ካለፉት 80 ዓመታት ወዲህ አገሪቱ ያወጣቻቸውን ከ600 በላይ በሥራ ላይ የሚገኙ ሕጎችን ብቻ በአንድ ጥራዝ ያካተተ የሕግ መጽሐፍ ተዘጋጀ፡፡
አገሪቱ በዚህ ወቅት 600 የሚደርሱ በሥራ ላይ የሚገኙ ሕጎች እንዳሏት የተገለጸ ሲሆን፣ እነዚህ አዋጅና ደንቦች በተዘጋጀው ጥራዝ ላይ እንደተጠቃለሉ ተነግሯል፡፡ በጥራዙ ላይ አዋጅና ደንቦች ብቻ እንደተካተቱ የታወቀ ሲሆን፣ መመርያዎች በባህሪያቸው በአጭር ጊዜ የሚስተካከሉ ስለሆነ በዚህ ጥራዝ እንዳልቀረቡ ታውቋል፡፡
በመጽሐፍና በበይነ መረብ አማራጮች የተዘጋጀው ጥራዝ፣ የሕጎችን ተደራሽነትና ታሪካዊ ሁኔታ በሚገባ ሊያሳይ የሚችል ሥራ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ በአገሪቱ መሰል ጥራዝ ለመጨረሻ ጊዜ የተዘጋጀው ከዛሬ 47 ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አማካይነት እንደነበር ታውቋል፡፡ ከዚህ ወዲህ በአገሪቱ የሚወጡት ሕጎች በተበታተነ መልኩ እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን፣ በዚህ ወቅት ሕጎች በአንድ ቋት መዘጋጀታቸው ይህንን ችግር የሚቀርፍ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በፍትህ ሚኒስቴር የፕሬስ ሴክሬተሪያት ኃላፊ የሆኑት አቶ አወል ሡልጣን ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ ሕጎቹ በሰባት ቅፅ የቀረቡ ሲሆን፣ ሰባተኛው ቅፅ ከ ‹‹ሀ›› እስከ ‹‹ሐ›› የሚደርስ ክፍል አለው፡፡ አንዱ ቅፅ 10 የሚደርሱ ቅፆች ሲኖሩት እነዚህ ቅፆች እያንዳንዳቸው በ29 ክፍሎች የተከፈሉ ናቸው፡፡
የጤና፣ የአሠሪና ሠራተኛ፣ የኢንቨስትመንት፣ የመንግሥት አስተዳደር ተቋማት ላይ የሚወጡ ሕጎች በቀረቡት ክፍሎች ላይ የተካተቱ ሲሆን፣ ሕገ መንግሥቱን ጨምሮ የኮንስትራክሽንና የከተማ ልማት፣ የእርሻና ግብርና፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር ተያይዘው የሚወጡ ሕጎች በጠቅላላ 29 የሚደርስ ክፍሎች ባሉትና 10 ቅፅ ባሉት መጽሐፍ ተደራጅተው በመፃፍና በበይነ መረብ አማራጭ እንደተጠረዙ ተብራርቷል፡፡
ጥራዙን የማዘጋጀቱ እንቅስቃሴ በ2009 ዓ.ም. ትኩረት ተሰጥቶት መሠራት ይጀምር እንጂ፣ ቀደም ብሎ በ1995 ዓ.ም. መዘጋጀት እንደጀመረ ያስታወቁት አቶ አወል፣ በወቅቱ የነበረው ቴክኖሎጂ በዚህ ደረጃ ስላልነበረ ይበልጥ ትኩረት ያገኘው ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ እንደሆነና በጠቅላላው የረዥም ዓመት የሕግ ባለሙያነት ልምድ ያላቸው ከ12 እስከ 14 የሚደርሱ ዓቃቢያንና ሌሎች ባለሙያዎች በዋናነት እንደተሳተፉበት ተገልጿል፡፡
በ1965 ዓ.ም. የወጡና እስካሁንም ድረስ በሥራ ላይ የዋሉ እንደ የሥራ ሰዓትን፣ የዕረፍት ቀናትንና ሌሎችም መሰል ጉዳዮችን ለማወጅ የወጡ ሕጎች በጥራዙ የተካተቱ ሲሆን፣ ሕጎቹ በዘመናዊ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ተጽፈው ባለመገኘታቸው ከዚህ ቀደም የተዘጋጀውን ጥራዝ በድጋሜ በኮምፒውተር ባለሙያ እንዲፃፉ መደረጉ ተነግሯል፡፡
የተዘጋጀው የመጽሐፍ ጥራዝ 7,200 የሚደርሱ ገፆች እንዳሉት የታወቀ ሲሆን፣ አንድ አዋጅ ወጥቶ በሌላ ተተክቶ ሥራ ላይ ሲውል ሙሉ ሥራውን የሚነካ በመሆኑ፣ የመጽሐፍ ዝግጅቱ በጊዜ ገደብ እንዲወሰን በሚል እንዲካተቱ የተደረጉት እስከ ሚያዚያ 2013 ዓ.ም. የወጡት ሕጎች እንደሆኑ ተገልጿል፡፡
ከመጽሐፍ ጥራዙ ህትመት ውጪ ለዝግጅቱ ሒደት አንድ ሚሊዮን ብር የሚፈጅ ወጪ እንደወጣ የታወቀ ሲሆን፣ ይህም ለባለሙያ ክፍያ፣ ለሕጎች ግዢና የቴክኖሎጂ ድጋፍ ላደረጉ ተቋማት ባለሙያዎች በተለያየ መልኩ የተከፈሉ ከፍያውን ያጠቃልላል፡፡
አንድ መቶ የሚደርሱ የመጽሐፍ ጥራዞች ለሕትመት እንደታዘዙ ያስረዱት አቶ አወል፣ ለምሳሌ አንድ ተቋም የሚያዘው መጽሐፍ እያንዳንዱ አሥር የሚደርሱ ጥራዞች ያሉትና በጠቅላላው ከ7,000 በላይ ገፆች አሉት፡፡ ይህም ሕትመት ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ የህትመት ወጪ የሚጠይቅ እንደሆነ ታውቋል፡፡
የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) የተጠቃለሉት ሕጎች መጽሐፍ በይፋ በተመረቀበት መድረክ ላይ እንዳስታወቁት፣ ሕጎችን በአንድ ቋት ማግኘት መቻሉ ከዚህ ቀደም በሕግ ሥርዓት ውስጥ ይገጥሙ የነበሩ ችግሮችን የመቅረፍ ዕድል አለው፡፡ በተለይም የሕግ ባለሙያዎች በሚያከናውኗቸው የክርክር ሥራዎች ውስጥ ሊገጥም የሚችልን የሕጎች ተደራሽነት፣ ውስንነትና በተሻሩ ሕጎች የመከራከር አደጋን የማስወገድ ዕድሉ ሰፊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚህ ወቅት በመጽሐፍት ተዘጋጅተው ከሚሠራጩት የተጠቃለሉ ሕጎች በተጨማሪ፣ ተገልጋዮች በቀላሉ መረጃ እንዲያገኙ ዕድል በሚሰጥ የበየነ መረብ አማራጭ ሕጎችን በአንድ ላይ እንዲገኙ ማድረጉ የሕግ የበላይነትን በማስፈን ረገድ የሚጫወተው ሚና ቀላል አይሆንም ብለዋል፡፡