Thursday, May 30, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናባልደራስ በቀጣዩ ወር አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ እንደሚሆን አስታወቀ

ባልደራስ በቀጣዩ ወር አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ እንደሚሆን አስታወቀ

ቀን:

በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ ተደራጅቶ ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ ሲንቀሳቀስ የቆየው ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ)፣ በመጪው የካቲት ወር 2014 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔውን አድርጎ አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ እንደሚሆን አስታወቀ፡፡

የባልደራስ ፕሬዚዳንት አቶ እስክንድር ነጋ፣ የፓርቲው ሕገ ደንብ በየሁለት ዓመቱ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲደረግ የሚያዝ መሆኑን ለሪፖርተር ገልጾ፣ በቀጣዩ ወር በሚካሄደው ጉባዔ ላይ ዋንኛ አጀንዳ የሚሆነው ድርጅቱን አገር አቀፍ ፓርቲ የማድረግ ጉዳይ መሆኑን አስታውቋል፡፡ “እሱን ከጨረስን በኋላ ሥራችንን በአገር አቀፍ ደረጃ እንዳርጋለን፤” ያለው ፕሬዚዳንቱ፣ ‹‹ከዚህ በፊት ተገደን ነበር የአዲስ አበባ ድርጅት የሆንነው፣ አሁን አገር አቀፍ የፖለቲካ ድርጅት ነው የምንሆነው፤›› ሲል የፓርቲውን ዕቅድ አስረድቷል፡፡

አቶ እስክንድር ባልደራስ በካቲት 2012 ዓ.ም. የተመሠረተው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በግንቦት ወር 2012 ዓ.ም. ሊደረግ ቀጠሮ ተይዞ በነበረበት ጊዜ መሆኑን አስታውሶ፣ በወቅቱ በአገር አቀፍ ደረጃ መደራጀት ከሚወስደው ጊዜ አንፃር ምርጫውን ለመሳተፍ ሲባል ፓርቲው በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ እንደተወሰነ ተናግሯል፡፡ ‹‹በጊዜው እንደ አገር አቀፍ ፓርቲ እንመሥርት ብንል ኖሮ ምርጫው ያመልጠን ነበር፤›› ያለው ፕሬዚዳንቱ፣ በዚህም የተነሳ በምርጫው ሙሉ ለሙሉ ካለመሳተፍ ይልቅ በአዲስ አበባ ደረጃ ተመዝግቦ መሳተፍን በአማራጭነት መወሰዱን ገልጿል፡፡

- Advertisement -

ፕሬዚዳንቱ፣ ‹‹የድርጅታችን ፕሮግራም በአዲስ አበባ የቆመ አይደለም፣ አገራዊ አጀንዳን የያዘ ነው፤›› በማለት አስረድቶ፣ ፓርቲው በተለያዩ ክልሎች ያለው የድጋፍ መጠን ከቦታ ቦታ ቢለያይም “በጣም በርካታ ደጋፊዎች አሉን” ብሏል፡፡ ‹‹በጣም በቀላሉ ብዙ አባላት የምናፈራባቸው ክልሎች አሉ፣ ሥራ ደግሞ የሚያስፈልጋቸው ክልሎች አሉ፤›› ያለው አቶ እስክንድር፣ ማኅበረሰቡ ስለባልደራስ ያለው አመለካከት “የተጣመመ” እንዲሆን የተደረገባቸው አካባቢዎች እንዳሉ ጠቁሟል፡፡

ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ በሚል ስያሜ በ2012 ዓ.ም. የተመሠረተው መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ባልደራስ አዳራሽ ከተመሠረተው የአዲስ አበባ ባለ አደራ ምክር ቤት በማደግ ነው፡፡ አቶ እስክንድር፣ ፓርቲው በቀጣዩ ወር በሚያደርገው ጠቅላላ ጉባዔው ላይ “ባልደራስ” የሚለው መጠሪያ ‹‹ይቀየር አይቀየር የሚለው አንዱ የጉባዔው አጀንዳ እንደሚሆን እገምታለሁ፤›› ያለ ሲሆን፣ ‹‹የጉባዔው ውጤት ምን ሊሆን ይችላል›› የሚለውን መናገር እንደሚያዳግተው ገልጿል፡፡

‹‹ስሙ ይቀየር ቢባል አይገርመኝም፣ ስሙ መቀጠል አለበት ቢባልም ደግሞ እረዳለሁ፣ በስሙ ዙሪያ ብዙ መስዋዕትነት ስለተከፈለ፣ ፖለቲካል ካፒታል ስላለው፤›› በማለት ፕሬዚዳንቱ ግላዊ አቋሙን አስታውቋል፡፡

በአዲስ አበባ ደረጃ በብቸኝነት እየተንቀሳቀሰ ያለው ባልደራስ አሁን እንደ ፓርቲ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ባይሆንም፣ በአዲስ አበባ ከተማ ካቤኔ ላይ ጥያቄ እንዳለው አቶ እስክንድር አስረድቷል፡፡ ፓርቲው አሁን ቅድሚያ የሚሰጠው ለወቅታዊ ለአገራዊ ጉዳዮች እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ባልደራስ ጥቅምት 5 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫው ይህንን አቋም ያንፀባረቀ ሲሆን፣ ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ጋር ተያይዞ መንግሥት ወደ ትግራይ ክልል ላለመግባት በወሰደው አቋም ላይ ወቀሳውን አቅርቧል፡፡ ‹‹መንግሥት ‘ምዕራፍ አንድ’ ያለውን ዘመቻ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ሳያረጋግጥ ማቆሙ ትልቅ አደጋ ያዘለ መሆኑን ገምግመናል፤›› በማለት፣ ‹‹ከሕዝብ በሚነሳው ተጨባጭ ሥጋት ዙሪያ በቂ ምላሽ አልሰጠም፤›› በማለትም ተችቷል፡፡ የፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ እስክንደር ነጋ ከ100 እስከ 200 ሺሕ የሚቆጠር ሠራዊት “ኢትዮጵያን ለማፍረስ” ሥጋት መደቀኑን በመጠቆም፣ ‹‹መስመራዊ ውጊያ ማድረግ የሚችለው የሕወሓት ሠራዊት መሰበር አለበት፤›› ብሏል፡፡

መንግሥት የትግራይ ክልልንም ከሕወሓት “ነፃ” የማውጣት ግዴታ እንዳለበት ያስታወቀው አቶ እስክንድር መንግሥት የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት “መረብ ወንዝ” ድረስ እንዲያስከብር ባልደራስ ያለውን ፍላጎት ገልጿል፡፡ በተጨማሪም ፓርቲው የአገሪቱን ‹‹የግዛት አንድነት ጥያቄ ውስጥ የሚከት ማንኛውንም ጉዳይ›› እንደማይቀበል አስታውቋል፡፡ አቶ እስክንድር፣ ‹‹የኢትዮጵያን አንድነት የሚሸረሽር ውሳኔ ለመወሰን መንግሥት መብት የለውም፤›› ብሏል፡፡

ባልደራስ ለአንድ ዓመት ከስድስት ወራት በእስር ላይ የቆዩት አመራሮቹ ታኅሳስ 29 ቀን 2014 ዓ.ም. ከተፈቱ በኋላ በሰጠው የመጀመርያ መግለጫው፣ በተመሳሳይ ቀን ክሳቸው እንዲቋረጥ የተደረጉትን የእነ አቶ ስብሃት ነጋን ክስ መቋረጥ ተቃውሟል፡፡

ባልደራስ በመግለጫው ክሳቸው የተቋረጠላቸውን ግለሰቦች፣ ‹‹የሕወሓት የፖለቲካና የጦርነቱ ዋነኛ ቀያሾች፤›› በማለት የገለጻቸው ሲሆን፣ የእስረኞቹ መፈታት ‹‹የሕግ የበላይነትን የጣሰ ውሳኔ›› ነው ብሏል፡፡ የእስር መቋረጡ፣ ‹‹አገሪቱን ግልጽ ለሆነ አደጋ አጋልጧል›› በማለትም ውሳኔውን እንደማይቀበል ገልጿል፡፡

ባልደራስ አመራሮቹ ከእስር የወጡት “በይቅርታ” ወይም “በምሕረት” አለመሆኑን አስታውቆ፣ አመራሮቹ በእስር በነበሩበት ጊዜ ለመንግሥት ‹‹የይቅርታና የምሕረት ጥያቄ እንደማያቀርቡ›› መግለጻቸውን ገልጿል፡፡ አመራሮቹ ታኅሳስ 29 ቀን 2014 ዓ.ም. ምሽት ላይ ከእስር ሲወጡ ‹‹ፍቺው ድንገተኛና ያልተጠበቀ ነበር›› ያለው ባልደራስ፣ ከፍቺው በፊት ‹‹ቢያንስ ላለፉት አራት ወራት ከመንግሥት ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ምንም ዓይነት የመልዕክት ልውውጥ አልነበረም፤›› ብሏል፡፡

በቅርቡ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው አገራዊ ምክክር ጉዳይ በባልደራስ መግለጫ ላይ የተነሳ ሌላኛው ጉዳይ ሲሆን፣ ፓርቲው ምክክሩን በተመለከተ ሦስት ምክረ ሐሳቦችን አቅርቧል፡፡ ‹‹መንግሥት ሒደቱን ሁሉም ባለድርሻ አካላት በባለቤትነት የሚመሩበት ሁኔታ መፍጠር፤›› እንዳለበት ገልጾ፣ “ከገዥው ፓርቲ ተፅዕኖ ነፃ” መሆን እንዳለበትም አሳስቧል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የምክክር ሒደቱ ላይ ግልጽነት እንዲፈጠር የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በታዛቢነት እንዲጋበዝ ጠይቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት የኬንያው ፕሬዚዳንት ያስተላለፉትን መልዕክት ተመልክተው ባለቤታቸውን በነገር ይዘዋቸዋል]

የኬንያው ፕሬዚዳንት ከሕዝባቸው ለቀረበባቸው ቅሬታ የሰጡትን ምላሽ ሰማህ? እንኳን ምላሻቸውን...

የኢትዮ ኤርትራ ሰሞነኛ ሁኔታና ቀጣናዊ ሥጋቱ

“ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ” የሚል ፖለቲካዊ መፈክር ጎልቶ በሚሰማበት፣...

ኦሮሚያ ባንክ ከተበዳሪ ደንበኞቼ ውስጥ 92 በመቶ የሚሆኑት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ናቸው አለ

ኦሮሚያ ባንክ ለደንበኞቹ ከሰጠው ብድር ውስጥ ለአነስተኛና ለመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች...

ሽቅብና ቁልቁል!

ጉዞ ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ ጀምረናል። ተሳፋሪዎች የዕለት ጉርሳቸውን መሸፈን...