Friday, September 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የተለያዩ የመንግሥት ዘርፎች ዳያስፖራውን ይስባሉ ያሏቸውን የኢንቨስትመንት አማራጮች አቀረቡ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ዳያስፖራዎች በተገባላቸው ቃል ተፈጻሚነት ላይ ጥያቄ አንስተዋል

የተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን፣ መንግሥት ያቀረበውን ጥሪ ተቀብለው ወደ አገር ቤት ለመጡ ዳያስፖራዎች፣ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ያበረታታሉ ባሏቸው አማራጮች ላይ ገለጻ አደረጉ፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ያዘጋጀውና ለሦስት ቀናት የሚዘልቀው የዳያስፖራ ኢንቨስትመንት ፎረም ትናንት ማክሰኞ ጥር 3 ቀን 2014 ዓ.ም. በስካይላይት ሆቴል ተጀምሯል፡፡ በፎረሙ ላይ ንግግር ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታ ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር)፣ ዳያስፖራዎች ላከናወኑት የዲፕሎማሲ ሥራ ምሥጋናቸውን አቅርበው፣ ‹‹በፖለቲካው ማሸነፍ የሚቻለው ምጣኔ ሀብቱ ሲዳብር ነው፤›› ብለዋል፡፡ በሌሎች አገሮች ድጎማ ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ እስካለ ድረስ፣ አሁን ኢትዮጵያ ያጋጠማት ዓይነት የውጪ ጫና በሌላ ሁኔታ መቀጠሉ እንደማይቀር የተናገሩት ሬድዋን (አምባሳደር)፣ ዳያስፖራው በፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ያሳየውን ጅምር በኢንቨስትመንትም እንዲያስቀጥል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ከ800 በላይ ዳያስፖራዎች ተገኝተውበታል በተባለው በዚህ ፎረም የጤና፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ፣ የኢንዱስትሪ፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴሮች ለኢንቨስትመንት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ዘርፎች ናቸው ያሏቸውን አማራጮች አቅርበዋል፡፡ የቱሪዝምና የግብር፣ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ደግሞ በሁለተኛ ደረጃ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ዘርፎች ሆነዋል፡፡

የጤናውን ዘርፍ የኢንቨስትመንት አማራጮች ያቀረቡት የጤና ሚኒስትሯ  ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) ከዚህ በፊት በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የበሽታ ሥርጭት በከፍተኛ ደረጃ ይዘውት የቆዩት ተላላፊ በሽታዎች፣ እንዲሁም የእናቶችና የሕፃናት ሞት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገሪቱ ውስጥ ከሚከሰቱት ሞቶች ውስጥ 52 በመቶው የሚከሰቱት ተላላፊ ባልሆኑ በሽዎችና ድንገተኛ አደጋዎች መሆናቸውን ያስረዱ ሲሆን፣ እነዚህን ለማከም ስፔሻላይዝድ ያደረጉ ባለሙያዎችና የሕክምና ማዕከላት እንደሚያስፈልጉ ገልጸዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ሕክምና የሚሰጡ ሆስፒታሎች እጥረት በመኖሩ ምክንያት ኢትጵያውያን ወደ ውጭ ሄደው ለመታከም በየዓመቱ 100 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያወጡ አስታውቀው፣ ዳያስፖራዎች በዚህ ዘርፍ ያለውን ክፍተት እንደ ዕድል በመጠቀም ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡

በጤናው ዘርፍ እንደ መድኃኒትና የሕክምና ቁሳቁሶች ያሉት 85 በመቶ የሚሆኑት ፍላጎቶች ከውጭ የሚገቡ በመሆናቸው፣ ዳያስፖራው በዚህ ዘርፍ ቢያመርት ሰፊ ገበያ እንዳለ ተገልጿል፡፡ የቂሊንጦ ኢንደስትሪያል ፓርክ ለዚህ ዓይነቱ ሥራ እንደተዘጋጀም ሊያ (ዶ/ር) አክለዋል፡፡

በኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምርጫ መሠረት የሎጂስቲክስ ዘርፉ ላይ ትኩረት አድርገው ማብራሪያ የሰጡት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ፣ በዓለም ባንክ ጥናት መሠረት የኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ ዘርፍ ቅልጥፍና ከ160 አገሮች ውስጥ 126ኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ መንግሥት በአሥር ዓመት ውስጥ ይህንን ደረጃ ወደ 40ኛ ለማሻሻል ዕቅድ እንዳለው ጠቁመው፣ ለዚህም ሲባል ዝርዝር ጥናቶች ተደርገው የፖሊሲና የስትራቴጂ ሰነዶች መፅደቃቸውን አስረድተዋል፡፡

ይሁንና በዘርፉ የተያዘውን ዕቅድ ለማስፈጸም ሦስት ትሪሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ የገለጹት ወ/ሮ ዳግማዊት፣ መንግሥት ይህንን ለማሟላት የግል ዘርፉ ላይ ተስፋ መጣሉን ተናግረዋል፡፡ ደረቅና ፈሳሽ ጭነቶች ማመላለስ፣ የደረቅ ወደቦችና የካርጎ ተርሚናሎች ግንባታን የመሳሰሉ ዘርፎች ላይ ዳያስፖራው ቢሳተፍ ካለው ፍላጎት አንፃር እጅግ አዋጭ እንደሆነ ሚኒስትሯ ለዳያስፖራዎች አስረድተዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ለዓመታዊ ጥቅል ምርት ያለው አስተዋጽኦ 6.9 በመቶ መሆኑን ገልጸው፣ ይህ በአፍሪካ ውስጥ አማካይ ከሆነው አሥር በመቶ አነስተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የግብርና ምርቶችን የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋት ላይ መሠራት እንዳለበት አጽንኦት የሰጡት ሚኒስትሩ፣ በተለይ ምግብ ነክና የቁም ከብቶችን ያካተቱ ሥራዎች ላይ መሰማራት ትልቅ ሀብት እንደሚያስገኝ ገልጸዋል፡፡ አራት የተቀናጁ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዳሉም አክለዋል፡፡

የጨርቃ ጨርቅ ዘርፉም በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ዕድገት እያሳየ መሆኑንና አሁንም መንግሥት ትኩረት እያደረገበት እንደሆነ አስረድተው፣ በቆዳ ምርቶች ላይ መሰማራትም አዋጭ መሆኑን አቶ መላኩ ለኢንቨስተሮች ተናግረዋል፡፡

መንግሥት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን ታሳቢ በማድረግ እንደ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ባሉ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች መሥራቱን ያስረዱት ሚኒስትሩ፣ የህዳሴው ግድብና ሌሎች የኃይል ማመንጫዎች እየተገነቡ መሆናቸው ለዘርፉ ትልቅ ሀብት እንደሚሆኑ ገልጸዋል፡፡ ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የተሰጡት ማበረታቻዎች ከሌሎች ዘርፎች የላቁ እንደሆኑም አስታውቀዋል፡፡

የኢንቨስትመንት አማራጮቹን ለዳያስፖራዎች ያቀረቡት የመንግሥት ተቋማት፣ ኢትዮጵያ ያላት መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ አገሪቱ ውስጥ ያለውና ወደ ሥራ መግባት የሚችል የሰው ሀብት ብዛትና በቅርቡ ይጀመራል ተብሎ የሚጠበቀው የአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን ለኢንቨስተሮች እንደ ትልቅ ዕድል አቅርበዋል፡፡ ከዚህ በተጨናሪ በየዘርፉ የተደረጉትን የፖሊስ ማሻሻያዎች የጠቀሱት ተቋማቱ ይሄም ለኢንቨስተሩ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል አስረድተዋል፡፡

በተቋማቱ ገለጻ የተደረገላቸው ዳያስፖራዎች በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ያላቸውን ልምድ በመጥቀስ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ያለው የአሠራር ችግር አሁንም ይቀጥላል የሚል ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ አስተያየት የሰጡት ተሳታፊዎች በየቢሮው ያሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት ‹‹የፖለቲካ ሹመኞች እንጂ ባለሙያዎች›› አይደሉም የሚል ቅሬታ ያቀረቡ ሲሆን፣ አሁንም ቢሆን ‹‹ትክክለኛ›› ሰዎች ለመሾማቸው ጥርጣሬ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

ለዚህ በምሳሌነት የተነሳው የመሬት ጉዳይ ነው፡፡ ለኢንቨስተሮች መሬት የመስጠት ሥልጣን ያለው ካቢኔ እንጂ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን አለመሆኑ፣ ኮሚሽኑ ለኢንቨስተሮች የሚገባውን ቃል ተፈጻሚ ላያደርገው እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

በአገሪቱ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ግጭቶች በተነሱበት ጊዜ ሀብታቸው የወደመባቸው ባለሀብቶች የካሳ ጉዳይን በተመለከተ በመድረኩ ላይ ጥያቄ የተነሳ ሲሆን፣ አሁንም ቢሆን መንግሥት ለኢንቨስተሮች ምን ዓይነት ጥበቃ ሊያደርግ እንዳሰበ ማብራሪያ እንዲሰጥበት ተሳታፊዎች ጠይቀዋል፡፡

ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ የሰጡት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር  ‹‹ትክክለኛ ማነቆ›› መሆኑን፣ ከላይ እስከ ታች ባለው የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያለ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ጉዳዩ አመራሮች ላይ ካለ ‹‹የአቅምና አመለካከት ችግር›› የተነሳ እንደሆነ ገልጸው፣ ችግሩ ተሿሚዎቹ ፖለቲከኛ መሆናቸው ላይ ሳይሆን በአጠቃላይ አሠራሩ ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ዳያስፖራዎች ከኢትዮጵያ ይልቅ የተሻለ ሥርዓት በተዘረጋባቸው አገሮች ውስጥ እንደሚኖሩ ያስታወሱት ሚኒስትሩ፣ ‹‹ያደጉት አገሮች ሥርዓት ወደዚህ እንዲመጣ ልታደርጉልን ይገባል፤›› ሲሉ ለዳያስፖራዎች ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ በተጨማሪም አቶ መላኩ፣ ‹‹መቋቋም ያለባችሁን ነገሮች ሁሉ ተቋቁማችሁ ኢንቨስት እንድታደርጉ እለምናለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ባለፉት አምስት ወራት ውስጥ 1.34 ቢሊዮን ዶላር ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት መገኘቱን ያስታወቁት የኢንቨስትመንት ኮሚሽነሯ ወ/ሮ ሌሊሴ ነሜ፣ በመድረኩ ላይ ከተገኙት 800 ያህል ዳያስፖራዎች ውስጥ ቢያንስ 50 በመቶው ኢንቨስት ያደርጋሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች