Friday, March 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

የአንድ ሰሞን መነጋገሪያ የሆነ አንድ አስደሳች መጽሐፍ ዛሬ እኔ በገጠመኝ የማነሳላችሁን ጉዳይ በሚገርም ሁኔታ እንዳቀረበው አስታውሳለሁ፡፡ የቋንቋ ጉዳይን በተመለከተ አገራችን ወደ የት እየተጓዘች መሆኑን ጥሩ ማሳያ ነበር፡፡ በአንድ ታዋቂ ሰው ሕፃናት ልጆች መነሻነት የመምህራንን ገጠመኝ እየተረከ፣ በተለይ በጣም ውድ በሆኑ የግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ የአገሪቱ የሥራ ቋንቋ የሆነው አማርኛ እንዴት ገደብ እንደተጣለበት በውብ አገላለጽ ያለውን አስፈሪ ሁኔታ አስፍሮታል፡፡ የአገሪቱ የሥራ ቋንቋ ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ይዞ በይፋ በሚነገርበት አገር ውስጥ ለራሳቸው ሌላ ዓለም የፈጠሩ ግን ተቀባይነት እንዳሳጡት ብዙ ተብሎበታል፡፡

ሰሞኑን አጋጣሚ ያገናኝ የኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች ጉዳይ ቢያሳስበኝ ነው የዛሬውን ገጠመኜን የምነግራችሁ፡፡ ለረጅም ጊዜ በአካል አግኝቼአቸው የማላውቅ የሩቅ ዘመዶቼ ዘንድ በአገር ጥሪ መሠረት ከካናዳ ከመጣ አንድ ዘመዴ ጋር ሄድን፡፡ ገና ግቢው ውስጥ ስንገባ ውጭ አገር የሄድኩ ነው የመሰለኝ፡፡ የምሰማቸው ንግግሮች በሙሉ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚቀላጠፉ ናቸው፡፡ ከአዋቂ እስከ ሕፃን ቤቱ ውስጥ ከእንግሊዝኛ ቋንቋ ውጪ መነጋገር ‹‹ክልክል›› ነው የተባለ ይመስል የአገሪቱን ቋንቋ ረስተዋል፡፡ በጣም ግር እያለኝ ከእንግዳው ዘመዴ ጋር ተቀመጥኩ፡፡ ባልና ሚስት ከውስጠኛው ክፍል መጥተው ሲያነጋግሩን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ነው የሚጠቀሙት፡፡ ልጆቹ በሙሉ ያናገሩን በእንግሊዝኛ ነው፡፡ ሰላምታ ስንለዋወጥ እኔ በተደጋጋሚ በአማርኛ ሳናግራቸው ከቁብ አልቆጠሩኝም፡፡ ይኼኔ በሆዳቸው ‹‹ይኼ ሰው ያመዋል እንዴ?›› ሳይሉ የቀሩ አይመስለኝም፡፡

ከአሜሪካ የመጣው ዘመዴ ነገሩ ክንክን አድርጎት ነው መሰለኝ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ሆናችሁ እንዴት መግባቢያችሁን በውጭ ቋንቋ ታደርጉታላችሁ?›› ብሎ ለአባወራው በአማርኛ ጥያቄ ሲያቀርብለት፣ አባወራው ዘና እያለ ‹‹ዌል…›› እያለ ሲጀምር፣ ሚስትየው በመገረም እየተመለከተችን፣ ‹‹ሶሪ ኢት ኢዝ ኤ ማተር ኦፍ ቾይስ…›› ብላ መለሰችልን፡፡ ‹‹የምርጫ ጉዳይ ነው›› ማለቷ ነው፡፡ የሚመረጥ ነገር አለማወቅ በጣም ያናድዳል፡፡ እንደምንም ብለን እየቀፈፈን በጉራማይሌ ስናወራ ቆይተን ሊቀርብልን የተዘጋጀውን ምሳ ሳንታደም ምክንያት ፈጥረን ‹‹ከሐበሾቹ ፈረንጆች›› ቤት ወጣን፡፡ ሸሸን ማለት ይሻል ነበር፡፡ በበኩሌ ሰዎቹ ‹‹ሥልጣኔ›› ብለው የያዙት ነገር የማንነት ቀውስ ስለመሰለኝ ውስጤ በንዴት ታውኳል፡፡ ዘመዴ ደግሞ አሁንም አሁንም ‹‹ወቸ ጉድ›› እያለ ወደ ጉዳያችን ሄድን፡፡

የገና በዓል ድግስ የተደገሰበት ዘመድ ተብዬዎች ቤት ስንሄድ እድምተኞቹ ቁጥራቸው ከ30 አይበልጥም፡፡ ግማሽ በግማሽ ወላጆችና ልጆች የተጠሩበት የቤተ ዘመዳሞች ድግስ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከተለመደው ድግሳችን ወጣ ብሎ ‹‹ባርቢኪዩ›› ለተሰኘው ድግስ፣ በአንድ ታዋቂ ዲጄ አማካይነት አልፎ አልፎ ከሚሰማው ትኩረት የተነፈገው ባህላዊ የሠርግ ዘፈን ውጪ የፈረንጅ ፓርቲ መስሏል፡፡ ራፕና ሂፕ ሆፕ መደለቂያ ሆነዋል፡፡ ከጥግ እስከ ጥግ አዋቂዎቹም ሆኑ ወላጆች የሚነጋገሩት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ነው፡፡ እንግዳው ወዳጄ በብሽቀት ውስጡ ሲነድና ጉንጩ ሲቀላ ይታየኛል፡፡

ወደ ጆሮዬ ጠጋ ብሎ፣ ‹‹ፊታችንን ካስመታን ይበቃናልና ከዚህ ጉድ ውስጥ ወጥተን እንሂድ፤›› አለኝ፡፡ በሐሳቡ ተስማምቼ ማንም ሳያየን ሹልክ ብለን ወጣን፡፡ ደጅ ከወጣን በኋላ እንግዳው ዘመዴ በረጅሙ ተንፍሶ ‹‹ግልግል›› እያለኝ የተከራየነውን መኪና አስነስተን ከአካባቢው ጠፋን፡፡ ከኒውዮርኩ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስ ዲግሪውን አግኝቶ በጥሩ ሁኔታ አሜሪካ ውስጥ የሚኖረው ዘመዴ፣ ባያቸው የተመሰቃቀሉ ነገሮች ከልቡ አዝኗል፡፡ አብዛኛውን ሕዝብ በእንግዳ ተቀባይነቱና ለአገሩ ባለው ፍቅር የወደደው ወዳጄ፣ በሞልቃቃ ዘመድ ተብዬዎቹ ድርጊት በግኗል ማለት ይቻላል፡፡

‹‹በቀጥታ ብዙ ሕዝብ የሚዝናናበት ድራፍት ቤት ውሰደኝና እያወራሁ ድራፍት ልጠጣበት፤›› ሲለኝ ስሜቱ ገባኝ፡፡ ሰፊው ሕዝብ ናፍቆኛል ማለቱ ነው፡፡ ስታዲዮም ዙሪያ ካለው የሰፊው ሕዝብ ባህር ውስጥ ስከተው በደስታ እቅፍ አድርጎ ሳመኝ፡፡ አስተናጋጁን ጠርተን በጃንቦ ድራፍት ስናዝ ወዲያውኑ በካሽ ሁለት መቶ ቦኖዎችን ገዝቶ፣ ‹‹እንኳን ለገና በዓል በሰላም አደረሳችሁ…›› እያለ አካባቢያችን ለነበሩ ሰዎች ቦኖ እየዘገነ አደላቸው፡፡ ዙሪያችን ከነበሩ ሰዎች ጋር የጦፈ ወሬ ጀምረን በገዛ ቋንቋችን እየቀለድን ስንጫወት አመሸን፡፡ አቤት ደስ ሲል፡፡ ሲመሽ በፍቅር ከሰዎቹ ጋር ተሰነባብተን ተለያየን፡፡ ይህ ዘመዴ እጅግ ከመደሰቱ የተነሳ ሁሉንም እያቀፈ ነበር የተሰነባበተው፡፡

ከመሸ በኋላ ቤት ደርሰን ስለዘመድ ተብዬዎቹ ገጠመኞቻችን እያነሳ እንዲህ አለኝ፡፡ ‹‹ማንነቱን የማያውቅ ሰው ራዕይ የለውም፡፡ የማንነት ቀውስ ውስጥ ገብተው በባዕድ ቋንቋ የሚግባቡ ዘለቄታቸው አያምርም፤›› ብሎኝ፣ ‹‹በጣም ይገርምሃል ነጋዴው፣ ፖለቲከኛው፣ ጊዜ ያነሳውና እንዳቅሚቲው ሁሉ ሕፃናቱን የተከበረውን ኢትዮጵያዊ ማንነት እያሳጡዋቸው ናቸው፡፡ በገዛ ባህላቸውና ቋንቋቸው እንደ ህንዶች፣ ቻይናዎች፣ ጃፓኖችና ኮሪያውያን ወደ ሥልጣኔ ከመውሰድ ይልቅ ቅኝ ግዛት ባልተገዛች አገር ውስጥ የቅኝ ግዛት መንፈስ እየፈጠሩ ነው…›› እያለ ተብከነከነ፡፡

‹‹ከሁሉም ነገር በላይ በጣም ምን እንዳናደደኝ ታውቃለህ?›› ብሎ ጠየቀኝ፡፡ እኔም ውስጤ ጥሩ ስላልነበር፣ ‹‹ከዚህ በላይ ምን አናዶህ ይሆን?›› አልኩት፡፡ ‹‹በአንድ የግል ትምህርት ቤት ውስጥ ‘በአማርኛ ቋንቋ መናገርና ድንጋይ መወራወር ክልክል ነው’ ተብሎ ማስታወቂያ ይለጠፍ እንደነበረ ሰምተሃል?›› ሲለኝ አንቀጠቀጠኝ፡፡ ይኼ የዕውቀት መገብያ ትምህርት ቤት ነው? ወይስ የቅኝ አገዛዝ ማሠልጠኛ ጣቢያ ነው? አገር ያለው ሰው በማንነቱና በታሪኩ ይኮራል እንጂ፣ ለዘመናት የበሰበሰ የቅኝ አገዛዝ መንፈስ መላበስ ዕብደት ነው፡፡ ከአሜሪካ የመጣው ዘመዴ፣ ‹‹ወንድሜ እኔ በዘመዶቼ ባፍርም በኢትዮጵያውያን ወጣቶች ኩራትና የአገር ፍቅር ተፅናንቻለሁ…›› ሲለኝ፣ መፅናኛ በማግኘቱ ደስ ብሎኝ የጥምቀት በዓልን በተስፋ እየተጠባበቅን ነው፡፡

(ዮናታን ገብረ ማርያም፣ ከሳር ቤት)  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...