Wednesday, March 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዲስ አፍሪካ የንግድ ትርዒትና ኮንቬንሽን ማዕከል የመጀመርያ ምዕራፍ ግንባታ 54 በመቶ መጠናቀቁ ተገለጸ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ይጠይቃል የተባለው የአዲስ አፍሪካ የንግድ ትርዒትና ኮንቬንሽን ማዕከል የመጀመርያው ምዕራፍ ግንባታ 54 በመቶ መጠናቀቁ ተገለጸ፡፡  

በኢትዮጵያ ብቸኛው የንግድ ትርዒትና ተያያዥ አገልግሎቶችን ለመስጠት እየተገነባ ያለው ይህ ማዕከል፣ የመጀመርያው ምዕራፍ ግንባታ በጥቅምት ወር 2010 ዓ.ም. የተጀመረ ሲሆን ሰኔ 2012 ዓ.ም. ይጠናቀቃል ተብሎ ነበር፡፡ ሆኖም በተለያዩ ምክንያቶች ዘግይቶ አሁን ላይ የመጀመርያው ምዕራፍ ግንባታ 54 በመቶ አካባቢ ደርሷል፡፡ በ2014 ዓ.ም. መጨረሻ ላይም የመጀመርያው አጠቃላይ ግንባታ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ የማኅበሩ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ጋሻው አባተ ገልጸዋል፡፡ 

በሦስት ምዕራፎች ተከፋፍሎ የሚገነባው ይህ ማዕከል የመጀመርያው ምዕራፍ በቻይናው ‹‹ሲጂሲኦሲ›› በመገንባት ላይ ሲሆን፣ ይህም ከ1.7 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቅ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከአክሲዮን ማኅበሩ የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ የማዕከሉ የመጀመርያ ምዕራፉ ግንባታ ተጠናቅቆ ወደ ሥራ የሚገባበት፣ እንዲሁም የሁለተኛ ምዕራፍ ግንባታ የሚጀምርበት ወቅት ቢሆንም፣ በተያዘው ዕቅድ መሠረት የመጀመርያው ምዕራፍ ግንባታ ማጠናቀቅ አልተቻለም፡፡ ለግንባታው መዘግየት ከአቅም በላይ የሆኑ ጉዳዮች በማጋጠማቸው እንደሆነ የሚያመለክው የተቋሙ መረጃ፣ በተለይ ግንባታው በተጀመረ በሦስተኛው ወር የብር ምንዛሪ ለውጥ በመደረጉ ከኮንትራክተሩ ጋር ሲደረግ በነበረው ድርድር ጊዜ መወሰዱ፣ ከዚያም በኋላ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰትና የግንባታ ዕቃዎች መወደድ በዋናነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው ተብሏል፡፡

ፕሮጀክቱ ለረዥም ጊዜ ሲያጓትቱ የቆዩ ችግሮች በ2013 ዓ.ም. ይፈታሉ በሚል ዕሳቤ በሒሳብ ዓመቱ ቀሪ ግንባታ የማጠናቀቅ ዕቅድ ተይዞ ነበር፡፡

በጀት ዓመቱ የግንባታ ዕቅድ መነሻ ያደረገው የተቋራጩን የሥራ መርሐ ግብር ሲሆን፣ ሥራ ተቋራጩም በተሰጠው ተጨማሪ ጊዜ ማለትም እስከ ነሐሴ 2013 ዓ.ም. ድረስ ግንባታውን አጠናቆ የማስረከብ ውል ገብቶ ነበር፡፡ በዚሁ መሠረት ከማዕከሉ የመጀመርያ ምዕራፍ አጠቃላይ ግንባታ 57 በመቶ የሆነው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ይከናወናል ተብሎ ይጠበቅ ነበር፡፡

ምንም እንኳን ወደ ማዕከሉ ግንባታ ከተሸጋገረ በኋላ ባጋጠሙት ችግሮች ምክንያት ግንባታውን በተያዘለት ጊዜ ማጠናቀቅ ባይችልም ፕሮጀክቱን ዳር ለማድረስ የሚደረገው ጥረት አልተቋረጠም፡፡ በመሆኑም እስካሁን ከ600 ቶን በላይ ስቲል ስትራክቸር ወደ አገር ውስጥ ገብቶ በመገጣጠም ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ሌላ 600 ቶን በመርከብ በመጓጓዝ ላይ ይገኛል፡፡

ቀሪው ሁለት ሚሊዮን ቶን ስቲል ስትራክቸር በመመረት ላይ እንደሚገኝም ተጠቅሷል፡፡     

እንደ አክሲዮን ማኅበሩ አመራሮች ገለጻ፣ ሁለተኛው የአክሲዮን ሽያጭ ሲጀመር ብዙዎች አክሲዮኑን የመግዛት ፍላጎት ይኖራቸዋል፡፡ ይህም በዚህ ዓመት የመጀመርያው ምዕራፍ ግንባታ ስለሚጠናቀቅና ገቢ ማስገኘት የሚጀምር በመሆኑ ነው፡፡ ብዙዎች ጅምር ሥራውን ዓይተው የሚሳቡ በመሆኑ በበለጠ ይሸጣል የሚል እምነት እንዳላቸው አቶ ጋሻው ሳያመለክቱ አላለፉም፡፡

የማዕከሉ አፍሪካዊ ገጽታንም የያዘ በመሆኑ የአፍሪካውያንን የእርስ በርስ የንግድ ልውውጥ ከማሳደግ አኳያ የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሎ ይታመናል፡፡

አሁን የተጀመረውን ሥራ ማጠናቀቅና ቀጣይ ምዕራፎቹን ሥራ ለማስጀመር ተጨማሪ ገንዘብ የማሰባሰብ ሥራ እንደሚቀጥል ታውቋል፡፡ ተቋሙ ከተፈቀደለት የ1.5 ቢሊዮን ብር ካፒታል ውስጥ ከ1.1 ቢሊዮን በላይ ዋጋ ያለውን የአክሲዮን ሽያጭ ያከናወነ በመሆኑ፣ በመጀመርያው ዙር የተፈቀደለት የካፒታል መጠን ቀሪ አክሲዮን በመሸጥ ሁለተኛ ዙር የአክሲዮን ሽያጭ እንደሚጀምር ታውቋል፡፡

የሁለተኛውን ዙር አክሲዮን ሽያጭ በተለየ ሁኔታ ለመሸጥ ዕቅድ እንዳለውና ትልልቅ ኩባንያዎች በተለይ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አክሲዮኖችን እንዲገዙ የሚያስችል ሥራ በመሥራት የሚፈለገውን ካፒታል ለማሰባሰብ መታሰቡንም ከተሰጠው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ይህ ማዕከል ከ20 ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አነሳሽነት የተጠነሰሰ ሲሆን፣ ግንባታውን ለመጀመር ግን ብዙ መንገድ መጓዝ ግድ ብሎታል፡፡

 944 የሚሆኑ ባለአክሲዮኖች ያሉት አክሲዮን ኩባንያው፣ እስካሁን ከተከፈለው 1.1 ቢሊዮን ብር ዋጋ ካላቸው አክሲዮኖች ውስጥ 90 በመቶ የሚሆነውን የአክሲዮኑን ድርሻ የያዙት የአዲስ አበባ አስተዳደርና አሥራ አንድ የሚሆኑ መንግሥታዊና የግል ኩባንያዎች ናቸው፡፡

እንደ መረጃው ከሆነ የዚህ ማዕከል ከፍተኛው ባለድርሻ በመሆን የተመዘገበው አዲስ አበባ አስተዳደር እስካሁን በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ስም 606 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን አክሲዮኖች የገዛ ሲሆን፣ ከዚህ ሌላ በአስተዳደሩ ሥር ያሉ የተለያዩ ተቋማት ስም ደግሞ 85 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን አክሲዮኖች በመግዛት በጥቅሉ ከ690 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን አክሲዮኖች ማለትም 77 በመቶ ድርሻ ያዟል፡፡

 የአክሲዮን ኩባንያው አሥር ሚሊዮንና ከአሥር ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን አክሲዮኖች ከገዙ አሥራ አንድ የሚሆኑ ኩባንያዎች ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን ኩባንያ፣ የመንግሥት ማኅበራዊ ዋስትና፣ ዳሸን ባንክ፣ ወጋገን ባንክና የመሳሰሉት ሲጠቀሱ፣ በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ያቋቋሙት ኢትዮ ሐውስ የተባለ ማኅበር ደግሞ 115 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው አክሲዮኖች በመግዛት ከአዲስ አበባ አስተዳደር ቀጥሎ የአክሲዮን ማኅበሩ ሁለተኛው ከፍተኛ ባለአክሲዮን ለመሆን ችለዋል፡፡ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ደግሞ በገንዘብና በዓይነት አሥር ሚሊዮን ብር አክሲዮን ያለው መሆኑ ታውቋል፡፡

ይህ ማዕከል ኢትዮጵያ ደረጃውን የጠበቀ የንግድ ትርዒት መሠረተ ልማት እንዲኖራት ያስችላል ተብሎ ታምኖበት ወደ ሥራ የገባ ሲሆን፣ በመጀመርያው ምዕራፍ እያንዳንዳቸው ስድስት ሺሕ፣ ስድስት ሺሕ ካሬ ሜትር ስፋት ያላቸው ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ሁለት ሁለገብ የንግድ ትርዒት አዳራሾች ግንባታ ተጠቃሽ ናቸው፡፡  ከዚህም ሌላ ባለአምስት ወለል ሕንፃም በዚሁ በምዕራፉ አንድ ግንባታ ውስጥ የሚጠቃለል ነው፡፡ ይህ ሕንፃ ለተለያዩ የንግድ ሥራዎች የሚውሉ ክፍሎችን የያዘ ነው፡፡ ለባንክ ኢንሹራንሶችና ለሌሎች አገልግሎት የሚውሉ ሌላ ባለአራት ወለል ሕንፃ በዚሁ ምዕራፍ ሥራ ውስጥ ተካትቶ የማጠናቀቂያ ሥራው እየተሠራ ነው፡፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ብሪጅ ሬስቶራንት የሚል መጠሪያ ያለው ትልቅ ምግብ ቤትም በዚሁ የመጀመርው ምዕራፍ ግንባታ ውስጥ ከሚጠቃለሉት ውስጥ የሚጠቀስ ሲሆን፣  አንድ አምፊ ቴአትርም በዚሁ ምዕራፍ አንድ ግንባታ ውስጥ ተካትቶ ሥራው እየተጠናቀቀ ይገኛል ተብሏል፡፡

በሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ ደግሞ ከ80 እስከ 3,500 ሰዎችን ሊይዙ የሚችሉ የተለያዩ አዳራሾችን ያካተቱ ግንባታዎች የሚካሄዱባቸው ሲሆን፣ በሦስተኛው ምዕራፍ ግንባታ የሚጠበቀው አንድ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል እንደሆነ ታውቋል፡፡

ማዕከሉ በአዲስ አበባ ሲኤምሲ አካባቢ ከአዲስ አበባ አስተዳደር በሊዝ በተገኘ ቦታ ላይ እየተገነባ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች