ለዘጠኝ ወራት ገደማ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ በመሆን ያገለገሉትን ጄፍሪ ፊልትማንን በመተካት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ዴቪድ ሳተርፊልድ፣ ኃላፊነታቸውን ከተረከቡ የመጀመሪያቸው የሆነውን ጉብኝት በኢትዮጵያ እንዲሚያደርጉ ተነገረ፡፡
ጉብኝታቸውን ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ሞሊ ፊ ጋር በሳዑዲ ዓረቢያ የጀመሩት ሳተርፊልድ በሱዳንና በኢትዮጵያ እንደሚያደርጉና ፕሬዚዳንት ባይደን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር ያደረጉትን የስልክ ንግግር ተከትሎ፣ በስልክ ጥሪው የተነሱ ጉዳዮች ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ከኢትዮጵያ መንግሥት ተወካዮች ጋር ይነጋገራሉ ተብሏል፡፡
በዚህም መሠረት ልዩ መልዕክተኛው አሁን የተከፈተውን የሰላም በር በማስፋት የአየር ድብደባዎችና የቀጠሉ ጥቃቶች እንዲቆሙ፣ በድርድር የሚደረስበት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲኖር፣ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች እንዲለቀቁ፣ ቀጣይነት ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እንዲኖር፣ እንዲሁም አካታች ለሆነ ብሔራዊ መግባባት መሠረት እንዲጣል ከመንግሥት ኃላፊዎች ጋር ይነጋገራሉ ሲል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ከዚህ ባለፈ ልዩ መልዕክተኛው ከውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ሞሊ ፊ ጋር በመሆን በሪያድና በካርቱም ሱዳን ስላለው ወቅታዊ የፀጥታ ቀውስና የሲቪል አስተዳደር ለመመሥረት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ምን ዓይነት ዓለም አቀፍ ድጋፍ መቀየስ እንደሚቻል ውይይት የሚያደርጉ ሲሆን፣ በሱዳን ከሲቪል መሪዎችና ከሰላማዊ ተቃውሞ አንቀሳቃሾች ጋር ይነጋገራሉ ተብሏል፡፡
‹‹በአፍሪካ ቀንድ ተያያዥ የሆኑ የፖለቲካ፣ የፀጥታና የሰብዓዊ ቀውሶችን ለመፍታት አሜሪካ የምታደርገውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ይመራሉ፤›› ተብለው የተሾሙት ሳተርፊልድ፣ ካሁን ቀደም በቱርክ የአሜሪካ አምባሳደር፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አማካሪ፣ የቅርብ ምሥራቅ ጉዳዮች አማካሪ፣ በኢራቅ አስተባባሪ፣ በኢራቅ የአሜሪካ ምክትል የልዑክ መሪ፣ በግብፅ የአሜሪካ ዋና ልዑክ እንዲሁም በሊባኖስ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል፡፡
በመካከለኛው ምሥራቅና ሰሜን አፍሪካ ደግሞ በሶሪያ፣ በቱኒዝያ፣ እንዲሁም በሳዑዲ ዓረቢያ ለአርባ ዓመታት ገደማ ልምድ ያካበቱ እንደሆነ የሚያሳየው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገጸ ታሪክ፣ የዓረብና የዓረብ-እስራኤል ጉዳዮች ዳይሬክተር በመሆን እንዳገለገሉም ይጠቅሳል፡፡ ልዩ መልዕክተኛው ከእንግሊዝኛ በተጨማሪ ዓረብኛና ፈረንሣይኛ ቋንቋዎችንም ይናገራሉ፡፡
ከአሁን ቀደም በዚህ ኃላፊነት ሲሠሩ የቆዩት ጄፍሪ ፊልትማን፣ የመጨረሻ ጉዟቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉት በኢትዮጵያ መንግሥት ጥሪ እንደነበርና በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይና በፕሬዚዳንት ባይደን መካከል የተደረገውን የስልክ ንግግር ዓይነት ይዘት ያለው ውይይት ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ማድረጋቸውም ተጠቁሟል፡፡