Friday, June 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የድንጋይ ከሰል ከውጭ ማስመጣት በሕግ ሊከለከል ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት ለአገር ውስጥ አውጪዎች የሚደረገውን ክልከላ ሊያነሳ ይችላል ተብሏል

በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የድንጋይ ከሰል ከውጭ ማስገባት በሕግ ሊከለከል መሆኑን መንግሥት አስታወቀ፡፡

በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ አገር በቀል የድንጋይ ከሰል አምራቾች የአገሪቱን ፍላጎት ማሟላት ካልቻሉ ለአገር በቀል አምራቾች የሚደረገውን ከለላ በማንሳት፣ የውጭ አምራቾችን ሊጋብዝ እንደሚችል የማዕድን ሚኒስትሩ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) በማስጠንቀቂያ መልክ ለተመረጡ አገር በቀል ድንጋይ ከሰል አምራቾች አስታውቀዋል፡፡

መንግሥት በተለይ በየዓመቱ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከቻይና፣ ከቱርክ የድንጋይ ከሰል ለማምጣት የሚወጣውን 300 ሚሊዮን ዶላር ለማስቀረት በመወሰኑ፣ ለስምንት የአገር ውስጥ ባለሀብቶች የድንጋይ ከሰል ማውጣት እንዲሁም ማጠብ ፈቃድ ሰጥቷል፡፡ ሐሙስ ጥር 5 ቀን 2014 ዓ.ም. ማዕድን ሚኒስቴር ከ11 ባለሀብቶች ውስጥ በጥንቃቄ ለተመረጡት ከስምንቱ ጋር የተፈራረመ ሲሆን፣ በጥቂት ወራት ውስጥ ማምረት እንዲጀምሩ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል፡፡

በአገሪቱ ያሉት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ወደ ሁለት ሚሊዮን ቶን የድንጋይ ከሰል ፍላጎት ያላቸው ሲሆን፣ በትልልቅ የብረታ ብረት፣ የጨርቃ ጨቅና ሌሎች ፋብሪካዎች በጥቂት ዓመታት ውስጥ ፍላጎቱን 7.5 ሚሊዮን ቶን እንደሚያደርሱት ታውቋል፡፡ ስምንቱ 4.2 ሚሊዮን ቶን በዓመት ማምረት እንደሚችሉና ለዚህም በጥቅሉ 6.1 ቢሊዮን ብር መዋዕለ ንዋይ ያፈሳሉ ተብሏል፡፡

‹‹ስምንቱ በመጀመርያው ዙር የተሰጡ ፈቃዶች ናቸው፡፡ የእነሱን አፈጻጸም ዓይተን በሁለተኛው ዙር ለሌሎች አገር በቀል ባለሀብቶች ሌሎች ፈቃዶችን እንሰጣለን፡፡ የመጀመርያዎቹ ካልተሳኩ ግን ለአገር ውስጥ አምራቾች እያደረግን ያለውን ከለላ አንስተን የውጭ አምራቾች ለመሳብ እንገደዳለን፤›› ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡

ኢትዮጵያ እስካሁን በተጠኑ አካባቢዎች ብቻ ወደ 250 ሚሊዮን ቶን የድንጋይ ከሰል ክምችት ሲኖራት ይህም የጭልጋ፣ የካማሺ፣ የኢሉ ባቦር፣ የጅማና የዳውሮ ቀለበቶችን ተከትሎ የሚገኝ ነው፡፡

‹‹የራሳችን ክምችት እያለን እስከ ዛሬ እንዳንጠቀምበት በበፊቱ መንግሥት ተጋርደን ኖረናል፡፡ የኢትዮጵያ ድንጋይ ከሰልም በቂ ሙቀት አያመነጭም እያሉ ሲነግሩን ቆይተዋል፡፡ ይህንን ሁሉ ለመቀየር ጭላንጭል እያየን ነው፤›› ብለው፣   ‹‹በአጭር ጊዜ የድንጋይ ከሰል፣ ማዳበሪያና ብረታ ብረት በአገር ውስጥ ምርት እንተካለን፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ ዓለም በበካይነት ቀዳሚ የሚባለውን የድንጋይ ከሰል መጠቀም  ለማቆም በሚንደረደርበት ጊዜ፣ ኢትዮጵያ ወደ ሙሉ የድንጋይ ከሰል ኢንዱስትሪ መግባቷ ለአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች የማይዋጥ መሆኑ ይነገራል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች