Friday, July 12, 2024

ፍትሕ የፖለቲካ ሥርዓቱ መሠረት መሆን አለበት!

ብሔራዊ ምክክር የወቅቱ ዋነኛ የፖለቲካ አጀንዳ ሆኖ ብቅ ካለ ወዲህ፣ ጥርትና ግልጽ ብለው መውጣት ያቃታቸው ጉዳዮች መኖራቸው አነጋጋሪ ሆኖ መሰንበቱ አይዘነጋም፡፡ ቀላል የማይባል ቁጥር ባላቸው ሰዎች ዘንድ ብሔራዊ ምክክርን ከድርድር ጋር አደባልቆ ማየት፣ ይህንን ጉዳይ ወደ አደባባይ ይዘው በወጡ የሚመለከታቸው አካላትም የሁለቱን ልዩነት አንጥሮ ያለ ማሳየት ችግር፣ እንዲሁም ከሁለቱም ወገኖች ሳይሆኑ የመንግሥትን እንቅስቃሴ የሚጠራጠሩና በመንግሥት ላይ ተስፋ ያደረጉ ወገኖች የሚያሰሙዋቸው ድምፆችም ነበሩ፡፡ በዚህ መሀል በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደው ጦርነት ሳይቋጭ በእንጥልጥል ቆሟል በማለት፣ ነገ ይዞት ሊመጣ የሚችለውን ነገር በጨፈገገ ስሜት የሚከታተሉም ነበሩ፡፡ እንዲህ ድብልቅልቅ ያሉ ስሜቶች በሚዋልሉበት ጊዜ ነው ከመንግሥት በኩል አዲስ ዜና የተሰማው፡፡ ተከሰው በእስር ላይ ከሚገኙ ፖለቲከኞች መሀል እንደ እነ አቶ ስብሃት ነጋ፣ አቶ ጀዋር መሐመድና አቶ እስክንድር ነጋ አብረዋቸው ከታሰሩት ጋር ክሳቸው ተቋርጦ እንዲፈቱ መወሰኑ የተነገረው፡፡ በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች አገሮች ታሳሪዎችን ክስ በማቋረጥ፣ በምሕረትም ሆነ በይቅርታ መፍታት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ነገር ግን እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ላይ ሲደረስ ብዙዎችን የሚያሳስባቸው የፍትሕ ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም ፍትሕ የአገሪቱ የፖለቲካ ሥርዓት መሠረት መሆን ስላለበት፡፡ 

በማንኛውም የሠለጠነ አገር በፍትሕ ሥራ ጣልቃ መግባት ተገቢ አይደለም፡፡ ማንም ሰው በወንጀል ተጠርጥሮ ሲከሰስ ፍርድ ፊት ቀርቦ ይዳኛል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ክሱን ማቋረጥ ከፈለገም ለፍርድ ቤት አቅርቦ ያስፈጽማል፡፡ ይህ በሕጉ መሠረት የሚፈጸም የተለመደ ተግባር ነው፡፡ በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ የመንግሥትን ጣልቃ ገብነት ለመከላከል፣ ይህ ዓይነቱ አሠራር ከፍተኛ ተቀባይነት ይኖረዋል፡፡ ማንም ሥልጣን ያለው ግለሰብ ወይም ቡድን እየተነሳ ፍትሕን እንዳያዛባ፣ የዳኝነት አካሉም በነፃነት ሥራውን እንዲሠራና ሕዝቡም በሕግ የበላይነት መኖሩን ማረጋገጥ እንዲችል ጠቃሚ ነው፡፡ ፍትሕ እንደ ሸቀጥ በሚቸረቸርበት አገር ውስጥ እንዲህ ዓይነቱ አሠራር ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል፡፡ ነገር ግን በድንገት ሳይታሰብ ከዚህ በተቃራኒ የሆነ ውሳኔ ከተሰማ  ድንጋጤ ይፈጠራል፡፡ የፍትሕ ጥያቄም ይነሳል፡፡ ምንም እንኳ መንግሥት በጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ በፍትሕ ሚኒስትሩ የተደረሰበትን ውሳኔ አመክንዮ ለማስረዳት ቢሞክርም፣ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚሰሙ ድምፆች መደመጥ አለብን እያሉ ነው፡፡ የመንግሥት አንዱ ኃላፊነትም የሚነሱ ጥያቄዎችን ማዳመጥና ተገቢ ምላሽ መስጠት ነው፡፡ ሥርዓተ መንግሥቱ መሠረቱን ፍትሕ ማድረግ አለበትና፡፡

ብዙዎችን ግራ ያጋባውና ያስደነገጠው የመንግሥት ውሳኔ የተደበላለቁ ስሜቶችን ፈጥሯል፡፡ መንግሥት ክስ ማቋረጡን ባስታወቀበት መግለጫው፣ ከዚህ በፊት በተፈጸመ ጥፋት የታሰሩትንም ሆነ በቅርቡ ከተፈጠረው ጦርነት ጋር በተያያዘ የታሰሩትን መፍታቱን አስታውቋል።  መንግሥት ይኼንን ውሳኔ ሲወስን ዓላማው የኢትዮጵያን ችግሮች ሰላማዊ በሆነ፣ ከእልህና ከመጠፋፋት በራቀ ሁኔታ፣ በአገራዊ ምክክር በዘላቂነት ለመፍታት እንዲቻል መንገድ ለመክፈት ነው ብሏል። በተጨማሪም የሕዝብን ጥያቄዎች ከግምት በማስገባትና ምንጊዜም ለሰላማዊ ፖለቲካ ያለውን ቁርጠኝነት ለማሳየት መሆኑን አክሏል። መጀመሪያ ላይ በመንግሥት በኩል ምሕረት መሰጠቱ ይፋ ቢደረግም፣  የፍትሕ ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ ግን መንግሥት ክስ አቋረጠ እንጂ ምሕረትም ሆነ ይቅርታ አላደረገም ብለዋል፡፡ ከእስር የተፈቱት ሰዎች ዳግም እዚያው ተግባር ውስጥ ከተገኙም የተቋረጠው ክስ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ታሪካዊ ዳራዎችን በመጠቃቀስ አሸናፊ ምሕረት ማድረጉ በኢትዮጵያ የተለመደ መሆኑን፣ መንግሥት እዚህ ውሳኔ ላይ ሲደርስ ለአገር ጥቅም አስቦ ስለሆነ ሕዝብ መንግሥትን አምኖ ውሳኔውን መቀበል እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ የመንግሥትን ውሳኔ የሰሙ ብዙ ታዋቂ ሰዎች ውሳኔውን ያልተጠበቀና አስደንጋጭ መሆኑን ገልጸው፣ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል የፀብ ግድግዳ እንዳይፈጠር እያስጠነቀቁ ነው፡፡

መንግሥት በአንድ በኩል እዚህ ውሳኔ ላይ ሲደርስ ያለፉት ዋጋ አስከፋይና ግጭት ጠማቂ አካሄዶች በጭራሽ እንዲደገሙ እንደማይፈቅድ፣ ፍትሕና ምሕረትም በየሚዛናቸው እንዲጓዙ እንደሚፈልግ፣ በሒደቱ የተጎዱ ወገኖች እንደሚኖሩ እንደሚያምን፣ የእነዚህ ተጎጂ ዜጎች ቁስል በሽግግር ፍትሕ እንደሚካስ፣ እነዚህ ተጎጂ ዜጎች ሕመማቸው ለኢትዮጵያ የከፈሉት ዋጋ በመሆኑ ሸክማቸውን መንግሥትና ሕዝብ በጋራ እንደሚሸከሙላቸው፣ ከእስር የተፈቱ ወገኖችም ጭምር የተጎጂዎችን ሸክም የመሸከም ዕዳ እንዳለባቸው፣ ይህ ውሳኔ የተላለፈውም በዋናነት ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያ የመሐሪነቷን ዋጋ እንድታገኝ፣ የኢትዮጵያን ምሕረት ያገኙት አካላትም ምሕረቱን ያገኙበትን ዋጋ ይረዱታል ብሎ እንደሚያምን፣ የኢትዮጵያ ነባር ችግሮች የሚፈቱት በሰላማዊ ፖለቲካዊ ተዋስኦ፣ በሆደ ሰፊነትና አዎንታዊ ሚናን በመጫወት መሆኑን፣ ለዚህ ደግሞ መንግሥት ዋጋ ከፍሎም ቢሆን ቀዳሚነቱን እንደሚወስድ፣ ለዘላቂ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና ሰላም ሲል የተወሰኑ እስረኞችን በምሕረት መፍታቱን ነው የገለጸው፡፡ ይህንን የፖለቲካ ውሳኔ ከፍትሕ አኳያ የሚኖረውን አንድምታ ብዙዎች በተለያዩ ማዕዘናት ላይ ሆነው እየተነጋገሩበት ስለሆነ፣ የጋራ ግንዛቤና አረዳድ እንዲፈጠር መንግሥትም የንግግሩ አካል መሆን ይኖርበታል፡፡

የፍትሕ ጉዳይ ሲነሳ በአገርና በሕዝብ ላይ በተፈጸመ ወንጀል ከሚጠረጠሩት ውስጥ በሕግ መጠየቅ ያለባቸው፣ በሌላ በኩል ደግሞ በነፃ መሰናበት የሚገባቸው ታሳሪዎች እንዳሉ ከተለያዩ ጎራዎች ድምፆች ሲስተጋቡ ከርመዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ተቃርኖ ባለበት ጊዜ የፍትሕ ሥርዓቱ በነፃነትና በገለልተኝነት ሥራውን ሲያከናውን በዳይና ተበዳይን መለየት እንደሚያስችል የሚያሳስቡ ድምፆች ይሰማሉ፡፡ ከዚያ በኋላ በሚደረግ ምክክር በሚደረስበት ስምምነት ለምሕረትም ሆነ ለይቅርታ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ውሳኔ ላይ መድረስ እንደሚቻል፣ ሕጉን እያጣቀሱ ከፖለቲካው ጋር ማሰናሰል እንደማያቅትና ለብሔራዊ መግባባት በር ለመክፈት የሚረዳ መደላድል እንደሚፈጠር የሚያሳስቡ ሙግቶች ይሰማሉ፡፡ ብሔራዊ ምክክሩም ቢሆን በተረጋጋ መንፈስ መካሄድ የሚችለው አገራዊ አንድነቱ ግለቱን ጠብቆ ሲሄድ መሆኑን በማስረዳት፣ በመሀል የሚፈጠሩ ንትርኮችና አለመግባባቶች እንቅፋት በመፍጠር ለማይፈለግ ትንቅንቅ ሊዳርጉ እንደሚችሉም ያሳስባሉ፡፡ የአገሪቱ ፈርጀ ብዙ ችግሮች በፖለቲከኞች ዙሪያ ብቻ እንዲታጠሩ ሲደረግ ስህተት መሆኑን፣ ከዚያ ወጣ በማለት የብዙኃኑን ሕዝብ አማካይ ፍላጎት መረዳትና ለመፍትሔያቸው መተባበርን ባህል ማድረግ አስፈላጊነት ላይ ምክረ ሐሳቦች ይቀርባሉ፡፡ ይህ ደግሞ ከመደበኛው ፍትሕ ባሻገር ማኅበራዊ ፍትሕ ለማስፈን ያለውን ጠቀሜታ ያስገነዝባል፡፡

የፖለቲካ ውሳኔና የፍትሕ ውሳኔ መንገዳቸው ለየቅል ቢሆንም፣ ሁለቱንም በሚዛናዊነት ለመመልከት የሚያስችል ርዕዮተ ዓለማዊ ትንተና በሚጎድልበት አገር ውስጥ ውዥንብር የበላይነት መያዙ አይቀሬ ነው፡፡ በዚህ መሀል ግን ሕዝብና አገር ሲጎዱ ጥፋቱ ከባድ ይሆናል፡፡ ፖለቲከኞች ሰላም ሲሆኑ ኮሽታ ሳይሰማ፣ በመሀላቸው ያለው ልዩነት ከፍቶ ጦር ሲማዘዙ ደግሞ ዕልቂትና ውድመት ይከተላል፡፡ አንዱ ሌላውን ሲያስርና ሲፈታ ውሳኔው ፖለቲካዊ ሲሆን፣ የፍትሕ ቦታው የት ነው የሚል ጥያቄ ከየአቅጣጫው መነሳቱ የሚጠበቅ ነው፡፡ ለምላሹም በቅጡ መዘጋጀት ያለበት መንግሥት ነው፡፡ መንግሥት ደግሞ በሕግ በተሰጠው ሥልጣን ግልጽነት፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ በተለያዩ የፖለቲካ ጎራዎች ውስጥ ያሉ ወገኖችም ከፍላጎታቸው መሳካት አኳያ ሳይሆን፣ ፍትሕና የፖለቲካ ውሳኔን ጎን ለጎን ማየት የሚያስችል ወኔ ሊላበሱ ይገባል፡፡ ከአገር በላይ ማንም ሊኖር አይችልም የሚል አቋም ሳይኖር፣ በደመነፍስ የሚደረግ የቃላት ጦርነት ለአገር አይጠቅምም፡፡ ዋናው ቁምነገር ግን ፍትሕ የፖለቲካ ሥርዓቱ መሠረት እንዲሆን ማድረግ መቻል ነው! 

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...

የታመቀ ስሜት!

የዛሬ ጉዞ ከመርካቶ በዮሐንስ ወደ አዲሱ ገበያ ነው፡፡ ታክሲ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት ተፃራሪ ላለመሆን ጥንቃቄ ይደረግ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ድብልቅልቅ ስሜት የሚፈጥሩ በርካታ ሁነቶች ማጋጠማቸው አዲስ ነገር ባይሆንም፣ በዚህ ወቅት ከተለያዩ ፍላጎቶችና ዓላማዎች ጋር የተሸራረቡ ሥጋት ፈጣሪ ችግሮች በብዛት እየተስተዋሉ ነው፡፡...

መንግሥት ቃሉና ተግባሩ ይመጣጠን!

‹‹ሁሉንም ሰው በአንዴ ለማስደሰት ከፈለግህ አይስክሬም ነጋዴ ሁን›› የሚል የተለምዶ አባባል ይታወቃል፡፡ በፖለቲካው መስክ በተለይ ሥልጣነ መንበሩን የጨበጠ ኃይል ለሚያስተዳድረው ሕዝብ ባለበት ኃላፊነት፣ በተቻለ...

ልዩነትን ይዞ ለዘለቄታዊ ሰላምና ጥቅም መተባበር አያቅትም!

መሰንበቻውን በአውሮፓ ታላላቅ ቡድኖች ተጫውተው ያለፉ ዝነኛ የአፍሪካ እግር ኳስ ከዋክብት በኢትዮጵያ ቆይታ አድርገው ነበር፡፡ ዝነኞቹ ንዋንኮ ካኑ፣ ዳንኤል አሞካቺ፣ ታሪቡ ዌስት፣ ካማራና መሰሎቻቸው...