በካሜሩን አስተናጋጅነት በመካሄድ ላይ በሚገኘው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በምድብ አንድ ከአስተናጋጇ ካሜሩን፣ ቡርኪና ፋሶና ኬፕ ቨርዴ ጋር ተደልድሎ ሦስት ጨዋታዎችን ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የካሜሩን ቆይታውን አጠናቋል፡፡ ቡድኑ በኬፕ ቨርዴና በካሜሩን ተሸንፎ፣ ከቡርኪና ፋሶ ጋር ደግሞ በአቻ ውጤት መለያየት በመቻሉ አንድ ነጥብ ይዞ ነው የመጀመርያው ተሰናባች መሆኑን ያረጋገጠው፡፡
ውጤቱን ተከትሎ የስፖርት ቤተሰቡን ጨምሮ በርካቶች አዎንታዊና አሉታዊ አስተያየቶችን እየሰጡ ይገኛል፡፡ አንዳንዶቹ አሠልጣኝ ውበቱ አባተና ረዳቶቻቸው የብሔራዊ ቡድኑን ኃላፊነት ከተቀበሉበት ጊዜ ጀምሮ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ጨምሮ ያደረጓቸው ጨዋታዎችና ያስመዘገቧቸውን ውጤቶች በመቶኛ በማሥላት ጊዜ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ሲናገሩ፣ በሌላ ወገን ደግሞ በተለይ ቡድኑ ከሚከተለው የጨዋታ ዘይቤ ጋር በማገናኘት ለውጤቱ መበላሸት ተጠያቂ የሚያደርጓቸው አልጠፉም፡፡
ለአሠልጣኝ ውበቱ አባተና ስብስባቸው ጊዜ እንዲሰጣቸው የሚጠይቁት የራሳቸውን ዕይታ ያንፀባርቃሉ፡፡ ‹‹አንድን ግብ ለማሳካት ከሚቀመጡ መለኪያዎች የስኬት ጉዞዎች ቢሆኑም፣ ከዚያ ጫፍ ለመድረስ ግን ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖ በስኬት ብቻ የታጀበ ጉዞ ማድረግ አዳጋች ነው፡፡ ሒደት፣ መውደቅና መነሳት የሚጠይቅ ነው፡፡ መነሳትና መውደቅ የሌለበት ግብ ያንን ያህል አርኪ ሊሆን አይችልም፡፡ በዚህ ሁሉ ሒደት ትልቁ ቁም ነገር ከውድቀት መማር መቻልና የማሻሻያ መንገዶችን ነድፎ ጉዞን ማቃናት መቻል ነው፤›› የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መማር ካለበት ከዚህ በፊት እንደነበረው ‹‹ከአንድ ሰሞን ጫጫታና ሆይ ሆይታ›› በመውጣት ከካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ከነበሩበት ጠንካራና ደካማ ጎኖች በመነሳት ራሱን መፈተሸ እንደሚጠበቅበትም እየተነገረ ይገኛል፡፡ ቡድኑ በምድቡ ካደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች ከረፈደም ቢሆን፣ በተለይ ከሥልጠና ጋር ተያይዞ ከሚነገረው አስተሳሰብ በመውጣት የአሠልጣኙ ስብስብ የራሱን የጨዋታ ዘይቤ የተከተለበት መንገድ ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚገባ ጭምር የሚናገሩ አልጠፉም፡፡
በጨዋታው ሒደት የቁጥር መረጃዎች (ስታስቲክስ) ይህን የሚያጠናክሩ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመጀመርያው ከኬፕ ቨርዴ ጋር በነበረው ጨዋታ ምንም እንኳ የቡድኑ እንቅስቃሴ በራስ ሜዳ ላይ ያመዘነ ቢሆንም፣ በአጠቃላይ ወደ ኬፕ ቨርዴ ግብ ክልል የተሞከሩ ኳሶች 11 ሲሆኑ፣ ሦስት ጊዜ ለግብ የቀረቡት ሙከራዎችን አድርጓል፡፡ በተቃራኒው የኬፕ ቨርዴ ቡድን ደግሞ ሰባት ሲሞክር፣ ለግብ የቀረበ ሙከራ ያደረገው አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡
የኳስ ቁጥጥርን በሚመለከት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 57 በመቶ ሲሆን፣ በኬፕ ቨርዴ በኩል ደግሞ 43 በመቶ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ቡድን 500 ጊዜ ሲቀባበል፣ በኬፕ ቨርዴ በኩል ደግሞ 387 ጊዜ እንደነበር የቁጥር መረጃው ያሳያል፡፡ ከዚህ ውስጥ የተሳካ የኳስ ቅብብል በማድረግ ረገድ የኢትዮጵያ ቡድን 84 በመቶ ሲሆን፣ በኬፕ ቨርዴ በኩል 78 በመቶ ነበር፡፡ የማዕዘን ኳሶችን በሚመለከት ኢትዮጵያ ስድስት ጊዜ ስታገኝ፣ ኬፕ ቨርዴ አንድ ጊዜ ማግኘቷን ነው መረጃው የሚያሳየው፡፡
ከአስተናጋጇ ካሜሩን ጋር በነበረው ጨዋታ የካሜሩን ቡድን 17 ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ግብ ክልል ሲሞክር፣ የኢትዮጵያ ቡድን ደግሞ 12 ጊዜ ሞክሯል፡፡ ከዚህ ውስጥ ካሜሩን ሰባት ጊዜ ለጎል የቀረበ ሙከራ ሲያደርግ፣ በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ አምስት ጊዜ ተሞክሯል፡፡ በአጠቃላይ የኳስ ቅብብል ካሜሩን 51 በመቶ ሲሆን በኢትዮጵያ በኩል 49 በመቶ ነበር፡፡
ውጤቱ ምንም እንኳ በካሜሩን 4 ለ 1 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ቢሆንም፣ የቁጥር መረጃው እንደሚያሳየው የካሜሩን ቡድን 452 ጊዜ ኳስ ሲቀባበል፣ በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ 456 ጊዜ እንደነበር ያሳያል፡፡ በዚህ ሒደት ካሜሩን 85 በመቶ የተሳካ የኳስ ቅብብል ያደረገው ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በኩል 86 በመቶ ነበር፡፡ የማዕዘን ኳሶችን በሚመለከት ካሜሩን ሰባት ጊዜ ሲያገኝ፣ በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ አንድ ጊዜ መሆኑን ያሳያል፡፡
በምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከተጋጣሚው ቡርኪና ፋሶ አንፃር ሲታይ አበረታች እንደነበር በቁጥር የተደገፈው መረጃ ያሳያል፡፡ በመረጃው መሠረት የኢትዮጵያ ቡድን በአጠቃላይ 11 ጊዜ ወደ ቡርኪና ፋሶ ግብ ክልል ሲሞክር፣ ከዚህ ውስጥ ስድስቱ ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርጓል፡፡ በተቃራኒው ቡርኪና ፋሶ ስድስት ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ግብ ክልል ሲሞክር ከዚህ ውስጥ ሁለት ጊዜ ብቻ ነበር ለግብ የቀረበ ሙከራ ያደረገው፡፡
ያልተሳካ የኳስ ቅብብል ስንመለከት የኢትዮጵያ ቡድን 502 ሲሆን፣ በተቃራኒው ቡርኪና ፋሶ 387 ያልተሳካ የኳስ ቅብብል አድርጓል፡፡ ከዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ ቡድን 81 በመቶ የተሳካ የኳስ ቅብብል ሲያደርግ፣ ቡርኪና ፋሶ ደግሞ 75 በመቶ መሆኑን ያሳያል፡፡ የማዕዘን ኳሶችን በሚመለከት በተክለ ሰውነታቸውም ሆነ በአካል ብቃታቸው ከኢትዮጵያ በእጅጉ ልዩነት እንደነበራቸው ሲነገርላቸው የነበሩት ቡርኪና ፋሶዎች አምስት ጊዜ ያገኙ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ ስድስት ጊዜ ስለመሆኑ የቁጥር መረጃው ያመለክታል፡፡
ጨዋታውን የተከታተሉ ሙያተኞች ብሔራዊ ቡድኑ ባደረጋቸው ሦስቱም ጨዋታዎች በቁጥር መረጃው መሠረት ብልጫ ቢኖረውም፣ የቁጥር መረጃውን ወደ ውጤት በመቀየሩ ረገድ ግን ከፍተኛ ክፍተት የነበረበት መሆኑ ይናገራሉ፡፡ እንደ ሙያተኞቹ ከሆነ ችግሩ የሚመነጨው በዋናነት ከሥልጠና ጋር ተያይዞ ብሔራዊ ቡድኑ በተለይ ካሜሩን ላይ ካደረጋቸው ጨዋታዎች በመነሳት የተጋጣሚ ቡድኖች ወቅታዊ ሁኔታና የጨዋታ ዘይቤ ግምት ውስጥ አስገብቶ በዚያው ልክ የቡድኑን እንቅስቃሴና ውህደት የማጣጣም የአቅም ውስንነት እንደነበር ያስረዳሉ፡፡
የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከቡርኪና ፋሶ ጨዋታ በኋላ ከጨዋታው ጋር ተያይዞ በሰጡት ማብራሪያ፣ የቡድናቸው ትልቁ ክፍተት ‹‹ልምድ ማጣት›› የሚለውን መጥቀሳቸው ይታወሳል፡፡ አሠልጣኙ ለብሔራዊ ቡድኑ ውጤት ማጣት ያቀረቡት ምክንያት እንደ አንድ ክፍተት ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባው፣ ነገር ግን ከዝግጅት ጋር ተያይዞ አሠልጣኝ ውበቱና ስብስቡ፣ በተለይ መከተል ስለሚገባቸው የጨዋታ ዘይቤ ጋር ተያይዞ ከሚደመጠው አስተያየት ወጥተው፣ ቡድናቸው ለካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ ሊኖረው ስለሚገባው የጨዋታ ዘይቤና ቁመና ምን መምሰል እንዳለበት በውል የተረዱት ስለመሆኑ ይጠራጠራሉ፡፡
ምክንያቱን አስመልክቶ ሙያተኞቹ እንዲህ ይላሉ፡- ‹‹ብሔራዊ ቡድኑ በሦስቱም ጨዋታ ላይ ያሳየው ብቃትና የጨዋታ አቀራረብ ፍፁም የተራራቀ ነው፡፡ ከኬፕ ቨርዴ ጋር በነበረው ጨዋታ፣ ቡድኑ የመረጠው ጨዋታ በራስ ሜዳ ላይ ካልሆነ ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል ለመጠጋት ሲሞክር እንቅስቃሴው እየተበላሸ ብልጫ እየተወሰደበት ለጥቃት ሲጋለጥ ታይቷል፡፡ ከአስተናጋጇ ካሜሩን ጋርም ቢሆን ቡድኑ ኳስ ከኋላ አደራጅቶ ለመውጣት አልፎ አልፎ የሚያደርጋቸው ሙከራዎች ካልሆኑ፣ በአሁኑ ወቅት እግር ኳስ ከደረሰበት ደረጃና እንቅስቃሴ አንፃር ይህ ነው ሊባል የሚችል ሙከራ አለማድረጉ በግልጽ ታይቷል፤›› በማለት የአሠልጣኝ ውበቱ አባተን የጨዋታ ምርጫና አቀራረብ ይተቻሉ፡፡
ከቡርኪና ፋሶ ጋር በነበረው ጨዋታ ግን ቡድኑ በሁሉም ረገድ ከተጋጣሚው ተሽሎ የቀረበበትን የጨዋታ ዘይቤ መከተል መቻሉ፣ አሠልጣኝ ውበቱ አባተና ስብስባቸው ቡድናቸው ቀደም ሲል ለካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ መዘጋጀት ያለበትን ቅድመ ዝግጅት በውል ተረድተው እንዳልተዘጋጁ፣ ቡድኑ ኬፕ ቨርዴ ላይ ካሳየው ድክመት ካሜሩን ላይ፣ እንዲሁም ካሜሩን ላይ የታየበትን ክፍተት ደግሞ ቡርኪና ፋሶ ላይ በተሻለ አቀራረብ ሙሉ ዘጠና ደቂቃውን ለማጠናቀቅ የነበረው የተጫዋቾቹ ቁርጠኝነት አመላካች ስለመሆኑ ጭምር ያስረዳሉ፡፡
በመጨረሻም በተለይ ከሥልጠና እንዲሁም ከጨዋታ ዘይቤና አቀራረብ ጋር አሠልጣኝ ውበቱ አባተና የአሠልጣኝ ስብስባቸው በራሱ አስተሳሰብና እምነት ሊቆም እንደሚገባና ውጤቱ ምንም ሆነ ምን ኃላፊነት መውሰድ መቻል እንዳለበት ያምናሉ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከቡርኪና ፋሶ ጋር በነበረው ጨዋታ በእንቅስቃሴ ብልጫ ለመውሰዱ ሌላው ማሳያ ከኢትዮጵያ ቡና የተመረጠው አማኑኤል ዮሐንስ የዕለቱ ጨዋታ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ መመረጥ መቻሉ ነው፡፡
በሌላ በኩል አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ቀደም ሲል በመግለጫቸው እንደተናገሩት፣ ብሔራዊ ቡድን በተለይ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎን ጨምሮ በሌሎችም አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች ብቁ ተፎካካሪ እንዲሆን ከተፈለገ፣ የተሻለ ልምድ ሊገኝባቸው ከሚችሉ ብሔራዊ ቡድኖች ጋር የተለያዩ የወዳጅነት ጨዋታዎች ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ የሚናገሩ አልጠፉም፡፡