Wednesday, February 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዳያስፖራዎች በኢንቨስትመንት ጉዳይ ላነሱት የደኅንነት ሥጋት መንግሥት ምላሽ ሰጠ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመንግሥትን ጥሪ ተከትለው ወደ አገር ቤት የተመለሱ ዳያስፖራዎች ኢንቨስትመንትን አስመልክቶ በተለያዩ መድረኮች ላይ ያነሷቸውን የደኅንነት ሥጋቶች በተመለከተ መንግሥት ምላሽ ሰጠ፡፡

በአገሪቱ ኢንቨስት እንዲያደርጉ የተለያዩ አማራጮች ሲቀርብላቸው የቆዩት ዳያስፖራዎች እንቅፋት ይሆናሉ ብለው ካነሷቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ፣ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ግጭቶችን ተከትሎ የሚመጣውን የደኅንነት ሥጋት ነው፡፡ ዳያስፖራዎቹ የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ሞት ተከትሎ በሻሸመኔ ከተማ የደረሰውን ውድመት በማሳያነት ያነሱ ሲሆን፣ መንግሥት ዳያስፖራዎች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ ሲያደርግ ለሚፈጠሩ የደኅንነት ሥጋቶች ምን ዓይነት ጥበቃ ሊያደርግ እንዳሰበ ጠይቀዋል፡፡

ዓርብ ጥር 6 ቀን 2014 ዓ.ም. በተዘጋጀው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍና የዳያስፖራ ትስስር መድረክ ላይ ተገኝተው ለዚህ ሥጋት ምላሽ የሰጡት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል፣ የፀጥታ ችግር ቢኖርም ‹‹እንዳናጋንነው›› ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው የፀጥታ ችግር ሲነሳ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካና ናይጄሪያ ያሉ አገሮች ግምት ውስጥ መግባት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹የወርቅ ጌጥ አድርጋችሁ እንደፈለጋችሁ የምትንቀሳቀሱበት ከተማ አዲስ አበባ እንጂ ናይሮቢ ወይም ዳሬሰላም አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር መንግሥት የደኅንነት ሥጋቶችን ለመቅረፍ ከሚያከናውነው ሥራ ባሻገር የሃይማኖት ተቋማት ያላቸው ሚናም መታሰብ እንዳለበት አስረድተው፣ ማኅበረሰቡ ዝርፊያንና ስርቆትን በተመለከተ ያለው አቋም ሥጋቶችን ለመቅረፍ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ ‹‹አሁን ያሉ የፀጥታ ችግሮች ዕለታዊና መንግሥትና ሕዝብ ተባብረው ሊፈቱ የሚችሏቸው ስለሆኑ፣ ዳያስፖራው በዚህ መረበሽ የለበትም፤››  ብለዋል፡፡

በዳያስፖራዎች የተነሳው ሌላው ችግር የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያለው የሙስና ችግር ሲሆን አቶ መላኩ በትክክል ችግሩ እንዳለ አውስተው፣ ሙስና የመንግሥት ተቋም ውስጥ ብቻ ሳይሆን ሃይማኖት ተቋም ውስጥም ገብቷል ብለዋል፡፡ ይኼንን ችግር ለመቅረፍ ከሰው ንክኪ የራቀ ዲጂታል ሥርዓት መዘርጋትን እንደ መፍትሔ ያቀረቡት ሚኒስትሩ፣ ዳያስፖራው ይኼንን ሥርዓት ለመዘርጋት ማገዝ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ያሉትን አማራጮች ለዳያስፖራዎች ለማቅረብ በተዘጋጀው በዚህ ፕሮግራም ላይ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ በጥጥ፣ በጨርቃ ጨርቅና በአልባሳት ዘርፎች ያሉት አማራጮች ቀርበዋል፡፡ አትዮጵያ ውስጥ በእነዚህ ዘርፎች ለመሰማራት የሚያስችል ሀብት ቢኖርም ዘርፎቹ በሚፈለገው መጠን ማደግ እንዳልቻሉ ተጠቁሟል፡፡

ይኼ ችግር የተፈጠረው በዕውቀትና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጉድለት እንደሆነ የተናገሩት አቶ መላኩ፣ ‹‹እንደ አገር ጤናማ የሆነ የዕድገት አካሄድ ስላልተከተልን የወጪና የገቢ ንግዱ ሊመጣጠን አልቻለም፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡ የንግድ ሚዛኑ ላይ የ15 ቢሊዮን ዶላር ጉድለት እንዳለ ተናግረዋል፡፡ ፍላጎትን መሠረት ያደረገ አቅጣጫ መከተልና ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኙ ዘርፎች ላይ መሰማራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ለዚህም ዳያስፖራው ኢንቨስት እንዲያደርግ ያበረታቱት አቶ መላኩ፣ ዳያስፖራው ከትናንሽና ከመካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ጀምሮ ኢንቨስት እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች