Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየሰበር አቤቱታ መብት እንጂ ችሮታ ሊሆን አይችልም

የሰበር አቤቱታ መብት እንጂ ችሮታ ሊሆን አይችልም

ቀን:

በላቀው በላይ

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ‹‹ሰበር መብት አይደለም›› በማለት የሰጡት መልስ በእጅጉ የተሳሳተ ከመሆኑም በላይ፣ በዚህ ደረጃ ካልታረመ የሚያስከትለው ውጤት በጣም ከባድ ነው፡፡ የሰበር አቤቱታ መብት መሆኑ ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ጭምር ያለው ነው፡፡ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 80 ‹‹የፍርድ ቤቶች ጣምራነትና ሥልጣን›› በሚለው ሥር የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበትን ማናቸውንም የመጨረሻ ውሳኔ ለማረም በሰበር ችሎት የማየት ሥልጣን ይኖረዋል ተብሎ የተደነገገ ሲሆን፣ ይኸው ሕገ መንግሥት ለክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶችም ተመሳሳይ ሥልጣን ይሰጣል፡፡ በሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች የትኛውም ቦታ ላይ ይህንን የጠቅላይ ፍርድ ቤቶችን ሥልጣን የሚቀንስ ወይም የሚያስቀር ድንጋጌ አይገኝም፡፡

አሁን በሥልጣን ላይ ያሉት የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የወጣው አዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 10 ሥር ከኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 80/3/ሀ ጋር የሚጋጭ ይዘት ያለው ቢሆንም እንኳን፣ ‹‹የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ሥልጣን›› የሚል ድንገጌ ይገኝበታል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር በሥልጣኑ የሚያያቸውን ጉዳዮችም ዘርዝሯል፡፡

በሕገ መንግሥቱም ሆነ በአዋጁ ለፌዴራል ጠይላይ ፍርድ ቤት የተሰጠውን የሰበር ሥልጣን ለማስፈጸም ሲባል የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት 3 የሰበር አጣሪ ችሎቶች፣ 3 የሰበር መርማሪ ችሎቶች፣ በአጠቃላይ ከ24 ሊያንሱ የማይችሉ የሰበር ዳኞች መድቦ ይገኛል፡፡ የሰበር ዳኞችን የሚያግዙ ከ40 ሊያንሱ የማይችሉ ሬጅስትራሮች፣ የመረጃና የዳታ ሠራተኞች፣ የችሎት ጸሐፊዎች፣ የችሎት መልዕክተኞች፣ የችሎት ሥነ ሥርዓቶች የመደበ ሲሆን ለዚህ ሁሉ መዋቅር የሚያወጣው ሀብት በእጅጉ ከፍተኛ እንደሆነ የሚታመን ጉዳይ ነው፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር የሥር ክፍል ከላይ በተገለጸው መልኩ ሕገ መንግሥታዊና ሕጋዊ ሥልጣን ተሰጥቶት በከፍተኛ የሰው ኃይልና የገንዘብ ሀብት ተደግፎ የተደራጀው፣ የኢትዮጵያውያንን መብት ለመጠበቅና ለማስጠበቅ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ከአገሪቱ ጫፍ ጀምሮ ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ወደ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በገፍ የሚጎርፉት ለፅድቅ ወይም ለሽርሽር ጉዞ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያውያን ወደ ሰበር ችሎቱ በገፍ የሚጎርፉት የሰበር አቤቱታ ችሮታ ሳይሆን ሕገ መንግሥታዊ መብታችን ጭምር ነው በሚል ሲሆን ዋናው ዓላማቸውም ሽርፍራፊ ጥቅም ለማስቀረት ሳይሆን፣ በሥር ፍርድ ቤቶች በሚሠሩ ዳኞች የተነጠቁትን የተፈጥሮ፣ ሕገ መንግሥታዊና ሕጋዊ መብት ለማስመለስ ነው፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት በቅርቡ ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ‹‹አንደኛ ሰበር መብት አይደለም›› ከማለታቸውም በተጨማሪ፣ ዜጎች ጉዳያቸውን ወደ ሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔም ሆነ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት መውሰዳቸው ተገቢ አይደለም በማለት የሰጡት ምላሽ በውጤት ደረጃ በጣም አደገኛ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ፍትሕ ተጓድሎብናል፣ መብታችን ተሸራርፏል ብለው ባመኑ ቁጥር እንዲሄዱ መበረታታት ያለባቸው ወደ ፍትሕ ተቋማት ሲሆን፣ የፍትሕ ተቋማትም ከሥራቸው ሁሉ ቅድሚያ ሰጥተው የዜጎችን ቅሬታ የመፍታት ግዴታም ኃላፊነትም አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን መብታቸው ተጥሶ፣ ፍትሕ አጥተው በፍትሕ ጥማት እየተንገበገቡ ወደ ሰበርም ሆነ ወደ ሕገ መንግሥት ጉባዔ አትምጡ፣ ብትመጡም የጠየቃችሁትን የማግኘት መብት የላችሁም ከተባሉ ወዴት ሂዱ እያልናቸው ነው? መልሱ ግልጽ ነው፡፡ በእጃችሁ ያለውን ሁሉ ጦር መሣሪያ ይዛችሁ፣ ከውጭ ጠላት ጋርም ተላልካችሁ የአገሪቱን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትና የግዛት አንድነት ወደ ማፍረስ ሂዱ እያልናቸው ይሆን?

የኢትዮጵያውያንን የፍትሕ ዕጦት አገሪቱ በብሔራዊ ደረጃ ምክክር የምትቀመጥበት ግንባር ቀደሙ ጉዳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያዊያን የፍትሕ ጥያቄ ሳይመለስ የአገሪቱንና የሕዝቧን ሰላምና ብልፅግና ማሳካት ቀርቶ፣ እነዚህን እሴቶች ለማሰብ የሚያበቃ ጊዜ እንኳን አይኖርም፡፡ አሁን እየሆነ ያለው ይኸው ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ከሰላም ውሎና ከልማት ጎዳና ወጥተው ሞተው ለመኖር ለህልውናቸው በመዋደቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያውያን የፍትሕ ጥያቄ በዚህ ደረጃ አገራዊ ጉዳይ በሆነበት ሰዓት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሰበር መብት አይደለም፣ ወደ ሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔም ሆነ ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት ቅሬታዎችን ይዞ መሄድ ተገቢ አይደለም ተብሎ የተገለጸው ካልታረመ፣ በዜጎች መብት ላይ ብሎም በአገሪቱ ሰላምና ብልፅግና ላይ የሚያስከትለው አደጋ በጣም ከፍተኛ፣ የማይካስና የማተካ ይሆናል፡፡ በጋዜጣው እንደተነሳው የይግባኝና የሰበር ቅሬታ ወደ ጉዳዩ ሳይገባ አስቀድሞ በተዘጋጀ ፎርም እየተዘጋ በሚመለስበት አገር፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ለሰበርም ሆነ ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ የሚቀርቡ አቤቱታዎች መብት አይደለም ባሉ ማግሥት፣ ማነው ወደ እነዚህ ተቋማት የሚሄደው? የተኛው ዳኛና ቅሬታ መርማሪስ ነው የፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት መብት አይደለም ያሉትን ጉዳይ ዋጋ ሰጥቶና መብት ነው ብሎ የሚመረምረው?

በየትኛውም አገር ተቀባይነት የሌለው ይግባኝ ትንተና የለውም በሚል የተሰጠው ምላሽ  የሕግም ሆነ የምክንያት መሠረት የለውም

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትም ሆነ በልዩ ልዩ ሕጎች በኢትዮጵያ ፍርድ ቤት ክርክር የጀመሩ ሰዎች የይግባኝ መብት ያላቸው ቢሆንም፣ በተጨባጭና በኢትዮጵያ ፍርድ ቤት ይግባኝ ስጦታ፣ ልመናና ችሮታ ነው ካልተባለ በቀር መብት ነው ሊባል በሚችልበት ደረጃ ላይ አይገኝም፡፡ በጋዜጣው እንደተነሳው ለፍርድ ቤት የሚቀርብ የይግባኝና የሰበር ቅሬታ ጭራሽ ወደ ጉዳዩ ሳይገባ አስቀድሞ በተዘጋጀ ፎርም እየተዘጋ በመመለስ ላይ ይገኛል፡፡ የፍርድ ቤት ባለጉዳዮች የይግባኝና የሰበር ቅሬታቸውን ለማሰማት በዳኛ ፊት የሚቀርቡት አንድም ጉዳዩን በተዘረጋው ኔትወርክ በኩል ጨርሰው ሌላም ፊታቸውን ወይም ኪሳቸውን በችሎቱ አስገምግመው የይግባኙ ወይም የሰበሩ ተጠቃሚ ለመሆን እንጂ፣ የጉዳያቸውን የፍሬ ነገርና የሕግ ስህተት ከዳኛ ጋር ተሟግተው በሥር ፍርድ ቤት የተጣሰውን መብታቸውን ለማስከበር አይደለም፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ባለው ተጠያቂነት የሌለው አሠራር የጉዳያችንን የፍሬ ነገርና የሕግ ስህተት አስረድተን የይግባኙ ወይም የሰበሩ ተጠቃሚ እንሆናለን የሚሉ ተከራካሪዎች ገና ከጅምሩ የተሸነፉ ናቸው፡፡ የፍርድ ቤቶቻችን ዋናና ተጨባጭ ገጽታ ይህ ነው፡፡

በሌላ በኩል በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 12 ሥር የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን ያለበት ስለመሆኑ የተደነገገ ሲሆን፣ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ ለበላይ ፍርድ ቤት በይግባኝም ሆነ በሰበር የቀረበ አቤቱታ ትንተና ሳይደረግበት አስቀድሞ በተዘጋጀ ፎርም በዘፈቀደ ውድቅ ሊደረግ እንደሚችል የተመለከተ የሕግ ድንጋጌ የለም፡፡ በየደረጃው በሚገኙ ፍርድ ቤቶች ግድግዳ ላይ ‹‹የፍርድ ቤት መሠረታዊ እሴቶች (Core Values of Courts)›› በሚል በተለጠፉ ፖስተሮች ‹‹ግልጽነት›› የሚል እንደ አንድ የፍርድ ቤት መሠረታዊ እሴት ሆኖ ተመልክቷል፡፡ ከእነዚህ ሕገ መንግሥታዊና ሕጋዊ ድንጋጌዎች፣ እንዲሁም እሴታዊ መርሆች አኳያ ይግባኝ ሰሚና ሰበር አጣሪ ችሎቶች የቀረበላቸውን ቅሬታ ያለ ምንም ምክንያትና ግልጽነት በሌለው የዘፈቀደ አኳኋን በፎርም ብቻ የሚዘጉበት የሕግ አግባብ የለም፡፡ ኢትዮጵያውያን አጠቃላይ መብታቸው በፍርድ ቤቶች ተከብሮ ከልዩ ልዩ ብጥብጥ፣ ከሴራና ከሙስና አሠራር ተላቀው ወደ ሰላምና ልማት መመለስ ካለባቸው ለፍርድ ቤት የሚቀርብ የይግባኝም ሆነ የሰበር ቅሬታ በሥር ፍርድ ቤት የተፈጸመ ስህተት የለበትም ተብለ ውድቅ ሲደረግ፣ ከቀረበው ቅሬታ አኳያ ተተንትኖ ምክንያቱ ለቅሬታ አቅራቢው ሊሰጠው ይገባል፡፡

የኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች የቀረበላቸውን የይግባኝና የሰበር ቅሬታ ግልጽነት በሌለው ሁኔታ ውድቅ በማድረግ በጀመሩትና የሥራ ባህል አድርገው በያዙት አሠራር በሁለት መንገድ ተጠቃሚ ሆነውበታል፡፡ በአንድ በኩል አሠራሩ በራሱ ቅሬታ አቅራቢው ከመጀመርያው ለሙስና ግንኙነት ራሱን አስቀድሞ እንዲዘጋጅ መልዕክት የሚያስተላልፍለት በመሆኑና ሙስናም ከዳኝነት ሥርዓቱ ሊነጠል የማይችል የዳኝነት ሥርዓቱ ዋና አካል (Intrinsic/Basic and Essential) እንዲሆን በማድረጉ፣ ለሙስና ጠያቂው መንገዱን በግማሽ አሳጥሮለታል፡፡ በሌላ በኩል የሙስና ግንኙነት ባለመመሥረቱ ምክንያት መሠረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበትንና የይግባኝ ወይም የሰበር ቅሬታ የቀረበበትን የሥር ፍርድ ቤት ፍርድ በዝምታ ውድቅ የማድረጉ አሠራር ዳኛውን ከተጠያቂነት እንዲያመልጥ አድርጎታል፡፡ ከዚህ አኳያ የፍርድ ቤቱ ኃላፊዎችና ዳኞች የቀረበላቸውን ይግባኝና ሰበር በበቂ ትችት ውድቅ የሚያደርግ አሠራር በራሳቸው ይዘረጋሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ይግባኝ ውድቅ ሲደረግ ትንተና አያስፈልገውም የሌሎች አገሮች ልምድም ይኸው ነው በማለት የሰጡት ምላሽ፣ ይህንን የፍርድ ቤቱን ሕገወጥ ነፃነት (Illegitimate Discretion) የማስቀጠል አካል ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

የይግባኝና የሰበር አቤቱታዎች ወደ ጉዳዩ ተገብቶ ሳይመረመሩ አስቀድሞ በተዘጋጀ ፎርም ላይ ቀን ብቻ ተጽፎበት እንዲዘጉ ይደረጋል በሚል ከጋዜጣው የቀረበው ጥያቄ ፍጹም እውነትና የኢትዮጵያውያንን መብት በእጅጉ ያዛባ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጭራሽ በፍርድ ቤት ተስፋ ሊቆርጥ አፋፍ ላይ በሆነበት ሰዓት የሌሎች አገሮችም ልምድ ይኸው ነው በሚል የተሰጠው መልስ ያለንበትን የችግር ደረጃና የፍርድ ቤቱን ፕሬዚዳንት የኃላፊነት ደረጃ አይመጥንም፡፡ ሌሎች አገሮች የቀረበላቸውን ይግባኝ ወይም የሰበር ቅሬታ ትንተና ሳይሰጡ ጉዳዩን የሚዘጉት በምን ያክል የዳበረና የተስተካከለ የዳኝነት ሥርዓት ውስጥ ሆነው ሊሆን እንደሚችል ግንዛቤ ሊወሰድበት ይገባል፡፡ አሁን ለክርክር መነሻ የሆነው የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት ላለፉት 30 ዓመታት ፍርድ ቤት ነበር ለማለት ይቻላል? እኛ አሁን ዛሬ ፍርድ ቤት ብለን የምንጠራው ከ30 ዓመት በፊት በዛሬው ጁንታ ቡድን አምሳል የተፈጠረ፣ ያደገና የሸመገለ መሆኑን ቅንጣት እንኳን ልንረሳው የሚገባ አይደለም፡፡

የአዋጅ ቁጥር 1234/2013 መውጣትን ተከትሎ አብዛኛው ጉዳይ ወደ ፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤትና ወደ አዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤት የወረደ በመሆኑ፣ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ይግባኝና ሰበር የሚያጣሩ ችሎቶች የቀረበላቸውን ቅሬታ ውድቅ ማድረግ ያለባቸው በበቂ ምክንያትና ተጠያቂነትን ሊያስከትል በሚችል መልኩ በመተቸት ብቻ እንዲሆን አስገዳጅ የሆነ አሠራር ሊዘረጋ ይገባል፡፡ አሁን ያለው የዳኝነት አካል ይህንን የማድረግ አቅም የለኝም የሚል ከሆነ ቀዳሚ ውሳኔው መሆን ያለበት፣ የዳኝነቱን ቦታ ለቆ ለኢትዮጵያውያን ማስረከብ ብቻ መሆን አለበት፡፡ የአዲሱ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሚቀርብለት ቀጥታ ክስ በመቀነሱ በዚህ ዘርፍ የተመደቡ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች እጃቸውን አጣጥፈው የሚውሉበት ሁኔታ እየታየ ነው፡፡ ይህ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ክፍል ከፍተኛ ዕድል ነው፡፡ በአብዛኛው ከቀጥታ ክስ ነፃ ስለሆነ ከአሁን በኋላ ሳይውል ሳያድር የቀረበለትን ይግባኝ ውድቅ ማድረግ ካለበት በበቂ ምክንያትና ተገቢው ትንታኔ በማድረግ ውድቅ ሊያደርግ ይገባል፡፡ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዚህ አግባብ ከተከናወነ ወደ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ከዚያም አልፎ ወደ ሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔና ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት የሚሄደው ጉዳይ በእጅጉ ይቀንሳል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ በላይ ፍርድ ቤቶች የሚጎርፈው ከበላይ ፍርድ ቤቶች ፍቅር፣ ወይም ቢሯቸውን በሰው ጎርፍ የማጥለቅለቅ ግብ ኖሮት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ በላይ ፍርድ ቤቶች የሚያመራው ከበላይ ፍርድ ቤቶች ኢፍትሐዊነት የበለጠ የማይመች የፍትሕ ዕጦት እየገፋው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የፍትሕ ጥማቱ በደጃፉ ግፋ ቢል እንኳን በአንድ ይግባኝ እርከን ቢመለስለት እስከ ፌደሬሽ ምክር ቤት የሚጓዝበት ፍላጎቱም አቅሙም የለውም፡፡

ከለውጡ በኋላ የዳኝነት አሠራር እንደተሻሻለና የዳኞች ተጠያቂነት እንደተዘረጋ ተደርጎ የተሰጠው ምላሽ የተሳሳተና የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሕመሙ እንዳይፈወስ የሚያደርግ ነው

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ከጋዜጣው ለቀረበላቸው ጥያቄ እሳቸው ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የዳኝነት አሠራሩ ተሻሽሏል የሚሉት የወጡትን አዋጆች፣ ደንቦችና መመርያዎች በመጥቀስና ለፍርድ ቤቱ ሠራተኞች ተከታታይ ሥልጣና እየተሰጠ ይገኛል በማለት ነው፡፡ አስቀድሞም ቢሆን የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ሥልጣናቸውን ለአስፈጻሚውና በኔትወርክ ለተደራጁ አካላት አሳልፈው የሰጡት የፍርድ ቤቱን ነፃነት የሚያስጠብቅ ሕግ ሳይኖር ቀርቶ አይደለም፡፡ ፍርድ ቤቱ በሕገ መንግሥቱ ነፃ የዳኝነት አካል ሆኖ የተቋቋመ ነው፡፡ የአዋጅ ቁጥር 1233/2013 እና የአዋጅ ቁጥር 1234/2013 መውጣት በፍርድ ቤቱ ነፃነት ላይ የጨመሩት አንዳችም ነገር የለም፣ ሊኖርም አይችልም፡፡ ፍርድ ቤቱ በሕገ መንግሥቱ ነፃ ተቋም ሆኖ የተፈጠረ በመሆኑ ለፍርድ ቤቱ ነፃነት ወይም ተጨማሪ ነፃነት የሚሰጥ አዋጅ ሊኖር አይችልም፡፡ ባለፉት 30 ዓመታት ፍርድ ቤቱ ነፃ አልነበረም ከተባለ ፍርድ ቤቱ ነፃ ያልነበረው የሕግ ከለላ ያልነበረው በመሆኑ ሳይሆን፣ በውስጡ በተሰገሰገው ኃይል ውስጣዊ ፍላጎት ብቻ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ባለፉት 30 ዓመታት የነበረው አሁንም ያለው ፍርድ ቤት ከአስፈጻሚው ጋር የታሪክና የራዕይ አንድነት የለውም ተብሎ ከጥርጣሬ ነፃ በሚሆንበት አቋም ላይ አይደለም፡፡

በፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት የተጠቀሱት ሁለቱ አዋጆች ለፍርድ ቤት ነፃነት የመስጠት አቅም የሌላቸው መሆኑ የተጠበቀ ቢሆንም፣ ሁለቱም አዋጆች በቀደሙት አዋጆች ላይ የነበረውን ችግር እንኳን ሳይቀርፉ ችግሮቹን ያስቀጠሉ አዋጆች ናቸው፡፡ አዋጅ ቁጥር 1234/2013 አስቀድሞ በአዋጅ ቁጥር 25/88 እና ተከታታይ ማሻሻያዎች ላይ ይታይ የነበረውን ችግር ሳይፈታ ችግሩን ያስቀጠለ አዋጅ ነው፡፡ የአዋጅ ቁጥር 25/88 እና ተከታታይ የማሻሻያ አዋጆች መሠረታዊ ችግር በአሁኑም ሆነ በአዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 3 እና 4 መካከል ያለው ግጭት ነው፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 3 ‹‹መሠረቱ›› በሚለው ሥር የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ሕገ መንግሥቱን፣ የፌዴራል መንግሥቱን ሕጎች ወይም ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸውንና ያፀደቀቻቸውን ዓለም ስምምነቶችን መሠረት በማድረግ በሚነሱ ጉዳዮች ላይ የዳኝነት ሥልጣን እንዳላቸው የሚደነግግ ቢሆንም፣ በአንቀጽ 4 ሥር ደግሞ ይህንን ሥልጣን ከፌዴራል ፍርድ ቤቶች የሚነጥቅ ድንጋጌ ሰፍሮበት ይገኛል፡፡ አዋጁ በአንቀጽ 3 እና 4 ሥር በተመለከተው ተቃርኖ እንዲገባ የተደረገው በሕግ አረቃቀቅ ስህተት ሳይሆን፣ በወቅቱ በነበረው የአፈና ሥርዓት የፌዴራሉ ባለሥልጣናት ዋና ዋና የፖለቲካ ባላንጣዎቻቸውን ለመቆጣጠርና የኢኮኖሚ የበላይነታቸውን ለማስጠበቅ በማሰብ ነው፡፡ የአሁኑ አዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 4 ይዘት አስቀድሞ በአቶ መለስ ዜናዊ ፍላጎት በተለያዩ ጊዜያት እንዲሻሻል የተደረገውን ይዘት ያካተተና ያስቀጠለ ነው፡፡ በአጭሩ የአዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 4 ይዘት ዋና ዓላማ የአቶ መለስ ዜናዊን ሌጋሲ ማስቀጠል ነው፡፡

የአዋጅ ቁጥር 1234/2013 ዓ.ም. መውጣት በፍርድ ቤቱ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኖች ዘንድ ለውጥ ይዞ እንደመጣ የተሰጠው ምላሽም ትክክል አይደለም፡፡ የፍርድ ቤቱ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኛ ድሮም ሆነ አሁን ተራ ዜጋ፣ መልካም ዜጋ ሲሆን ከድካሙ ወይ  ምሥጋና ወይ ጥቅም ያላገኘ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ በጋዜጣው እንደተነሳው የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት ችግር ድጋፍ ሰጪው ሠራተኛ አይደለም፡፡ ድጋፍ ሰጪው የፍርድ ቤት ሠራተኛ ምንጊዜም ታታሪና ተባባሪ ነው፡፡ የፍርድ ቤቱ ችግር ከዳኞችና ከዳኞች ጋር ብቻ የተያያዘ ነው፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የወጣው አዋጅ ቁጥር 1234/2013 ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዕድል ሳይሆን፣ ዕዳ ይዞ የመጣ አዋጅ ነው፡፡ በአዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 38 ሥር የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ያለ ምንም ምክንያት ከነሐሴ 1 ቀን እስከ መስከረም 30 ቀን ዝግ ናቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ዋስትና ተከልክሎ በማረሚያ ቤት የሚገኝ የወንጀል ተጠርጣሪ ፍትሕ የማግኘት መብት የለውም፣ ወይም የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብቱ ከሁለት ወራት በላይ ይጓተታል፡፡ በሥር ፍርድ ቤት ጥፋተኛ የተባለና ይግባኝ ጠይቆ በማረሚያ ቤት የሚማቅቅ የሕግ እስረኛ በይግባኝ/በሰበር የመለቀቅ መብቱ ከሁለት ወራት በማያንስ ጊዜ ይራዘማል፡፡ ሐምሌ 30 ላይ የፍርድ ባለመብት የሆነ የፍትሐ ብሔር ተከራካሪ ፍርድ ቤቱ ከጥቅምት 1 በኋላ ሥራ እስኪጀምር የፍርድ መብቱን ለሁለት ወር እንዳያገኝ ይደረጋል፡፡ በሌላ በኩል ፍርድ ቤቱ በአዋጅ ተዘግቷል ቢባልም ዳኞች የተንከባለለ መዝገብ ላይ ፍርድ ሰጥተዋል፣ በጊዜ ቀጠሮ በቢሮ ተገኝተዋል በማለት ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ሀብት በአበል መልክ ለዳኛ የሚከፈልበት አሠራር ተዘርግቷል፡፡ ይህ በራሱ ፍርድ ቤቱ በሕዝብ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት ዝቅ የሚደርግ ከመሆኑም በላይ የክረምቱ አበል ከሚያመልጥ በሚል ማስረጃ ተሟልቶ ሳይቀርብ፣ በሕግ አግባብ በመዝገቡ ላይ ፍርድ ለመስጠት የማይገባው፣ ክርክሩን ያልሰማው ምስክሩን ያልሰማው ዳኛ በመዝገብ ላይ ፍርድ እንዲሰጥ እየተደረገ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊወጣው የማይችል ማጥ ውስጥ እንዲገባ ተደርጎ ይገኛል፡፡

የአሁኗ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የፌዴራል ዳኝነት አስተዳደር አዋጅ ተብሎ የወጣው አዋጅ ቁጥር 1233/2013 የአቶ መለስና የአቶ በረከት ስምኦንን ሌጋሲ ከማስቀጠል ባለፈ ይዞት የመጣው ለውጥ የለም፡፡ አቶ መለስ ዜናዊና አቶ በረከት ስምኦን እንደቀየሱት በሚታመንበት የ30 ዓመታት የዳኝነት ሥርዓት ድሮም የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የሚባል ነበረ፡፡ ይህ ጉባዔ በማቋቋሚያ አዋጁ ንባብ የዳኞችን ተጠያቂነት የሚያረጋግጥ ተቋም መስሎ ቢታይም፣ ዋናው ዓላማ በመለስ ዜናዊ ፈቃድ ለተሾመውና መለስ ዜናዊ ያዘዘውን እንዲሁም የራሱን ፍላጎት ለማሟላት ጥፋት የሚሠራውን ዳኛ ከመጠየቅ መጠበቅ ነበር፡፡ በዚህ በዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ታሪክ በዳኛ ላይ የቀረበ የክስ መዝገብ ጠፍቶ ተፈልጎ፣ በሠራተኞች መቀመጫ ወንበር ካርቶን ተደርቦበት የሠራተኛ መቀመጫ ሆኖ ተገኝቶ ያውቃል፡፡ ይህ ላለፉት 30 ዓመታት ለነበረው የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ዓላማ ዋና መገለጫ ነው፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት በፍርድ ቤት አሠራር ላይ ከፍተኛ ተጠያቂነት ያመጣል በማለት የጠቀሱት አዋጅ ቁጥር 1233/2013 የመለስን ሌጋሲ ከማስቀጠል ባለፈ የለውጡ መንፈስ እንኳን ያልነፈሰበት አዋጅ ነው፡፡ በዚህ አዋጅ ዋናው ተቋም የዳኞች አስተዳደር ጉባዔን ያቋቋመው አንቀጽ 6 እና ልዩ ልዩ ኮሚቴዎችን ያቋቋመው አንቀጽ 14 ነው፡፡ በሁለቱም አንቀጾች ለተቋቋመው አካል ዋና አባላት ሕዝብ ቅሬታ የሚያነሳባቸው ዳኞችና የፍርድ ቤት ኃላፊዎች ናቸው፡፡ አዋጁ የፍርድ ቤቱን ተጠያቂነት ያሰፍናሉ ብሎ አመኔታ የጣለባቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጭራሽ አመኔታ ባጣባቸው፣ የአፈናውን ዘመን ፖሊሲና ራዕይ እየተጋሩ በዳኝነት ሥራቸው ላይ በቀጠሉ ዳኞች ላይ ነው፡፡ በዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ዳኞች ራሳቸው ተከሳሽ ሆነው በሚሰጠው ውሳኔ ላይ ሁለት ሦስተኛ ድምፅ ያላቸው ራሳቸው ዳኞች ናቸው፡፡ በጉባዔው ውስጥ የሚመለከታቸው አካላትና የሕዝብ ውክልና የለም፡፡ በዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ከሳሽ፣ ተከሳሽና ዳኛም ናቸው፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ራሳቸው በከሰሱበት ጉዳይ ራሳቸው ዳኛ ናቸው፣ ራሳቸው በሚከሰሱበት ጉዳይም ራሳቸው ዳኛና የጉባዔው ሰብሳቢ ናቸው፡፡ ከዚህ አሠራር የዳኝነት ተጠያቂነት ሊወለድ አይችልም፡፡ የአዋጁ ዓላማ ተስፋ የማይቆርጠውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ሞኝ ማድረግና ሞቱን ቀስ እያለ እንዲሞተው ማስቻል ብቻ ነው፡፡

የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ በሥራ ላይ እንደሆነ ተደርጎ የተሰጠው ምላሽ ስህተት ነው፡፡ አሁን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሰብሳቤ የሆኑበት የዳኞች አስተዳደር  ጉባዔ ቢያንስ በወር አንድ ጊዜ የመሰብሰብ ግዴታ ያለበት ቢሆንም፣ ከጽሕፈት ቤቱ በተገኘው ማስረጃ ጉባዔው ለሁለት ዓመት ያክል በተከሳሽ ዳኞች ላይ የቀረበን ክስ ለመመርመር ተሰብስቦ አያውቅም፡፡ የጉባዔ ጽሕፈት ቤት የቀጠራቸው ሠራተኞች በጉባዔው ውስጥ ባገኙት ሥራ ለመቀጠል ፍላጎት የሌላቸው ስለመሆኑ ጸሐፊው በተደጋጋሚ ወደ ጽሕፈት ቤቱ ሲሄድ አረጋግጧል፡፡ ዛሬ የነበረውን ሠራተኛ ከሦስት ወራት በኋላ ሄዶ ማግኘት አይቻልም፣ ለቋል፡፡ ጸሐፊው ለጽሕፈት ቤቱ የኮሙዩኒኬሽን ሠራተኞችና ለፍርድ ምርመራ ሠራተኞች በዚህ ሥራ የምትቆዩ ይመስላችኋል የሚል ጥያቄ አንስቶላቸው ለመቆየት እርግጠኛ አለመሆናቸውን አረጋግጠውለታል፡፡ ምክንያታቸው ሥራ አጥነትና የሥራ እርካታ ዕጦት እንደሆነ ገልጸውለታል፡፡ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔና ጽሕፈት ቤት በሕግ ተቋቁሞ፣ ነገር ግን በሥልታዊ መንገድ እንዳይስል እንዳይተነፍስ ታፍኖ የአገሪቱን ከፍተኛ ሀብት በማባከን ላይ ይገኛል፡፡

ይህንን ጉዳይ በንፅፅር መመልከት አስፈላጊ ሆኖ ይገኛል፡፡ በአሜሪካ ካሊፎርኒያ በሚባለው ግዛት የተቋቋመው የግዛቱ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ፣ በሥልጣኑ ክስ የሚቀርብባቸውን 1,868 ዳኞችና 250 ኮርት ኮሚሽነሮች በድምሩ 2,118 ሰዎችን የዲሲፕሊን ክስ የመከታተል ኃላፊነት አለው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2020 ጉባዔው በ874 ዳኞች ላይ 1,063 ክሶችን የተቀበለ ሲሆን፣ ካለፈው ዓመት የተንከባለሉ 108 ክሶችን ጨምሮ 1,050 ቅሬታዎች ላይ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ጉባዔው በዚህ ደረጃ ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው ቅሬታዎች ውሳኔ ከመስጠቱም በላይ፣ ከ1960 ዓ.ም. ጀምሮ ጉባዔው ውሳኔ የሰጠባቸውን ጉዳዮች በዳታ ቤዝ አደራጅቶ ለሕዝብ ተደራሽ አድርጓል፡፡ ጉባዔው በዳኞች ላይ የቀረበውን ክስ ከተቀበለበት ጊዜ ጀምሮ ጉዳዩ ለሕዝብ ግልጽ በሆነ አሠራር እንዲታይ የሚያደርግ ሲሆን፣ የዳኞችን ክስ በድረ ገጽ ጭምር በመጫን ስለ አሠራሩ፣ ስለ ክስ አቀራረቡ፣ ስለመርሁ፣ ስለሥልጣኑና ኃላፊነቱ ያለውን ሕጋዊ ሁኔታ በድረ ገጹ ለሕዝብ ግልጽ አድርጓል፡፡ እዚህ ላይ ትርጉም ያለውና የሕዝብ አመኔታ ያለው የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ቢቋቋም፣ በእኛ አገር ምን ያህል ቅሬታ ሊቀርብ እንደሚችል ከካሊፎርኒያ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ተሞክሮ መማር ይቻላል፡፡ በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት ተራ የዳኞች ስህተት ይፈጸማል ተብሎ የማይገመት ቢሆንም፣ የቀረበው የክስ ብዛት ግን ከላይ የተጠቀሰው ነው፡፡

በኢትዮጵያ ላለፉት 30 ዓመታት ለይስሙላ በሥራ ላይ ከነበረው የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ለትምህርትና ለሙከራ አንድ ማስረጃ ቢጠየቅ ይገኛል ተብሎ አይገመትም፡፡ አሁን የፍርድ ቤትን አሠራር ተጠያቂ ያደርጋል የተባለው የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አስቀድሞ ለ30 ዓመታት የነበረው ጉባዔ የመንፈስ ወራሽ ነው፡፡ እንግዲህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተጠያቂነት ያለው የዳኝነት አሠራር ይኖራል ብሎ ተስፋ የሚያደርገው፣ ከአፈናው ዘመን መንፈሱን ወርሶ ከመጣው የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ነው፡፡

ለመሆኑ የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት መሠረታዊ ችግር ምንድነው?

ዛሬ ላይ ሆነን ጉዳዩን ስንገመግመው የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት መሠረታዊ ችግር ባለፉት የ30 ዓመታት የአፈና ዘመን ወደ ፍርድ ቤቱ በዳኝነት ሥራ የተሰማራው የሰው ኃይል ይዘት ችግር ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት ቀርበው የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት ፍትሕን በገንዘብ ሲቸበችብ ነበር የሚል ትችት በማቅረብ ብቻ ተወስነው መቅረት አልነበረባቸውም፡፡ ይህ ፍትሕን በገንዘብ ሲቸበችብ የነበረው ፍርድ ቤት ለውጡን ተከትሎ ከሥር መሠረቱ ተነቅሎ፣ ፍትሕን ለመሸከም በሚችሉ ዳኞች እንዲተካ መደረግ ነበረበት፡፡

ሁለተኛው የፍርድ ቤቱ ችግር ፍርድ ቤቱ በዚህ ደረጃ ላይ ሆኖም ቤቱን የሚጠርግበት መጥረጊያ፣ ፊቱን የሚያይበት መስታወት የሌለው ተቋም መሆኑና ተቋሙም ይህንን ገጽታውን ዕድል አድርጎ መውሰዱ ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ አፈጻጸሙን የሚለካው አበላሽቶ በዘጋው መዝገብ ብዛት ወይም በጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተነገረው ፍትሕን በገንዘብ በቸበቸበበት መዝገብ ብዛት ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ በማበላሸት የዘጋቸው የመዝገብ ብዛቶች የፍርድ ቤቱን ትክክለኛነት የሚያሳይ መስታወት ሊሆን አይችልም፡፡ ፍርድ ቤቱ ሥራው ትክክል መሆኑንና አለመሆኑን የሚመለከትበት ሌላ የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት ያለበት ሲሆን፣ በሥራው ውጤታማነት ላይ በሚያደርገው ግምገማ የሚመለከታቸውን አካላት፣ የሲቪክ ተቋማትንና በየደረጃው ያሉ የሕዝብ ወኪሎችን የሚያሳትፍበት አሠራር መዘርጋት ይኖርበታል፡፡

የፍርድ ቤቱ ሌላው ችግር የሕዝብን አመኔታ ባገኙ መሪዎች አለመመራቱ ነው፡፡ አሁን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱን በኃላፊነት የሚመሩትን ፕሬዚዳንት አሿሿም ብንመለከት እንኳን፣ በአመዳደባቸው ላይ የአብዘኛው ስምምነት የለም፡፡ ራሳቸው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ለሸገር 102.1 ሬዲዮ እንደነገሩት እሳቸው የፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት መልካም አፈጻጸም ካላቸው ሁሉም ኢትዮጵያውያን ጋር ተወዳድረውና የተሻለ ተቀባይነት አግኝተው አይደለም፡፡ እሳቸው የተመረጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት ሴት እንዲሆኑ በመፈለጋቸው ብቻ ነው፡፡ ከዚህ መረዳት የሚቻለው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት የተሾሙት መልካም አፈጻጸም ካላቸው ግማሽ የኅብረተሰቡ ክፍል መካከል መሆኑን ነው፡፡

አሁን በሥራ ላይ ያሉት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት መልካም አፈጻጸም ካለቸው ሴቶች መካከል ብቻ መመረጣቸው ሳያንስ፣ በዚህ ላይ ለሚነሳው ቅሬታ ምን እናድርግ ተብለው የተጠየቁ ሰዎች ሁሉ ሹመቱን አልፈለጉትም የሚል ምላሽ ተሰጥቷል፡፡ በዚህ ሁኔታ የሚሰጠውን ምላሽ እውነትነት ይህ ጸሐፊ ይጠራጠረዋል፡፡ ብቃት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ለዚህ ከፍተኛ አገራዊ ፋይዳ ላላው ኃላፊነት ተጠይቀው አንቀበልም ይላሉ ተብሎ የማይገመት ሲሆን፣ ግብዣው ‹‹እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው›› ከሆነ ችግሩ የተጋባዦች ሳይሆን የጋባዡ ነው፡፡

አሁን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው የተሾሙት ሹመቱን ከላይ በተጠቀሰው መንገድ ያገኙት ከመሆናቸውም በላይ፣ በፍርድ ቤቱ ውስጥ ለዘመናት የተንሰራፋውን ብልሹ አሠራር ከመታገል ተቆጥበው መታየታቸው፣ በመሬት ላይ የሌለ የፍርድ ቤት መሻሻል በዜና መግለጫ ሰፍኖ እንዲታይ ጥረት ማድረጋቸው፣ በሕግ ከተሰጣቸው ኃላፊነት አልፈው ከፖለቲከኞች ጀርባ በተደጋጋሚ መታየታቸው፣ የፖለቲካ ይዘት ባላቸው መድረኮች የመገኘት ፍላጎት ማሳየትና የፍርድ ቤቱን ስኬት ተጨባጭነት ከሌለው የሴቶችና የሕፃናት መብት መከበር ጋር ለማያያዝ መሞከራቸው፣ ራሱን መሠረታዊውን የዳኝነት ሥራ መርህ የጣሰ ሆኖ ይታያል፡፡

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት የነበረበትና አሁንም ያለበት ሁኔታ አገራዊ ምክክር ከሚፈልጉ ጉዳዮች ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ አሁን በፍርድ ቤት በኃላፊነትና በዳኝነት የሚሠሩ ሰዎች ለዚህ አገራዊ ምክክር ተባባሪ የመሆንና ፍርድ ቤቱ የዳኝነትን ኃላፊነት ሊሸከሙ በሚችሉ ሰዎች እንዲሠራ የማድረግ ግንባር ቀደም ኃላፊነት አለባቸው፡፡ አሁን ያለንን ፍርድ ቤት በተገቢው የሰው ኃይል እንዲሠራ ካላደረግነው አገራዊ ምክክር አድርገን በአለም ምርጥ ሊባል የሚችል ሕገ መንግሥት ብንጽፍ፣ አሁን ካሉን ምርጥ ምርጥ ሕጎች የበለጠ ምርጥ ምርጥ ምርጥ ሕጎች ብናወጣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመዘረፍ፣ ከመዋረድና ከእርስ በርስ ብጥብጥ ልንታደገው አንችልም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...