የዛሬው ጉዞ ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ ነው። አጀማመራችን በፀጥታ የተጠነሰሰ ነው። ተሳፋሪው በሙሉ የሚተነፍስ አይመስልም። በውጥረት የታፈነው ጎዳና መንገደኛውን አየር የነሳው ይመስላል። ጩኸት ኑሮው የሆነው ወያላ ዕድሜው በለቅሶ ተጀምሮ በጩኸት በሚገባደድ ሕዝብ መሀል ያለ ዕረፍት ይጮኻል። እንደ ንጋት ጎርናና ድምፁ ሁሉ ጎርበጥባጣ ኑሮው የሚቀጥል ይመስል እሪ ሲል አይታክትም። ጥሪ በማይፈልገው የትግል ጎዳና ላይ የወያላው ልፋት መና የቀረ ይመስላል። ከወዲያ ወዲህ ሲሯሯጥ ቆይቶ ዳግም ለሌላ ሩጫ መንደር፣ ክልል፣ አገር የሚቀያይረው ሕዝብ ፍልሰት የሚያባራ አይመስልም። ሰው የሚደርስበትን ቦታ እያሰበ ስለአዋዋሉ፣ ስለኑሮው፣ ስለቤተሰቡ፣ ስለሥራው እያውጠነጠነ ባላሰበው በሚገኝበት በዚህ ጊዜ፣ የህልማችንና የሩጫችን ውጤት በአብዛኛው አንገት ያስደፋል። ከደሳሳ ጎጆ መፈናቀልም አለ፡፡ ይህ ደግሞ ከሚችሉት በላይ ነው!
ሲዘሉ መሰበር የመንገዱ ህልውና መሠረት ቢሆንም ቅሉ፣ በዚህ በአገራችን የአረማመድ ዘዬ ሳንዘል በተቀመጥንበት የተሰበርን ጥቂት አይደለንም። የዚህ ጎዳና ትርክት ብዙ ነው። መውጣትና መውረድ አክርማና ስንደዶ ሆነው ያልቀየሱት ጎዳና የትም አገር ታሪክ አይኖርም። ነፃ ብሎ መንገድ፣ እንደ ጨርቅ የሚጠቀለልና አልጋ በአልጋ የሆነ ጎዳና ለሰው ልጅ አይገባውም የተባለ የተፈጥሮ ሕግ ነው። በዚህ ግጭቱ፣ ተንኮሉ፣ ተግዳሮቱና ሸሩ በማያልቅ የሰው ልጅ ሕይወት ሁሉም እንደ ራሱ አረማመድ እየተጓዘ፣ እንደ ሕዝብ ደግሞ በጋራ መጓጓዣ ሆኖ የደቦ ታሪኩን ይፈትላል። ዓመት ይመጣል ዓመት ይሄዳል። በፈተለው ልክ ሁሉም የድርሻውን ሕይወት እየሸመነና እየለበሰ፣ ለታሪክ ደግሞም ለታዛቢ በሩን ይከፍታል። መንገድ ሁሉን ይዳኛል። ዘመን ሁሉን ያስተዛዝባል። የፍትሕ ያለህ ባዩ ወዮታ ግን አድሮ ይባባሳል። መልካሙና በጎው ነገር እየናፈቀ ዕድሜ ይነጉዳል!
ጉዟችን ተጀምሯል። ‹‹ጠላም ይጠጣና ይፈሳል አተላው፣ ጠጅም ይጠጣና ይፈሳል አንቡላው፣ ሥጋም ይበላና ይጣላል አጥንቱ፣ ዕዳም ይከፈላል እየሰነበቱ ዓይኑን ያፈጥና ይቀራል ትዝብቱ፤›› ይላል በክራር የሚቀኘው፡፡ ዕድሜና ዘመን አሳላፊው መንገደኛ ታክሲያችን ጣራ ሥር ተሰባስቦ አንገቱን እየወዘወዘ ያፏጫል። እኩል ሲያፏጭ የቆየው መልሶ፣ ‹‹ማን እያለቀሰ ማን ያፏጫል?›› ብሎ ሲያፈጥበት፣ ‹‹እገጭ እገው ይላል ቆርቆሮ ሲመታ፣ ዘንድሮ ልወዝወዝ በሃቻምናው ፋንታ፤›› ብሎ ዘፋኙ ያቋርጣቸዋል። ‹‹ይወዘውዘኛል ይወዝውዝ አባቱ አለ ያገሬ ሰው። እንዲህ ከተፈጠርኩ ጀምሮ እንደ ዘንድሮ ተወዝውዤ አላውቅም፤›› ሲሉ ከሾፌሩ ጀርባ የተሰየሙ አዛውንት ተናገሩ። ክራሩ ይከራል። ተጫዋቹ፣ ‹‹ዝንጀሮ በገል አድጦት አይወድቅም፣ እንዲህ ያለ ዘመን አጋጥሞኝ አያውቅም፤›› ሲል ከአዛውንቱ ጋር ብቻ ሳይሆን ሐዘን ውስጥ ከወደቁ ጋር አንድ ላይ ያለ ይመስላል። ግጥምጥሞሽ!
‹‹እሱንስ ማን አየ? ጨለማ በመልበስ ከጀመሩት ጎራ ቢሆኑስ ኑሮ?›› ሲላቸው ከጎናቸው የተሰየመ ወጣት ከጀርባቸው የተሰየመች ወይዘሮ ደግሞ፣ ‹‹እሱንማ ኤልፓ ቀድሞ ጀመረው። እንዲሁ ብልጭ ድርግም ሲያደርግብን ዋለ፤›› ብላ አሽሟጠጠች። ‹‹ብልጭ ድርግሙንማ ለመድነው እኮ። እኛን መልመድ ያቃተን ከኃይል ብዛት የተነሳ እየተቆራረጠ ያስቸገረንን መግባባት ነው፤›› አላት አጠገቧ የተሰየመ ጎልማሳ። ‹‹ኦ ለካ እሱም አለ? ነገር እየበዛ ሚሞሪዬ ሞላ እኮ እናንተ?›› ብላ ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየመች ዘመናይ ፈገግ አለች። ‹‹ለምን ‘ዴሊት’ አታደርጊም የተወሰነውን?›› መጨረሻ ወንበር ከተሰየሙት ወጣቶች አንድ ፀጉረ ጨብራራ ሲያናግራት፣ ‹‹እስኪ መጀመሪያ የውስጣችንን ቆሻሻ በቅጡ ማስወገድ እንቻል። መጀመሪያ ሰው በሰው ዴሊት መደረጉ ይረሳ። ከዚያ ሚሞሪ እናፀዳለን፤›› ብላ ጮኸችበት። በትንሽ ትልቁ የሚጯጯኸው ሰው ግን አልበዛባችሁም? ‹‹ምን ይደረግ ደህና ጊዜ መጣ ሲባል ተረኛ አልቃሽ በመብዛቱ እኮ ነው…›› የሚለን ልጅ እግር ቢጤ ነው፡፡ ያሰኛል!
‹‹ሐሜትማ ዘንድሮ ዘምና ዘማምና የቴክኖሎጂ ቆቧን ጭና በየፌስቡክ ማኅበር በማዋቀር የትናየት ሄዳለች። ምላስ ቀደም ቀደም እግር ቀረት ቀረት ብሎ ሥራና ሠራተኛ እንደ ዋዛ ታዩ፤›› አዛውንቱ ደረቅ ሳላቸው ብን ብን ማለት ጀመረችና ማውራት አቆሙ። ይኼኔ ጋቢና የተሰየመው ወጣት ንዴት በተቀላቀለው ድምፅ ስልኩን እንደያዘ ጮኸ። ‹‹ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዓለምን በሚመራበት በዚህ ዘመን ወሬ እንዴት አገር በፍጥነት እንደሚያዳርስ አትጠይቅም? ለስሙ ኢንተርኔት ላይ አፍጠህ ትውላለህ። ምናለበት ይኼን ይኼን እንኳን ብታጣራበት?›› ብሎ ሳይጨርስ ስልኩ ባትሪ ጨርሶ ዘጋ። ይኼኔ ወደ ሾፌሩ ዞሮ፣ ‹‹በአስተሳሰብና በአመለካከት ሰው እንደ አዲስ ባልተፈጠረበት አገር ወሬኞች የበዙት ምን አድርገን ነው?›› ብሎ ጠየቀው፣ መሪ የጨበጠ ሁሉ ለሁሉም ነገር መልስ ያለው ይመስል፡፡ አልሰማም እንዴ መልስ እንደናፈቀን!
ወያላችን ሒሳብ መቀበል ጀምሯል። መጨረሻ ወንበር የተሰየሙ ወጣት የሱቅ ነጋዴዎች ሳይታሰብ ጭቅጭቅ ጀመሩ። አንደኛው፣ ‹‹እንዴት ያለ ደረሰኝ የገዛሁት ዕቃ አለ ትለኛለህ? ሒሳብ እንደምናወራርድ አርባ ጊዜ ማስረዳት አለብኝ? መቼ ነው ግን አንተ የምትሠለጥነው?›› ይላል። ያኛው ደግሞ፣ ‹‹ይኼ ከመሠልጠን ጋር ምን ይገናኛል?›› ይለዋል። ወያላው ከመቅፅበት ከተፍ ብሎ፣ “ሒሳብ” ሲለው አንደኛው ወያላውን ትኩር ብሎ ዓይቶት፣ ‹‹ለስንቱ እንክፈል ዘንድሮ? ከታች እስከ ላይ መቀበል ብቻ? እዚህ ወዳጄ እንደ ቤት እመቤት ያለ ደረሰኝ ይሸምታል…›› ሲል አጉረመረመ። ‹‹አትበሳጭ ወንድሜ ብታወራርደውም ያው ማዋጣትህ አይቀር፤›› ይላል ከጎኑ የተቀመጠ ወጣት። ‹‹ኧረ ተወኝ! ሞባይል ሲጎረጉር ሲውል አንደኛ ነው። ሥልጣኔ እሱ ቤት ‘ፌስቡክ’ ላይ ማፍጠጥ ነው። ሥራ ላይ ደግሞ ያለምጣል፤›› ሲል ስለባልደረባው ተረከለት። ስንት ጉድ አለ!
‹‹መቼ እሱ ብቻ ሆነ ብለህ ነው? በሥልጣኔና በዘመናዊነት ስም መስሎኝ ሁላችንም አሳራችንን የምናየው። ደርሰው ሠለጠንን ባዮች ዕድሜ ለቴክኖሎጂ ምጥቀት በመገንባት ፈንታ ሲያፈርሱ፣ አንድ በማድረግ ስም ሲሰነጣጥቁ ስንታዘባቸው እንውላለን፤›› ካለው በኋላ የአፍታ ዝምታ ነገሠ። ወያላው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይመስላል አምጦ፣ ‘‘ሒሳብ” አለው። ‘ከዚህ በኋላ ብታስጮኸኝ አንተ ታውቃለህ’ ይመስላል ነጋዴው ሒሳቡን ከፍሎ ሲያበቃ በሐሳብ እንደተዋጠ ተክዞ ቀረ። ይኼን የሚታዘቡ ከሾፌሩ ጀርባ የተሰየሙ ሁለት ጎልማሶች፣ ‹‹ነጋዴ ሁሉ ሌባ፣ ነጋዴ ሁሉ አጭበርባሪና አቁስል ተደርጎ በሚታሰብበት አገር ይኼን ሰው እንዲህ ሆኖ ማየት አይገርምም?›› ይባባላሉ። ቆም ብለው ሲያጤኑት ሁሉም በራሱ ጭንቀት ተውጦ የሰው የሚያዳምጥበት ጊዜ አጥሮታል። ይኼኔ ችግርና ችግርተኛ በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ እየተላከኩ በመፍትሔ ዕጦት ዘመን የሚቆጥረው ወገን እያደር በእጥፍ ይጨምራል። ማጣፊያው ሲያጥር መጥኔ ያሰኛል!
ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ‹‹ምን ዓይነት ዘመን ነው ዘመነ ድሪቶ፣ አባቱን ያዘዋል ልጁ ተቀምጦ፤›› ብለው አዛውንቱ ሲያንጎራጉሩ፣ ‹‹ምን ይደረግ? ይኼ አሁን ያሉት በደስታ ተቀብለን በመከራ የምንሸኛቸው ጊዜያት ድምር ውጤት ነው፤›› አላቸው ከጎናቸው የተሰየመ ወጣት። ‹‹እንዲህ አይደለም ወይ ሰው ያለ ቦታው፣ ብሳና ይሆናል ሸንኮራ አገዳው’ የተባለው ታዲያ እኮ ለእኔ ነው። ሰንብት ብሎ ይኼን የሚያሳየኝ፤›› ይሉታል። ‹‹ተመሥገን ነው። ደግ ደጉን ካዩ እኮ ብዙ ለውጥ አለ። ግን አንዳች ከሚያህል ነጭ ይልቅ ትንኝ የምታህል ጥቁር ነጥብ ትጎላለች፤›› ብሎ ሳይጨርስ ከወደ ጋቢና፣ ‹‹ተው! ተው! እንደዚህማ ነገር አታቃል፤›› ብሎ አንዱ አቋረጠው፡፡ ይሻላል!
አዛውንቱ ይኼኔ ፈገግ ብለው፣ ‹‹አይ ወጣት መሆን እንዴት ደስ የሚል ነገር ነው። አደራ ልጆቼ ይኼ ያገባኛል ባይነታችሁ፣ ይኼ ለአገር ለወገን የማሰብ ስሜታችሁ መቼም ቢሆን አይቀዝቅዝ። ብቻ…›› ብለው ድምፃቸውን ሲውጡ፣ “ብቻ ምን?” አለች ከጎኔ። ‹‹…ብቻ ከክፉ መካሪ፣ ከሐሰት መስካሪና ከነገር አዳዋሪ እየራቃችሁ። አገርን ለማስቀጠል መጀመሪያ ለራስ ነው ማሰብ ተገቢ ነው። አገር ማለት እያንዳንዳችን ነን። በነገር ሠሪዎች አትታለሉ። በልዩነት ዕመኑ፣ ልዩነትን ማክበር ራስን ማክበር ነው፣ አገር ማክበር ነው፣ መሠልጠን ነው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ፈጣሪን አትርሱ፣ በገዛ ወገናችሁ ላይ ሰይፍ አትምዘዙ፣ ድሆችን አትበድሉ፣ ጊዜ ሰጠን ብላችሁ አትመፃደቁ፣ ሥልጣን ስትይዙም ለደሃ እዘኑ፣ አገራችሁን አስቡ፡፡ አንዳችሁ ሌላችሁን ጠብቁ፡፡ እርስ በርስ ስትጠባበቁ አትጠቁም…›› እያሉ ታክሲያችን ጥጓን ይዛ ቆማለች። እውነት ነው እንጠባበቅ! መልካም ጉዞ!