Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናመኢአድ ሁለት አመራሮቹ እንደታሰሩና አንዱ ያለበትን እንደማያውቅ አስታወቀ

መኢአድ ሁለት አመራሮቹ እንደታሰሩና አንዱ ያለበትን እንደማያውቅ አስታወቀ

ቀን:

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ በደቡብ ክልል ኮንሶ ዞን ውስጥ የሚገኙ አመራሮቹ መታሰራቸውንና አንደኛው አመራር ያለበትን እንደማያውቅ አስታወቀ፡፡

ለእስር ተዳርገዋል የተባሉት የፓርቲው የሰገን አካባቢ ወረዳ የማኅበራዊ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ከበደ ኡርጋቸውና የፓርቲው የደራሼ ወረዳ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ገዛኸኝ ሮባዮ ሲሆኑ፣ ከጥቅምት 16 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በእስር ላይ እንደሚገኙ፣ ነገር ግን ክስ እንዳልተመሠረተባቸው የመኢአድ የሸገን አካባቢ ሰብሳሲ አቶ ገልገሎ ኩይሳ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

አቶ በየነ ኩሴ የተባሉት የመኢአድ የሰገን አካባቢ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ኃላፊ ደግሞ ሌሎቹ አመራሮች ከታሰሩበት ጊዜ አንስቶ ያሉበት እንደማይታወቅ ሰብሳቢው አስረድተዋል፡፡ በደራሼ ወረዳ የሚኖሩት የአቶ በየነ ቤተሰቦችም ግለሰቡ ያሉበትን እንደማያውቁ የተናገሩ ሲሆን፣ ‹‹ይሙት፣ ይኑር ያለበትን አናውቅም፣ በስልክም አንገናኝም፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ከበደ በ2013 ዓ.ም. በወረዳው ጋሶ ቀበሌ ተከስቶ በነበረው ግጭት ምክንያት ለአራት ወራት ለእስር ተዳርገው እንደነበር፣ ነገር ግን ‹‹ጥፋተኛ አይደለህም›› ተብለው ነፃ እንደወጡ የተናገሩት ሰብሳቢው፣ አመራሩ እስር ቤት ውስጥ በነበሩበት ጊዜ ቤታቸው እንደተቃጠለና ቤተሰባቸውም ከአካባቢው እንደተሰደዱ ገልጸዋል፡፡ አቶ ከበደ ከእስር ከተፈቱ በኋላ በ2013 ዓ.ም. በነበረው ግጭት ምክንያት፣ ‹‹ቤታቸው የተቃጠለባቸውን ሰዎች ጉዳይ በፍርድ በቤት ስለሚከታተሉ ለእስር ተዳርገዋል፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ገዛኸኝ የተባሉት የፓርቲው የደራሼ ወረዳ ሥራ አስፈጻሚም በተመሳሳይ ቀን ለእስር እንደተዳረጉ አስረድተው፣ በግጭቱ ውስጥ ቤታቸው የተቃጠለባቸውን ሰዎችን ጉዳይ አስመልክቶ ስብሰባ በመጥራት ንግግር በማድረጋቸው ምክንያት ነው የታሰሩት የሚል እምነት እንዳላቸው አቶ ገልገሎ ገልጸዋል፡፡ ሰብሳቢው ለሁለቱ አመራሮች እስር በወረዳው የሚገኙ ሁለት ባለሥልጣናትን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡

‹‹ያሉበት አይታወቅም›› የተባሉት አቶ በየነ ኩሴ ግን እንደ ሌሎቹ አመራሮች በእስር ቤት ውስጥም እንደማይገኙ ማረጋገጣቸውን አስረድተው፣ ‹‹የእኛ ፓርቲ አባላት ያልሆኑ ሌሎች ሰዎችም እንዲሁ ጠፍተዋል፣ ያሉበት አይታወቅም፤›› ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ገልገሎ ገለጻ፣ ፓርቲው የታሰሩበትን አመራሮች ጉዳይ በተመለከተ በተደጋጋሚ ከወረዳው አስተዳደርና ኮማንድ ፖስት ጋር ንግግር ቢያደርግም መፍትሔ ማግኘት አልተቻለም፡፡ ከዚህም ባሻገር ጥር 3 ቀን 2014 ዓ.ም. የታሰሩትን የመኢአድ አመራሮች አስመልክቶ የወረዳውን ዓቃቤ ሕግን ማናገራቸውን ያስታወቁት ሰብሳቢው፣ ዓቃቤ ሕጉ በወረዳው የሚገኙ አንድ ባለሥልጣንን በመጥቀስ የአስተዳደሮቹን ጉዳይ በተመለከተ፣ ‹‹ባለሥልጣኑን ማነጋገር አለብኝ›› የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው አስታውቀዋል፡፡

የደራሼ ወረዳ የፖሊስ አዛዥ ረዳት ኢንስፔክተር ስለሺ ተሻለ በእስር ላይ ናቸው ስለተባሉት የመኢአድ አመራሮችን በተመለከተ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹ሰዎቹ ታስረው ቆይተዋል የሚል እምነት አለኝ፤›› የሚል ምላሽ የሰጡ ሲሆን፣ በተለያዩ ምክንያቶች የታሰሩ ሰዎች በመኖራቸው በስም ለይተው መናገር እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡

‹‹በወረዳው ውስጥ አንዳንድ የፀጥታ ችግሮች አሉብን፤›› ያሉት አዛዡ፣ ከዚህ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር የሚውሉ ሰዎች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በወረዳው መፈናቀልና ሞት እንዳይከሰት ከሕዝቡ ጋር ንግግር በማድረግ ሥራ ተጠምደናል፤›› ብለው፣ ‹‹አሁን ግን ፖሊስ ወደ መደበኛ ሥራዎች እየተመለሰ በመሆኑ በቅርቡ ጉዳዮችን እያየን ምላሽ እንሰጣለን የሚል እምነት አለኝ፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ማንኛውም ዜጋ ያላግባብ መታሰር እንደሌለበት አምናለሁ፤›› ያሉት አዛዡ፣ ሰዎች የፓርቲ አባልነታቸውን ያላግባብ እንደ ሽፋን እየተጠቀሙ ነው የሚል ወቀሳ አቅርበዋል፡፡

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...