የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያን ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን እ.ኤ.አ. በ2022 ሥራ ለማስጀመር በብሔራዊ ባንክ የተቋቋመው ፕሮጀክት፣ ቅድመ ቴክኒካዊ ሥራዎችን እንያገባደደ መሆኑ ተገለጸ፡፡
አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎችን ከፋይናንስ ምንጮች ጋር በማገናኘት ኢንቨስትመንትን ለማበረታት፣ ኢንቨስተሮችን ለመጠበቅ፣ ገበያውን ፍትሐዊ፣ ተዓማኒና ቀልጣፋ በማድረግ፣ በአገሪቱ የፋይናንስ ሥርዓት ላይ የሚፈጠሩ መዋቅራዊ ሥጋቶችን ለመለየት፣ ለመከላከልና ለመቀነስ ያስችላል የተባለለት የካፒታል ገበያ ባለሥልጣንን የሚያቋቁመው አዋጅ፣ በሰኔ 2013 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወሳል፡፡
አዋጁ ከፀደቀ ጀምሮ ተቆጣጣሪ ባሥልጣኑን ለማቋቋም የሚያስችሉ ቴክኒካዊ ሥራዎችን ለማከናወን በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የተካተቱበት 13 የባለሙያዎች ቡድን ተዋቅሮ፣ ሥራውን የሚፈጽም ፕሮጀክት ተቋቁሞ መመርያ በማውጣት፣ እንዲሁም እንግሊዝ አገር ከሚገኘው ስታንዳርድ ባንክ ጋር በመተባበር የአቅም ግባታ ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ በብሔራዊ ባንክ የካፒታል ገበያ ከፍተኛ አማካሪ አቶ መለሰ ምናለ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም የውጭ ኢንቨስትመንት ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በተለይም የካፒታል ገበያ አክሲዮን ማሻሻጥ፣ የቦንድ ዲዛይን መሥራት፣ የኢንቨስትመንት ምክር አገልግሎትና መሰል የካፒታል ገበያ ኢንቨስትመንት ላይ እንዲሰማሩ ሕጉ የሚፈቅድ በመሆኑ፣ በቅርቡ የውጭ ኢንቨስትመንት ባንኮች ፍጎታቸውን ሊገልጹ እንደሚችሉ በመግለጽ፣ ለአብነትም ስታንዳርድ ባንክ በኢትዮጵያ ላሉ ባለሙያዎች በነፃ ሥልጠና መስጠት መጀመሩ አንዱ የፍላጎት ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ብለዋል፡፡
የመንግሥት የኢኮኖሚክ ሪፎረም አካል የሆነው የካፒታል ገበያ መመሥረት የአጠቃላይ የኢኮኖሚውን ሚዛን ለመጠበቅና ምርታማነትን ለመጨመር ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የገለጹት አቶ መለሰ፣ ከሚቋቋመው ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ጋር አብረው ይሠራሉ ለሚባሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሥልጠናና ማረጋገጫ (Certification) እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የንግድ ሥራ ትምህርት ቤት የአካውንቲንግና የፋይናንስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዳኪቶ ዓለሙ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ምንም እንኳ የካፒታል ገበያም ሆነ የፋይናንስ ተቋማት ገንዘብ ያለውና የሌለው ሰው አንድ ላይ የሚገናኙባቸው መድረኮች ቢሆኑም፣ አሁን ካለው አሠራር በተለየ የካፒታል ገበያ መምጣት የፈጠራ ሥራዎች የበለጠ እንዲደገፉና አዳዲስ የኢንቨስትመንት አማራጮች ወደ ሥራ እንዲገቡ ያግዛል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ የካፒታል ገበያ ሲመሠረት የኢትዮጵያ ባንኮች ተወዳዳሪና ጠንካራ ሆነው እንዲወጡ ቅድመ አስተዳደራዊ ዝግጅት ካላደረጉና ራሰቸውን አሁን ካሉበት ደረጃ ከፍ ማድረግ ካልቻሉ፣ በመንግሥት የተጀመረው ገበያን ነፃ የማድረግ ጉዞ ጋር ተዳምሮ የመዳከም ዕድላቸው ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል ስለካፒታል ገበያ የመነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት የምጣኔ ሀብት ተማራማሪው አቶ ተስፋዬ ኃይለ ሚካኤል፣ በመመሥረት ላይ ያለውን ተቋም እንዲመራ የሚሰየም አካል ጠንካራ የሞራል ልዕልና፣ ኃላፊነት የሚሰማውና ለሥራው ፅኑ ፍላጎት ያለው ሊሆን እንደሚገባ አበክረው አሳስበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የንግድ ሥራ ትምህርት ቤት ከ400 በላይ ከዘርፉ የተወጣጡ ተሳታፊዎች በተገኙበት ጥር 7 ቀን 2012 ዓ.ም. እየተቋቋመ ስላለው ካፒታል ገበያ አመሠራረት ውይይት ተደርጓል፡፡