Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊዳያስፖራውን ከኢትዮጵያ ጋር የሚያስተሳስረው የቴክኖሎጂ ፎረም

ዳያስፖራውን ከኢትዮጵያ ጋር የሚያስተሳስረው የቴክኖሎጂ ፎረም

ቀን:

በውጭ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ከቤተሰብ ጀምሮ አገራዊ ልማትን በመደገፍ፣ በኢንቨስትመንት በመሳተፍና ሰብዓዊ መብት ጥሰትን በመቃወም የሚያደርጉትን ተሳትፎ ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

ለአገራቸው ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ የመጣው ደግሞ በኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል ጦርነት ከተቀሰቀሰና ኃያላን አገሮችና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ለአንድ ወገን ያደላ አቋም ከያዙ በኋላ ነው፡፡

ከ‹‹ኖ ሞር›› ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ጀምሮ በአገር ውስጥ በሚደረጉ ድጋፎች ዕውቀታቸውንና ገንዘባቸውን ሲለግሱ ከከረሙት ዳያስፖራዎች ውስጥም የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የበዓል ጥሪን ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ የገቡት በተዘጋጀላቸው መርሐ ግብር መሠረት በተለያዩ የውይይት መድረኮች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ጋዜጠኞችን ጨምሮ በተለያዩ ሙያዎች የተሰማሩ ዳያስፖራዎችም ለኢትዮጵያ ሊያደርጉ በሚችሉት አበርክቶና መስተካከል ስላለባቸው አደናቃፊ አሠራሮች መክረዋል፣ ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡

ዳያስፖራውን

 

ምክክር ከተደረገባቸው መድረኮች አንዱ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር ‹‹የዳያስፖራው ሚና በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን›› የሚለው ይገኝበታል፡፡

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በሰኔ 2012 ዓ.ም. ከፀደቀ ወዲህ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የቆመባቸውን የግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግና አገልግሎት ዘርፎች እንዲሁም የሥራ ዕድል ፈጠራና የውጭ ምንዛሪ ግኝት መሠረት አድርጎ የተዘጋጀውን ስትራቴጂ በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ ይህን ሥራ በተጠናከረ መልኩ መሬት ለማውረድ ደግሞ ዕውቀቱና ክህሎቱ ያላቸው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲተፉ ጥሪ ቀርቧል፡፡

ጥር 5 ቀን 2014 ዓ.ም. በተዘጋጀው መድረክም ዳያስፖራው ከመንግሥትና ከግሉ ዘርፍ ጋር በመቀናጀት በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ ባሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ምክክር ተደርጓል፡፡

የኢኖቬሽንና ምርምር ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) 115 ሚሊዮን ገደማ ሕዝብ ያላትን አገር ወደ ብልፅግና ለማሸጋገር የዳያስፖራ፣ የግል ባለሀብቶችና ተመራማሪዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግሥት በምርምርና ልማት፣ በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ ኢንቨስትመንትን ለማሳለጥ በርካታ ሪፎርሞችን እያደረገ ነው ያሉት ባይሳ (ዶ/ር)፣ ዳያስፖራው በዘርፉ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የአይሲቲና ዲጂታል ኢኮኖሚ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ ዓሊ በበኩላቸው፣ ዳያስፖራው በሚኖርበት አገር ለኢትዮጵያ ያደረገውን ታሪክ የማይረሳው ተጋድሎን፣ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂና በኢኖቬሽን ዘርፍም እንዲደግመው አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንድትሆን በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍም ዳያስፖራው በሚችለው ሁሉ አገሩን እንዲደግፍ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ ከመድረኩ ተሳታፊዎችም ዕውቀታቸውን፣ ክህሎታቸውንና ሀብታቸውን ለአገራቸው እንዲያውሉ በኢትዮጵያ ሊያሠራና ታች ድረስ የሚወርድ መደላድል ያስፈልጋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ለመሰማራት በመንግሥት በኩል ፍላጎቱ ቢኖርም፣ እዚህ ከመጡ በኋላ ለመሥራት እንደሚቸገሩ፣ አሠራሮች ላይ ክፍተት እንዳለ፣ ይህንን ችግር የሚፈታ አካል ሊኖር እንደሚገባም ጠይቀዋል፡፡

ይህን ችግር ይፈታል፣ ዳያስፖራውን ከመንግሥትና ከግሉ ዘርፍ ጋር በማገናኘት በኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሰማራ ያግዛል የተባለው የዳያስፖራ ፎረምም ተመሥርቷል።

 በኢትዮጵያ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ዕምቅና ያልተነኩ የሥራ ዓይነቶች መኖራቸው በመድረኩ የተገለጸ ሲሆን፣ በተለያዩ የቴክኖሎጂ ዘርፎች ለመሰማራትም ሆነ የዕውቀት ሽግግር ለማድረግ፣ በአንድ ጥላ ሥር ሆኖ ዕውቀትና ሀብትን በማጣመር ለመሥራትም ፎረሙ ጉልህ ሚና ይኖዋል ተብሏል፡፡

በልማት ለመሳተፍ መረጃ ከማግኘት ጀምሮ ጉዳዮችን በሠለጠነና ባጠረ መንገድ ለመጨረስ ከባድ መሆኑን፣ ሥራን ለመሥራት ከታቀደው ጊዜ በላይ እንደሚባክን፣ የዕውቀትም ሆነ አዋጆችና መመርያዎችን ታች ድረስ በመተግበሩና አገሪቷ የምትፈልገውን ልማት ዕውን በማድረጉ በኩል ክፍተት መኖሩን በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩና ለመሰማራት በሒደት ላይ ያሉ ዳያስፖራዎች ያነሱ ሲሆን፣ የፎረሙ መመሥረት ችግሮችን ከመንግሥት ጋር ሆኖ ለመፍታት፣ አስፈላጊ ፖሊሲዎችና መመርያዎች እንዲወጡ ለማስቻልና መረጃን በቀላል አግኝቶ ወደ ሥራ ለመግባት ያስችላል ተብሏል፡፡

የፎረሙን መመሥረት አስመልክቶ ለሪፖርተር ማብራሪያ የሰጡት በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር አብዮት ባዩ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ በአገር ውስጥ ያለውም ሆነ ውጭ ያለው ዳያስፖራ ሙያውንና በምን ዘርፍ አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚችል ምዝገባ ይከናወናል፡፡ በዲጂታል ኢኮኖሚ፣ በጥናትና ምርምር፣ በፈጠራና በሌሎችም ዘርፎች ግብረ ኃይል ተቋቁሞም ወደ ሥራ ይገባል፡፡

በመድረኩ በተደጋጋሚ የተነሳው በቴክኖሎጂው ዘርፍ ያሉ ዳያስፖራዎች ዕውቀታቸውን፣ ክህሎታቸውንና ሀብታቸውን ለአገራቸው ለማካፈል አብረዋቸው የሚሠሩ ተቋማትና የት መሄድ እንዳለባቸው አለማወቃቸው ነው፡፡ አብዮት (ዶ/ር) ይህን አስመልክተው እንዳሉት ፎረሙ እንዲህ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ያስችላል፡፡

በተወሰኑ አገሮች መረጃ የሚሰጡ ባለሙያዎችና የራሱ ድረ ገጽ እንደሚኖረው የገለጹት አብዮት (ዶ/ር)፣ ግንኙነቶችን የሚያመቻቹ ባለሙያዎች መመደባቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በመንግሥትና በዳያስፖራው መካከል ግንኙነቱን ለማሳለጥ በሰሜን አሜሪካ ሰሎሞን ነጋሽ (ፕሮፌሰር)፣ በደቡብ አፍሪካ ፍሥሐ መኩሪያ (ዶ/ር)፣ በካናዳ መስፍን ንጋቱ (ዶ/ር)፣ በአውሮፓ ፍፁም ደምሴ እንዲሁም በአውስትራሊያ ኢያሱ ተሾመ  የተመረጡ መሆናቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

እነዚህ ባለሙያዎች በየሙያው ፍላጎቱ ያላቸውን ዳያስፖራዎች የሚሰበስቡ ሲሆን፣ ይህ የአባላት ስብሰባ እንደተጠናቀቀ በሚደረገው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የመተዳደሪያ ደንብና ሌሎች የአሠራር ሕጎች የሚወጡ ይሆናል፡፡

የፎረሙ ዓላማ ዳያስፖራው በሳይንስ፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ እንዲሳተፍ መደላድል መፍጠር ሲሆን፣ ይህም በአገር ውስጥ በዘርፉ ለተሰማሩትም ሆነ ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ለመሥራት ፍላጎት ላላቸው አሠራርን ያቀላጥፋል ተብሏል፡፡

በዘርፉ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉ የኢኖቬሽን፣ ቴክኖሎጂና ሳይንስ ባለሙያዎች በበጎ ፈቃደኝነት አባል መሆን እንደሚችሉ፣ በዓመት አንዴ በበይነ መረብ (ቨርቹዋል) ወይም የገጽ ለገጽ ጉባዔ እንደሚኖርም ተነግሯል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ በተለያዩ የቴክኖሎጂ ዘርፎች የተሰማሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተሞክሯቸውንም አካፍለው ነበር፡፡ ሁሉም ያጠነጠኑበት ዋና ጉዳይ በዘርፉ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመሰማራት የዕውቀትን ጨምሮ የተለያዩ ችግሮች ቢኖሩም ኢትዮጵያ ከችግሮች እንድትወጣ በትዕግሥት መሥራትን ነው፡፡

በኢትዮጵያ ለመሥራት የሚመጡ ዳያስፖራዎች፣ ትርፍን ብቻ አልመው ሳይሆን፣ አገርን ወደ ተሻለ ዕድገት ለማራመድ፣ አስፈላጊ ዘርፎችን ለማስተዋወቅ፣ የዕውቀት ክፍተቶችን ለመሙላት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ አስበው መሆን እንዳለበት መክረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...