Tuesday, May 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናቤሕነን የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ከተስማሙ ኃይሎች ጋር ተሳትፏል መባሉን አስተባበለ

ቤሕነን የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ከተስማሙ ኃይሎች ጋር ተሳትፏል መባሉን አስተባበለ

ቀን:

  • ከብልፅግና ጋር የጋራ መንግሥት ማቋቋም ትክክለኛ አቋሙ መሆኑን ተናግሯል

የቤኒሻንጉል ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ (ቤሕነን) በቅርቡ በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ፣ በሕዝብ የተመረጠን መንግሥት ለማፍረስ ከተስማሙት የፌዴራሊስት ኃይሎች ጋር ተሳታፊ ነበር ተብሎ የቀረበበትን ክስ አስተባበለ፡፡

ፓርቲው የቤንኒሻንጉል ጉምዝ ብልፅግና ፓርቲ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባቀረበበት አቤቱታ ላይ መልስ የሰጠ ሲሆን፣ ከቀረበበት አቤቱታ መካከል በቅርቡ በዋሽግተን ዲሲ ውስጥ መንግሥትን በማፍረስ በምትኩ ሌላ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ከተስማሙት የፌዴራሊስት ኃይሎች ጋር የቤሕነን አመራሮች ተሳትውበታል የሚለው ተጠቃሹ ነው፡፡

ቤሕነን ጥር 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በላከው ማብራሪያ እንዳስታወቀው፣ የቤንኒሻንጉል ብልፅግና ፓርቲ ባቀረበው አቤቱታ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ከተስማሙት ኃይሎች አንዱ የቤሕነን አመራር ነው ከማለት ውጪ፣ የትኛው አመራር እንደተሳተፈ ያስቀመጠው ማስረጃ የለም፡፡

በውጭ አገር የሚኖርም ሆነ ለተጠቀሰው የጥምረት ስብሰባ በማለት  ወደ አሜሪካ ሄዶ እንዲሳተፍ የተደረገ አመራር እንደሌለው፣ ፓርቲው በመግለጫው አስታውቋል፡፡

ቤሕነን የዘመናት ብሶት የፈጠረው ድርጅት እንደሆነ፣ ከዚህም ውስጥ ለረዥም ጊዜ የክልሉን ሀብት ሲዘርፉና ሲያዘርፉ፣ ሕዝቡን በእስርና ግድያ ሲያሰቃዩ የኖሩት የሕወሓት/ኢሕአዴግ የጡት ልጆች በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማስወገድ ዋነኛው ዓላማው እንደሆነ አስረድቷል፡፡ ከጥገኝነትና ከሙስና ነፃ ከሆኑት ከብልፅግና አመራሮች ጋር የጋራ መንግሥት መመሥረት የፓርቲው ትክለለኛ አቋምም እንደሆነ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

የቤንኒሻንጉል ጉምዝ ብልፅግና ፓርቲ ከዚህ በሻገር በቤሕነን ላይ ተጨማሪ አቤቱታዎችን ያቀረበ ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ ብልፅግና ከቦሮ ሽናሻ ፓርቲ ጋር የሥልጣን ክፍፍል አድርጎ እየሠራ ቢገኝም፣ የቤኒሻንጉል ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ (ቤሕነን) ግን ከሕወሓት ጋር በመቀናጀት የሥልጣን ክፍፍሉን ባለመቀበል ሸፍታነትን መርጧል የሚለው ይገኝበታል፡፡

በተጨማሪም የንቅናቄው ምክትል ሊቀመንበርን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮችና አባሎች ከሕወሓት አመራሮች ትዕዛዝ ተቀብለው ወደ ሱዳን ተሻግረው ለመቀላቀል ሲሉ ተይዘው ክሳቸው ተቋርጦ መፈታቱን፣ እንዲሁም ጉሕዴን ከሚባል ሌላ ድርጅት ጋር በመጣመር በዜጎች ላይ የሞትና መፈናቀል ተግባር እንደፈጸመ፣ በርካታ ወጣቶችን በመመልመል ሱዳን ቦካሪ ማሠልጠኛ ለመላክ ሲሞክር ምልምሎቹ ተይዘው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ተይዟል የሚለው ተጠቃሹ እንደሆነ  ተገልጿል፡፡

ቤሕነን በሰጠው ምላሽ የብልፅግና ፓርቲ ሥልጣን የማጋራት ሐሳቡ ዋነኛ ምክንያት ክልሉ አገር አቀፍ ምርጫ ያልተደረገበት ብቸኛ ክልል መሆኑ ስለሚታወቅ፣ የሕጋዊነት ጥያቄዎች ተነስተው ፌዴራል መንግሥት በተፈጠረው የሥልጣን ክፍተት ሳቢያ እጁን በክልሉ አስገብቶ ከሥልጣን ሊያነሳን ይችላል፣ ስለሆነም ይህ ሳይፈጠር ሥልጣን አጋርተን ብንሻገር ይሻላል ተብሎ በመታሰቡ ነው ብሏል፡፡

ድርጅቱ በምንም ምክንያት የሚደረግን የትጥቅ ትግል እንደማያምንበት ያስታወቀ ሲሆን፣ ‹‹የቤኒሻንጉል ነፃነት ግንባር›› የሚልና  ሌሎች ስያሜዎችን በመያዝ በጎረቤት አገር የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች በራሱ በአቤቱታ አቅራቢው ድርጅት የሚደራጁ እንጂ፣ ከቤሕነን ጋር ግንኙት የሌላቸው እንደሆኑ አስተባብሏል፡፡

የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ በዘመድ አዝማድ ተሳስሮ ገሚሱን በአገር ውስጥ የፓርቲው አባል፣ ሌላውን ከአገር በማስኮብለል የተቃዋሚ ኃይል አድርጎ በማሰማራት የቤሕነን ስም እያጠፋና እያጠለሸ ይገኛል ያለው ንቅናቄው፣ በክልሉ ሰላም ከሰፈነና  የፌዴራል መንግሥት ከተረጋጋ የአቤቱታ አቅራቢው ፓርቲ ማንነት ስሚጋለጥ፣ ይህንን የክልሉን የፀጥታ ችግር እየፈጠረ ያለው ይኸው ሙሰኛ ኃይል ነው በማለት  ለምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡

የንቅናቄው ምክትል ሊቀመንበርን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮችና አባሎች ከሕዋሓት አመራሮች ትዕዛዝ ተቀብለው ወደ ሱዳን ተሻግረው ለመቀላቀል ሲሉ ተይዘዋል ስለሚለው ጉዳይ፣ የግለሰቦቹ መያዝ ንቅናቄው ያረጋገጠው ጉዳይ ቢሆንም፣ በተያዙበት ቀን ከፓርቲው የተሰጣቸው ተልዕኮና ሥምሪት እንዳልነበረ ይህንንም የሚመለከታቸው አካላት እንዲያውቁት ማደረጉ ተገልጿል፡፡

በክልሉ ሕዝብ ማሸበር፣ ማፈናቀል፣ መግደልና መሰል ጉዳዮች ስለመፈጸማቸው በሕግ ተረጋግጦ በማረሚያ ቤት የሚገኙት የቤንኒሻንጉል ጉምዝ ብልፅግና ፓርቲ ቁንጮ አመራሮች ስለመሆናቸው ፓራቲው ራሱ በመገናኛ ብዙኃን ያረጋገጠው ጉዳይ እንደሆነ ያስታወቀው  የቤኒሻንጉል ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ፣ ይህም አመራሮች ወጣቶችን ከገጠር ወረዳዎች  መልምለው በማምጣት በአሶሳ ከተማ ብጥብጥ በማስነሳት ለበርካታ ንብረት መውደም፣ እንዲሁም የሰው ሕይወት መጥፋት መንስዔ እንደነበሩ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

የቤንኒሻንጉል ጉምዝ ብልፅግና ፓርቲ ታኅሳስ 1 ቀን 2014 ዓ.ም.  ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተጻፈ ደብዳቤ በቤኒሻንጉል ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ ተፈጽመዋል ያላቸውን የተለያዩ ችግሮች ገልጾ፣ ቦርዱ በቀረበው አቤቱታ ላይ ዕርምጃ እንዲወሰድ የጠየቀ ሲሆን፣ ምርጫ ቦርድ በቀረበው አቤቱታ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጥ ቤሕነን ታኅሳስ 25 ቀን 2014  ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ መጠየቁ ይታወሳል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...