Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልኤጲፋንያ- የጥምቀት ክብረ በዓል ከከተራ እስከ ቃና ዘገሊላ

ኤጲፋንያ- የጥምቀት ክብረ በዓል ከከተራ እስከ ቃና ዘገሊላ

ቀን:

በኦርቶዶክሳዊቷ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን፣ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ጥር 11 ቀን የሚከበረው የጥምቀት በዓል፣ እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ 30 ዓመት ከሞላው በኋላ በአጥማቂው ቅዱስ ዮሐንስ እጅ በፈለገ ዮርዳኖስ ጥር 11 ቀን 5531 ዓመተ ዓለም (31 ዓ.ም.) የተጠመቀበትን ዕለት የሚያስታውስ ነው፡፡ ኤጲፋንያ በመባልም ይታወቃል፡፡

በቅዱስ ወንጌል እንደተጻፈው፣ እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ሄዶ በዮሐንስ እጅ ተጠምቋል፡፡ ይህንን በማሰብም በየአብያተ ክርስቲያኑ ያሉ ታቦታት ከቅዱስ መንበራቸው  ተነስተው በዓሉ ወደሚከበርበት ባህረ ጥምቀት ይዘልቃሉ፡፡

ዋዜማው ጥር 10 ቀን ከተራ ሲሆን፣ በገጠርም ሆነ በከተማ ታቦታት ከየአብያተ ክርስቲያናቱ ወደ የጥምቀተ ባሕር የሚያደርጉት ጉዞና መንፈሳዊ አዳር በማግሥቱ የጥምቀት ዕለት ‹‹ተጠምቀ ሰማያዊ በእደ መሬታዊ›› ሰማያዊው በመሬታዊው እጅ ተጠመቀን ይዞ የሚኖረው ያሬዳዊ ዝማሬ የበዓሉ ገጽታ ነው፡፡

ከተራ ‹‹ከተረ›› ከሚለው ቃል የተገኘ ሲሆን የሚወርድ ውኃ መገደብ ማለት ነው፡፡ ውኃው የጥምቀት ዕለት ምዕመናን የሚጠመቁበት ነው፡፡ በኢትዮጵያ በገጠራማ አካባቢዎችም ይሁን በከተማ ጥምቀት የሚከበረው ውኃ በሚገኝበት አካባቢ ነው፡፡

በአንድ ወቅት ስለ ከተራ ማብራሪያ የሰጡት አባ ይለ ማርያም መለሰ (ዶ/ር)፣ ‹‹ከተራ ስንል በዋዜማው ምዕመናን ተሰብስበው በአንድነት የሚሆኑበት ነው። ከተራ ማለት መሰብሰብ ክብ ሠርቶ በአንድ ላይ ምስጋና ማቅረብን የሚያመለክት ቃል ነው፤›› ብለዋል፡፡ አያይዘውም ‹‹በአራቱም ማዕዘን ምዕመናን በአንድ ላይ ሆነው በዓሉን ያከብራሉ፡፡ ይህም በዓል መገለጥ /ኤጲፋኒያ/ ይባላል። ይህም ጌታችን በተጠመቀ ጊዜ መገለጥ ሆኗል። የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ አንድነትና ሦስትነት ተገልጿል። ክርስቲያኖችም ይህንን በዓል የምናከብረው ለበረከትና ለረድኤት ነው፤›› ሲሉ አክለዋል።

ከሃይማኖታዊው ሥነ ሥርዓት በኋላ ካህኑ በሃሌታ፣ ወንዱ በሆታ፣ ሴቱ በእልልታ ታቦተ ሕጉን አጅበው፣ እንደያመጣጣቸው ወደየአጥቢያቸው ይመለሳሉ። በዑደታቸውም ምእመናኑ ታቦታቱን በዝማሬያቸው ያጅቡታል።

መምህራኑ እንደሚናገሩት፣ ዘመነ አስተርእዮ (ኤጲፋንያ) የሚባለው፣ ከጥር 11 ቀን ጀምሮ እስከ ጾመ ነነዌ ዋዜማ ያለው ጊዜ ነው (ዘንድሮ እስከ የካቲት 6 ድረስ ይሆናል)። በዚህ ጊዜ ውስጥ አምላክ ሰው ሆኖ በሥጋ መገለጡ፣ በዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜ የአንድነትና የሦስትነት ምሥጢር መታወቁ፣ በቃና ዘገሊላ በተደረገው ሠርግ ላይ የመጀመሪያው ተዓምር በመፈጸሙ፣ አምላካዊ ኃይሉ መገለጡ፣ እየታሰበ ምስጋና ይቀርባል።

በየዓመቱ  በመላ  ኢትዮጵያና ኦርቶዶክሳዊቷ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በምትገኝባቸው አገሮች  የሚከበረው  የጥምቀት በዓል፣ ታቦታት ከመንበራቸው ወጥተው፣ በየባሕረ ጥምቀቱ የሚከበሩ በመሆናቸው፣ አገሬውን ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ መስህብነትን በመጎናጸፉ፣ ቱሪስቶችን እንደሳበ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ እስከ ላሊበላ፣ ከአክሱም እስከ ጎንደር፣ ከማይጨው እስከ ዝዋይ፣ ከሐዋሳ እስከ ጅማ፣ ከአሶሳ እስከ ጋምቤላ በሁሉም ሥፍራዎች በዚሁ ዓይነት ይከበራል። የምዕመናኑም ሆነ የካህናትና ዲያቆናት አለባበስ  በሚማርኩ ባህላዊ አልባሳት የተዋበ በመሆኑ ከውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ ለሚመጡ ጎብኚዎች ሁልጊዜ አዲስ ነው።

የጥምቀት ክብረ በዓል፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን

የሐይቁ ላይ አከባበር

ዓመታዊው የጥምቀት በዓል ከሚከበርባቸው ቦታዎች መካከል በዝዋይ ሐይቅ ውስጥ የሚገኙት ገዳማት ይጠቀሳሉ፡፡ ከአዲስ አበባ 161 ኪሎ ሜትር ርቀት በምትገኘው ዝዋይ (ባቱ) ከተማ ዳርቻ፣ ባለው ሐይቅ የሚገኙት ገዳማት አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ ቅዱስ ሚካኤል፣ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም፣ አርባዕቱ እንስሳትና ፀዴቻ አቡነ አብርሃም ናቸው፡፡ ከአምስቱ ገዳማት አቡነ ተክለሃይማኖትና ደብረ ጽዮን ከደሴታቸው በመውጣት ሦስት ኪሎ ሜትር የሚሆነውን የሐይቁን ክፍል አቋርጠው ምድር ላይ በማክበር ብቸኛ ያደርጋቸዋል፡፡ የተቀሩት ሦስቱ ደግሞ ከሐይቁ ዳር በጣም የራቁ በመሆናቸው ከቤተ መቅደሳቸው በመውጣት በግቢያቸው የሐይቁ ጠርዝ ላይ ድንኳን በመጣል እዚያው ያከብሩታል፡፡

ባህላዊው ገጽታ

‹‹ኅብረ ብዕር›› በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ አቶ ካሕሣይ ገብረእግዚአብሔር   እንደጻፉት፣ ጥምቀት ከመንፈሳዊ በዓልነቱ በተጨማሪ ባህላዊ ገጽታው የጎላ ነው፡፡ ሰው ሁሉ አምሮና ተውቦ አጊጦና ለብሶ የሚታየው በዚህ ጊዜ ነው፡፡ ከዚህም አልፎ ወጣቶች የፍቅርና የዘፈን አምሮታቸውን የሚወጡበት ጊዜም ነው፡፡ በተለይ ልጃገረዶች ተኳኩለውና  ሹሩባ ተሠርተው ከሁሉም በላይ ደግሞ አዲስ ልብስ ለብሰው የሚታዩበት  ከምንጊዜም በላይ ደስ ብሎአቸው ጊዜያቸውን በዘፈንና በጭፈራ የሚያሳልፉበት የዓመቱ ምርጥ ቀን ነው ማለት ይቻላል፡፡

በቀደመው ጊዜ የሎሚ ውርወራው፣ የከተራው ሽልምልም ብትር አሁን አሁን በከፊል ሎሚው ወደ ፕሪም፣ ሽልምልሙ ብትር ወደ ረዥም ቄጠማ (ጨፌ ላይ የሚበቅል) ተለውጦ መታየቱ፣ ከባህላዊ ጭፈራው በተጓዳኝ ወጣቱ በአመዛኙ ከመንፈሳዊ ማኅበራት (ሰንበት ትምህርት ቤቶች) መዘምራን ጋር ወደ ዝማሬ አዘንብሏል፡፡

‹‹እጣን እጣን ይላል መሬቱ፣

ሚካኤል ያረፈበቱ፡፡

ማር ይፈሳል ጠጅ፣

ባርባራቱ ደጅ፡፡›› እያሉ ወጣቶች በዘፈንና በጭፈራ ታቦታቱን የሚያሞጋግሱት በየዓመቱ የጥምቀት በዓል ሲመጣ ነው፡፡ በተለይ በጥምቀት ማግሥት የሚከበረው የቃና ዘገሊላ እና የቅዱስ ሚካኤል በዓላት ላይ ተዘውትሮ ይደመጣል፡፡

የጥምቀት በዓልን ከጃንሜዳ ጋር አስተሳስረው የተመለከቱት የባህል ባለሙያው አቶ ዓባይነህ ታደሰ እንዳመለከቱት፣ ወንድና ሴት ወጣቶች ከቤተሰብ ነፃ ሆነው ለመጫወት እና ለመተዋወቅ የጥምቀት በዓል ምክንያት በማድረግ ወደ ጃንሜዳ መሄድን እንደ ልዩ አጋጣሚ ይቆጥሩታል፡፡

በአገር ባህል ቀሚስ ቀጭን ኩታ ያሸበረቁ በድሪ ያጌጡ ልጃገረዶች አታሞ እየመቱ እንደሚከተለው ይጫወታሉ፡፡

‹‹አባቴ ጊዮርጊስ እኔን ይወደኛል፣

 ብርሌ ስሰጠው ብር ያሠራልኛል፡፡

 የቅዱስ ሚካኤል አፋፉ ደብር፣

 መሳለሚያው ዋርካ ጥዱ ምን ያምር፡፡

 አለው አለው ሞገስ፣

 ታቦት ሲነግሥ፡፡››

በዓለም አቀፍ የፌስቲቫሎች መድበል የአፍሪካ ኤጲፋኒያ/ጥምቀት (The African Epiphany) እየተባለ በዓለም የክብረ በዓላት ድርሳን ላይ በየጊዜው የሚተዋወቀው፣ የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ የማይዳሰስ ወካይ ቅርስነት መመዝገቡ ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...