በዋካንዳ ኢትዮጵያ
የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ፈጣንና ሚስጥራዊ ከመሆኑ የተነሳ፣ ዱብ ዕዳ ዕርምጃዎችን በመውሰድና የሕዝብን ጆሮ ጭው የሚያደርጉ መረጃዎችን በመልቀቅ ይታወቃል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ሰሞኑን በእነ እስክንድር ነጋ በእነ ጃዋር መሐመድ፣ እንዲሁም በስድስት የሕወሓት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ የነበሩትን ክሶች ማቋረጡን ለኢትዮጵያ ሕዝብ በሰበር ዜና ያስታወቀው ድርጊት ነው፡፡
ይህ ሰበር ዜና ድንጋጤን የፈጠረው በሁለት ሳምንታት ያሸነፍናቸው ጠላቶቻችን ምን ኃይል አግኝተው ነው መንግሥት እንዲህ ድንገተኛ ውሳኔ ለመወሰን ያስገደደው በሚል ይመስለኛል:: በተለይ ደግሞ በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የመንግሥትን ጥሪ ተቀብለው በአገሪቱ ውስጥ በሙሉ ኃይላቸው ጉልህ ተሳትፎ እያደረጉ ባሉበት ወቅትና የተለያዩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በመገናኛ ብዙኃን በመቅረብ ከሕወሓት ጋር ድርድር አይታሰብም ባሉበት ‹‹ማግሥት›› መሆኑ፣ ጉዳዩ ድንጋጤ ብቻ ሳይሆን ቁጣም አስከትሏል፡፡
ይህ ጉዳይ ትልቅ የአገር ጉዳይ ነውና ኢትዮጵያውያን ሁሉ እየተነጋገሩበት ይገኛሉ፡፡ እኔም ጉዳዩን ከሰማሁበት ጊዜ ጀምሮ በግሌም ሆነ ከወዳጆቼም ጋር በመሆን ማብሰልሰሌ አልቀረም፡፡ በተለይ ደግሞ በሁለት የአገራችን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ማብራሪያ ተሰጥቶ ውሳኔያችን ለኢትዮጵያ ጠቃሚ ነውና እባካችሁ ተቀበሉልን የሚል የአክብሮት መማፀኛ ከቀረበልን በኋላ፣ ለምን ሙሉ ለሙሉ መርካት አቃተን የሚለው ጥያቄ ትኩረቴን ስለሳበው በ2010 ዓ.ም. የታወጀውን የምሕረት አዋጅና በ2008 ዓ.ም. የዓቃቤ ሕግን ሥልጣንና ኃላፊነት ለመወሰን የወጣውን አዋጅ ሳነብ፣ በመንግሥትና በተራው ሕዝብ መካከል ‹‹ምሕረት›› የሚለው ቃል ፍቺውና ጽንሰ ሐሳቡ የተለያዩ መሆናቸውን አስተውያለሁ፡፡
እርግጥ ነው የፍትሕ ሚኒስት ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ምሕረትም ይቅርታም አላደረግንም የሆነው ክስ መቋረጥ ነው ቢሉም፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ማብራሪያ ግን ክስ ማቋረጥና ምሕረት ተደባልቀዋል፡፡ ክስ ማቋረጥ፣ ምሕረትና ይቅርታ ልዩነት ቢኖራቸውም በፍትሕ ሚኒስትሩ የተሰጡት ፍቺዎችና አሠራሮች ለባለሙያ ይጠቅማሉ እንጂ፣ በተራው ሕዝብ ዘንድ የጎላ ልዩነት የላቸውም፡፡ ምክንያቱም እውነታው የወንጀል ተጠርጣሪዎች ለጊዜውም ይሁን በቋሚነት ከእስር ተፈተው በተከሰሱባቸው ወንጀሎች አሁን አይጠየቁም፡፡
‹‹ምሕረት›› የሕግ ብቻ ሳይሆን የሃይማኖት ቃል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ ሃይማኖተኛ ነውና ከሃይማኖቱ የወረሰው ፍቺ አለው፡፡ ለነገሩ ‹‹የቃል ትርጉም የሚገኘው በማኅበረሰቡ ውስጥ ነው›› ይባል የለ፡፡ በተጨማሪም የምሕረት ትርጉም በግዕዙ ግስ መቅጣትን ከማቅናት ጋር ያስተካክላል፡፡
መንግሥት ‹‹ምሕረት›› ሲል የእንግሊዝኛ አቻው ‹‹Amnesty›› ሲሆን እንደ እኔ ያለው ተራው ሕዝብ ‹‹ምሕረት›› ሲል የእንግሊዝኛ አቻው ‹‹Mercy›› ነው፡፡ ከእንግሊዝኛው ልዩነት ባሻገር መንግሥትና ሕዝብ በቃሉ አጠቃቀም ላይ መሠረታዊ ልዩነት አላቸው፡፡ መንግሥት ‹‹ምሕረት›› አደረግሁ ሲል ወንጀለኛው በጥፋቱ መፀፀቱንና ከጥፋቱ መመለሱን ማረጋገጫ ኖሮት ሳይሆን፣ የግለሰቡ መፈታት ለአገር ጥቅም አለው በሚል መነሻ ነው፡፡ እንዲያውም የመንግሥትን የሞራል ልቀትን የሚያጎላ ነው፡፡ በሕዝብ አረዳድ ግን ከምሕረት በፊት ፀፀትና ንስሐ አሉ፡፡
ስለዚህ ወንጀለኛ በመንግሥት ምሕረት ተደረገለት ሲባል ሕዝብ ወንጀል ከሠራው ግለሰብ በጥፋቱ መፀፀቱንና ሁለተኛ አይለምደኝም ማለቱን ይጠብቃል:: የሕዝብ ሥጋት ምንጩ ለምሕረት ካለው መረዳት አንፃር ስለሆነ ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር የተፈቱት ግለሰቦች እንደገና በሕዝብ ላይ ፍጅትና በደል ላለማድረሳቸው ምን ዋስትና አለ ነው፡፡ ተፀፅተዋል? ሁለተኛ እንደ በፊቱ አናደርግም ብለዋል? ፈጣሪ እንኳን ምሕረት የሚያደርገው በፍፁም ልባቸው ለተፀፀቱ ነው፡፡
ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ አዎንታዊ ምላሽ ካልተገኘ በስንት ፀሎትና እግዚኦታ፣ በስንት መስዋዕትነት የተገላገልናቸው ሰዎች ተመልሰው በመካከላችን መከሰታቸው ምቾት አይሰጥም፡፡ መንግሥት ከፈጣሪ በላይ ርኅራሔ ያሳየ መስሎ ታይቶኛል፡፡
ሌላው ያለ መግባባቱ መንስዔ መንግሥት ክሱን ያቋረጠው በዳዮችን ነፃ ለማውጣት እንጂ፣ ተበዳዮችን ከግምት ውስጥ ሳያስገባ በመሆኑ ነው፡፡ ለውጡ በተጀመረበት ወቅት መንግሥት የብዙ ሰዎችን ክስ አቋርጧል፣ የምሕረት አዋጅ አውጥቶ ምሕረት አድርጓል፡፡ በዚያን ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝብ ደስ አለው እንጂ አልከፋውም፣ አልተቆጣም፡፡ ምክንያቱም በዚያን ጊዜ ከእስር የተፈቱትና ወደ አገር ቤት የገቡት ተበዳዮች ስለሆኑ፣ መንግሥት ደግሞ በዳይ ስለነበር ነው፡፡ የመንግሥት ዕርምጃ በሕዝብ ላይ በሠራው በደል መፀፀቱን ማሳያ ነበር፡፡
የአሁኑ ግን የተለየ ነው፡፡ አሁን ከእስር የተለቀቁት ግለሰቦች በዳዮች ናቸው፡፡ ለዚያውም ሕዝብን፡፡ በሕዝብ የምሕረት ጽንሰ ሐሳብ አረዳድ መሠረት ምሕረት የሚያደርገው የተበደለው አካል ነው፡፡ በሃይማኖቶቻችን ምሕረት አድራጊው የበደልነው ፈጣሪ ነውና፡፡ ፈጣሪ ምሕረት ሲያደርግ ወዶና የአጥፊውን ዕዳ ራሱ ችሎ ነው፡፡ መንግሥት የወንጀለኞችን ክስ ሲያቋርጥ ለተበደሉት ምን አስቧል? የተበደሉትን ማማከር ለምን አልቻለም? በተበደሉት ስም ምሕረት ማድረግ ይችላል ወይ? ለእነዚህና መሰል ጥያቄዎች መልስ ስላልተሰጠ ቁጣ ብቻ ሳይሆን፣ ሐዘንም በሕዝብ ልብ ውስጥ እየፈሰሰ ነው፡፡
እነዚህን የአረዳድ መዛባቶች ተገንዝበን ማስተካከያ ብናደርግ ወይም በሚቀጥሉት ውሳኔዎች ከግምት ውስጥ ቢገቡ፣ በመንግሥትና ሕዝብ መካከል የሚፈጠሩትን ክፍተቶች ማጥበብ ይቻላል የሚል አስተያየት አለኝ፡፡ ሕዝብ በመንግሥት ውሳኔ ላይ እምነትን በመጣል ከቁጣና ቁጭት ይልቅ ድጋፉን ይቀጥላል፡፡ ውስብስብ ችግሮችና ግጭቶች ባሉባት አገራችን ኢትዮጵያ መንግሥት የባለሙያ ቃላት ትርጉምን ብቻ ሳይሆን፣ በሕዝቡ ውስጥ ያለውን ፍቺ ተረድቶ ጥያቄውን ለመመለስ ጥረት ቢያደርግ ጥቅም እንጂ ጉዳት አይኖረውም፡፡
የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን (ዶ/ር) ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት በአገራችን ኢትዮጵያ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት በመደበኛ የፍትሕ ሥርዓት ስለማይቻል፣ ‹‹የሽግግርና የተሃድሶ ፍትሕ›› ሥርዓትን እንከተላለን ብለው ነበር፡፡ እንግዲህ በዚህ ሒደት ውስጥ የተበደሉት በቂ ውክልና እንዲያገኙ፣ ድምፃቸው እንዲሰማ፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉትን እሴቶችና ጽንሰ ሐሳቦች ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ፍትሕ፣ ምሕረት፣ ይቅርታና የመሳሰሉትን ቃላት ‹‹ሕዝባዊ ትርጉም›› በመስጠት፣ በአገራችን ዘላቂ ሰላምና ዕድገት የሚመጣበት ጊዜ ቅርብ እንዲሆን ምኞቴም የዘወትር ፀሎቴም ነው፡፡
በመጨረሻም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ማብራሪያና ተማፅኖ ያቀረቡት፣ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በተደረገው ግጭት የመጀመርያው ሰለባ በሆኑትና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር ከሌሎች የአገራችን የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን መስዋዕትነት በከፈሉና እየከፈሉ ባሉ ከፍተኛ፣ መካከለኛና ዝቅተኛ የጦር መኮንኖች፣ ውዶቻቸውን በሞት በተነጠቁ ቤተሰቦችና ወታደሮች፣ የአገሪቱና የክልሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የውጭ አገሮች ተወካዮች በተገኙበት ፊት ቆመው ነው፡፡
የእዚህን አንድምታ ግምት ውስጥ በማስገባት፣ በጭንቅ መልሰን ያገኘነውን አንድነታችንን በሚያፈርስ መንገድ ትናንት ለአገራችን አንድነት የቆመና ከለላ የሆነን የመንግሥት አመራርን ‹‹አሳልፎ ሰጠን›› በማለት በችኮላ ባንመዝን የተሻለ ነው እላለሁ፡፡ ከዚህ ይልቅ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያሉትን ክፍተቶች ለማጥበብ ከችግሩ ይልቅ የመፍትሔ አካል ብንሆን ለወደፊቱ ዕርምጃችን ጥቅም ይኖረዋል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡