በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ቦታዎች ላይ የፕላስቲክ ባልዲ ቆርጠው የማሸናት አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶችን ማየት ከተለመደ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ባልዲዎቹ የከተማዋን ውበት ቢያጠፉም፣ ለአላፊ አግዳሚ ተባዕቶች ግን ትልቅ መፍትሔ ሆነው ሲያገለግሉ ይታያል፡፡
በተለይ በየአጥር ጥግ ሥርና በሌሎች ቦታዎች ላይ ለሚፀዳዱ ተባዕቶች አማራጭ ሆነዋል፡፡ በገበያ፣ በትራንስፖርትና ግርግር በበዛባቸው አካባቢዎችም መፀዳጃ ቤት አለመኖሩ ክፍተቱ ጎልቶ እንዲታይ አድርጎታል፡፡ በዚህም የተነሳ በርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎች ሌላ አማራጭ እንዲጠቀሙና የከተማዋን ውበት መላ ቅጡ እንዲጠፋ እንዲያደረጉ መንገድ ከፍቷል፡፡
ችግሩን ለመቅረፍ በፒያሳ፣ በሜክሲኮ፣ በመገናኛ፣ በአራት ኪሎና በሌሎች ቦታዎች የፕላስቲክ ባልዲ አስቀምጠው የማሸናት አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶችን ሪፖርተር መመልከት ችሏል፡፡
አገልግሎቱም ደረጃውን ያልጠበቀና ከተማን የማይመጥን በመሆኑ በብዙ ሰዎች ዘንድ ጥያቄን ፈጥሯል፡፡ መንግሥት ችግሩን ተረድቶ በከተማዋ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ከዚህ ቀደም እንደነበረው የመፀዳጃ ቦታ መገንባት አለበት የምትለው ወጣት ሳምራዊ ናት፡፡
ወጣቷ እንደምትለው፣ በተለይ ሴት ልጆች የውኃ ሽንት ለመጠቀም በሚፈልጉ ጊዜ እንደሚቸገሩና ላልሆነ የጤና ችግር እንደሚጋለጡ አስረድታለች፡፡ በአሁኑ ወቅት የኩላሊት በሽታ በተስፋፋበት ጊዜ የውኃ ሽንት መቋጠር ከባድ እንደሆነ የምትናገረው ወጣት ሳምራዊ፣ መንግሥት ይህንንም ተረድቶ አፋጣኝ ሥራ መሥራት እንዳለበት ተናግራለች፡፡
በአብዛኛው በገበያ አካባቢ ችግሩ እንደሚታይ፣ አማራጭ ተደርገው የሚወሰዱ ሆቴሎች ውስጥ ገብቶ ለመጠቀም ከባድ መሆኑን ገልጻለች፡፡ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ለሴቶች ባይሆንም በባልዲ የማሸናት አገልግሎት የሚሰጡ እንዳሉ፣ መንግሥት ይህንን አይቶ ወደ ተሻለ መፀዳጃ ቤቶች በመሥራት የሰዎችን ችግር መታደግ እንዳለበት ትናገራለች፡፡
ስሟ እንዳይጠቀስ የምትፈልገው ሌላዋ ወጣት እንደገለጸችው፣ ከሁሉም በላይ ጤና ወሳኝ ነው፡፡ በከተማዋ በቂ የሆነ መፀደጃ ቤት አለመኖሩ ሰዎች ለኩላሊት ሕመም እንዳይጋለጡ አንድ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ አዲስ አበባ ዋና ከተማ እንደመሆኗ መጠን የመፀዳጃ አገልግሎት በየቦታው መኖር አለበት፡፡ ይህም የከተማዋን ውበት ለማስጠበቅ ብዙ ሰዎች ሽንት በመቋጠር የሚገጥማቸውን ስቃይ ማስቀረት ይቻላል፡፡
የከተማዋን ውበት በተመለከተ በየአጥር ጥግ ሥር የሚፀዳዱ የማኅበረሰብ ክፍሎችን እንደምትመለከት፣ ይህም መንግሥት ዘርፉ ላይ ብዙ አለመሥራቱን እንደሚያሳይ ተናግራለች፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ምርጫ ባለመኖሩ በፕላስቲክ ባልዲ የውኃ ሽንት የሚያሸኑ ወጣቶች ግን መበረታታት ያለባቸው መሆኑን ተናግራለች፡፡
አብዛኛውን ጊዜ በተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ የግንዛቤ እጥረት እንዳለ፣ የእኔነት ስሜት እንደማይታይ የምታስረዳው ወጣቷ፣ ካለፉት ስህተት በመረዳት፣ እንዲሁም ከመንግሥት ጎን በመቆም ያሉትን ችግሮች መቅረፍ ያስፈልጋል ብላለች፡፡
ሥራውን መሬት አውርዶ ለመሥራት ብዙ ጊዜ እንደሚፈልግ፣ በአሁኑ ወቅት ከከተማ ውበት ጋር ተያይዞ ብዙ ጅማሮዎች እንዳሉ ከዚህ ጎን ለጎን የሕዝብ መፀዳጃ ቤት መዘንጋት እንደሌለበት ተናግራለች፡፡
አብዛኛው የከተማዋ ነዋሪ በተለያዩ ቦታዎች ላይ እንቅስቃሴ የሚያደርግ መሆኑን፣ እንቅስቃሴ በሚያደርግበት ጊዜ መፀዳጃ ቤት መጠቀም ከተማዋ ላይ የሚገኙ መፀዳጃ ቤቶች ውስን በመሆናቸው ለጭንቀት ሲጋለጡ ይታያሉ ስትል አስረድታለች፡፡
በፒያሳ አካባቢ በፕላስቲክ ባልዲ የውኃ ሽንት በማሸናት አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ከዓመት በላይ ያስቆጠረው ስሙ እንዲጠቀስ የማይፈልገው ወጣት ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ በከተማዋ ከፍተኛ የሆነ የመፀዳጃ ቦታ እጥረት መኖሩን በመረዳት ከሁለት ጓደኞቹ ጋር በመሆን ለተባዕቶች በባልዲ የማሸናት አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡
በየሳምንቱ በየፊረቃ እየተቀያየሩ አገልግሎት እንደሚሰጡ የሚናገረው ወጣቱ፣ አንድ ሰው አገልግሎቱን ለመጠቀም ከፈለገ ሁለት ብር ከፍሎ እንደሚጠቀም ተናግሯል፡፡
በቀን እስከ 100 ብር ድረስ እንደሚሠራ፣ በተለይ በክረምት ወቅት ላይ ከፍተኛ ተጠቃሚ ስላለ በቀን እስከ 200 ብር ድረስ የሚሠራበት አጋጣሚ እንዳለ አስረድቷል፡፡ አገልግሎቱን ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ 1፡00 ሰዓት ድረስ የሚሰጡ መሆኑን የሚያስረዳው ወጣቱ፣ ሰዎች ተጠቅመው ከጨረሱ በኋላ፣ በአካባቢው ከሚገኘው ወንዝ ዳር የውኃ ሽንቱን እንደሚደፉት ተናግሮ፣ መንግሥት እየሠሩ ያለውን መልካም ሥራ ተረድቶ በዘመናዊ መልክ መፀዳጃ ቤት ቢሠራ የከተማዋን ውበት በማስጠበቅ መልኩ አገልግሎቱን መስጠት እንደሚቻል ተናግሯል፡፡ ከዚህ ሥራ ውጪም ከጓደኞቹ ጋር በመደራጀት የፓርኪንግ ሥራ አገልግሎት እንደሚሰጡ አክሏል፡፡
በአካባቢው በመንግሥት በኩል የተሠራ መፀዳጃ ቤት ቢኖርም፣ የሚጠቀመው ሰውና መፀዳጃ ቤቱ ባለመመጣጠኑ ምክንያት ሰዎች ሲቸገሩ እንደነበር የሚገልጸው፣ ወጣቱ ይህንን ታሳቢ በማድረግ ወደዚህ ሥራ መግባታቸውን አክሎ ገልጿል፡፡
በተለይ ሆቴል ቤቶች ለተገልጋዮች ካልሆነ መፀዳዳት ለሚፈልጉ ሰዎች በራቸው ክፍት ባለመሆኑ ሲንገላቱና በየአጥር ጥግ ሥር ሲጠቀሙ እንደነበር፣ ሴት ልጆች ደግሞ ይበልጥ እየተቸገሩ መሆኑን ተናግሯል፡፡
ይህ ሥራ በተለያዩ ከተሞች ላይ ተግባራዊ እየሆነ እንደሚገኝ፣ በዚህም ተጠቃሚ የሆኑ ሰዎች አንድም ራሳችውን ከተለያዩ በሽታዎች ማዳናቸውን በሌላ በኩል ደግሞ ዕፎይታን ማግኘታቸውን አስታውሷል፡፡
የአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ፅዳት አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወ/ሮ አስቴር ጫንያለው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአካባቢው ላይ የፕላስቲክ ባልዲ አስቀምጠው ለማኅበረሰቡ የውኃ ሽንት አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያደርጉ ወጣቶች ሕገወጥ ሲሆኑ አገልግሎቱን በራሳቸው ተነሳሽነት እየሰጡ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
አገልግሎቱን የሚሰጡ ወጣቶች በአንድ በኩል የሚበረታቱ መሆኑን የሚናገሩት ወ/ሮ አስቴር፣ ነገር ግን ከተማዋ የብዙ ዜጎች መዳረሻና ዋና ቦታ እንደመሆኗ መጠን አስፈላጊውን ፅዳት በማድረግ በቦታው ላይ አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶች በቅርቡ የማስነሳት ሥራ እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ዘመናዊ የመፀዳጃ ቦታ በአካባቢው ላይ እንዲገነባ ጥያቄ ማቅረባቸውን፣ ይሁን እንጂ እስካሁን ጥያቄያቸው መልስ እንዳላገኘና ወጣቶቹ ዘመናዊ መፀዳጃ ቤት ላይ እንዲሠሩ መንግሥት ትልቁን ኃላፊነት መወጣት አለበት ብለዋል፡፡
ከግንባታ ፈቃድና ከውበት መናፈሻ ጋር በመነጋገር ወጣቶች የሚሠሩበት ቦታ ሙሉ በሙሉ እንዲነሱ ውሳኔ መወሰኑን፣ ውሳኔው የተላለፈበት ምክንያት በየአካባቢው ከፍተኛ ሽታ በመፍጠሩና የከተማዋን ውበት በማጥፋቱ ጭምር መሆኑን ለሪፖተር ገልጸዋል፡፡
ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የገነባው መፀዳጃ ቤት በየአካባቢው እንዳለ የገለጹት ኃላፊዋ፣ ይህም ቦታ የማኅበረሰቡን ጤና ባማከለ መልኩ በመገንባቱ ምክንያት አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል አገልግሎቱን ስለሚያገኝ ለተለያየ የጤና እክል አይጋለጥም ብለዋል፡፡
ከዚህ በፊት ይህ ዓይነቱ አገልግሎት እንደማይታይ፣ አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል በየአጥር ጥግና በየወንዝ ዳሩ ይፀዳዳ እንደነበር ኃላፊዋ አብራርተዋል፡፡
መንግሥት በከተማዋ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ዘመናዊ የመፀዳጃ ቤቶችን በመገንባትና ማኅበረሰቡ በፈለገው ልክ እንዲጠቀም በማድረግ የበኩሉን ኃላፊነት መወጣት እንዳለበትና ባለሀብቶችም በዚህ ዘርፍ አሻራቸውን እንዲጥሉም ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡