Sunday, December 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊየማኅፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት ከ55 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ልጃገረዶች ሊሰጥ ነው

  የማኅፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት ከ55 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ልጃገረዶች ሊሰጥ ነው

  ቀን:

  የማኅፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት ለ55,342 ልጃገረዶች ሊሰጥ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡

  ክትባቱ የሚሰጠው በ2013 ዓ.ም. የመጀመርያውን የማኅፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት ወስደው፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ሁለተኛ ዙር ያልወሰዱና በዘንድሮ 14 ዓመት ለሞላቸው ታዳጊዎች መሆኑን፣ ጥር 5 ቀን 2014 ዓ.ም. በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ተገልጿል፡፡

  የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዮሐንስ ጫላ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ ክትባቱ የሚሰጠው ዕድሜያቸው 14 ዓመት ለሆናቸው በግልና በመንግሥት ትምህርት ቤቶች እንዲሁም በጤና ጣቢያ ውስጥ ነው፡፡

  በዚህ ዓመት 14 ዓመት የሞላቸውና ክትባቱን ለመጀመርያ ጊዜ የሚወስዱ ልጃገረዶች የሚከተቡም ይሆናል፡፡ የመጀመርያ ዙር ክትባትን የሚያገኙት 28,291 ልጃገረዶች ሲሆኑ፣ 27,051 የሚሆኑ ደግሞ ሁለተኛ ዙር የሚወስዱ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

  የማኅፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት ከጥር 4 እስከ ጥር 10 ቀን በዘመቻ እንደሚሰጥ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

  ዕድሜያቸው 14 ዓመት የሞላቸው ልጃገረዶች ክትባቱን በትምህርት ቤቶችና ከትምህርት ውጪ ያሉት ደግሞ በጤና ጣቢያዎች እንዲያገኙ ይደረጋልም ብለዋል፡፡

  የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክትባት የወሰዱ ታዳጊዎች እንዳሉ የጠቆሙት ዮሐንስ (ዶ/ር)፣ እነዚህ ታዳጊዎች (ልጃገረዶች) ክትባቱን ከወሰዱ ከ14 ቀን በኋላ የማኅፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባትን እንዲወስዱ ይደረጋል ብለዋል፡፡

  የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ክትባት ወስደው 14 ቀን ያልሞላቸው ልጃገረዶች የማኅፀን በር ካንሰር ክትባቱን እንዲያገኙም ተመቻችቷል ብለዋል፡፡

  ዕድሜያቸው 14 ዓመት ለሞላቸው ልጃገረዶች ብቻ መስጠት ያስፈለገው፣ ለማኅፀን በር ካንሰር ተጋላጭ ከመሆናቸው በፊት ክትባቱን በመስጠት ትውልድን መታደግ ስለሚጠበቅ መሆኑን አክለዋል፡፡

  የ14 ዓመት በሞላቸውን ላይ ብቻ ትኩረት የተደረገውም የክትባት እጥረት በመኖሩ መሆኑን፣ የ12 እና የ13 ዓመት ታዳጊዎችንም መከተብ ያስፈልግ እንደነበር አስረድተዋል፡፡

  ለማኅፀን በር ካንሰር በይበልጥ ተጋላጭ የሚሆኑበት ዕድሜ 14 ዓመት ሲሞላቸው መሆኑን፣ ከዚህ ዕድሜ በላይ ላሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች የማይሰጠው መጀመርያ ምርመራ ማድረግ ስላለባቸው መሆኑን አብራርተዋል፡፡

  ዮሐንስ (ዶ/ር)፣ ‹‹እነዚህ ልጃገረዶች መጀመርያ ቅድሚያ የተሰጣቸው ፆታዊ ግንኙነት ከመጀመራቸው በፊት ክትባቱን ካገኙ ለቫይረሱ ተጋላጭ ስለማይሆኑ ነው፤›› ብለዋል፡፡  

  የማኅፀን በር ካንሰር በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲታይ፣ ሴቶች ላይ ከሚከሰቱ የካንሰር ዓይነቶች በአራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይቀመጣል፡፡

  የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው፣ ሒውማንፓፒሎማ ቫይረስ (ኤችፒቪ) በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፍ ቫይረስ ነው፡፡ ቫይረሱ ለማኅፀን በር ካንሰር ዋነኛ አጋላጭ ነው፡፡

  ከ99 በመቶ በላይ የሚሆነው የማኅፀን በር ካንሰር ከሒውማንፓፒሎማ ቫይረስ ጋር በተያያዘ የሚመጣ ሲሆን፣ በወቅቱና በጊዜው ክትባት ከተወሰደ ቫይረሱን በቀላሉ መከላከል ይቻላል፡፡

  በዚህ ቫይረስ በየዓመቱ 7,000 የሚሆኑ ሴቶች ሲጠቁ፣ ከእነዚህ ውስጥ 5,000 የሚሆኑት ደግሞ ይሞታሉ፡፡

  እየተስፋፋ የመጣውን የማኅፀን በር ካንሰር ለመከላከል በአገር አቀፍ ደረጃና በአዲስ አበባ ከተማ ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ ክትባቱ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡

  የማኅፀን በር ካንሰር ክትባቱ 14 ዓመት ለሆናቸው ልጃገረዶች በዓመት ሁለት ጊዜ በየስድስት ወራት ልዩነት የሚሰጥ ሲሆን፣ በአገር አቀፍ ደረጃ 3.6 ሚሊዮን በአዲስ አበባ ከተማ ደግሞ 150,000 ለሚሆኑ ልጃገረዶች ክትባቱ መሰጠቱ ተገልጿል፡፡  

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...