Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይና ፕሬዚዳንት ባይደን በድርድር ስለሚደረስበት የተኩስ አቁም ስምምነት ተነጋገሩ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይና ፕሬዚዳንት ባይደን በድርድር ስለሚደረስበት የተኩስ አቁም ስምምነት ተነጋገሩ

ቀን:

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የኢትዮጵያን ወቅታዊ ጉዳዮችና የሁለቱን አገሮች ግንኙነቶች በተመለከተ ባደረጉት የስልክ ውይይት፣ በድርድር ስለሚደረስበት የተኩስ አቁም ስምምነት መነጋገራቸው ተገለጸ፡፡

ሰኞ ጥር 2 ቀን 2014 ዓ.ም. ይፋ የሆነው የዋይት ሐውስ መግለጫ፣ በመንግሥትና በሕወሓት መካከል በድርድር የሚደረስ የተኩስ አቁም ስምምነት በፍጥነት እንዲደረግ መነጋገራቸውንና ይኼም ሊሆን በሚችልበት መንገድ ላይ መወያየታቸውን ይጠቁማል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሁለቱ መሪዎች በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሰብዓዊ ዕርዳታዎች በፍጥነት እንዲደርሱ፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታሰሩ ሰዎችን ጨምሮ ሌሎች የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ማረም በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸው ተገልጿል፡፡

በቅርቡ መንግሥት በተለያዩ ምክንያቶች በእስር ላይ የሚገኙ ተጠርጣሪዎች ክሳቸው ተቋርጦ እንዲፈቱ ማድረጉን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባይደን እንዳደነቁ የተነገረ ሲሆን፣ የንፁኃንን ሕይወት ቀጥፏል የተባለውን የመንግሥት የሰሞኑ የአየር ድብደባን ጨምሮ አሁንም ያልረገበው ግጭት ያሳስበኛል ብለዋል፡፡ ስለሆነም አሜሪካ ከአፍሪካ ኅብረትና ከተለያዩ ቀጣናዊ አጋሮች ጋር በመሆን፣ ኢትዮጵያውያን ግጭቱን ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲፈቱ ለማገዝ ቁርጠኛ እንደሆነችም ተናግረዋል ሲል፣ የነጩ ቤተ መንግሥት መግለጫ ያትታል፡፡ ግጭቱን ለመፍታትም ተጨባጭ የሆነ ለውጥ ማየት ያሻል ማለታቸው በመግለጫው ተካቷል፡፡

በተመሳሳይ ቀን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባይደን ጋር በስልክ ተወያይተዋል ብሎ፣ ሁለቱ መሪዎች በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች፣ የሁለትዮሽ ግንኙነትና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ተነጋግረዋል ብሏል።

መግለጫው አክሎም፣ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ በሰሜናዊው የአገራችን ክፍል የሕግ የበላይነትን የማስከበር ክንውኑ የሚገኝበትን ደረጃ፣ እንዲሁም መንግሥት የሰብዓዊ ዕርዳታ፣ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችና በቅርቡ ነፃ በወጡ አካባቢዎች የሚደረገውን መልሶ የመገንባት ርብርብ አስመልክቶ፣ መንግሥት እያደረገ ያለውን ጥረት ለፕሬዚዳንት ጆሴፍ ባይደን ገልጸዋል፤›› ሲል አትቷል፡፡ መሪዎቹ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከርና በጋራ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመሥራት ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል ብሏል።

በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም. ማብቂያ ገደማ፣ በትግራይ ክልል በሰሜን ዕዝ ላይ የሕወሓት ኃይሎች ጥቃት በመፈጸማቸው፣ የአገር መከላከያ ሠራዊት የተሰነዘረበትን ጥቃት በመመከት መልሶ እንዲያጠቃ ትዕዛዝ መስጠታቸውንና በዚህ ምክንያት የተከሰተውን ጦርነት አስከትሎ የአሜሪካና የኢትዮጵያ ግንኙነት ከሻከረ ቆይቷል፡፡

አሜሪካ የኢትዮጵያ መንግሥትንና ሕወሓትን እኩል አድርጎ በመመልከት ተደራደሩ ማለቷን፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀቦችን ከመጣል ጀምሮ ከአጎዋ የቀረጥ ነፃ ንግድ ተጠቃሚነት ኢትዮጵያን እስከ ማገድ መድረሷን በተደጋጋሚ የተቃወመው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ቅሬታዎቹን በተለያዩ መንገዶች ሲገልጽ ቆይቷል፡፡ ከዚህ ባለፈም የአሜሪካ መንግሥትና በአሜሪካ ይመራል የተባለውን የምዕራቡ ዓለም በመቃወም በተደረጉ የተለያዩ ሠልፎች፣ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አሜሪካ ከኢትዮጵያ ላይ እጇን እንድታነሳ ሲጠይቁም ታይተዋል፡፡

አሜሪካ ከፕሬዚዳንት ባይደን ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ በመሾም፣ በዋናነት የኢትዮጵያን ጉዳይ ስትከታተል የቆየች ሲሆን፣ ፕሬዚዳንቱም ሆኑ ልዩ መልዕክተኛ ተደርገው የተሾሙት ጄፍሪ ፊልትማን ስለኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮችና ኢትዮጵያን ይደግፋሉ ወይም በኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖን ሊያሳድሩ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ አገሮችን ሲያነጋግሩ ቆይተዋል፡፡

ይህም በኢትዮጵያውያንና በመሪዎች ዘንድ ቅሬታን ሲያስነሳ ከርሟል፡፡ የአሁኑ የባይደንና የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የስልክ ውይይት በሁለቱ መሪዎች መካከል የተደረገው የመጀመሪያው ውይይት ሲሆን፣ ይህንን የታዘቡ አስተያየት ሰጪዎች ዕውን አሜሪካ የኢትዮጵያን ችግር መፍታት የምትሻ ከሆነ፣ እንዲህ በቀጥታና በመሪዎች ደረጃ የሚደረግ ውይይትና ምክክርን ምርጫ ልታደርግ ይገባት ነበር ይላሉ፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...