Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገት ‹‹እያማረ››በት የመጣው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን

 ‹‹እያማረ››በት የመጣው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን

ቀን:

በአብዱ አሊ

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽንን በተራ የሕዝብ ቋንቋ ‹‹አላማረብህም!››፣ ‹‹ያማረብህ መስሎሃል?›› ብዬ ሳወግዝና ስወቅስ፣ በእሱም ላይ ስቆጣ የመረጥኩት ቋንቋ ውስጥ የተቃውሞዬ ልክና መልክ፣ የቁጣዬ ይዘትና ልክ እንዳይበረዝብኝና እንዳይደበዝዝብኝ ስለምፈራ ተጨማሪ ማስታወሻ ማከል እፈልጋለሁ፡፡ የመንግሥትን ኮሙዩኒኬሽንን ‹‹አላማረብህም›› ስል እዚህ ውስጥ በተፈጠረው ስህተትም ጥፋትም ምክንያት አገር ላይ፣ የአገር ጉዳይ ላይ የደረሰው ጣጣ፣ ጠንቅና አደጋ በጭራሽና በምንም መለኪያ ከሚሸከሙት በላይ መሆኑንም መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ስህተቱና ጥፋቱ እንዴት ሆኖ እንደምን አደርገው እንደሚያብራሩት፣ ጣጣው፣ ጠንቁና አደጋው እንዴት ሆኖ እንደሚከላ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ በግልጽ ቋንቋ ‹‹የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን›› የሠራው ስህተትና ጥፋት ያስከተለው ጣጣ፣ ጠንቅና አደጋ ‹‹አላማረብህም›› ብቻ የሚባል አይደለም፡፡ ለምን? ለምን? መባል ያለበት በሰፊው የተቋሙ ግንባታ ሥራችንም መፍትሔ የሚፈለግለት ጉዳይ ነው፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ስልም እስከ 2001 ዓ.ም. መጀርያዎቹ ወራት ድረስ የማስታወቂያ ሚኒስቴር፣ ከዚያ በኋላ ደግሞ እስከ 2011 ዓ.ም. የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ተብሎ የተቋቋመው መሥሪያ ቤት ‹‹ሲሠራ›› የቆየውን፣ አሁን በ2014 ዓ.ም. ደግሞ እንደገና የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ተብሎ መልሶ የተቋቋመው የመንግሥት ‹‹አስፈጻሚ አካል››ን ወይም እሱ የሚሰጠውን፣ ይሰጠዋል የሚባለውን ‹‹አገልግሎት›› አይደለም፡፡ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን የመረጥኩት ርዕስ ከሚገልጸው በላይ ‹‹ጉድ ሠራን››፣ ‹‹አጋለጠን›› ስል ማንንም መሥሪያ ቤት፣ ማንንም የመንግሥት ባለሥልጣን፣ የመንግሥት ሠራተኛ፣ በተለይ ገንጥዬ ሳይሆን መላውን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ሥርዓትና አገልግሎት በሙሉ ነው፡፡ የመንግሥትንና የሕዝብን ግንኙነት የሚመራው፣ የሚያስተባብረው፣ እንዲህ ያለ ነገር መኖሩን የሚያረጋግጠው (ወይም ይህ ሁሉ መኖሩን ማረጋገጥ ያለበት) የመንግሥት የሠራ አካላት እንዳለ ነው፡፡

ወደ ዋናው ጉዳዬ ከመግባቴ በፊት አሁንም ከፍ ሲል ባሉት አንቀጾች እንዳደረግሁት አንድ ሌላ ማስታወሻ ላክል፡፡ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን የሠራ አካላት ጉድ ሠራን ስል፣ አንዳንዶች ብቻ ሳይሆኑ ብዙ ሰው ምናልባትም አብዛኛው ጉዳዩ ያስቆጣው ሰው፣ አንተን ያስቆጣህና ያሳዘነህ ከዋናው ስህተት/ጥፋት ይልቅ ነገርየውን መንግሥት ኮሙዩኒኬት ያደረገበት መልክ ነው? ብሎ እንደሚጠይቀኝ፣ እንደሚሞግተኝ ይገባኛል፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን የሠራንን ጉድ ላሳይና ወደ ዋናው፣ ወይም ዋናው ወደ ተባለው ጉዳይ እመለሳለሁ፡፡ ከዋናው፣ ዋናው ከተባለው ጉዳይ ይልቅ ብዙ ጊዜዬን የሚወስድብኝ ይኼው ‹‹ጉድ ሠራን›› የምለው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ሥራና አሠራር ነው፡፡

ድሮም ቢሆን፣ ከዚህ ቀደምም ሆነ ወደፊት ጠቅላላ ‹‹ፍጥርጥራችን››ን ፈትሸን፣ መላ ፈልገን ቁጥጥር ሥር እስካልዋልን ድረስ የማይተማመኑበት፣ የማይመኩበትና የማይወራረዱበት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽናችን ለይቶለት፣ በግዴለሽነትም፣ በአላዊቂነት፣ በዝርክርክነት፣ በፍርኃትም፣ እኔ ምን በወጣኝ ባይነትም በወጠረው አየር ውስጥ ጉድ የሠራን፣ ጉድ ሲሠራን ያየነውና የሰማነው ታኅሳስ 29 ቀን 2014 ዓ.ም.  ከምሽቱ 2፡30 ሰዓት በኋላ በ‹‹ላይቭ›› ቴሌቪዥን በ‹‹ሰበር ዜና›› ነው፡፡ ኢቲቪ 2፡38 ደቂቃ ላይ ሰበር ዜና ብሎ መንግሥት በምሕረት የታሰሩ/የተከሰሱ ሰዎችን መፍታቱን ነገረን፡፡ በሰበር ዜናው መጨረሻም ላይ የዜናው ‹‹ምንጭ›› ብቻ ሳይሆን፣ የሰበር ዜናው ‹‹ባለቤት›› የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት መሆኑን፣ የዚህን መሥሪያ ቤት ስም በመጥራትና በተለመደው የዜናው አቀራረብ ሥርዓትም አስታወቀን፡፡ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ራሱ በፌስቡክ ገጹ ዜናውን (መግለጫውን) በ2፡48 ደቂቃ ላይ ለጠፈው፡፡ ከዚያም ማንን ምንጩ እንዳደረገ ባላውቅም፣ ዓለም ዜናውን አስተጋባው፡፡ እነ እከሌ በምሕረት (ይቅርታ ጭምር እየተደባለቀ) ተፈቱ ማለት ከኢትዮጵያ የተገኘ ትኩስ ዜና ሆነ፡፡ በዚያው ዕለት በዚያው ሰዓት፣ እንዲያውም የገጹን ‹‹ኤዲት ሒስትሪ›› ልብ ብሎ ለሚያይ ሰው፣ የፍትሕ ሚኒስትር የፌስቡክ ገጽ ዜናውን ይፋ ያደረገው ምሕረት ሳይሆን፣ ይቅርታ ሳይሆን፣ ክስ ማንሳት ብሎ በ2፡44 ደቂቃ ላይ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ግን የፍትሕ ሚኒስትሩ በማግሥቱ ምሕረት፣ ይቅርታ፣ ክስ ማንሳት ለየቅል ናቸው በማለት የትናንትናውን ‹‹የምሕረት›› ዜና ትክክል አለመሆኑን ከመግለጻቸው በፊት፣ በዕለቱ ለዚያውም ከመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን የፌስቡክ ‹‹ልጠፋ›› በፊት በ2፡44 ደቂቃ ላይ ዕርምጃው ክስ ማንሳት ነው ብሎ እየተነገረ፣ ታኅሳስ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. የወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ‹‹መንግሥት ስብሃት ነጋና ጃዋር መሐመድን ጨምሮ በርካታ እስረኞች በምሕረት ከእስር እንዲፈቱ ወሰነ›› ብሎ ዘገበ፡፡ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ማተሚያ ቤት የሚገባው በዋዜማው ቀን በጊዜ (በዚህ ጉዳይ ታኅሳስ 29 ቀን ማታ) ቢሆንም፣ ያን ዕለት በትክክል በስንት ሰዓት እንደገባ ማጣራትና ማወቅ ቢያስፈልግም፣ የመንግሥትን የክስ ማንሳት ዕርምጃ ምሕረት ብሎ ላለመዘገብ መጠባበቂያው መሣሪያ በቂ ጊዜ ብቻ አለመሆኑን መረዳት በጣም ቀላል ነው፡፡ ይህን ያህል የሥርዓተ ግንባታ ሥራችንን እጀ ሰባራ ባላደረገ፣ ‹‹ስም ባላጠፋ››፣ ጥላሸት ባልቀባ ነበር፡፡

ሥርዓት ግንባታ ግን እንዲህ ቀላል አይደለም፡፡ ወይም እንዲህ ቀላል ነገር አይደለም ማለትን የመሰለ ማብራሪያ መስጠት ድረስ የሚያስገድድ፣ ውስብስብና ያልተረዳነው ሥራና ግዳጅ ሆኗል፡፡ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት የሚባለው የመንግሥት መሥሪያ ቤት የምሕረት ዕርምጃ ያለውን የመንግሥትን ተግባር ዜና አድርጎ በመግለጫ ‹‹አሳምሮ›› ለመገናኛ ብዙኃን፣ በተለይም በዚህ ጉዳይ የሁላችንም የመንግሥት ዜና ምንጭ ለሆነው ለኢቲቪ የሰጠ ስለምሕረት፣ ስለፍትሕና ስለሽግግር ፍትሕ ከተሰጠ ዲስኩር ጋር ነው፡፡ ለምን ከዲስኩሩ ውስጥ አንዳንዱን እንደገና አንሰማውም፡፡

‹‹የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋትና ለአካታች አገራዊ ምክክር ሲል መንግሥት በምሕረት የፈታቸው አካላትም፣ ካለፈው የጥፋት መንገድ ተምረው፣ የተሻለ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ አስተዋጽኦ በማድረግ፣ አገራቸውንና ሕዝባቸውን ይክሳሉ ብሎ መንግሥት ያምናል፡፡ ከግጭትና ከከፋፋይ መንገዶች ይልቅ ለሰላማዊ ፖለቲካ የበኩላቸውን እንደሚያደርጉም መንግሥት ተስፋ ያደርጋል፡፡ መንግሥት ይህንን ውሳኔ በአንድ በኩል ሲወስን በሌላ በኩል ደግሞ ዋጋ አስከፋይና ግጭት ጠማቂ አካሄዶች በጭራሽ እንዲደረጉ አይፈቅድም፡፡ ፍትሕና ምሕረትም በየሚዛናቸው እንዲጓዙ መንግሥት ይፈልጋል፡፡ በሒደቱ የተጎዱ ወገኖች እንደሚኖሩ መንግሥት ያምናል፡፡ የእነዚህ ተጎጂ ዜጎች ቁስል በሽግግር ፍትሕ የሚካስ ይሆናል፡፡ እነዚህ ተጎጂ ዜጎች ሕመማቸው ለኢትዮጵያ የከፈሉት ዋጋ በመሆኑ ሸክማቸውን መንግሥትና ሕዝብ በጋራ እንሸከምላቸዋለን፡፡ ከእስር የተፈቱ ወገኖችም ጭምር የተጎጂዎችን ሸክም የመሸከም ዕዳ አለባቸው፡፡

‹‹መንግሥት ይህንን ውሳኔ የወሰነው በዋናነት ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የመሀሪነቷን ዋጋ እንድታገኝ፣ የኢትዮጵያን ምሕረት ያገኙ አካላት፣ ምሕረቱን ያገኙበትን ዋጋ ይረዱታል ብሎ መንግሥት ያምናል፡፡ የኢትዮጵያ ነባር ችግሮች የሚፈቱት በሰላማዊ ፖለቲካዊ አስተዋጽኦ፣ በሆደ ሰፊነትና አዎንታዊ ሚናን በመጫወት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግሥት ዋጋ ከፍሎም ቢሆን ቅድምናውን ይወስዳል፡፡ ዛሬም ለዘላቂ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና ሰላም ሲል መንግሥት የተወሰኑ እስረኞችን በምሕረት ፈትቷል፡፡››

የትኛውም ሥራ፣ በተለይም የመንግሥት ሥራ አደራ ነውና ዕውቀት ይፈልጋል፡፡ ‹‹እኛ የኢትዮጵያ ሕዝቦች›› ለመረጥናቸው ሰዎች ውክልና ስንሰጥ እንደራሴያዊ ዴሞክራሲ በወኪሎቻችን ላይ ይህን ያህል ሲበዛ ጥብቅ ባይሆንም፣ የመረጥናቸው ሰዎች የሚሾሟቸውና በእነሱ አማካይነት የተሾሙ ሰዎች የሚያስተዳድሩት ሠራተኛ ግን ለተገቢው ሥራ ተገቢው ዕውቀት ሊኖረው ይገባል፡፡ የእኛ አላዋቂ ሳሚዎች ግን በምሕረት፣ በይቅርታና ክስ በማንሳት መካከል ያለውን ልዩነት ማወቅ ያለባቸው የሚመስላቸው አይደሉም፡፡ የፍትሕ ሚኒስትሩ በማግሥቱ መጥተው የምሕረትና የይቅርታን፣ የክስ ማንሳትን ልዩነት ማንሳትና ማስተማር የተገደዱት፣ የ‹‹ጠላት›› ፕሮፓጋንዳን የማስተባበል ያህል መከራ ያዩት፣ የመንግሥት አገልግሎት ራሱ ይህን የመሰለ ንቃትና ግንዛቤ መሸከምና ባህርይው ባላደረገ አመራር ስለሚካሄድ ነው፡፡

ስህተቱና ጥፋቱ ግን የዜናው፣ የመግለጫው ደራሲ የሆነው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት መሥሪያ ቤት ላይ ብቻ የሚጀምርና የሚያበቃ አይደለም፡፡ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት መሥሪያ ቤት ያሳሳተኝ ታኅሳስ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ከፀደቀው ከአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ ሕግ በኋላ የተደረገው ውይይት ስለፍቅር፣ ስለምሕረት፣ ስለይቅርባይነት ስላወራ ነው፡፡ ወይም ያሳሳተኝ ‹‹ጀግና ሕዝብ በቀን እጁ ድልን የሚጨብጥ፣ በግራ እጁ ይቅርታና ምሕረትን የሚቸር ነው›› (እንዲሁም በማግሥቱ ጭምር የወጣው) የጠቅላይ ሚኒስትሩ የታኅሳስ 29 መግለጫ ይቅርታና ምሕረት ብሎ ‹‹ጮኾብኝ›› ነው ብሎ ቅርታም ምሕረትም ሊጠይቅ አይችልም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው ቢሆኑም ‹‹ከደሙ ንፁህ ነኝ›› ሊሉ አይችሉም፡፡The Buck Stops Here” ማለት አለባቸው፡፡ ዞሮ ዞሮ ኃላፊነቱ ከእኔ ራስ አይወርድም ሊሉ ይገባል፡፡ ለምን እንዲህ ያለ ስህተት/ጥፋት ፈጸምን ማለት ይገባቸዋል፡፡

ጉዳዩ/መግለጫው ዝም ብሎ ዘሎ፣ ወይም ተተኩሶ ኢቲቪ ደረሰ ቢባል እንኳን፣ ኃላፊነት የሚሰማው ሙያና ባለሙያ ከእነ ሥነ ምግባሩ፣ ከእነ ጨዋነቱና ከእነ ኃላፊነት ስሜቱ ባለበት አገር ኢቲቪ ጠረጴዛ ላይ ጥያቄና ማጣራት ቀርቦበት ቢያንስ ይጣራ ይባል ነበር፡፡ እንዴት? እና ለምን?

ከ‹‹መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን›› ክልል ወጥተን ወደ ኢቲቪ በአጠቃላይ ወደ ሚዲያው ክልልና ግዛት ስንገባ ዋናው ጉዳያችን (በእኔ በኩል ጉዳዬ)፣ እንዴት አድርጎ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን ዘርፍ፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ሥራ ተግባርና አደራ ክስ የማቋረጡን ወይም ይቅርታ የመስጠቱን ወይም ምሕረት የማድረጉን ዕርምጃ መሸጥና ማሻሻጥ አልችል አለ? የሚለው አይደለም፡፡ በጭራሽ፡፡ በፍፁም፡፡ መቼ እዚያ የ‹‹ዕድገት ደረጃ›› ደረስን? በሚያሳፍርና በሚያሳዝን ሁኔታ ያቃተንና የወደቅነው የሚጨበጥ፣ የሚታይ፣ የሚዳሰስ ነባራዊ እውነት (ፋክት) ላይ ነው፡፡ የተሳሳትነው ዱባና ቅል መለየት ላይ ነው፡፡ የተምታታብን (ዱባና ቅልን ለመለየት የተቸገረ ሰው ተምታታበት የሚባል ከሆነ) ዱባውን ቅል፣ ቅሉን ዱባ ስንል ነው፡፡

ክስ ማንሳት፣ ይቅርታ፣ ምሕረት ከዱባና ቅል በላይ የተለያዩ ናቸው፡፡ ሦስቱም በባለመብቱ የመንግሥት የሥልጣን አካል ይለያያሉ፡፡ ለጊዜው ከይቅርታና ከምሕረት እንጀምር፡፡ ይቅርታ የማድረግ ሥልጣን የአስፈጻሚው አካል ነው፡፡ ምሕረት የሕግ አውጪው አካል ነው፡፡ የአዋጅ ምሕረት የሚባለውም (ሲባል የኖረውም) በዚህ ምክንያት ነው፡፡ የሚሰጠው በአዋጅ፣ ሕግ የማውጣትን ሥርዓት ተከትሎ፣ ከአስፈጻሚው አካል መንጭቶ፣ በቀረበው የሕግ ሐሳብ ላይ ውይይት ተደርጎበት፣ ረቂቅ አዋጅ ለተወካዮች ምክር ቤት ተልኮ የተወካዮች ምክር ቤትም ሕግ የማውጣት መሠረታዊ ሥነ ሥርዓቶችን፣ መረማመጃዎችንና ፌርማታዎችን ተከትሎ ሕግ በማውጣት የሚፈቅደው ዕርምጃ ነው፡፡ ሁለቱም በይዘታቸው፣ በወሰናቸው ይለያያሉ፡፡ ይቅርታ የመጨረሻ ፍርድ በተሰጠበት ጉዳይ ላይ የሚወሰድ ዕርምጃ ነው፡፡ ስለዚህም የሕግ አስፈጻሚው አካል በዚህ ጉዳይ ላይ የይቅርታ ሥልጣን አለኝ ለማለት ሲጀምር፣ የመጨረሻ ውሳኔ ያገኘ ክስ/መዝገብ ያስፈልገዋል፡፡ ምሕረት ከዚህ የተለየ ነው፡፡ የወንጀል ምርመራ ከመጀመሩም በፊት፣ ከተጀመረም በኋላ በተከሰሰም/ባልተከሰሰም ሰው ላይ ይሠራል፡፡ ምሕረት የመጨረሻ ፍርድ ያገኘ ጉዳይ የ‹‹ይቅርታ›› ነው ብሎ እዚህ ላይ አያገባኝም አይልም፡፡ የመጨረሻ ፍርድ ባገኘ ጉዳይም ምሕረት ይሠራል፡፡ ምሕረት ከዚህም በላይ ሰፊ ነው፡፡ የሚምረው የተጠረጠሩትን፣ የተከሰሱትን ሰዎች ሳይሆን ራሱን ወንጀሉን ነው፡፡ ወንጀሉን ራሱን ይደመስሳል፡፡ ሁለቱም በአገራችን የይቅርታ ወይም የምሕረት አሰጣጥና አፈጻጸም ሥነ ሥርዓት የተደነገገበት ሕግ አላቸው፡፡ እነዚህ ሕጎች እንደ አቀማመጣቸው በ1996 እና በ2010 ዓ.ም. ከመውጣታቸው በፊት በፍርድ ሚኒስቴር/በሕግና፣ ፍትሕ ሚኒስቴር/በፍትሕ ሚኒስቴር የተቋቋመና የካበተ አሠራር ውስጥ የተዘረጋ መላው አገዛዙ ውስጥ (የንጉሠ ነገሥቱንም፣ የፓርላማውንም አካሄድና አሠራር የሚገዛ) ወግና ደንብ ነበር፡፡

እዚህ ድረስ ታሪክና ሕግ ማወቅና ማጥናት ሳያስፈልግ የይቅርታ ጉዳይ አብሮን የኖረ፣ በተለይም ዋና ዋና የፖለቲካ ጉዟችንን ‹‹ማቆሚያ››ዎች፣ ‹‹መተጣጠፊያ››ዎች፣ ‹‹መተላለፊያ›› እና ‹‹ማቋረጫ››ዎች፣ ወዘተ ሲነቀሉ ሲተከሉ፣ ሲገነቡ ሲፈርሱ ያሳየን ‹‹ክስተት›› ነው፡፡ ሌላው ቢቀር ከምሕረት ጋር እየተምታታ ብዙ የተባለበት በዚህም ምክንያት ‹‹ሲጠላ መጠናት›› የነበረበት ነገር ነው፡፡ ሚዲያዎች ከዚያ ጊዜ በኋላ፣ ከዚህ ሁሉ የገሃድ ትምህርት ወዲህ ተደናቁረው መታየት አልነበረባቸውም፡፡ የምሕረት አሰጣጥና አፈጻጸም ሥነ ሥርዓት ሕግና (1083/2010) በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ውስጥ ለተሳተፉ ሰዎች ምሕረት ለመስጠት (1096/2010) የወጡት አዋጆች የመጋቢት 2010 ለውጥ ማግሥት (ነሐሴና ጳጉሜን 2010 ዓ.ም.) ሕጎች ስለሆኑ ከእነ ሁለመናቸው የሚታወሱ ናቸው፡፡

እና የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ያንን ያህል ይቅርታም ምሕረትም የማይደረግለት፣ የማይረሳም ስህተትና ጥፋት ሲሠራ (የመንግሥትን መልዕክት ትርጉምና አንድምታ አይደለም የተሳሳተው፣ በአካል መለየት በስሙ መጥራት ነው የተሳነው፣ ዱባን ቅል፣ ቅልን ዱባ ነው ያለው) ሚኒስትሮች ምክር ቤትም፣ ተወካዮች ምክር ቤትም፣ ሁለቱም ጋ ቋሚና ምድብተኛ ሠራተኛ ያለው፣ ሁሉም ቦታ ምንጭና ‹‹ጠቋሚ›› የሚያጣ የመንግሥቱ ሚዲያ፣ ማለትም ኢቲቪና ጋዜጠኞቻቸው ለምን ‹‹ምሕረት›› ሳያስደነግጣቸው፣ የጠያቂነት፣ የተጠራጣሪነት፣ የማጣራት፣ የማረጋገጥ ህዋሳቸውን ሳያተረማምሰው ቀረ? ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል፡፡ የከሸፍነው የከሸፈብን ግን እዚህ ወይም እዚያ መሥሪያ ቤት ወይም አንዱ ወይም ሌላው ሰው ላይ ሳይሆን፣ ለመጀመርያ ጊዜ ከምር የጀመርነው ተቋማትን ገለልተኛና ፕሮፌሽናል አድርጎ የመገንባት፣ የኢንፎርሜሽንና የሚዲያ ሥርዓቱን ጭምር እንደገና የማዋቀር ሥራው ላይ የደረሰው ችግር ነው፡፡ ጥቃት የደረሰበትም፣ ጥቃት ብቻ ሳይሆን ክህደትና አደጋ ያጋጠመውም፣ ጦርነት ውስጥ ያስገባንም ይኼው ለውጡንና ሽግግሩን ያደናቀፈው አድህሮትና ቅልበሳ ነው፡፡ ሕዝብ ውስጥ እየኖሩ መረጃን አነፍንፎና አጣርቶ የማሳወቅ ጋዜጠኝነት ገና የለንም፡፡ ወጉን ከመጀመር ያለፈ አቅምና ችሎታ ገና አልገነባንም፡፡ አሁን የምንነጋርበት ስህተትና ጥፋት ግን ይህን ያህል ውስብስብ አይደለም፡፡ የተሳሳትነውና ያጠፋነው ዱባና ቅልን አምታተን ነው፡፡ ሚስጥራዊ ወይም ውስብስብ አናድርገውና ዱባን ቅል፣ ቅልን ዱባ ብለን ነው፡፡

ይህ የሲኤንኤንን ‹‹ዚስ ኢዝ አን አፕል›› ማስታወቂያን ያስታውሰኛል፡፡ “Facts First” የሚለው የጣቢያው አቋም ማስታወቂያ ነው፡፡ ሲኤንኤን ለዚህ መርህ ያለውን መታመን በገዛ ራሳችን ጉዳይ እናውቀዋለን፡፡ ፋክትስ ፈርስት ማለት ለሲኤንኤ ፖለቲካዊ ዝንባሌ፣ አንጋዳጅነትና ጥላቻ ውስጥ መነከር፣ መዘፍዝፍና መበስበስን መከላከል የማይችል የውሸት ወሬና መርህ ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ሲኤንኤን በተግባር አያውቀውም ተብሎ የዚስ ኢዝ አን አፕልም ሆነ የፋክትስ ፈርስት መርህ/ሕግ የሚናቅ አይደለም፡፡

‹‹ይህ አፕል ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ይህ ሙዝ ነው ይሏችኋል፡፡ ሙዝ ነው! ሙዝ ነው ኧረ! እያሉም ደጋግመው ያስቸግሯችኋል፡፡ አላስቆም አላስቀምጥ ይሏችኋል፡፡ ሙዝ ነው፣ ሙዝ ነው እያሉ በደማቅና በትልልቅ ፊደል መከራ ያሳዩዋችኋልም፡፡ እናንተም ሙዝ ነው ብላችሁ ማመን ትጀምሩ ይሆናል፡፡ ግን ሙዝ አይደለም፡፡ ይህ አፕል ነው፡፡››

ጉዳዬንና ነገሬን ለማስረዳት ያህል አፕልና ሙዝ ተመሳሰሉም፣ ተለያዩም ግድ የለንም፡፡ ወደ ዱባና ቅላችን ልመለስና ዱባ ቅል አይደለም፣ ቅል ዱባ አይደለም፡፡ አበቃቀላቸውም ለየቅል ነው፡፡ ክስ ማንሳትን ምሕረት ማለታችን በገዛ ራሱ ምክንያት ስህተት ነው፡፡ ጥፋት ነው፡፡ ክስ ማሳትን ምሕረት ያልነው ደግሞ ከድንቁርና ይልቅ/ካለማወቅ ይልቅ ነገር እናሳምራለን፣ የመንግሥት የፖሊሲ ውሳኔን/ምርጫን እናሻሽጣለን ብለን ከሆነ ደግሞ አደገኛና ከፍ ያለ ችግር ነው፡፡ ስህተትና ጥፋት የፈጸሙት ሰዎች ግን ይህን ያህል የተካኑ ናቸው ማለት ይቸግረኛል፡፡ ዱባን ቅል ነው፣ ወይም ቅልን ዱባ ነው ያሉት አውቀው፣ ለሌላ ዓላማ ሲሉ ነው ከማለት ይልቅ ሳያውቁት ነው፣ ያላዋቂ ሥራ ነው ብል ይቀለኛል፡፡ ለውጡና ሽግግሩ ምንም እንኳን ጥቃትና አደጋ፣ ችግርና መከራ ቢደርስበትም፣ ጦርነት ውስጥ መግባትን የመሰለ ክፉ አጋጣሚ ጋር ቢጋፈጥም በየትኛውም ደረጃ ላይ ያለ ሳይጠየቁ መቅረትን ከመታገል፣ ከመዋጋት ሊቦዝንና ዕረፍት ሊወስድ አይገባም፣ አይችልምም፡፡ የምንገነባው ወይም እንገነባዋን የምንለው፣ ጥቃትና ክህደት የደረሰበት ዴሞክራሲ ሳይጠየቁ መቅረትን መዋጋት አለበት፡፡ ሕገወጥነትንና አጥፊነትን መጠየቅ መቻል ችግሩ፣ ጥፋቱ እንዳይከሰት ጠያቂውና ጠባቂው፣ ሲከሰትም አጋላጭና/ተፈራጁ እንዲበዛ ባህል እንዲሆን ያደርጋል (በነገራችን ላይ ረቡዕ ጥር 4 ቀን 2014 ዓ.ም. የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት በሚኒስትሩ በለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) አማካይነት ከዚያ ብዙ ከተነጋገርንበት ‹‹ድንገት›› ወዲህ የመጀመርያውን የመሥሪያ ቤታቸውን መግለጫ ይዘው ከጋዜጠኞች ጋር መገናኘታቸውን በዜና ዓይቻለሁ፡፡ በዚህ መግለጫ ‹‹ክስ መቋረጥ›› ተብሎ የተስተካከለው ጉዳይ የዕለቱም መግለጫ አንዱ ዋናው ርዕስ ቢሆንም፣ ‹‹እንዲያው ምን ሆናችሁ ነው? ያን ዕለት ክስ ማቋረጡን ምሕረት ያላችሁት?›› ብሎ መጠየቅም ማጠየቅም ሳልሰማ ቀረሁ)፡፡

ዋናውን ጉዳይ ትተህ፣ በየትኛውም ስም ይጠራ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመከላከያ ሚኒስቴር አዲሱ ዋና መሥሪያ ቤት ምረቃ ሥነ ሥርዓት አጋጣሚ ባደረጉት ንግግር እንዳመኑትና እንዳረጋገጡት፣ ብዙዎችን ኢትዮጵያውያን ያስቆጣውን የመንግሥትን የታኅሳስ 29 ቀን ዕርምጃ ዝም ብለህ ዱባ ቅል ተባለ፣ አፕልን ሙዝ አሉት ትላለህ፣ ደግሞም ሳይጠየቁ ስለመቅረት ታወራለህ ተብሎ መጠየቅ እንዳለብኝ አውቃለሁ፡፡ ወደ ዋናው፣ መንግሥት ክስ በማንሳት አማካይነት የወሰደው ዕርምጃ ተገቢ ነው? አይደለም? ልክ ነው አይደለም? ወደሚለው ጉዳይ የማይመራው በዚህ አማይነት ነው፡፡

ቀደም ብዬ እንዳልኩት ክስ ማንሳትም፣ ይቅርታና ምሕረት ማድረግም አነሰም በዛም በሕግ የተደነገጉ ጉዳዮች ናቸው፡፡ በቂና የተፍታታ የሕግ ማዕቀፍ አላቸው ወይ? ዳኝነትስ (የፍርድ ቤት ውሳኔ) አበልፅጓቸዋል ወይ ብሎ መጠየቅን ያህል ገና ብዙ አልታደልንም፡፡ በተለይም የመጀመርያውና አሁን መንግሥት ለወሰደው ውሳኔ መነሻ የሆነው ሕግ (ክስ የማንሳት ጉዳይ) ድኩምና ራሱ ጉዳትና ጥቃት የደረሰበት፣ አሁንም ድረስ ባለበት ያለ ነው፡፡ የ1954 ዓ.ም. የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት አንቀጽ 122 የአገር የክስ ማንሳት በሕግ ሆኖ ኖሯል፡፡ ዓቃቤ ሕግ በራሱ ሥልጣንና ፈቃድ ውስጥ፣ እንዲሁም በመንግሥት ታዝዣለሁ ሲል በፍርድ ቤት ፈቃድ ክስ የሚያነሳበት የሕግ አሠራር ግን በሕግ ተሽሯል፡፡ ይህንን የዓቃቤ ሕግን/የፍትሕ ሚኒስቴርን ‹‹በሕግ መሠረት›› ሕግ የማንሳት ሥልጣን መልሶ ያቋቋመው የዓቃቤ ሕግን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣ ሕግ ነው፡፡ ያ ሕግ አለኝ የሚለው ሕግ አለን ወይ? አዲሱ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ ይህንን ወደ ነበረበት ብቻ ሳይሆን፣ ይበልጥ አበልፅጎታል ወይ? መመለስ ያለበት ጥያቄ ነው፡፡ ዋናውና አንገብጋቢ ጥያቄ ግን ሕግ መኖሩ ክስ ለማንሳትም፣ ይቅርታና ምሕረት ለማድረግም የሚፈቅድ ሕግና አሠራር መኖሩ ሳይሆን፣ በዚህ ሕግ መሠረት የተወሰደው ዕርምጃው ራሱ ልክ ነው ወይ? ተገቢ ነው ወይ? የሚለው ነው፡፡ መንግሥት ይህንን ጥያቄ መመለስ፣ የወሰደውን ዕርምጃ ትክክለኛነት (ወይም በወሰደው ዕርምጃ ላይ የተነሳውን ቁጣ መከላከልና መጋፈጥ) ማስረዳት ቻለ ወይ? ገና ያልተመለሰ እስካሁን ድረስ ገና አቅጣጫውን ሲይዝ ማየት ያልቻልኩት ጥያቄ ነው፡፡

አገር ያለችበትን ታይቶ የማይታወቅ ችግር እናውቃለን፡፡ ጦርነቱ ራሱ ያደረሰው ሞት፣ ውድመት፣ ጥፋት ሲጫነን የሚኖርና ለመሻርም ለመሻገርም ብዙ ጊዜ የሚጠይቅ ቁስል አለብን፡፡ የዓለም አቀፍ ጉልበተኛ አገሮች ጫና፣ ጭቆናና ማዕቀብ፣ ወዘተ የጠላትን፣ የጠላትነትን ሚናን የሚያስንቅ፣ የሚያስከነዳ ነው፡፡ ጠላትነት ብሎ ዝም ይኼው ራሱ ነው፡፡ ይህን ያህል እናውቃለን፡፡ የህልውናውን ጦርነት የሚመራው፣ ይህን ሁሉ ሕዝብ ያስተባበረው መንግሥት የሚያውቀውን በሙሉ ግን አናውቅም፡፡ ሁሉንም እውነት፣ እውነቱን ሁሉ ገልጸህ ንገረን፣ እርቃንህን ቆመህ እንይህ አንለው ነገር እንኳንስ ጦርነት ውስጥ፣ እንኳንስ የህልውና ጦርነት ውስጥ የዘወትርና የአዘቦት ሕይወትና ኑሮ ውስጥም ቢሆን የሚደብቁት የሚጠብቁት ሚስጥር አለ፡፡ ‹‹በአደባባይ የሚላጩት ፀጉር አለ፣ ተደብቆ/ተከልሎ የሚላጩትም ፀጉር አለ›› ይላል የአፋር ምሳሌያዊ አነጋገር፡፡ የክብር ወይም የኃፍረተ ሥጋ ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ የህልውና ጉዳይ፣ የህልውና ጥያቄ የሞት የሽረት ነገር ነው፡፡

ከመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ራስ የማንወርድበት (የምናወራው ስለአንድ ባለበጀት መሥሪያ ቤት ሳይሆን፣ ስለአገር የሠራ አካላት የመነጋገሪያ፣ የመገናኛ ሥርዓት  ነው) ውሳኔ መወሰንን ያህል ውሳኔውን ለሕዝብ ‹‹ማርዳት››ም ዕውቀት፣ ጥበብ፣ ብልኃት የሚጠይቅ በመሆኑ ነው፡፡

በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን መንግሥት የአደባባዩን ፀጉር ‹‹ሚስጥር›› አላጋራንም፡፡ ሁሉን ነገር አልነገረንም፡፡ ለዚህም ነገርና መነጋገር አላዘጋጀንም፡፡ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ስለዘባረቀው እንኳን ይቅርታ አልጠየቀም፡፡ በአምስተኛው ቀን አገር ቁና ከሆነች በኋላ ምሕረት ያለውን ምንም እንዳልተፈጠረ፣ ያለ ምንም መግቢያና ማስተዋወቂያ ክስ ማንሳት ሲል ምንም እንዳልተፈጠረ ዝም ብሎ ተደባለቀን፡፡ ለምንድነው ክስ ማንሳትና ምሕረት የሚምታታባችሁ ብሎ የጠየቀውም የለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒትሩም ለተፈጠረው ዝም ብሎ ያልሆነ (ሌጅትመት) ቁጣ ተቃውሞና ኩርፊያ፣ እንዲሁም የብዙዎች ምስኪን እናቶች ሐዘን ተገቢ ማብራሪያ ልብ ጠብ የሚል ፍቺና ትርጉም አልሰጡም፡፡ ፓርላማው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥያቄ ላፋፍምብህ፣ ለሠራኸው ሥራ ለሕዝብ ቅያሜና ኩርፊያ ምን ምላሽ አለህ ብሎ ግዳጁን አልተወጣም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...