- በጥር ዘጠኝ ቀኖች 142 ሰዎች ሞተዋል
የጥምቀት በዓልን ኅብረተሰቡ ሲያከብር ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ራሱን በመጠበቅ በከፍተኛ ጥንቃቄ ሊሆን እንደሚገባ የጤና ሚኒስቴር ማሳሰቢያ ሰጠ፡፡
የከተራና የጥምቀት በዓልን አስመልክቶ የጤና ሚኒስቴር በዋዜማው ባስተላለፈው መልዕክት እንደገለጸው፣ የከተራና የጥምቀት በዓል በምዕመናን በብዛት የሚታጀብና አካላዊ ንክኪውና ጥግግቱ የጠነከረ ከመሆኑ ባሻገር ሰዎች በተጠጋጋና በተቀራረበ መንገድ ስሜቶቻቸውን የሚገልጹባቸው ቀናት ናቸው፡፡ በተለይ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ከሰው ወደ ሰው በማስተላለፍ ረገድ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራልና በዓሉን ለማክበር የሚሰባሰቡ ሰዎች ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በእስካሁኑ ሒደት ከ4.2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተመርምረው ከ459 ሺሕ ያላነሱ ሰዎች ላይ ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፡፡ 7,162 ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸው ማለፉን፣ 435 ሰዎች በጽኑ ሕመም ላይ እንዳሉም አስታውቋል፡፡ ከጥር 1 ቀን እስከ ጥር 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ 142 ሰዎች መሞታቸውም ታውቋል፡፡
በመሆኑም የበዓሉ ተሳታፊ ምዕመናን በተቻለ መጠን ርቀታቸውን በመጠበቅ ከንክኪ በመቆጠብና በተደጋጋሚ እጃቸውን በማጽዳት እንዲሁም የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ሳያወልቁ በመንቀሳቀስ በዓሉን ማክበር እንዳለባቸው አጥብቆ አሳስቧል፡፡
‹‹ዛሬን ተጠንቅቀን በጤንነትና በሕይወት ከቆየን ወደፊትም ብዙ በዓሎችን በጋራ እናከብራለን!›› ሲልም አስገንዝቧል፡፡
በተያያዘም የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንዳመለከተው፣ እየታየ ያለው የወረርሽኙ ሥርጭት በተከታታይ ቀናት ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት፣ ማኅበራዊ መሰባሰቦችና የተለያዩ ስብሰባዎች ጋር ተያይዞ በከፍተኛ ፍጥነት በመሠራጨት በርካታ ሰዎችን ሊይዝና የጤና እክሎችን ሊያስከትል ይችላል፡፡
ተገቢው ጥንቃቄና የመከላከል ሥራ መሥራት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን የጠቆመው ኢንስቲትዩቱ ኅብረተሰቡ፣ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች የሃይማኖት መሪዎች፣ የመንግሥት አመራሮች፣ አስተማሪዎች፣ ተማሪዎችና የወላጅ ተማሪና አስተማሪ ኮሚቴ፣ ከምንጊዜውም በተሻለ መንገድ በዓላትን አስመልክቶ በሚኖሩ ልዩ ልዩ ዝግጅቶች ተገቢው የኮቪድ-19 ጥንቃቄ መደረጉን እንዲያረጋግጡ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የበሽታው ምልክቶች ሲታዩ በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ አስቸኳይ ምርመራ ማድረግና ቫይረሱ መኖሩ ከተረጋገጠ አስፈላጊውን የባለሙያ ዕርዳታ በጊዜ ማግኘት ይገባል ሲልም መክሯል፡፡
በሌላ በኩል የኮቪድ-19 ክትባትን ያልተከተቡ በአቅራቢያ ወደሚገኝ ጤና ተቋም በመሄድ እንዲከተቡ ከዚህ በፊት ሙሉ የኮቪድ-19 ክትባት ወስደው ስድስት ወርና ከዚያ በላይ ከሆነ የማጠናከሪያ ክትባት መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን ተቋሙ አስታውቋል፡፡