ ካልተጠነሰሰ በስተቀር፣ አገርን ለማልማት ሲባል ዜጎች የሚከፍሉት ዋጋ ነው እንጂ፣ ማንኛውም መንግሥት የራሱን ዜጎች ለመጉዳት ሲል የሚያደርገው የማፈናቀል ሴራ አይደለም፡፡ የተፈናቀሉ ካሉም ጉዳዩ በዚህ መንፈስ ግንዛቤ ሊያገኝ ይገባል፡፡ ይህ ነው ወደፊት በጥብቅ ሊታሰብበትና መግባባት ሊያዝበት የሚገባው ሌላው ቁምነገር፡፡

ከዚህ ቀደም በአገራችን በተተገበረው የመሬት ሀብት ልማት (በገጠርም በከተማም) ረገድ ያለውን ችግር ከሕገ መንግሥትና ከፖሊሲ ሐሳብ ውጪ የሚመለከቱት ብዙዎች እንደሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ በተለይ በከተሞች ያለው የመሬት ዘርፍ ግልጽነት የሌለው፣ በቡድን የሚፈጸም ዘረፋና ሙስና የሚበዛበት፣ የሥርዓቱ ሰዎች በዋናነትም ጥቂት ቱባ በለሀብቶችና ባለሥልጣናት ያሻቸውን የሚፈጽሙበት አደገኛ መስክ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ዜጋው ገንዘብ ስላለውና ማልማት ስለፈለገ ብቻ አገልግሎቱን በቀላሉ እንደማያገኝ ብዙ የተባለበት ጉዳይ ነው፡፡

እሱ ብቻ ሳይሆን በቅርቡ ከተማ አስተዳደሩ በጀመረው ማጥራት እንደተረጋገጠው፣ በወረዳና ክፍለ ከተማ ደረጃ ያሉ አመራሮችና የዘርፉ ባለሙያዎች በሚሊዮኖች የሕዝብ ሀብት የሚዘርፉበት መስክ መሬት፣ በተለይም የከተማ መሬት ነው፡፡ ይህን አገር አድካሚና ሕዝብ አቆርቋዥ አካሄድ በሕግና በሥርዓት ለማስቆም፣ በብሔራዊ መግባባት መንፈስ በአንድነት ተነስቶ መታገል ካልተቻለ የፖሊሲ ለውጥ መፍትሔ ሊሆን እንደማይችል ብዙዎች የሚያሳስቡት ለእዚህ ነው፡፡

እነዚህ ወገኖች የአገራችን ዕድገት የሚረጋገጠውና ሕዝቡም ከድህነት ወጥቶ የልማቱ ተጠቃሚ የሚሆነው፣ በሕገ መንግሥቱ ላይ የሰፈረውን የመሬት ይዞታ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግና የተስተካከለ የመሬት አጠቃቀም ስትራቴጂዎችን ማራመድ ሲቻል ነው ብለው ያምናሉ፡፡ በኒዮሊብራል አስተሳሰብ የሁሉም ነገር ይሸጥ ይለወጥ የሚባለውን ሊቀበሉት አይሹም፡፡

ምንም ተባለ ምን በታሪክም ሆነ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አገራችን ያለፈችባቸውን እውነታዎች አገናዝቦ፣ ትርፍና ኪሳራውን አሥልቶ፣ በመደማመጥ የሚበጀውን የመሬት ልማት ሀብት ፖሊሲም ይባል ድንጋጌ በጋራ መንደፍ/ማሻሻል የብሔራዊ መግባባት አንዱ ፍሬ ነገራችን መሆን እንዳለበት ይሰማኛል፡፡ እናንተስ!?

 ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

  

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...