የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁንም ሰላምና መረጋጋት እንደናፈቀው ነው፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀው ጦርነት ወደ መቋጫው የተቃረበ መስሎ የነበረ ቢሆንም፣ አሁንም በአፋርና በተለያዩ አካባቢዎች ከቀላል እስከ ከባድ መሣሪያዎች እየተተኮሱ ነው፡፡ የጦርነቱ ገጽታ እየተለዋወጠ ንፁኃን በከባድ መሣሪያ አረር እየተጨፈጨፉ መሆናቸው ሲሰማ፣ ለሰላምና ለመረጋጋት አመቺ ሁኔታ ለመፍጠር ሲያዳግትና የነገ ብሩህ ተስፋ ሲደበዝዝ፣ ከዚህ ሁሉ ጉድ ውስጥ የመውጫው ጊዜ መናፈቁ አይቀሬ ነው፡፡ ጦርነቱ ጋብ ሳይል በመሀል ግራ አጋቢ አጀንዳዎች ከየሥርቻው እየወጡ አየሩን ሲሞሉት፣ የኢትዮጵያ መከራና ሰቆቃ ማብቂያው ቢናፍቅ አይገርምም፡፡ ይህንን ሕዝብ የሚፈጅና አገር የሚያወድም ጦርነት በፍጥነት ማቆም ባልተቻለባት አገር፣ ጎራ ለይቶ ነገር መፈላለግና በተመሰጠሩ ቃላት መነጃጀስ ማንን እንደሚጠቅም ግራ ያጋባል፡፡ መንግሥት ከጦርነቱ ጋር ስለሚያያዙ ዋነኛና አባሪ ጉዳዮች በበቂ መጠን መረጃ ሳይሰጥ ሲቀር፣ በጎን በኩል አገራዊ አንድነትን የሚበትኑና ለኪሳራ የሚዳርጉ ጉዳቶች ይደርሳሉ፡፡ የወፍ ቋንቋ የሚመስል የተመሰጠረ መልዕክት ሲተላለፍ፣ ለፖለቲካ ትርፍ ያለው ፋይዳ ምን እንደሆነ አይታወቅም፡፡
እንደ አንድ ምሳሌ ለማንሳት የሚሞከረው በቅርቡ ክሳቸው እንዲቋረጥ ተወስኖ ከእስር ከተፈቱ ግለሰቦች መሀል፣ የሕወሓት የቀድሞ አመራሮችን በተመለከተ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪዎች አንዱ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ያሰፈሩት ይጠቀሳል፡፡ ‹‹መንግሥት ሰሞኑን ምንድነው ያደረገው? በእጁ ላይ በሚገኝ የፖለቲካ ገንዘብ ለኢትዮጵያ የሚጠቅም ነገር ነው የገዛው፡፡ አንድን ቅርስ እንዳይታወስ ከፈለግህ ያንን ቅርስ ወደ ገንዘብ መቀየር ነው፡፡ ከዚያ ሌላ ነገር ትገዛበታለህ፡፡ በቅርሱ ምትክ በቅርሱ የተገዛው ነገር ሲታሰብ ይኖራል፡፡ በሕወሓት ቅርሶች ሌላ ለኢትዮጵያ የሚጠቅም ነገር በመግዛት በቅርሱ ፋንታ የተገዛው ነገር እንዲታወስ ማድረግ የብልህ ነጋዴ ሥልት ነው፡፡ ሕወሓትን ከምናጠፋበት መንገድ አንዱ እርሱን ለሌላ ነገር መግዣ በማዋል ነው፡፡ ይህንን ገንዘብ ይዘኸው ብትኖር ሁለት ነገር ይገጥምሃል፡፡ ወይ ዋጋው ይቀንሳል ወይም ጨርሶ ይጠፋል፡፡ ሁለቱም ኪሳራ ናቸው፡፡ ለዚህ የተሻለው አማራጭ በተገቢው ጊዜ ተገቢውን ነገር መግዛት ነው፡፡ የሆነውም ይኸው ነው፡፡ ምን እንደተገዛ በሒደት የምናየው ይሆናል፤›› በማለት ሹሙ የተመሰጠረ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ እንቆቅልሽ የሚመስለው ይህ ማብራሪያ ግልጽነት ስለሚጎድለው፣ ትርፍና ኪሳራን ለማስላት ያለው ፋይዳ አይታወቅም፡፡ እንዲያው በግርድፉ መንግሥት አገርን የሚጎዳ ውሳኔ አያስተላልፍም ከተባለም፣ ቢያንስ አሳማኝ የሆነ ነገር ይዞ መቅረብ ተገቢ ይሆን ነበር፡፡
በተደጋጋሚ ለማስታወስ እንደሚሞከረው የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ መሆን እንዳለበት፣ በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት በማያወላዳ አኳኋን ደንግጓል፡፡ ተወደደም ተጠላም ሕገ መንግሥቱ የሕጎች ሁሉ የበላይ ነው፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 12 የመንግሥት አሠራርና ተጠያቂነትን በተመለከተ፣ ‹‹የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን አለበት፡፡ ማንኛውም ኃላፊና የሕዝብ ተመራጭ ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ ይሆናል፡፡ ሕዝብ በመረጠው ተወካይ ላይ እምነት ባጣ ጊዜ ከቦታው ለማንሳት ይችላል፡፡ ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፤›› ይላል፡፡ ይህ ድንጋጌ ግልጽነትን፣ ተጠያቂነትንና ኃላፊነትን ከመንግሥት አስፈጻሚ አካል እስከ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ድረስ የሚያስገነዝብ ሲሆን፣ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥትም ኃላፊነቱን በሕግ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት እንዲያከናውን ያስገድዳል፡፡ እርግጥ ነው ለብሔራዊ ደኅንነት ሲባል በሚስጥር መያዝ ያለባቸው ጉዳዮች ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን የሕዝብን የማወቅ መብት በማድበስበስ፣ ‘የምነግርህን ያለ ምንም ማንገራገር ተቀበል’ ማለት አይቻልም፡፡ ከዚህ ይልቅ በመንግሥትም ሆነ በገዥው ፓርቲ የተደረገ ውይይት ወይም ምክክር ካለ፣ በምክክሩ አመክንዮ ላይ በመመሥረት ጎጂና ጠቃሚው እንዴት እንደተንገዋለለ መነገሩ የተሻለ ይሆን ነበር፡፡
በዚህ ላይ በመመሥረት የተብራራ ነገር መቅረብ ሲገባው፣ በጉዳዩ ላይ በአንድ የመንግሥት አፍ የተለያዩ ልሳኖች መሰማታቸው ቁጣውን አንሮታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰሞኑን ሒደቱን የገለጹበት መንገድ ቀደም ሲል እንዲታወቅ ቢደረግ ኖሮ መልካም ይሆን ነበር፡፡ የመንግሥት ውሳኔ የሚመሠረትባቸው በርካታ ውስጣዊና ውጫዊ ሁኔታዎች መኖራቸው ግልጽ ቢሆንም፣ ውሳኔው ድንገተኛ ሆኖ በሰበር ዜና ሲለቀቅ ሊያስከትል የሚችለው ውጤት ተገማች መሆን ነበረበት፡፡ የውሳኔው ውጤት ከወዲሁ ቢገመትና ሊኖረው የሚችለው አንድምታ ታሳቢ ቢደረግ፣ ቢያንስ ሰሞነኛ መነጋገሪያ በማድረግ የተለያዩ አስተሳሰቦችን ማስተናገድ ይቻል ነበር፡፡ ከግብረ መልሱ በሚገኘው ስሜት ላይ በመመሥረትም አማካይ ለመፍጠር ጥረት ማድረግ አይገድም ነበር፡፡ እዚህ ላይ ሊዘነጋ የማይችለው አንድ መሠረታዊ ጉዳይ፣ መንግሥት ለሕዝብና ለአገር ይበጃል የሚለውን የመወሰን ኃላፊነት ነው፡፡ ይህ ኃላፊነት ግን እንደ ጦር ሜዳ የሬዲዮ ግንኙነት በተመሰጠረ መንገድ የሚከናወን ሳይሆን፣ የውሳኔውን አስፈላጊነትና ጠቃሚነት ሕዝብ በሚገባው ቋንቋ የማስረዳት ወኔን የተላበሰ መሆን ነበረበት፡፡ የፖለቲካው ትርፍና ኪሳራም በዚህ መንገድ ሲለካ መግባቢያ አማካይ አይጠፋም ነበር፡፡
በጣም በርካታ ችግሮች በሚርመሰመሱባት አገር ውስጥ በቀላሉ ተግባብቶ አብሮ ለመሥራት ያለው ችግር ይታወቃል፡፡ ነጩን ጥቁር፣ ጥቁሩን ነጭ እየተባባሉ ሁሌም መነታረክ የሚፈልጉ ስመ ፖለቲከኞች በበዙባት ኢትዮጵያ፣ እንኳንስ ለመግባባት በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ ለመነጋገር የሚስተዋለው ዳተኝነትና ክፋት ከባድ እንደሆነም ግልጽ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ውስብስብና አስቸጋሪ የፖለቲካ ባህል ይዞ ለመግባባት የሚያስቸግር ነገር ለአደባባይ ማብቃት፣ በነበሩ ችግሮች ላይ ተጨማሪ ችግሮች ከመፈልፈል የዘለለ መፍትሔ አያስገኝም፡፡ የነገዋ የተስፋ ምድር ኢትዮጵያን ለማሰብ እኮ ቢያንስ መሠረቷን የሚያሳምሩ ጅምሮች መታየት አለባቸው፡፡ በተለያዩ መስኮች ተስፋ የሚሰጡ አመርቂ ነገሮች ቢታዩም፣ በፖለቲካው መስክ ደግሞ ‘አድሮ ቃሪያ’ መሰል ነገሮች ሲበዙ ተስፋ ያስቆርጣሉ፡፡ በግልጽ መነገር ያለባቸው ብሔራዊ ጉዳዮች እየተሸፋፈኑ ለሴራ ትንተና ሲጋለጡና የሰዎችን አዕምሮ ሲያውኩ፣ እንዲሁም በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት ሲያበላሹና ተስፋ ሲያሳጡ ቀልጠፍ ብሎ እርማት ማድረግ የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ ካልሆነ ግን፣ ‹‹ትክ ብለው ሲያዩት ወተት ደም ይመስላል›› የሚሉ ነገር አነፍናፊዎች አጋጣሚውን ተጠቅመው፣ እየታየ የነበረውን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እንደሚበትኑት መጠራጠር አይገባም፡፡ ይህ ደግሞ ኪሳራውን ያከፋዋል፡፡
መንግሥት በሕዝብ የተመረጥኩ በመሆኔ የምወስነውን አውቃለሁ ይላል፡፡ ውሳኔውም አመርቂ ውጤት እንደሚያመጣም በእርግጠኝነት ይናገራል፡፡ ከሆነ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥትን ለማመን ያለው ልምድ ምን ይመስላል የሚለውን መቃኘት ተገቢ ነው፡፡ ከረጅሙ ዓመት የኢትዮጵያ ታሪክ በመጀመር አሁን ያለንበት ዘመን ድረስ፣ ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለው እምነት በጣም ዝቅተኛ ለመሆኑ ቀባሪን እንደ ማርዳት ነው የሚቆጠረው፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት ውስጥ በነበረው አስከፊ ውጣ ውረድ፣ ሕዝብ ከመንግሥት ያገኝ የነበረው መረጃና እውነታው ምን ያህል ልዩነት እንደነበረው የሚታወቅ ነው፡፡ መንግሥት ጦርነቱ አለቀ ካለ በኋላ የታለፈበት ሰቆቃ አይረሳም፡፡ አሁንም ጦርነቱ ተጠናቋል ቢባልም ከአፋር በኩል የሚሰማው ሌላ ዙር ችግር ነው፡፡ ጦርነት በጦር መሣሪያ ከሚደረገው ፍልሚያ በተጫማሪ በሚዲያና በዲፕሎማሲ ጭምር ጣጣው ብዙ ነው፡፡ ሌላው ትልቅ ትኩረት የሚያስፈልገው የኢኮኖሚ ጉዳይ አለ፡፡ እነዚህና መሰል በርካታ ራስ ምታቶች የተደበላለቁበት የጦርነት ፈርጀ ብዙ ገጽታ፣ በሕዝብና በመንግሥት መሀል ግልጽነት እንዲሰፍንና ለመፍትሔው በጋራ ለመሥራት ይጎተጉታል፡፡ ግልጽነት ጎድሎ የተድበሰበሱ ነገሮች ሲበዙ ግን መተማመን አይቻልም፡፡ ስለዚህ የፖለቲካው ትርፍና ኪሳራ የሚለካው በውጤት መሆኑን መዘንጋት አይገባም!