- ክቡር ሚኒስትር የሰሞኑ ውሳኔ ምንም ሊገባኝ አልቻለም፣ ምንድነው ምክንያቱ?
- የትኛው ውሳኔ?
- እስረኞቹ እንዲፈቱ የተደረገበት ውሳኔ?
- እሱን እኔም ስሰማ ደንግጫለሁ፡፡
- ስለውሳኔው ቀድመው አልሰሙም ነበር?
- በጭራሽ፣ በቴሌቪዥን ነው መወሰኑን የሰማሁት፡፡
- በጋራ የተወሰነ አይደለም ማለት ነው?
- ነገሩን ለመረዳት ሌሎች ባልደረቦቼ ጋ ደውዬ ነበር፡፡
- እሺ…?
- እነሱም እንደ እኔ በቴሌቪዥን ዜና ነው የሰሙት፡፡
- እኩልነት ማለት እንዲህ ነው፡፡
- እንዴት?
- በዚህ ጉዳይ እኩል ሆነናል ማለቴ ነው? ማን እንደወሰነው ግን የሰሙት ነገር የለም?
- መንግሥት ነዋ፡፡
- የትኛው መንግሥት?
- የእኛ መንግሥት ነዋ፣ ሌላ ማን ሊሆን ይችላል?
- መንግሥትማ ደንግጫለሁ አለ አይደለም እንዴ?
- ምን ሆኖ ነው የሚደነግጠው?
- መለቀቃቸውን ስሰማ ደንግጫለሁ አለ እኮ?
- አይ… እሱ የአፍ ወለምታ ነው፡፡
- የአፍ ወለምታ ማለት?
- ሐሳቡ ሲቀርብ ለመቀበል ተቸግሬ ነበር ለማለት እንጂ፣ ውሳኔውማ የመንግሥት ነው፡፡
- ምን ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ቢመጣ ነው መንግሥት ይህንን ውሳን ተጣድፎ የወሰነው? የሚጠረጥሩት ነገር አለ ክቡር ሚኒስትር?
- ነገሩ ከአሜሪካ መንግሥት የፖለቲካ አቋም ጋር የተገናኘ ይመስለኛል።
- እንዴት ምን የተለየ ነገር አለ?
- አሜሪካኖቹ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሩሲያን አቋም ማስቀየር የሚችሉበትን ጫፍ በዩክሬን ቀዳዳ ገብተው አግኝተዋል።
- አልገባኝም?
- አሜሪካኖቹና አውሮፓውያኑ ሩሲያን በዩክሬን ጉዳይ አጣብቂኝ ውስጥ ከተዋታል፣ ሩሲያ ይህንን አጣብቂኝ ለማለፍ ራሷን ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ማራቅ ይጠበቅባታል፣ ይህ ደግሞ አሜሪካኖቹ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚፈልጉት ውሳኔ በፀጥታው ምክር ቤት እንዲወሰን ዕድል ይሰጣቸዋል።
- ምን ሊወሰን ይችላል?
- የሩሲያ ተቃውሞ ከሌለ አሜሪካኖቹ በሰብዓዊ ምክር ቤት በኩል ያስወሰኑትን አጠናክረው በመግፋት የፀጥታ “R2P” የተባለውን ውሳኔ እንዲወስን ሊያደርጉ ይችላሉ፣ ይህም እንደ ሊቢያ በኢትዮጵያ ጣልቃ እንዲገቡ ያስችላቸዋል።
- የቻይና ድጋፍስ?
- ቻይና ላይ ሙሉ እምነት ማሳደር አይቻልም።
- ለምን?
- ቻይና ለረዥም ጊዜ የምትታወቀው በድምፀ ተዓቅቦ ነው።
- እና አሜሪካኖቹ እስረኛ በመፍታታችን ይተውናል?
- እሱ የሁላችንም ጥያቄ ነው፣ ምናልባት ሁሉን አቀፍ ውይይት የሚደረግ መሆኑን ታሳቢ አድርገው ሊያልፉን ይችሉ ይሆናል።
[ክቡር ሚኒስትሩ የከፈቱትን ዩቲዩብ እንዲያንቀሳቅስ የቀጠሩት ወጣት ጋዜጠኛ ጋ ደወሉ]
- የላኩልህን መረጃ አይተኸዋል አይደል?
- አዎ፣ አይቼዋለሁ ክቡር ሚኒስትር።
- ጮማ ዜና ነው አይደል?
- በጣም ጮማ ወሬ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በል ቶሎ ብለህ ልቀቀው፣ ሰበር ዜና ማለትህን እንዳትረሳ፡፡
- ቪዲዮውን አቀናብሬ ጨርሼ ነበር ግን…
- ግን ምን?
- ሰበር ዜና ለማለት አልቻልኩም፡፡
- ለምን?
- ባላንጣችን የሆኑት ሚኒስትር ከሁለት ደቂቃ በፊት በዩቲዩባቸው ለቀውታል።
- አትለኝም?
- አዎ፣ ለጥቂት ቀድመውናል።
- ሰበር ብለውበታል?
- አዎ፣ ግን እነሱ ቪዲዮውን አላገኙትም።
- እንደዚያ ከሆነማ ጥሩ ነው።
- ምኑ ነው ጥሩ?
- በቪዲዮ አልቀደሙንማ፣ በል ቶሎ ብለህ ልቀቀው፡፡
- ምን ብዬ ልልቀቀው?
- ሰበር ቪዲዮ እጃችን ገብቷል በልና ልቀቀው።
- ጥሩ ሐሳብ ነው ያመጡት ክቡር ሚኒስትር፣ ትክክል ሰበር ቪዲዮ እጃችን ገብቷል!