Tuesday, October 3, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮ ቴሌኮም በብሔራዊ መታወቂያ ዋስትና የሞባይል ስልኮችን በዱቤ ሊሸጥ መሆኑን  አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮ ቴሌኮም ስማርት ሞባይል ስልኮችን ለግለሰቦች በዱቤ ለመሸጥ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን፣ ሽያጩንም ብሔራዊ መታወቂያ ሲሰጥ እንደሚጀምር አስታወቀ።

ስማርት የሞባይል ስልኮችን ድርጅቶች ዋስትና ለሚገቡላቸው ሠራተኞች በድርጅታቸው አማካይነት ላለፈው አንድ ዓመት በመሸጥ ላይ መሆኑን፣ እስካሁንም አሥር ሺሕ በላይ ስልኮችን መሸጡን ገልጿል።

ግለሰቦች ዋስትና ሊሆናቸው የሚችል ማስያዣ ማቅረብ ስለማይችሉና በሥራ ላይ ያለው መታወቂያ በቂ መተማመኛ ስለማይሆን፣ አገልግሎቱን ለማቅረብ አስቸጋሪ እንዳደረገውና በድርጅቶች አማካይነት ብቻ ሲሠራ እንደነበር የገለጹት የኢትዮ ቴሌኮም የሽያጭ ክፍል ኃላፊ አቶ መሐመድ ሃጂ ናቸው፡፡ በሚቀጥሉት ዓመታት ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው ብሔራዊ መታወቂያ ይህንን ችግር ይፈታል ብለዋል፡፡

በዚህም መሠረት የዱቤ ሽያጩ ማንኛውም ግለሰብ የብሔራዊ መታወቂያ ከመያዝ በተጨማሪ፣ ብድሩን የመክፈል አቅሙ ተገምግሞ የዱቤ አገልግሎቱን የሚያገኝ መሆኑን ሌላ ተጨማሪ ዋስትና እንደማያስፈልገውም አብራርተዋል።

የዱቤ ሽያጩ ከሞባይል ስልኮች በተጨማሪ የኢንተርኔት፣ የድምፅና የመልዕክት ጥቅል አገልግሎትን የያዘ ሲሆን በየወሩ የሚከፈልና ለሁለት ዓመታት የሚቆይ እንደሚሆን አስረድተዋል።

ሰባት ዓይነት የዱቤ አማራጮች የተዘጋጁ መሆናቸውን፣ ከእነዚህም መካከል ያልተገደበ የኢንተርኔት፣ የድምፅና የመልዕክት አገልግሎትን የያዘ ‹ሃይሴንስ ኤች 30› ሞባይል ስልክ እንደሆነና በየወሩ 2,557 ብር የሚከፈልበት ይሆናል። ሌላው አማራጭ ደግሞ በየወሩ የሚሰጥ ያልተገደበ የድምፅ አገልግሎት፣ 15 ጂቢ ኢንተርኔትና 200 መልዕክቶች የያዘ ሲሆን፣ በየወሩ 2,253 ብር ይከፈልበታል። በየወሩ 1,410 ብር የሚከፈልበት ሦስተኛው አማራጭ ደግሞ ‘ሳምሰንግ ጋላክሲ ኤ10’ ስልክ ሲሆን፣ በየወሩ የሚሰጥ 1,500 ደቂቃ፣ 20 ጂቢ ኢንተርኔትና 100 የመልዕክት አገልግሎቶችን የያዘ ነው።

ኢትዮ ቴሌኮም ስማርት ስልኮቹን ለማቅረብ በአገር ውስጥ ከሚገኙ ሰባት የሞባይል ስልክ አምራች ድርጅቶች ጋር እንደሚሠራ የገለጹት አቶ መሐመድ፣ ቴክኖ ሞባይል፣ ስማድልና ሌጀንድ ስልኮችን ለደንበኞች በዱቤ ሽያጭ እንደሚያቀርብ ጠቁመዋል።

አሁን ከተዘጋጁት ስማርት የሞባይል ስልኮች በተጨማሪ በቀጣይ የደንበኞችን ፍላጎት መሠረት በማድረግ፣ የተለያዩ ዓይነት ስልኮች ለሽያጭ እንደሚቀርቡና የአገልግሎት ክፍያውም ሊሻሻል እንደሚችል አስረድተዋል።

ከ50 ሚሊየን በላይ ደንበኞች ያሉት ኢትዮ ቴሌኮም በ2013 በጀት ዓመት 56 ቢሊዮን ብር ገቢ ያገኘ ሲሆን፣ በ2014 በጀት ዓመት የመጀመርያ ሦስት ወራት ደግሞ ትርፉ 5.9 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች