በ2003 ዓ.ም. በወጣው የግል ድርጅቶች ጡረታ አዋጅ፣ የግል ሠራተኞችን የጡረታ ፈንድ አዋጭ በሆኑ ዘርፎች ኢንቨስት ማድረግ ቢፈቀድም፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ለአዋጁ ማስፈጸሚያ መመርያ ባለማውጣቱ ለአሥር ዓመታት ያህል ገንዘቡ ሳይሠራበት ለዋጋ ግሽበት እንደተጋለጠ ተገለጸ፡፡
በአዋጁ መሠረት የጡረታ ፈንዱ የገንዘብ ሚኒስቴር አዋጭ የኢንቨስትመንት ከባቢ ናቸው ብሎ በሚለያቸው አስተማማኝ ዘርፎች ሥራ ላይ እንዲውል ቢጠበቅም፣ የገንዘብ ሚኒስቴር መመርያ ባለማውጣቱ ምክንያት አለመቻሉን የግል ድርጅቶች ማኅበራዊ ዋስተና ኤጄንሲ የሕግ ዳይሬክተር አቶ ግርማ ሲሳይ ተናግረዋል፡፡
በዚህ ምክንያትም በአዋጅ የተሰጠውን ሥራ ለማስፈጸም አቅጣጫም ሆነ መመርያ ለኤጄንሲው ባለመሰጠቱ፣ ፈንዱ ለዋጋ ግሽበት እንዲጋለጥ መደረጉን፣ የጡረታ አበል ተጠቃሚዎችም ከጊዜው ጋር አብሮ የሚሄድ የተመጣጠነ የጡረታ ክፍያ እንዳያገኙ ተፅዕኖ ማሳደሩን አክለው ገልጸዋል፡፡
አቶ ግርማ ይህን የተናገሩት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የመንግሥትና የግል ሠራተኞችን ጡረታ ለመደንገግ በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ሰኞ ጥር 9 ቀን 2014 ዓ.ም. የሕዝብ ይፋ ውይይት መድረክ ላይ በተገኙበት ወቅት ነበር፡፡
ተሻሽሎ የቀረበው አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ኤጄንሲው ፈንዱን ወደ ኢንቨስትመንት ለማስገባት ሙሉ ሥልጣን ስለሚሰጠው፣ አዋጭ የሚላቸውን ዘርፎች በማጥናትና በመለየት ወደ ኢንቨስትመንት ይገባል ብለዋል፡፡
ከአሥር ዓመት በኋላ ተሻሽለው የቀረቡት ሁለት ረቂቅ አዋጆች በግልጽ ሥርዓት ላይ የተመሠረተ ጠንካራ የፈንድ አስተዳድር ለመገንባት በማለም፣ ማኬንዚ የተባለ የውጭ አማካሪ ድርጅት ተቀጥሮ በተገኘው የጥናት ውጤት መሠረት ተሻሽለው መቅረባቸው ተገልጿል፡፡
ከተሻሻሉት አዋጆች መካከል አንደኛው ተቀጣሪ ሠራተኞች መጀመርያ ላይ ሥራ ሲቀጠሩ የሞሉትን የልደት ዘመን ማስረጃ፣ አሁን በሥራ ላይ ባለው አዋጅ አልፎ አልፎ ማስተካከያ እያደረጉ አስቸጋሪ ሁኔታ እየፈጠሩ በመሆናቸው፣ ተሻሽሎ በወጣው ረቂቅ አዋጅ መሠረት በመጀመርያ የቅጥር ዘመን የተሞላን የልደት ዘመን ማስረጃ ለመቀየር በምንም ዓይነት ሕግ የሚፈቀድ አይሆንም ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል በአዋጅ ግዴታ የተጣለባቸው ባንኮች አሠሪ ድርጅቶች ከሠራተኞቻቸው የሚሰበስቡትን የጡረታ ገንዘብና ያለባቸውን ውዝፍ ዕዳ፣ ባንክ ውስጥ ካላቸው ሒሳብ ላይ፣ የግል ድርጅቶች ጡረታ ኤጄንሲ ለባንኮች በሚጽፈው ደብዳቤ መሠረት፣ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ቀንሰው ወደ ጡረታ ፈንድ ገቢ እንዲያደርጉ ግዴታ የተጣለባቸው ቢሆንም፣ አንዳንድ ባንኮች ይህን ግዴታ በመተላለፍና ለድርጅቶች በማድላት ገንዘቡ ሳይቀነስ አውጥተው ለድርጅቶች ሲሰጡ ተስተውሏል ተብሏል፡፡
በዚህ የተነሳ ይህን ችግር ለመቅረፍ በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ መሠረት ባንኮች ከኤጄንሲው ደብዳቤ ከደረሳቸው ቀን ጀምሮ ከአሠሪው ድርጅት የባንክ ሒሳብ ላይ፣ ውዝፍ የጡረታ መዋጮውን ቆርጠው ለጡረታ ፈንድ ማስገባት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ነገር ግን ባንኮች ደብዳቤ ከደረሳቸው ቀን ጀምሮ ገንዘቡን ወጪ አድርገው ለድርጅቶች ሰጥተው ቢገኙ፣ በወጣው ገንዘብ ልክ እንዲከፍሉ አስገዳጅ ድንጋጌ ሠፍሯል፡፡