በካሜሩን አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ሐሙስ ጥር 5 ቀን 2014 ዓ.ም. ሁለተኛውን የምድብ ጨዋታ ከአስተናጋጇ ካሜሩን ብሔራዊ ቡድን ጋር ተጫውቷል፡፡ በውጤቱም ካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ ከተጀመረ በተጋጣሚ ቡድን ላይ ብዙ ጎሎችን በማስቆጠር የመጀመርያዋ መሆን የቻለችበት ኢትዮጵያን 4 ለ 1 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፋለች፡፡
ጎል የማስቆጠሩን ቅድሚያ የወሰደው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መሪነቱን ማስቀጠል የቻለው ለአራት ደቂቃ ብቻ መሆኑ፣ በአንድ በኩል የኢትዮጵያ እግር ኳስና ውጤቱ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ያመላከተ እንደሆነ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ብሔራዊ ቡድኑ በአስተናጋጇ ካሜሩን ላይ ቀድሞ ጎል ለማስቆጠር የተንቀሳቀሰበትን የጨዋታ ዓይነት በመጥቀስ፣ ችግሩ የአገሪቱ ተጫዋቾች ያላቸውን አቅምና ክህሎት የዘመኑ እግር ኳስ ከደረሰበት ደረጃ ጋር አጣጥሞ፣ በተለይም ሥልጠናና መሰል የብሔራዊ ቡድን ግንባታዎችን ማስቀጠል የሚችል የሙያተኛ ክፍተት እንደሆነ የሚገልጹ አሉ፡፡
በካሜሩን የሚገኙት አሠልጣኝ ውበቱ አባተና ስብስባቸው ኳስ ተቆጣጥሮ ለመንቀሳቀስ የሚያደርጉበት የጨዋታ መንገድ፣ የኬፕ ቨርዴን 1 ለ 0 ውጤት ጨምሮ በአካል ብቃቱም ሆነ በቴክኒክ ክህሎታቸው ከዋሊያዎቹ ትልቅ ልዩነት ከነበራቸው ከካሜሩን ተጫዋቾች ጋር ያደረጉት ጨዋታ መሠረታዊ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ሰፊ ልዩነት መኖሩ የአደባባይ ሚስጥር እንደሆነ የሚገልጹ የክለብ ሙያተኞች ጭምር አልጠፉም፡፡
ብሔራዊ ቡድኑ ከካሜሩን ጋር በነበረው ጨዋታ በተለይም በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ላይ የተጋጣሚውን እንቅስቃሴ ተቆጣጥሮ ጎል ለማስቆጠር የሞከረበት መንገድ ካልሆነ፣ ኳስ በተቃራኒ ተጫዋቾች እግር ሥር ሲገባ መከተል ስለሚገባው ግብረ መልስ ግን ምን እንደሆነ የመረዳት አቅም እንዳልነበረው፣ የካሜሩን ተጫዋቾች ካስቆጠሯቸው ጎሎች በቀላሉ መረዳት እንደሚቻል ነው ሙያተኞቹ የሚናገሩት፡፡
በእንዲህ መሰሉ ወቅትና ጊዜ ማንነትን ገልጾ ስለብሔራዊ ቡድኑ ድክመቶችና ክፍተቶች መናገር ‹‹የአሠልጣኙን ቦታ ከመፈለግ›› ጋር ተያይዞ ትርጉም ሊኖረው ስለሚችል ማንነታቸውን ከመግለጽ የተቆጠቡት እነዚሁ ሙያተኞች፣ የክለብ አሠልጣኞችና አመራሮች፣ እንዲሁም በአጠቃላይ በእግር ኳሱ ዘርፍ የተሰማሩት ሙያተኞች መማር ካለባቸው በካሜሩን የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሌሎች አገሮች ብሔራዊ ቡድኖች እንቅስቃሴ አንፃር ያላንዳች ‹‹መሸነጋገል›› ደካማና ጠንካራ ጎኖቹን ተመልክቶ ለቀጣዩ ዕርምት መውሰድ ብቻ ሳይሆን፣ አቅዶ መሥራት እንደሚያስፈልግ ያምናሉ፡፡
እንደ ሙያተኞቹ ከሆነ በአሁኑ ወቅት ዓለም ላይ ባለው ተጨባጭ እውነታ የእያንዳንዱ አገር እግር ኳስ፣ እንዲሁም ተጫዋቾቹ ጭምር የሚታወቁበት የጨዋታ ዓይነትና መንገድ ምን እንደሚመስል የሚገለጽበት መለያ እንዳላቸው፣ ይሁንና በዚህ መመዘኛ መሠረት ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ፣ ለብሔራዊ ቡድኑ ግብዓት ተብለው የሚጠቀሱ ክለቦችን ጨምሮ አገራዊ የሆነ የሥልጠና ማኑዋል (ስታንዳርድ) በዋናነት ብሔራዊ ቡድኑ ሊከተለው ስለሚገባው የአጨዋወት መንገድና ዘይቤ በሙያተኞች ደረጃ ሳይቀር ምን መምሰል እንዳለበት መግባባት ላይ አልተደረሰም፡፡
ብሔራዊ ቡድኑ ከሰሞኑ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ያስመዘገበው ውጤትና ለውጤቱ መነሻ የሆነውን የቡድኑን የአጨዋወት ዘይቤ ተከትሎ ከሚደመጡ አሉታዊና አዎንታዊ አስተያየቶችና ትችቶች መካከል፣ ቡድኑ በእንቅስቃሴ ደረጃ ተስፋ ሰጪ እንደሆነ፣ ችግሩ ግን ተጫዋቾቹ በተፈጥሮ ያላቸውን ክህሎት፣ ካላቸው አካላዊ ቁመናና አቅም ጋር ማጣጣም እንዳልተቻለ በተለይም ከሥልጠና ጋር ተያይዞ የሚጠቅሱ በአንድ በኩል፣ በሌላ ወገን ደግሞ በራስ ሜዳ ውስጥ ካልሆነ በተቃራኒ ግብ ክልል ሁለትና ሦስት የኳስ ቅብብል በሌለበት ተጨባጭ እውነታ ውስጥ ሆነን፣ አሁንም ‹‹ኳስ እንችላለን›› በሚሉ ነገሮች እያመለጡ ከመሄዳቸው በፊት፣ እግር ኳስ ምን ይፈልጋል? የሌሎች አገሮች ተሞክሮና መሰል ዘመናዊ እግር ኳስ የሚጠይቀውን ሥራ መሥራት ለነገ ሊባል እንደማይገባ የሚሞግቱ አሉ፡፡
ቡድኑ ከኬፕ ቨርዴ ጋር ካደረገው ጨዋታ በመነሳት ከካሜሩን ጋር ያደረገው ጨዋታ መጠነኛ መሻሻሎች እንደነበሩት የሚናገሩት ሙያተኞቹ፣ እግር ኳስ በተለይም በዚህ ወቅት በእያንዳንዱ ደቂቃና ሰከንድ የማይታመኑ ክስተቶች ዕውን ሆነው የሚታዩበት እንደመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአብዛኛው በራሱ ሜዳና የግብ ክልል የሚከተላቸው የጨዋታ ዘይቤዎች አላስፈላጊ ስለመሆናቸው ጭምር ያስዳሉ፡፡
ክፍተቱ የብሔራዊ ቡድኑ ችግር ብቻ ተደርጎ ሊወሰድ እንደማይገባ የሚናገሩት እነዚሁ ሙያተኞች፣ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ እንደ አገር በጣም ብዙ መሥራት ያለበት ነገር እንዳለ፣ ለዚህ ችግር ዋነኛው ባለድርሻ ደግሞ የአገሪቱ የሊግ ደረጃ፣ ተጫዋቾች፣ አሠልጣኞችና የአመራር አካላት፣ በተለይም ከሙያው ጋር ያላቸው የብቃትና የጥራት ደረጃ ዓይነተኛ ተጠቃሽ እንደሆነ ይታመናል፡፡
ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው በዚህ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ከሚገኙት ተጫዋቾች መካከል ከፋሲል ከተማ እግር ኳስ ክለብና ከኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ የተመረጡ ይጠቀሳሉ፡፡ ሁለቱም ክለቦች በቅርቡ በተደረገው ለአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግና ለአፍሪካ ክለቦች ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳታፊ የነበሩ መሆናቸው ነው፡፡ ይሁንና ፋሲልም ሆነ ኢትዮጵያ ቡና ከአኅጉራዊ የክለቦች ፉክክር ውጪ የሆኑት በመጀመርያው የደርሶ መልስ ጨዋታ መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ስለመሆኑ ማስታወስ ተገቢ ይሆናል፡፡ ይህ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምን ዓይነት መሠረት ላይ የተገነባ ቡድን ስለመሆኑ ጭምር የሚናገሩ አሉ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከኬፕ ቨርዴ ጋርም ሆነ ከካሜሩን ጋር ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ‹‹መሻሻሎችን ተመልክተናል›› የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች አሉ፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹ ከሚያነሷቸው መከራከሪያዎች መካከል፣ ብሔራዊ ቡድኑ ከበረኛ እስከ አጥቂ የአጭር ኳስ ቅብብልና በረዥም የሚጣሉ ኳሶችን በመቋቋም ደረጃ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎችን እንደተመለከቱ ይናገራሉ፡፡ ቢሻሻሉ የሚሏቸው ደግሞ የዳኞችን ውሳኔ አለማክበር፣ የረዥም ኳስ ቅብብል አናሳ መሆን፣ ፍራቻና አለመረጋጋት እንዲሁም ከመደበኛ ጨዋታ ውጪ የሌሎች ቡድኖችን የጨዋታ ቅጂ ተመልክቶ ልምምድና ሥልጠና አለመውሰድ የሚሉትና ሌሎችንም ይጠቅሳሉ፡፡
በዚህ መልክ እያከራከረ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፣ በካሜሩን ቆይታው ብዙ ጎሎችን ከጨዋታ ብልጫ ጋር እያስተናገደ ቢሆንም የዚያኑ ያህል ተቺዎችም ሆነ አድናቂዎች አላጣም፡፡ ተቺዎቹ፣ ‹‹የካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ በግልጽ ያመላከተ ነው፤›› ሲሉ እንቅስቃሴውን በአዎንታዊ ጎኑ የሚመለከቱት ደግሞ፣ ሙሉ ዘጠና ደቂቃና ከዚያም በላይ በጀመረው እንቅስቃሴ መቀጠል የማይችለው የኢትዮጵያ እግር ኳስ እንዲሁም የተጫዋቾች የአካል ብቃት ዝግጁነትና የጨዋታ ትኩረት ማነስ ካልሆነ በእንቅስቃሴ ደረጃ ሊያድግ የሚችል ስለመሆኑ ነው የሚናገሩት፡፡
በሌላ በኩል አሁን ያለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንና የክለቦች መዋቅራዊ ይዘት ባለበት፣ ብሔራዊ ቡድኑ የተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ አገር አሠልጣኞች ተቀያይረው ሲያሠለጥኑት ቆይቷል፡፡ በውጤት ደረጃ ክለቦችን ጨምሮ ብሔራዊ ቡድኑ ባደረጋቸው የተለያዩ ጨዋታዎች ይህ ነው የሚባል ሊጠቀስ የሚችል ውጤት እንዳልተመዘገበ ይታመናል፡፡
አንዳንዶች በዚህ ዓይነቱ ገጽታ እየታመሰ የሚገኘውን እግር ኳስና ብሔራዊ ቡድን፣ ከድክመቱ ይልቅ ጥንካሬውን በማጉላት፣ ብሔራዊ ቡድኑ ዕምቅ አቅሙን የመጠቀም ክህሎት ክፍተት ካልሆነ፣ ከማይጠቅሙ እንቅስቃሴዎች ርቆ በኅብረትና በመናበብ መሥራትና መንቀሳቀስ ከቻለ ማድረግ የሚፈልገውን ማሳካት እንደሚችል በካሜሩን ምድር በተግባር ለሚሊዮኖች እንዳረጋገጠ ሲናገሩ በመደመጥ ላይ ናቸው፡፡
በሌላ ወገን ካሜሩናውያን እንደ ብሔራዊ ጀግናቸው የሚመለከቱት አንጋፋውና የማይበገሩት አንበሶች አምበል የሆነው ቪሴንት አቡበከርና ጓደኞቹ፣ በጥንካሬው የተጠቀሰውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንቅስቃሴና የጨዋታ ዘይቤ ለመረዳት ብዙም እንዳልተቸገሩ በርካታ ማሳያዎች መጠቀስ እንደሚቻል የሚናገሩ አሉ፡፡ ከእነዚህ ማሳያዎች መካከል የማይበገሩት አንበሶች በዋሊያዎቹ ላይ ያስቆጠሩትን አራት ጎልና ለጎል የቀረቡ በርካታ ሙከራዎችን ከመመልከት የተሻለ ማረጋገጫ ሊኖር እንደማይችል በመጥቀስ ይከራከራሉ፡፡
በኬፕ ቨርዴና በካሜሩን የተሸነፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የምድቡን የመጨረሻ ጨዋታ ሰኞ ጥር 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ከቡርኪና ፋሶ ጋር በሌላዋ የካሜሩን ከተማ ባፎሳም ኩኮንግ ስታዲየም የሚጫወት ይሆናል፡፡ ከምድቡ ካሜሩን ቡርኪና ፋሶንና ኢትዮጵያን በማሸነፏ በስድስት ነጥብ ከምድቡ ቀድማ ማለፍ ችላለች፡፡ ቀሪ ጨዋታዋ ሦስት ነጥብ ካላት ከኬፕ ቨርዴ ጋር ይሆናል፡፡ ከምድቡ ምንም ነጥብ የሌላት ኢትዮጵያ ኬፕ ቨርዴን 1 ለ 0 በሆነ ውጤት ያሸነፈችው ቡርኪና ፋሶን ስትገጥም፣ በጥሩ ሦስተኛነት የማለፍ ዕድሏ በሒሳብ ሥሌት 4 ለ 0 ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን፣ ነጥቧ በሌላው ምድብ የሚገኙ ቡድኖች ውጤት ላይ የሚወሰን እንደሚሆን ጭምር ይጠበቃል፡፡